Print this page
Monday, 03 April 2017 00:00

በአባቶቻችን መንገድ እንሂድ----

Written by  ነጋ ፍቅሬ ባህርነሽ
Rate this item
(19 votes)

በጣና ደሴት ላይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ የብራና መጽሐፍትን ወደ ኮምፒውተር ጽሑፍ እየገለበጥን ሳለ አብሮኝ ስራውን የሚያከናውን ጓደኛዬ አንዲት የብራና ቅጠል ወደ እኔ እየሰደደ፤ ‹‹አንብበው ትወደዋለህ፡፡›› ብሎ ሰጠኝ፡፡ በፊቱ ላይ የተረጨውን የደስታ ብርሃን አይቼ፣ በችኮላ ተቀብዬው ማንበብ ቀጠልኩ፡፡ ወረቀቱ እንዲህ ይላል፡-
‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ይእዜ ንነግረክሙ አኀዊነ ፍቁራን ውሉዳ ለዛቲ ሀገር ኢትዮጵያ ምስጢረ ሑረታ ለሕይወት፡፡ እግዚአብሔር ያብርህ አዕይንተ አልባቢክሙ ወይትወከፍ ጸሎተክሙ ወኢይምጻእ ውስተ ብሔርክሙ ምንዳቤ ወሀውክ፡፡
አንድ አምላክ በሚሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምነን የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን የኢትዮጵያ  ልጆች፣  የሕይወትን  ምስጢራዊ  መንገድና መተላለፊያዋን እንነግራችኋለን። እግዚአብሔር ዓይነ ልቦናችሁን ያብራላችሁ፤ ጸሎታችሁንና ልመናችሁን ይስማ፡፡ ችግርና መከራ ወደ ሰፈራችሁ አይምጣ፡፡
የአንዲትን ዕፅ ቅጠል በመቁረጥ ከግንዷ ተለይታ ደርቃ እንድትከስም ማድረግ ቀላል እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም የመኖር ጉጉቱና ምኞቱ እስካላገደው ድረስ ራሱን ያጠፋ ዘንድ ቀላል ነው እንላለን፡፡ እንደምን ነው ቢሉ፡- በዚህ ዓለም ነዋሪ ከሆኑ መካከል ብዙዎች የስህተት መንገድ ተጠቅመው፣ራሳቸውን ሲያጠፉ ታይቷልና ነው። ‹ከስንፍና መንገድ ራቁ› እንዲል አባ አርማቆስ፡፡ አንድ ሰው ራሱን ማጥፋት የፈለገ እንደው በገመድ ራሱን አንቆ፣ በወንዝ ውስጥ ራሱን ጨምሮ አሊያም በቅጠል በጣሽ፣ በስር ማሽ የተቀመመ መድኃኒት አኝኮ፣ ያለችውን ደግቱን ነፍስ ከራሱ ሊነሳ ይችላል፡፡
እኛ ግን ስለ ከባዱ ሞትና ስለ ዓባይ (ትልቅ) ትንሳኤ እንናገራለን፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ፣ ሰነፍ ራሱን አጥፍቶ ትልቅ ማንነቱን ትንሳኤ ማድረግ ነው፡፡ (ራስን - ሀሳብ፣ ማንነት ተብሎ እንዲፈታ፡፡ ይህ ራስ ስጋዊ አካል ያይደለ ውስጣዊ ማንነት ነው እንጂ፡፡) ታዲያ ይህ አሟሟት እንዴት ከበደ ቢሉ፣ በዚህ ዓለም ነዋሪ ከሆኑት መካከል ጥቂቶች ብቻ የቀና መንገድን ተጠቅመው ራሳቸውን አጥፍተው፣ ለታላቅ ስራ ትንሳኤ ሲያደርጉ ታይተዋልና፡፡ ያንዲት ዕፅን ፍሬ ቆርጠው ቢጥሉዋት እሷንም ከታገሷት አፍርታ በዝታ እንደምትነሳ ሁሉ የሰነፍ ማንነትን ቆርጠው ከጣሉት፣ በታላቅ ማንነት ትንሳኤ ያደርጋሉ እንላለን፡፡ ለዚህም አባቶቻችንን አብነት እንጠራለን፡፡
በሀገረ አክሱም ያሬድ የሚባል ሕፃን ልጅ ነበር። መምህሩ የሆነው ማር (መምህር) ጌድዎን፤ ይህ ሕፃን ያሬድ ትምህርት አይገባው ስለነበር እለት ተእለት ዱላ ያሳርፍበታል፡፡ በዚህ የተመረረው ያሬድ ቤቱን ጥሎ ተሰደደ፡፡ የትምህርት ቦታውን ጥሎ ሲሰደድ ባገኘው ረሃብና ጥም ዝሎ ስለነበር ከአንዲት ጥላ ካላት ዛፍ ስር አረፍ አለ፡፡ በዚያችም ጥላ አርፎ ሳለ፣ አንዲት ትል ከዛፉ ጫፍ ያለን ፍሬ ለመመገብ ሽታ ሰባት ጊዜ ወድቃ፣ ሰባት ጊዜ ተነስታ ስትመገብ አስተዋለ። አስተውሎም አደነቀ ፤አድንቆም አልቀረ ለትጋት ራሱን አነሳሳ፡፡ ዛቲ ዕጼ ቀለተለት ስንፍናሁ ለያሬድ እንዲል፣ ያቺም ትል የያሬድን ስንፍና ማንነት ገድላ ለታላቅ ስራ አስነሳችው። እናም ቅዱስ ያሬድ አምስት የዜማ መጽሐፍትንና የቤተክርስቲያንን ዜማ ደረሰ፤ ለዜማውም ምልክት አኖረላቸው፡፡ ለዜማ ምልክት በመስጠት ከሱ የቀደመ ማንም ማን አልተገኘም፡፡ ከዜማው መጣፈጥ የተነሳ እንስሳት እንኳ ያዳምጡት ስለነበር እሱ ባዜመ ጊዜ በዚያ የነበሩ ገበሬዎች የእርሻ ስራቸውን በቅጡ ማከናወን አይችሉም ነበር፡፡
አንድም እንዲሁ ካሳ የሚባል ከተናቀ ዘር የተወለደ ልጅ ነበር፡፡ ጠቢብ መሆን ከፈለክ መጽሐፍትን ውደዳቸው፤ ዓይኖችህንም ከነሱ አትለይ እንዲል፤ ይህ ልጅ መጽሐፍትን መመልከት አብዝቶ ይወድ ነበር፡፡ እንዲሁ አንድ ቀን ፍካሬ ኢየሱስ የሚባለውን መጽሐፍ በማንበብ ላይ ሳለ፣ ‹ቴዎድሮስ የሚባል ንጉስ ይነሳል፤ ይህም ንጉስ ለተበታተነች ኢትዮጵያ የጠፋ አንድነቷን ይመልስላታል፡፡› የሚል ቃል አነበበ፡፡ ያ ፊደል የተሳለ ሰይፍ ሆኖ ካሳን ወግቶ ጥሎ ቴዎድሮስን ለተሻለ ስራ አስነሳው፡፡ ከዚያ ቀን በኋላ ያ የተነሳ ማንነት ከገደል ገደል፣ ከዱር ዱር ዞሮ የኢትዮጵያን አንድነት መለሰ፡፡ ከዚህም አልፎ አንድነት ይጠበቅ ዘንድ መድፍም ሰርቷል። በዚህም ስራው በሰዎች ዘንድ ሲደነቅ ይኖራል፡፡
አንድም እንዲሁ አባ ጊዮርጊስ የተባሉ አባት አሉ። ታላቅ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ቤት በሆነው ሐይቅ እስጢፋኖስ ተምረዋል። በዚያ ተማሪ በነበሩ ጊዜ ለሰባት ዓመታት ያክል ምንም አዲስ እውቀት ባለመጨመራቸው የተነሳ የስንፍና ምሳሌ ሆነው ነበረ። አብረዋቸው የሚማሩ ተማሪዎችም በርሳቸው ይዘባበቱና ይሳለቁ ነበር። ይህ ልጅ ትምህርት የማይገባው ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ ይመልሱ ዘንድ ይሟገቱም ነበር። አባ ጊዮርጊስ ግን ይህ ሁሉ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው በትዕግስት ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ በቁ። ትምህርቱን ባጠናቀቁ ጊዜ ግን በእውቀታቸው አስደናቂ ሆኑ። ግሩም ጣዕም ያላቸው መጽሐፍትን ጻፉ። ደረቅና አስቸጋሪ የሆነውን የነገረ ሃይማኖት ክርክር በግጥም መልክ አለስልሰው በማስፈር እንዲወደድ አደረጉት። በኢትዮጵያ የሳቸውን ያህል ሊቅ እና ጸሃፊ ማንም የለም።
እኛም በአባቶቻችን ምሳሌነት መሰረት፣ ፍሬ እናፈራ ዘንድ በአባቶቻችን መንገድ እንሂድ እንላለን። የእኛን የስንፍና ማንነት አጥፍተን፣ ለትልቅ ማንነት ማስነሳት ይገባናልና፡፡ ራስን ማጥፊያ መንገዶች፡- አስተውሎት፣ ንባብ፣  ትዕግስት ናቸው፡፡ አንዱ ሊቅ በድርሳኑ ‹ሦስቱን ነገሮች የያዘ ሰው ፍጹም ይባላል› አለ፡፡ ‹እኒህም ማስተዋል፣ ማወቅ (ንባብ)፣ ትዕግስት ናቸው፡፡ እኒህ ሦስቱ በዓለም ለመኖር ክብር ሲሆኑ ልቡና (ማስተዋል) ለስጋ ገዢዋ ነው፤ አእምሮ (ንባብ) መሪዋ ነው፤ ትዕግስት ደግሞ ብርሃኗ፡፡›ከአባታችን ያሬድ ማስተዋልን እንማራለን፡፡ እሱም ትሁት ስለሆነ ከታናሿ ዕጼ (ትል) እውቀት አገኛለሁ ብሎ ልቡናውን አስገዝቶ ድርጊቷን ተከታትሏልና፡፡ እኛም በውሎአችን ፈጣሪ በተፈጥሮ ብዙ የሚነግረን ነገር እና ምክር አለና አስተውለን ልንጓዝ ይገባናል፡፡ ከታላቁ ንጉሣችን ደግሞ ንባብን እንማራለን፡፡ ሰው መጽሐፍትን እንደ ምግብና መጠጥ ሊመገብ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ሲባል የአባቶች ጨዋታና ምክር፤ የቀደመ ልምድ ሁሉ ነው እንጂ። ሁሉ ነገር ካስተዋሉትና ካነበቡት ጥሩ መጽሐፍ ነውና፡፡
ትዕግስት ግን ለሁሉ….›› የመጀመሪያውን የብራና ገጽ አንብቤ፣ ሌላኛውን ገጽ ለማንበብ በመቻኮል ‹‹ቀጣዩስ?›› ብዬ ጓደኛዬ ላይ አፈጠጥኩ።
‹‹በአይጥ ተበልቶ ተበላሽቷል›› ጥቁር ገጽ እያሳየ መለሰልኝ፡፡
ተበሳጨሁ፤ ነደደኝ፤ ያረፈድኩ መስሎ ተሰማኝ።

Read 8899 times