Monday, 03 April 2017 00:00

የሰብአዊ መብት ተቋማት አቅም፣ ነፃነትና ተዓማኒነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግስትን በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚወነጅሉ ጠንካራ ሪፖርቶችን ያወጣሉ፡፡ መንግስት በበኩሉ “ሪፖርቶቹ ርዕዮተ አለማዊ ዘመቻ ማካሄጃ ናቸው” በማለት ያጣጥላቸዋል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲከኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን በሪፖርቶቹ ላይ የተለየ አቋም ነው ያላቸው፡፡
ለመሆኑ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች በአገሪቱ ገፅታ ላይ ምን አንድምታ አላቸው? ተአማኒነታቸውና
ተቀባይነታቸውስ ምን ያህል ነው? በመንግስት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖና ጫና ይኖር ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በጉዳዩ
ዙሪያ የመንግስት ሃላፊና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

• ሪፖርቶቹ ሌላው አለም ስለ ኢትዮጵያ እንዲረዳ በማድረግ ረገድ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል
• የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቀጥል ያደረገው ነፃ ተቋማት ያለመኖራቸው ነው
• የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንኳን ለሌላው ሊደርሱ ለራሳቸውም ነፃነት የላቸውም
• የሥርአት ለውጥ መጥቷል ማለት የሚቻለው ተቋማቱ ሲለወጡ ብቻ ነው
• የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች ርዕዮት አለማዊ ዘመቻ ማካሄጃ ናቸው



“ነፃና ገለልተኛ አካላት መፍጠር ገና አልተጀመረም”
አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

ተቋማቱ የሚያቀርቡት ሪፖርት ምን ያህል ታማኝ ነው የሚለውን በመጀመሪያ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በዓለም ላይ ታዋቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሚሰሩት ስራ ሁሉ የተዋጣለትና ፍጹም ትክክል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም የሚያወጧቸው መግለጫዎች የራሳቸው መሰረት ያላቸው ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ሪፖርቱን ከሚያቀርበው ወይም ከሚሰበስበው ሰው አሊያም መረጃ ከሚያገኙበት አካል አንዳንድ ሪፖርቶች ሊጋነኑና ሊዛቡ ይችላሉ፡፡ ግን በአጠቃላይ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ስህተት ናቸው ማለት አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ሁልጊዜ የሚያወጧቸው መግለጫዎች ጠንከር ያለ ትችት ያዘሉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ እውነትነት ያላቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ሙሉ ለሙሉ ትክክል ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ በተለይ ከሰብአዊ መብት ጋር ተያይዘው የሚወጡ ሪፖርቶች በጥቅሉ ትክክል አይደሉም ማለት አይቻልም፡፡ ከእነ ችግራቸውም ቢሆን ሪፖርቶቹ ተአማኒ ናቸው፡፡
ምንጮቻቸው እነማን ናቸው የሚለውን ካየን፣ ጉድለቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ከነዚህ ጉድለቶች ጋር የሚወጡ መረጃዎች በአመዛኙ እውነትነት አላቸው። የኢትዮጵያ መንግስት አንድ ጊዜ ከነዚህ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶችን “የምዕራባውያኑ መሳሪያዎች ናቸው” ብሎ ፈርጆ የደመደመ በመሆኑ፣እነሱ የሚያቀርቡት ነገር እውነትም ይሁን ሀሰት መቀበል አይፈልግም፡፡ ብዙ ስህተቶቹን ሊያርምባቸው የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም እንኳ አያያቸውም አይቀበላቸውም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ አምጥተዋል ወይ ከተባለ፣ በቀጥታ አላመጡም ግን ደግሞ ሌላው አለም ስለ ኢትዮጵያ እንዲረዳ በማድረግ ረገድ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ድርቶች በሌላው አለም በጣም ግዙፍ     ቁመና ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙ መንግስታትና ተቋማት እነሱ ላይ ተመስርተው ፖሊሲ ያወጣሉ፤ አቋምም ይወስዳሉ፡፡ ይህ ማለት በምዕራባውያኑ ዘንድ ተቋማቱ ተሰሚነት አላቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ግን አንዴ አቋም ስለያዘ ሪፖርታቸውን የሚያነበውም አይመስለኝም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ እንዲህ ያለውን ሚና የሚጫወቱ ተቋማት በበቂ አቅም አልተፈጠሩም። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማት ይቋቋማሉ ግን ተቋማቱ የሥርአቱ መሣሪያ እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው እንጂ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ አይፈለግም፡፡ እነዚህ ተቋማት በሚቋቋሙበት ህግ ላይ አይደለም ችግሩ፤ በተቋማቱ ውስጥ የሚቀመጡት ሰዎች ለሥርአቱ ታማኝ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ተቋማቱ ለሥርአቱ አገልጋይ ነው የሆኑት፡፡ ይሄ ደግሞ በግራ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያደገ ሃይል የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ በደርግ ጊዜም ሆነ አሁን ያለው እውነታ ይሄው ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ መሰረታዊ ችግር ተቋማት ነፃ አለመሆናቸው ነው፡፡ ተቋማት ፓርቲን መሻገር አለባቸው፡፡ መንግስታት ወይም ፓርቲዎች በምርጫ ሲቀያየሩ ተቋማቱ የማይቀያየሩ መሆን አለባቸው፡፡ ህግን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ገለልተኛ አካላት የመፍጠር ጉዳይ ገና አልተጀመረም፡፡ መንግስት ሁልጊዜ ተቋማቱን የራሱን ጥቅም ማስጠበቂያና አላማውን ማስፈፀሚያ አድርጎ ነው የሚጠቀምባቸው፡፡ ለዚህ ነው በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተቋማት መካከል ሁለት ጫፍ የያዘ ሪፖርት ሲቀርብ የምናየው፡፡ በኔ እምነት የውጭዎቹ የተሻሉ ናቸው፡፡ ቢያንስ ሙያዊ የሆነ ነገር ለመስራት ይሞክራሉ፡፡ የራሳቸውን መንግስትና ሥርአት ለመተቸትም ወደ ኋላ አይሉም። እነ አምነስቲ የእንግሊዝ መንግስትን ችግር በደንብ ይተቻሉ፡፡ እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች የአሜሪካ ወታደሮች ወይም ባለስልጣናት የፈፀሟቸውን ስህተቶች በደንብ ያጋልጣሉ፡፡ የኛ አገር ተቋማት ግን እንደዚያ አይደሉም፡፡ የመንግስታችንን ገመና እና ስህተት እንደብቅ የሚሉ ናቸው፡፡ የተቋቋሙበትንም አላማ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ በአገሪቱ የዜጎች መብት እንዳይከበርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቀጥል ያደረገው ነፃ የሚባሉ ተቋማት ያለመኖራቸው ነው፡፡ የሚቋቋሙት ተቋማት በሙሉ የስርዓቱ ጥቅም ማስጠበቂያ ስለሚሆኑ ነው። ይሄ አስተሳሰብ ከመሠረቱ ካልተቀየረ የፈለገ ተቋም ብናቋቁም ዋጋ የለውም፡፡
ብዙ ጊዜ ምርጫዎች ሲካሄዱ እነ አምነስቲ ሪፖርት ይወጣሉ፡፡ አብዛኞቹ ትክክል ናቸው ግን አንዳንዴ ሳያጣሩ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ለመንግስት ትችት በር ሲከፍቱ ይታያል፡፡ ይሄን እኛ መረጃ ተቀባዮቹ ማጣራት አለብን፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ተቋማት ለኔ በትክክል የተቋቋመበትን አላማ እያሳካ ነው የምለው አንድ ተቋም አለ፡፡ እሱም የዋና ኦዲተር ቢሮ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ ከተባለ መልስ የለኝም፡፡ ግን በትክክል ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ሙስና፣ ምን ያህል ብክነት እንዳለ ጠንካራ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ለምን ሌሎቹ እንደዚህ አልሆኑም? አላውቅም፡፡ ውልና ማስረጃ የሚባል መሥሪያ ቤትም ከምዕራባውያኑ ጋር የተስተካከለ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በነዚህ ተቋማት ለውጥ እንዴት መጣ ለሚለው መልስ የለኝም፡፡
ከሰብአዊ መብት ጋር ተያይዞ የተቋቋሙ ተቋማት ግን ህዝብን ማዕከል አድርገው አይደለም የሚሰሩት፡፡ የተቋቋሙለትን አላማ በአግባቡ እየተወጡ አይደለም፡፡ እነዚህ ተቋማት ለውጥ እንዲያመጡ መንግስት ተቀያያሪ መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ ይሄን ባህል ማድረግ አለባቸው፡፡ ብዙ የዋና ኦዲተርና የውልና ማስረጃ አይነት መሥሪያ ቤቶች ያስፈልጉናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥርአት ለውጥ መጥቷል ማለት የሚቻለው እነዚህ ተቋማት ሲለወጡ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ካልተደረገ ችግሩ አይፈታም፤ ቀጣይ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ መንግስት ግን በዚህ የሚያምን አይደለም፡፡ የአመለካከት ችግር በመኖሩ ምክንያት ነው ይሄን ተግዳሮት መሻገር ያልቻልነው፡፡

========================


“የተቋማቱ ሪፖርት ተፅዕኖ ሲፈጥር አላስተዋልኩም”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛ)


ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የአለም መንግስታት እንዲያውቅ ያደርጋሉ፡፡ ተፅዕኖ የሚኖረው ግን እርዳታ ሰጪ ሀገራት ምን አይነት አቋም ይወስዳሉ ከሚለው ጋር የተያያዘ ሲሆን ነው፡፡ ከፍተኛ የእርዳታ ለጋሽ የሆነችው የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ተመሳሳይ ሪፖርት ያወጣል፡፡ እነዚህ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያወጡትንም ሪፖርት ሊቀበል ይችላል፡፡ ግን ትርፍ የሚኖረው መንግስቶቻቸው የሚወስዱት እርምጃ ሲኖር ነው፡፡ ተቋማቱ ኢትዮጵያን የተመለከተ ሪፖርት ሲያወጡ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያውቅ ነው፡፡ መንግስትም ሪፖርቶቹ ይደርሰዋል፡፡ ግን የሚቀበላቸው አይመስልም። ባይቀበላቸውም ተቋማቱ ሪፖርታቸውን ማውጣታቸውና ጉዳዩን ለአለም ማሳወቃቸውን መቀጠላቸው ትክክል ይመስለኛል፡፡
ሪፖርቶቹ ለውጥና ማሻሻያ እንዲያመጡ ከተፈለገ የኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርቶቹን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ለዚህ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን እነሱ ይሄን አስተካክሉ፣ያንን አድርጉ ማለታቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ተቋማት የሚያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ ሲወስድ እስካሁን አላየሁም፡፡ የተለየ ተፅዕኖ ሲፈጥርም አላስተዋልኩም፡፡
የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተቋማት ማንነት የሚመሰረተው ስልጣን ላይ ባለው መንግስት አመለካከት ነው፡፡ እኔ በግሌ እንደማውቀው በሚያዚያ ወር 1996 ደንቢዶላ በአንድ ት/ቤት ላይ ፖሊሶች መጥፎ እርምጃ ወስደው ነበር፡፡ ያንን ለመንግስት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አድርጌ ነበር፡፡ አስታውሳለሁ ባለሙያ ልከው ጉዳዩን አስጠንተው፣ ይሄ የመብት ጥሰት ተፈፅሟል ብለው የክልሉ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበው ነበር፡፡ እርምጃው በተግባር ይወሰድ አይወሰድ አላረጋገጥኩም፤ ግን በወቅቱ ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ስራ ሰርቷል፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ እነዚህ አካላት በሀገሪቱ ፖሊሲ ልክ ስራቸውን እየሰሩ ይመስለኛል፡፡ ግን ለምን የሚያወጡት ሪፖርት ተአማኒነት የለውም የሚለውን አላውቅም። መንግስት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶችን ምን ያህል ተቀብሎ ማሻሻያ ያደርጋል የሚለውንም ለማወቅ ይከብዳል፡፡  
======================

“ሪፖርቶቹ ርዕዮት አለማዊ ዘመቻ ማካሄጃ ናቸው”

አቶ መሃመድ ሰይድ
(የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ኦክላንድ ኢንስቲቲዩትን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ ድርጅቶች ናቸው በኢትዮጵያ ላይ ሪፖርት የሚያወጡት፡፡ አንዳንዶቹ ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን የሚተቹ መረጃዎች ያወጣሉ። ሌሎች ደግሞ ሀገሪቱ የምትገነባቸው የኃይል ማመንጫዎች፣ የስኳር ፋብሪካዎች ወዘተ ከአካባቢ ስነ ምህዳር ጋር የተወዳጁ አይደሉም፤ነባር ህብረተሰቦችን ያፈናቅላሉ በሚል የተለያዩ ሪፖርቶችን ያወጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የመረጃዎቻቸው ምንጮችና መረጃን የሚያሰባስቡበት መንገድ በራሱ መሰረታዊ ችግር አለበት፡፡ ይሄን ስንል አንደኛ እነሱ መረጃ የሚያገኙባቸው ምንጮች በትክክልም የኢትዮጵያን ህብረተሰብ የሚወክሉ አይደሉም። የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው መረጃ የሚሰጧቸው፡፡ እነዚህ የተለየ የፖለቲካ ርዕዮት የሚከተሉ ግለሰቦች፣ ከርዕዮተ ዓለም ፍላጎታቸው በመነሳት ስለ መንግስትና ስለዚህች አገር ጥሩ ነገር ያወራሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ትክክልም ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተለየ የፖለቲካ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ደንታ ቢስ የሆኑ ግለሰቦች የፈጠራ መረጃ ይሰጧቸዋል። እነዚህ ድርጅቶች ይሄን መረጃ ተጠቅመው ነው መግለጫዎች የሚያወጡት፡፡  
ነፃና ገለልተኛ የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ፣ ብሄር ብሄረሰቦችንና ህብረተሰቡን የሚወክሉ አካላት የሚሰጧቸውን ነፃ መረጃ ቢጠቀሙ ነበር የተሻለ የሚሆነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ መንግስትም በሪፖርቱ ላይ ሃሳቡ እንዲካተት ከማድረግ አንጻር ችግሮች አሉባቸው፡፡
የአንድ ወገን ሀሳብ ይዘው ነው ሪፖርታቸውን የሚያወጡት፡፡ ይሄን ማድረግ እንዳለባቸው ሳያውቁ ቀርተው ግን አይደለም። ኢትዮጵያ የምትከተለው የራሷ ሀገር በቀል የሆነ ርዕዮተ ዓለም አለ፡፡ ሀገር በቀል የሆነ ዲሞክራሲ አለን፡፡ ይሄ በተጨባጭም ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያመጣ፣ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡ ህዝቡን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት እያወጣ ያለ ስርአት ነው፡፡ ይሄ ሀገር በቀል የሆነና ከምዕራባውያን የኒዮ ሊበራል አስተሳሰብ ወጣ ያለ ስርአት እያደገ መምጣቱና ለሌሎችም ተምሳሌት መሆን መጀመሩ ያላስደሰታቸው ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች፣ በነዚህ ተቋማት አማካይነት ርዕዮተ ዓለማዊ ዘመቻ እያደረጉ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
 የዜጎችን ሰብአዊ መብት መጠበቅ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ድርድር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በጥብቅ መከበር አለባቸው የሚል እምነት አለው - ሥርአቱ፡፡ ይሄ የሚመነጨው ለዜጎች ካለው ተቆርቋሪነትና ኃላፊነት ነው፡፡
ሁለተኛ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ በህገ መንግስቱ የተቀመጠና ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነን እንኳ የዜጎች ሰብአዊ መብት በምንም አይነት መልኩ መነካትና መሸራረፍ የለበትም የሚል ፅኑ አቋም ነው የተያዘው፡፡ ከዚህ ተነስተን እነዚህ አካላት ምን ውጤት አመጡ ካልን፣ በመጀመሪያውኑ የዚህች ሃገር እጣ ፋንታ ያለው በዜጎቿ እጅ ነው፡፡ እጣ ፈንታዋን ሊወስኑ የሚችሉት ዜጎቿ እንጂ እነዚህ አካላት አይደሉም፡፡ ስለዚህ በውስጥ አቅማችን እናድጋለን የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ይሄ ነው ዋናው ማዕከሉ፡፡ ይሄ መተማመን ስላለ እነዚህ አካላት በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡
በሌላ በኩል የሃገር ውስጥ ተቋማት በተለይ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የመሳሰሉት ‹‹ቼክ ኤንድ ባላንስ›› ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ አሁን ካሉበት ደረጃ የበለጠ እየተጠናከሩ መሄድ አለባቸው፡፡ እየተጠናከሩ ሲሄዱ ደግሞ በህብረተሰቡ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነታቸው እየጨመረ ይሄዳል። አሁንም በዚህ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው ያሉት፡፡ ይበልጥ ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ በራሳችን ተቋማት የመተማመን፣ ያልተጠናከሩ ተቋሞቻችን ይበልጥ እንዲጠናከሩ የማድረግ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ በውጭ ተቋማት ላይ በመተማመን ከችግር ልንወጣ አንችልም፡፡ የፈረንጅ ተቋማትን የማምለክና እነሱ ትክክል ናቸው ብሎ የማመን የተዛቡ አመለካከቶች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ በሂደት እየተስተካከሉ ይመጣሉ የሚል እሳቤ አለን፡፡
መንግስት ተቋማቱ በተለያዩ ጊዜያት ለሚያወጧቸው ሪፖርቶችና መግለጫዎች ቋሚ ምላሽና ማብራሪያዎች የሚሰጥበት አካሄድ አለው። ዋነኛው ጉዳይ ግን የራሳችንን የቤት ስራ መስራት ነው፡፡ ዲሞክራሲያችን እየተጠናከረና ገፅታችን እየተቀየረ ሲሄድ ቀዳዳ ያጣሉ፡፡ ስለዚህ ሥራችንን አጠናክረን መቀጠል ነው ያለብን፡፡

==========================

“የአገራችን የሰብአዊ መብት ተቋማት ነፃነት የላቸውም”

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

ሌሎች አገራት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት መግለጫዎችን ለፖሊሲ ግብአትነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚወጡ ሪፖርቶችንም ለጋሽ አገራት በሀገሪቱ ላይ የሚከተሉትን ፖሊሲ ለመፈተሽና ለመገምገም እንደሚጠቀሙበት አረጋግጫለሁ፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ሪፖርቶች፣ ይሄ መንግስት በዲፕሎማሲውና ከሌሎች ሀገራት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥሩበታል፡፡ በፖለቲካ ረገድ በአለማቀፍ መድረኮች ተቀባይነትና ተሰሚነት የማጣት ነገርም ይፈጠራል፡፡ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የፈረመች ሀገር እንደመሆኗም መሪዎችን ያሳፍራቸዋል፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ያሉ የነፃነት ታጋዮች፣ ትግላቸው ለአለማቀፉ ህብረተሰብ እንዲደርስና እንዲሰማ በማድረግ ረገድም ጠቀሜታ አለው፡፡ ሰዎች እንደሚገምቱት ግን እነዚህ ሪፖርቶች  በቀጥታ በመንግስት ላይ የሚያሳርፉት ጫና የለም፡፡ ሪፖርቶቹ ግን ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው፡፡ ለጋሽ መንግስታት ፖሊሲዎቻቸውንና አጀንዳቸውን እንዲፈትሹ ያደርጋቸዋል፡፡
የኛ መንግስት ደግሞ የጉልበት አገዛዝ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች አይቀበልም አያከብርም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የአሜሪካ መንግስት የሚሰጠን እርዳታ ከሀገሬው የግብር ከፋይ ህዝብ የሚሰበሰብ ነው፡፡ የሀገሬው ህዝብ እነዚህን ሪፖርቶች ሲሰማ “የታለ ዲሞክራሲው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
ከዚያ ውጪ ግን እስከ ዛሬ መንግስት የነዚህን ተቋማት ሪፖርት ሰምቶ የለወጠውና ያሻሻለው ነገር አለ ለማለት ይቸግረኛል፡፡
በአገሪቱ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በነፃነት የሚከታተሉና ሪፖርት የሚያደርጉ ነፃ ተቋማት የሉም፡፡ ህግ አውጪውም፣ ህግ አስፈፃሚውም፣ ደህንነቱም፣ ፍ/ቤቱም በአንድ ፓርቲ መዳፍ ውስጥ ያሉ በመሆኑ፣ ነፃ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድን ሀገር ውስጥ መፍጠር አልተቻለም፡፡
ህዝብ ሲፈልግ የሚሾመውና የሚሽረው መንግስት ሲኖር ነው እነዚህ የፍትህና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ሊጠናከሩ የሚችሉት፡፡ በሌላው አገር እነዚህ ተቋማት ናቸው እንደ 4ኛ የመንግስት አካል ተቆጥረው፣ ዲሞክራሲውን በመጠበቅ ረገድ አስተዋፅኦዋቸው ጎልቶ የሚታየው፡፡ እነዚህ አካላት ሲኖሩ ነው ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሆኖ፣ “ቼክ ኤንድ ባላንስ” ሊፈጠር የሚችለው፡፡
አሁን ባለበት ሁኔታ ግን እነዚህ ተቋማት በነፃነት እንንቀሳቀስ ቢሉ ለጥቃት ነው የሚጋለጡት፡፡ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም፣ የሚዲያ አካላትም ሆኑ የሲቪክ ተቋማት፣ በአሣሪ አዋጅና ህጎች የታጠሩ ናቸው። እንኳን ለሌላው ሊደርሱ ለራሳቸውም ነፃነት የላቸውም፡፡

========================

“የሰብአዊ መብት ተቋማት አሉን ለማለት እቸገራለሁ”

አቶ አብርሃ ደስታ (የፖለቲካ መምህር)

እነዚህ ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ሁለት ጠቀሜታ አላቸው፡፡ አንደኛ የሚፈፀሙ ግፍና በደሎችን ለአለም ማጋለጥ ነው፡፡ መንግስት እንደሚታወቀው በደሉን መፈፀሙ ሳይሆን የተፈፀመው በደል መጋለጡ ነው ትንሽ የሚያስደነግጠው፡፡ ከዚህ አንፃር መጋለጡና መደንገጡ ጥሩ ነው፡፡ ግን ከመደንገጡ ውጪ የሚያሻሽለው ወይም የሚያስተካክለው ነገር የለም። ይሄ ደግሞ ከስርአቱ ባህሪ የመነጨ ነው፡፡ ስለዚህ እስከ ዛሬ ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች ወደ ተጨባጭ ለውጥ መሸጋገርና ተጽዕኖ መፍጠር ካልቻሉ ትርጉም የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጨቋኝና ግፍ የሚፈፅም መንግስት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን መንግስት ግፍ ትፈፅማለህ ብሎ መንገር ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ እነሱ ግን የሚፈጸሙ ግፎችን ማጋለጣቸው ተገቢ ነው፡፡
 የሚታይ ባይሆንም የነዚህ ተቋማት ሪፖርት የተወሰነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ምክንያቱም ሪፖርቶች በወጡ ቁጥር የኢህአዴግ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንቅፋት ይገጥመዋል፡፡ ተፅዕኖ የሚፈጥሩም የተወሰኑ መንግስታት አሉ፡፡ መንግስታቱ የኢትዮጵያ መንግስት በህዝቡ ላይ ግፍ ይፈፅማል ብለው ካሰቡ መንግስት መቀየሩ አይቀርምና ከህዝብ ጎን መሰለፉ ይጠቅማል የሚል አቋም ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ይሄ ድጋፍና እውቅና በማግኘት ረገድ ተፅዕኖው ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ግፍና በደሉ መጋለጡ አስፈላጊ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሪፖርቶቹ ሲወጡ ስንመለከት፣ ምናልባት ከመረጃ እጦትም ሊሆን ይችል ከሚያጋልጡት ይልቅ የማያጋልጡት ይበዛል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ችግሩን አያጋልጡም፡፡ መንግስት ደግሞ ዋነኛ ስራው በደልና ግፍ ይፋ እንዳይወጣ ማፈን ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት በሌላው አለም የታወቁና ስም ያላቸው በመሆኑ የሚያወጡት ሪፖርት ተቀባይነት አለው፡፡
ዜጎች በመንግስት የሚደርስባቸውን በደል እንዳይከላከሉና እንዳያጋልጡ የተቋቋሙት የአገር ውስጥ የመብት አስጠባቂና ተከራካሪ ተቋማት ነጻ አይደሉም፡፡ የፓርቲ ተቋማት ናቸው፡፡ የፓርቲውን ገበና ለመደበቅና ለመሸፈን የሚሰሩ ናቸው፡፡ ነፃ ሆነው የህዝብን መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ስላልሆኑ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት አሉን ለማለት እቸገራለሁ፡፡ በግል የተቋቋሙትም ቢሆኑ በጭቆና ውስጥ ያሉ ተቋማት ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈፀሙ በደሎችን ለማጋለጥ ብቁ አይደሉም ብዬ ነው የማምነው፡፡

Read 3900 times