Monday, 03 April 2017 00:00

ቦብ ዲላን ከ5 ወራት በኋላ የኖቤል ሽልማቱን ለመቀበል ተስማማ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ2016 የኖቤል ሽልማት በስነጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊ የሆነውና ስራ ስለበዛብኝ ሽልማቱን ለመቀበል አልችልም በማለት በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ የቀረው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ቦብ ዲላን፣ ከወራት ማንገራገር በኋላ ሰሞኑን ሽልማቱን ለመቀበል መስማማቱ ተዘግቧል፡፡
ባልተለመደ ሁኔታ ስለ ሽልማቱ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጥ በመቆየቱና ሽልማቱን ባለመቀበሉ ብዙዎችን ሲያነጋግር የቆየው ቦብ ዲላን፤ አሸናፊነቱ በይፋ ከታወጀ ከአምስት ወራት በኋላ ስቶክሆልም ወደሚገኘው የኖቤል ተቋም በማምራት ሽልማቱን ለመቀበል መወሰኑን ቢቢሲ ገልጧል፡፡
የ75 አመቱ ቦብ ዳይላን በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ በስቶክሆልም ሁለት የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንደሚያቀርብ የጠቆመው ዘገባው፣ እግረ መንገዱን  የ900 ሺህ ዶላር ሽልማቱን ይቀበላል ተብሏል፡፡
በተቋሙ ህግ መሰረት የኖቤል ተሸላሚ የሆነ ሰው በአንድ ዩኒቨርሲቲ በእንግድነት ተጋብዞ ትምህርት ካልሰጠ የሽልማት ገንዘቡን እንደማያገኝ ያመለከተው  ዘገባው፤ ዲላን ግን በአካል ተገኝቶ ለማስተማር እንደማይችል ጠቁሙ ይሄም ሆኖ ግን ትምህርቱን በቪዲዮ ቀርጾ ለማስተላለፍ ማቀዱን ገልጧል፡፡
ዲላን በኖቤል የስነጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያው አሜሪካዊ የዘፈን ግጥም ደራሲ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ በ1993 በስነጽሁፍ ዘርፍ ከተሸለመው የረጅም ልቦለድ ደራሲው ቶኒ ሞሪሰን በመቀጠል በዘርፉ ለሽልማት የበቃ አሜሪካዊ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

Read 1191 times