Monday, 03 April 2017 00:00

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና የ50 ዓመት ራዕዩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

• ከአፍሪካም ጭምር ቴአትርን ለመማር የሚመጣበት ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ታቅዷል
• አገራችን ውስጥ እየተሰሩ ያሉት ቴአትሮች ኢትዮጵያንና ታሪኳን አያውቋትም
• ኢትዮጵያ የሙዚቃ እንጂ የቴአትር ፍልስፍና የላትም

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዓለም የቴአትር ቀንን ሲያከብር ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ከመጋቢት 16-18 ለሶስት ተከታታይ ቀናት፣ 55ኛውን የዓለም የቴአትር ቀን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ቴአትር ቤቶች ከመጡ አርቲስቶችና ምሁራን እንዲሁም ተማሪዎች ጋር አክብሯል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተርና የቴአትር መምህር የሆነው ወጣት አስተዋይ መለሰ፤ የዘንድሮው የቴአትር ቀን አከባበር በጣም ይለያል - ይላል፡፡ እንዴት? ዩኒቨርሲቲው እንዴት የዓለም የቴአትር ኢንስቲቲዩት (ITI) አባል ለመሆን በቃ? ፋይዳውስ ምንድነው? ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ትምህርት ዙሪያ ምን አቅዷል?------ በእነዚህና ተያያዥ
ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከቴአትር መምህሩና ዳይሬክተሩ አስተዋይ መለሰ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡መቼ ነው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር የጀመርከው?
በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ነው የተመረቅሁት፡፡ በዛን ጊዜ ብዙ የስራ እድል አልነበረም፤ቴአትር ቤቶችም እንደሚታወቀው እድል አይሰጡም ነበር፡፡ በግላችን ቡድን መስርተን ለመስራት ሞክረን ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ገንዘብ ስላልነበረን ተሰብስበን መቆየት አልቻልንም፤ ሁሉም በየቤቱ ገባ፡፡ እኔ አክስቴ አዲስ አበባ ስላለች፣ እሷ ጋር ቆይቼ ከአንድ አመት የሥራ እጦት በኋላ ነሐሴ ላይ የድሮው ኢቴቪ፣ የአሁኑ ኢቢሲ በማስታወቂያ አንባቢነት ተቀጠርኩ፡፡ ስራው ዲፕሎማና የስራ ልምድ የሚጠይቅ ነበር፡፡ እኔ ድግሪና ዜሮ የስራ ልምድ ነው ያለኝ፡፡ በሚገርም አጋጣሚ የሰው ሀብት አስተዳዳሪው ሳይኖር ፀሐፊዋ መዝግባኝ ስለነበር እንጂ ጓደኞቼ ድግሪ አንፈልግም ተብለው ተመልሰዋል፡፡ አራት ልጆች አለፍንና ለ10 ወራት ማስታወቂያ ክፍል ከሰራሁ በኋላ ኮንትራት ሰራተኞች በመሆናችን መወዳደር እንችል ነበር፤ ተወዳድሬ እንግሊዝኛ ክፍል በሪፖርተርነት ተቀጥሬ ከአንድ ዓመት በላይ ሰራሁ፡፡ ከዚያ ወደ አማርኛ ክፍል ተጠራሁ፡፡ “ምስራቅ አፍሪካ” ለሚባል ፕሮግራም፣ ዜና ሆስት እንድናደርግ ነበር የተፈለገው። እዚያ ለ8 ወራት ከሰራሁ በኋላ ለቀቅሁ፡፡
 የተሻለ ሥራ አግኝተህ ነው?
መጀመሪያ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ላስተምር እዚያ ካሉ መምህራን ጋር ተነጋግሬ ነበር፡፡ ከዚያ በ2004 መጨረሻ ላይ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ የቴአትር ትምህርት ዲፓርትመንት ሊከፈት ነው ተባለ። እናም ፈተና ሲወጣ ተፈተንኩኝ፡፡ ሶስት ልጆች አልፈን፣ ከ2005 ጀምሮ ቴአትር ዲፓርትመንት ማስተማር ጀመርን፡፡
አሁን በዩኒቨርሲቲው የቴአትር መምህር ብቻ አይደለህም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሹመቱ ከየት ተገኘ?
በጣም ጥሩ! እንዳልሺው ከመምህርነቴ ባሻገር የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነኝ፡፡ ይህ ከየት ተገኘ ላልሺኝ፣ የአሁኑ ፕሬዚዳንታችን ፕሮፌሰር ደጀኔ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የመጡት በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ እኛ ደግሞ የዛሬ ሁለት ዓመት 53ኛውን የዓለም የቴአትር ቀን አክብረን ነበር። በዓሉን ስናከብር ከፕሮፌሰሩ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አለመግባባቱ የተፈጠረው የቴአትር ቀን አይከበርም በሚል ከልክለውን ነው፡፡ በእርግጥ እኛን አያውቁንም፤ እኛም እሳቸውን በመልክ አናውቃቸውም ነበር። ለዚሁ ስራ ነበር ያኔ የዲፓርትመንት ሀላፊና መምህር የነበረችው ሜሮንና እኔ ቢሯቸው የገባነው። እናም ስንጠይቃቸው፤”እናንተ ምን አላችሁና ነው እናክብር የምትሉት?” በሚል ትንሽ ወርፈውን ነበር። በወቅቱ ግቢውም እንደ አሁኑ መልክ አልያዘም ነበር፡፡ “ይሄን ሁሉ አርቲስትና ጋዜጠኛ ጠርታችሁ ግቢያችንን ልታሰድቡ ነው” አሉ፡፡ ከዚያ እንደ ምንም ተብሎ የአለም የቴአትር ቀን ተከበረ። የመጀመሪያው የበዓሉ መክፈቻ ላይ አልመጡም። ችግር ይፈጠራል ብለው ሰግተው ይሆናል ብዬ አስቤያለሁ፡፡ እሳቸው በእርግጥ እንደዚያ አላሉንም፤ ከዚያ በመጨረሻው ቀን መጡ፡፡ ነገሩ እሳቸው ከጠበቁት በጣም በተቃራኒው ሆኖ አገኙት፡፡ በጣም ተደሰቱ፡፡ ፕሮግራሙ እንደ መጀመሪያ ስራ የራሱ ክፍተቶችና ችግሮች ነበሩበት፤ እሳቸው ከጠበቁት ግን በጣም የላቀ ነበር፡፡ በጣም አመሰገኑን፡፡ በወቅቱ እኔ የማስተርስ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ ግቢ ውስጥ እየሰራሁ አልነበረም፡፡
ማስተርስህን ምን ላይ ሰራህ?
‹‹ቴአትርና ዴቨሎፕመንት›› ነው ያጠናሁት። በምረቃ ሰሞን የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ቦታ ሰው አልነበረውም፤ በውክልና የተቀመጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ የመመረቂያዬ ጊዜ ደርሶ ነበር፤ ፕ/ር ደጀኔ አዲስ አበባ መጥተው በቦታው ላይ እንድሰራ ጠየቁኝ፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ መስከረም ላይ እጀምራለሁ አልኳቸው፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ክረምቱ ላይ ተማሪዎችን ያስመርቅ ስለነበር፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንድሰራ ጠየቁኝ፤ ስራውን ተቀብዬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቦታው በውድድር የሚገኝና ለመምህራን የሚሰጥ ነው፤ የተለየ ነገር ካልመጣ በስተቀር በሹመት አይሰጥም፡፡ እኔ ላይ ምን እንዳገኙ አላውቅም፣ ቦታው ላይ ተሹሜ እየሰራሁ ነው፡፡
የዘንድሮውን 55ኛውን የዓለም የቴአትር ቀን፣ ዩኒቨርሲቲያችሁ “እንተዋወቅ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 16-18 አክብሯል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ካከበራችሁት 53ኛው የዓለም የቴአትር ቀን በምን ይለያል? ከዚያን ጊዜ ተመክሮስ ምን ተማራችሁ?
ያን ጊዜ ያከበርነው እንደ ዲፓርትመንት ብቻ ነው፤ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ብቻውን ነው ያከበረው፡፡ ያን ጊዜ ስናዘጋጅ ትኩረት ያደረግነው በእኛ ላይ ብቻ ነው፡፡ የኛ ፕሮዳክሽኖች ነበሩ ለእይታ የቀረቡት፡፡ በእርግጥ ጥናታዊ ጽሁፎች ከተለያየ ቦታ መጥተው ቀርበው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ቀደም ብዬ በነገርኩሽ ምክንያቶች ብዙ ክፍተቶች ቢኖሩብንም፣ የጋበዝናቸው እንግዶች ክፍተቶች ላይ ሳያተኩሩ፣ ጥረታችንን በማድነቅ የሰጡን አስተያየት፣ አሁን ላዘጋጀነው ፌስቲቫል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ያን ጊዜ በዓል ለማክበር እንጂ ለውጥ ያመጣል ብለን አልነበረም፡፡ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንትም አላመነብንም፡፡ ያኔ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት፣ አሁን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ መሀመድ አህመዲን፣ ፕሮግራሙ ሳምንት ሲቀረው፣ “በቃ አንዴ ገብተንበታል፤ የፈለጋችሁትን ጠይቁ” ብለው በጣም እረዱንና እንደሆነው ሆኖ አለፈ። በጣም አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ሆኖም ሚዲያዎችም ልፋታችንን ፕሮሞት አደረጉ፤ አንጋፋ አርቲስቶችም እዚህ ድረስ ተገኝተው አበረታቱን። ከዚያ በኋላ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሲነሳ፣ ቴአትር አብሮ መነሳት ሁሉ ጀመረ፡፡ የዘንድሮው በጣም ይለያል፡፡
እስኪ ልዩነቱን ንገረኝ …
ያን ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ብር ነበረው፡፡ በዓሉን ለማክበር የጠየቅነው 89 ሺህ ብር ብቻ ነው። ከጠየቅነው 89 ሺህ ብር 32 ሺህ ብር ለእንግዳ ማስተናገጃ ተፈቅዶልን፣” ይሄን ሁሉ ብር” ብለው ጮኸውብን ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ለእንግዶች ማስተናገጃ ብቻ 763 ሺህ ብር ነው የተመደበው። ያኔ ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ሳይሆን እምነት ነበር ያጣው፡፡ ዘንድሮ ግን ዩኒቨርሲቲው እንደምታይው በግንባታ ላይ ነው፡፡ አስፓልት ተሻግሮ የምታይው ቲቺንግ ሆስፒታል ተሰርቶ፣ በቀጣይ ዓመት ትምህርት ለመስጠት መምህራን ተቀጥረዋል፡፡ በአጠቃላይ ተቋሙ ብዙ ወጪ ላይ ነው፤ ሆኖም ዩኒቨርሲቲው ይህን ሁሉ ወጪ፣ የህትመትን ጨምሮ ተበድሮ ነው የመደበልን፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአቅም በላይ የገንዘብ ችግር ውስጥ ነው፤ ነገር ግን በእኛም ሆነ በቴአትር ኃይል አምኗል፡፡ ይሄ ውጤት የተገኘው ባለፈው ተሟሙተን ሰርተን በማሳየታችን ነው፡፡ ስፖንሰር ለመጠየቅ ደብዳቤ በትነናል፤ ከተገኘ ተገኘ ካልሆነም እንግዲህ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡
ዘንድሮ ቴአትር የሚስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናታዊ ፅሁፍም ሆነ ፕሮዳክሽን እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል፡፡ እንዳየሽው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ተማሪዎችና መምህራን፣ የጸሃፌ ተውኔት ጌትነት እንየውን ድርሰት ‹‹መንደርተኞቹን›› መድረክ ላይ አሳይተዋል፡፡ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲም በወሎ ባህል ላይ በጥናት የተሰራውን ‹‹ፋቂዎቹ››ን እና በጋሞ ባህል ላይ የተሰራው ‹‹ጋሞታ ወጋ››ን አሳይተናል፡፡ ብሔራዊ ቴአትርም ‹‹የቃቄ ወርዲዩት›› የተሰኘውን ትውፊታዊ ቴአትር፣ ከ70 በላይ ተዋንያኑን ይዞ መጥቶ ለእይታ አብቅቷል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የወልቂጤ፣ የመቀሌ፣ የጂማ፣ የወሎና ሌሎችም የቴአትር ትምህርት ክፍል መምህራን ያቀረቧቸው ፅሁፎች እንዴት ሲያሟግቱ እንደነበር አይተሻል፡፡ ለዩኒቨርስቲያችንም ትልቅ አቅም የሚሆኑ ግብአቶች ተነስተው ውይይቱ ጦፎ ነበር፡፡ አሁን ዩኒቨርስቲያችን እየተንቀሳቀሰ ያለው ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ የልዕቀት ማዕከል ሆኖ ነው። ካችአምናም እንቅስቃሴውን ስንጀምር ይህን አላማ አድርገን ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ የሚገኘው ሞሪቲሞር ዩኒቨርሲቲ፣ ሰዎች ከመላው ዓለም ቴአትር ለመማር ባህር አቋርጠው የሚሄዱበት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ እኛም ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካም ጭምር ሰዎች ቴአትርን ስፔሻላይዝድ ለማድረግ የሚመጡበት ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ነው እቅዳችን፤ይሳካልናል ብለን እናምናለን፡፡
 በቀጣይ 15 ዓመት ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆኑት 10 ዩኒቨርሲቲዎች ወልቂጤ አንዱ እንዲሆን ማድረግ የዩኒቨርሲቲው ራዕይ ነው፡፡ የዛሬ 50 ዓመት ሊሆን ይችላል፤ ከመላው ዓለም ቴአትር ለመማር የሚመጣበት ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ዕቅድ አለ፡፡ መቼም የተለጠጠ ምኞት ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ልዕቀትን ለማምጣት ጥናት ወሳኝ ነው፡፡ ፕሮፌሽናሊዝምም ያስፈልጋል። ፕሮፌሽናሊዝም የሚያድገው በጥናትና በትንታኔ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የቴአትር ቀን ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡት ጥናቶች ትልቅ ግብአቶች ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ ቃል መግባት ቢቸግርም በሚቀጥለው የቴአትር ቀንን ስናከብር፣ የኢትዮጵያን የቴአትር ፍልስፍና ይዘን እንመጣለን፡፡
እስካሁን የኢትዮጵያ የቴአትር ፍልስፍና አይታወቅም ማለት ነው?
ኢትዮጵያ የሙዚቃ እንጂ የቴአትር ፊሎዞፊ የላትም፡፡ የሙዚቃውን ፍልስፍና ስትመለከቺ፤ ቅዱስ ያሬድ ያመጣውን ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይን ታገኛለሽ፡፡ በቴአትር ግን የለም፡፡ እኛ ለተማሪዎቻችን የቴአትር ፍልስፍና ብለን የምናስተምራቸው በጅሮንድ ተክለሀዋርያት ተ/ማሪያም በ1905 ዓ.ም የፃፉት፣ “የአውሬዎች ኮሜዲያ መሳለቂያ” (ፋቡላ) የተሰኘውን ቴአትር ነው፡፡ እንዳየሺው መልቲ ሚዲያ ቴአትር በተባለው አዲስ የቴአትር ጥበብ፣ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ለመድረክ በቅቷል፡፡ ነገር ግን ይሄ ቴአትር የያዘው የራሺያን ፍልስፍና ነው፡፡ የእኛ የቴአትር ፊሎዞፊ ገና አልተገኘም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አልችልም፡፡
አሁን አገራችን ውስጥ እየተሰሩ ያሉት ቴአትሮች ኢትዮጵያንና ታሪኳን አያውቋትም፤ የውጭ ቅጂዎች ናቸው፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከምናያቸው እንደነ “የቃቄ ወርዲዩት”፣ “የቴዎድሮስ ራዕይ”፣ “ህንዴኬ” እና “አደብና” የመሳሰሉ ጥቂት ትውፊታዊ ቴአትሮች በስተቀር፡፡ ፊልሞቹም እንደዛው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝ ቴአትር ይታወቃል፤ እነ ሼክስፒር የሚሰሩት ‹‹ኤልዛቤቲያን›› ነው፡፡ የራሺያ አክቲንግ እነ ስታንላቪስኪ ያመጡት በግልፅ ይታወቃል፡፡ የጃፓን የካቡኪ ቴአትርም እንዲሁ ይታወቃል፡፡ የእነዚህ አገራት ቴአትሮች ዓለም ላይ ገብተው የሚወዳደሩት የራሳቸውን መለያና ቀለም ይዘው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴአትር ምንድን ነው? መልስ የለም፤ ተበርዘን ነው የምንጓዘው፡፡ ለዚህ ነው የትም መሄድ ያልቻልነው። አንድ ነገር ልንገርሽ፤ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ተቀጥቅጠው ተገዝተው፣ የራሳቸው የሚሉትን ባህል አጥተው ሰለባ ሆነዋል፡፡
እኛ የዚህ መጥፎ እጣ ተቋዳሽ ባለመሆናችን ባህል አለን፤ ሁሉ ነገር አለን። ታዲያ የራሳችን ቴአትር ፍልስፍና እንዳይኖረን ያደረገን ምንድን ነው? ብዙ መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ከቀረቡት ጥናቶች አውጣጥተን የኢትዮጵያ የቴአትር ፍልስፍና ምንድን ነው የሚለውን ፈልገን የምናገኘው ይመስለኛል፡፡
በተለያዩ ዩኒቨርሲዎች የቴአትር ትምህርት ክፍል ባልተሟሉ መሰረተ ልማቶች ትምህርት እንደሚሰጥ በቀረቡ ጥናቶች ላይ ተገልጿል፡፡ የእናንተ የቴአትር ትምህርት ክፍል ቀድመው ከነበሩ የትምህርት ክፍሎች የተሻለ ነገር አለው ወይስ ከሌላው ታንሳላችሁ?
በዚህ በኩል ዩኒቨርሲቲያችን በጣም ያነሰ ነው። ብዙ አቅም የለንም፣ ከሌላው የምንሻለው ባለን ቁርጠኝነትና ትጋት ይመስለኛል፡፡ ይሄ ማለት ሌሎቹ አይተጉም፤ ፓሽን የላቸውም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በእኛ ውስጥ ያሉት ተማሪዎችና መምህራን ለሙያቸው ጥልቅ ፍቅር ያላቸውና ቁርጠኞች ናቸው፡፡ በመምህራኑ አንድነትና መተባበር፣ በተማሪዎቹ ድጋፍ ነው ለዚህ የበቃነው። ቁሳቁስን በተመለከተ አሁን ቴአትር እየታየ ያለበት አዳራሽ ለመጋዘንነት የተሰራ ነው፡፡ እንዲሰጠን ለጉራጌ ዞን ፖሊስ እስከመክሰስ ደርሰናል። ከትምህርት ሚኒስቴር በሚሊዮን ብሮች የተገዛን እቃ አውጥተው ሊጨፍሩበት ነው ተብለን በወቅቱ ከነበሩት የግዢ አስተዳደር ጋር ችግር ተፈጥሮ ነበር። አንድ ቆርቆሮ ቤት ሰጥተውን ነበር፤ እዚህ ያለውን ፀሐይ እያየሽ ነው፤ በዚህ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ውስጥ ቴአትር እንዲለማመዱ ማድረግ ተማሪዎቹ እንዲሞቱ መፍረድ ነው ብለን ለበፊቱ ፕሬዚዳንት (አድማሱ ሽብሩ ይባላሉ) ነግረን፣ በእሳቸው ኃይል ነው ይህ አዳራሽ የተፈቀደው፡፡ ይህን መድረክ ለማሰራት ብዙ ፈተና ደርሶብናል፡፡ አልባሳት የተወሰኑ ናቸው፡፡ ለቴአትር ተብሎ ሳይሆን ለብሄር ብሔረሰቦች ተብሎ የተገዛ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ቁስ የለንም፡፡ ልጆቹ ክርኤቲቭ ሆነው ነው የሚሰሩት። ለምሳሌ አምና “ክሊዮፓትራ” የተሰኘ ቴአትር ሰርተው ነበር፡፡ የድሮ ክላሲክ አልባሳት ስለሌለ አፋሮች የሚያገለድሙትን ልብስ በልዩ ፈጠራ ዲዛይን አድርገው ነው የሰሩት፡፡ በደንብ ልብሱን ግን አምጥተውታል፡፡
በአዳራሽ በኩል መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ ነው፡፡
ፕሮፌሽናል አዳራሽ አላቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቁርጡ እኛ እንሻላለን፤ የለም ማለት ይቀላል፡፡ ባህል ማዕከላቸው ጥሩ ነው፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአንድ የዲኤስ ቲቪ መመልከቻ፣ በጣም በሚያሳዝን ቦታ ነው የሚሰሩት፡፡ ሌሎቹም ከዚህ የተሻለ ነገር ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ቴአትር ትምህርት ቤቶች ለሁሉም በዓላት ድምቀቶችነን። ብሄራዊ በዓል፣ የሴቶች ቀን፣ የልማት ስራዎች በዓላት፣ የእጅ መታጠብም ይሁን የኤችአይቪ ቀን ሲመጣ ድምቀቶች ነን፡፡ ግን ለሙያው እውቀት ስለሌለ አይከበርም፡፡
ቴአትር ጥበብ እንደሆነ፣ ትልቅ ሙያ እንደሆነ ማሳየት አልቻልንም፤ እኛም ጋ ጥፋት አለ፡፡ ለዚህ ነው ሙያው ትኩረት ያላገኘው፡፡ እኛ ትምህርት ክፍሉ ሲጀመር እኮ አንድ መፅሐፍ አልነበረንም። እኛ መስከረም 28 ቀን 2005 ተቀጥረን ጥቅምት 15 ነው ተማሪ መቀበል የጀመርነው፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሄደን ኮፒ አድርገን ነው ትንሽ የተረጋጋነው፡፡ ይህን አሟሉልን ስንል፤ “አንተ ቴአትር አውቃለሁ ትላለህ፤ ሼክስፒር እኮ ሽንት ቤት ውስጥ ቴአትር ያሳይ ነበር” ያሉኝ ኃላፊ አሉ፡፡ ሼክስፒር መቼና የት ሽንት ቤት ውስጥ እንዳሳየ ከዚህ ሰው በስተቀር የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ “እስኪ ሰብሰብ በሉና ለከሰዓት አንድ ቴአትር አዘጋጁልን” ብለውን ዱላ ቀረሽ ጠብ የተጣላናቸውም አሉ፡፡ እና ብዙ ፈተና ያለበት ዘርፍ ነው፡፡ በዓል ለማድመቅ ሲሆን ብቻ ነው እኛ የምንፈለገው፡፡
ታዲያ ለምን በየዩኒቨርሲዎቹ ቴአትር ት/ቤቶች ይከፈታሉ? አሁን 8 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ቴአትር እያስተማሩ ነው …
አላውቅም፡፡ ሙያውን ለማሳደግ ተብሎ ከሆነ ሙያው አሁን ባለው መንገድ ሊያድግ አይችልም፤ ስህተት ነው፤ ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ ይህ የመጣው የዘርፉን ጥቅም ካለመረዳት ይመስለኛል። አሁን ችግሩ ስር የሰደደ በመሆኑ በየሚዲያውና በየሚመለከተው አካል ቢሮ እየሄድን ብንጮህ፣ ለእኔ ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ነው፡፡
ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?
መፍትሄው ድንጋዩን ሰብሮ መግባት ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው በስራ ነው፡፡ የድንጋዩን ብልት ማግኘትና መስበር ያስፈልጋል፡፡ ይህን የምናደርገው እኛ ፈላጮች ሆነን ነው፡፡ ድንጋዩ ካልተፈለጠ ሌላ መንገድ የለም፡፡
ዘንድሮ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያን ወክሎ የዓለም የቲያትር ተቋም (ITI) አባል ሆኗል፡፡ እንዴት ዕድሉ ሊገን ቻለ?
እንግዲህ እኛ አንዱን ድንጋይ መስበርና መግባት ችለናል የምንልበት አንዱ ትልቅ የምስራች ይሄው የዓለም የቴአትር ተቋም አባል መሆናችን ነው፡፡ ይህ አባልነት ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡ ለአገሪቱ የቴአትር ዕድገትና ለውጥ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ዓለም ውስጥ የሚደረጉ የቴአትር ልማቶች አሉ፤ እኛም በዚህ ልማት ውስጥ ተካትተን ማለፍ እንችላለን። በኢኮኖሚም ቢሆን ከአባል አገራት ጋር ግንኑነት በመፍጠር ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከትልልቅ የቴአትር ተቋማት፣ የትምሀርት እድል፣ የልምድ ልውውጥና በቁስ ራሳችንን ማደረጃት እንችላለን፡፡
ለምሳሌ እነሱ ተጠቅመው የጣሉትን አንድ ስፖት ላይት ቢሰጡን ለእኛ ምን ማለት መሰለሽ … አንድ ስፖት ላይት ለመግዛት 400 ሺህ ብር ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ ብሄራዊ ቴአትር ያሉት ስፖት ላይቶች በእርዳታ የገቡ እንጂ የተዘጉ አይደሉም፡፡ ይህን መሳሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ እንኳን መግዛት አልተቻለም፡፡ አባል መሆናችን በጣም ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ቴአትር በትልልቅ ባለሙያዎችና በከፍተኛ በጀት ጥናት እንዲደረግም እድል ይፈጥራል፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ቢፈጠርና የዓለም ቴአትር ቀን እዚህ አገር ቢከበር፣ ብዙ ዶላሮች እዚህች አገር ላይ ይቀራሉ፡፡ ይሄ ሁሉ እድል ይኖራል፡፡ አባል እንድንሆን ሂደቱን የዛሬ ሁለት ዓመት የጀመረው ጋሽ ደበበ እሸቱ ነው፤ ተቀብለውናል ገና ከአሁኑ አንዳንድ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
አንተ በግልህ ቴአትር የት ደርሶ ማየት ትፈልጋለህ?
እኔ አሁን ሐምሌ ላይ 29 ዓመት ይሞላኛል፡፡ ቢያንስ በእኔ ዕድሜ ቴአትር ተከብሮ ማየት በቂዬ ነው፡፡ አንድ ነገር የሚከበረው ጥቅሙ ሲታወቅ ነው፣ ሲወደድ ነው፤ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ አሁን ቴአትር ሸቀጥ ሆኗል፡፡ በቴአትር ድሮን እየናፈቅን ነው፤ የድሮ ባለሙያዎች ሙያቸውን ስለሚያስቀድሙ፣ ለሙያው መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡  
የድሮ ሰው ለሙያው ቅድምያ እንደሚሰጥ በተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ አይተናል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል መድረክ ላይ ጋሽ ተስፋዬ የዛሬ 50 ዓመት የሰራውን “ሀምሌት”ን ያለምንም መደናቀፍ መነባንቡን አቅርቦልናል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ሙያው ምን ያህል ከስጋና ደሙ ጋር እንደተቀላቀለ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሙያውን የሚያከብር ትውልድ ሆነን ማየት እመኛለሁ፡፡
በመጨረሻ …
በመጨረሻ ለዚህ በዓል መሳካት ከልብ የደከሙትን፣ ለበዓሉ አስተዋፅኦ ለማድረግ ከተለያየ ቦታ እዚህ የተሰበሰቡትን አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች፣ የቴአትር መምህራንና ተማሪዎች፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች፣ አላማችንን ደግፈው የመጡ ጋዜጠኞች፣ የስራ ባልደረቦቼንና ተማሪዎቼን በሙሉ ለፕሮግራሙ ስኬት የማዕዘን ድንጋይ ነበራችሁና አመሰግናችኋለሁ እላለሁ፡፡  
Read 603 times