Monday, 03 April 2017 00:00

ሒልተን ሆቴልና ቡክ ወርልድ ልዩ የፋሲካ ፕሮግራም አዘጋጁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ሒልተን አዲስ አበባ ሆቴልና ቡክ ወርልድ በመተባበር ለሁለተኛ ጊዜ ልዩ የፋሲካ የመዝናኛና የመፅሐፍት አውደ ርዕይ አዘጋጁ፡፡ ሰዎች በፋሲካ ዋዜማና ከዚያም በኋላ ሒልተን ባዘጋጀው ልዩ መዝናኛ ከቤተሰባቸው፣ከፍቅረኛቸውና ከትዳር አጋራቸው ጋር በመሆን የተሰናዳውን  የምግብና የመጠጥ ድግስ እየተቋደሱ እግረ መንገዳቸውንም በትልልቅ ደራሲያን የተፃፉ የአገር ውስጥና የውጭ መፅሐፍትን ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው እየገዙ መሄድ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን የሂልተን ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ክላውስ ስቴይነርና የቡክ ወርልድ (ሻማ ፒኤልሲ) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስፍሀ ተስፋዬ ባለፈው ረቡዕ በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ሆቴሉ ዓለም አቀፍ የምግብ ቡፌ፣ የወይን ጠጅ፣ ቢራና የመድረክ ቀጥታ መዝናኛ ያዘጋጀ ሲሆን ለልጆች እንደየእድሜያቸው ማቆያ፣እንዲሁም ፊታቸውን በቀለም የማሸብረቅና መሰል መዝናኛዎችን አሰናድቷል ተብሏል፡፡  
ቡክ ወርልድ በበኩሉ፤ከ3ሺህ በላይ ከውጭ የሚያስገባቸውን የልብወለድ፣ የሳይኮሎጂ፣ የፖለቲካና የልጆች መፅሐፍት የሚያቀርብ ሲሆን ዋጋውም በየመደብሩ ከሚሸጥበት በቅናሽ እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 15 2009 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ የመፅሐፍ አውደ ርዕይ፣ለጎብኚዎች የተለያዩ የመፅሐፍት ሽልማቶች የሚበረከቱ ሲሆን ቡክ ወርልድ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ከሂልተን ጋር በትብብር መስራቱን  እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
“አፍቄሜሌፅ” የግጥም ሲዲ ሰኞ ይመረቃል
የገጣሚ በላይ በቀለ ወያ “አፍቄሜሌፅ” የተሰኘ የግጥም ሲዲ ከነገ በስቲያ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ አንዱዓለም ይስሀቅ፣ ፍቃዱ ጌታቸው፣ ረድኤት ተረፈ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ሚካኤል ምናሴ፣ ደስታ ነጋሽ፣ አቤል አያሌውና ኢዮብ ሙሴ ግጥሞቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ዮሐንስ ተ/ማሪያም ለታዳሚው ወግ እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
ገጣሚው በ2006 ዓ.ም “እየሄዱ መጠበቅ” እና በ2008 ዓ.ም "እንቅልፍና ሴት” የተሰኙ የግጥም መድበሎች ለአንባቢ ማድረሱ ይታወሳል፡፡
"ሴቶች ይችላሉ" ማህበር አንጋፋ ሴቶችን ሸለመ
“ሴቶች ይችላሉ” (women can do it) ማህበር የዘንድሮውን "የሴቶች ቀን" ምክንያት በማድረግ “ጣዝሙቶቻችንን እናመስግን” የተሰኘ የኪነጥበብና የሽልማት ፕሮግራም ከትላንት በስቲያ አካሂዷል፡፡ የኪነጥበብ ዝግጅቶቹ በወንዶች የተከወኑ ሲሆን ግጥም፣ የክራር ድርደራ፣ “ትችያለሽ” የተሰኘ ቴአትርና ስታንዳፕ ኮሜዲ ለታዳሚው ቀርቧል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ 20 ያህል አንጋፋ ሴቶች የተሸለሙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት ኮሚሽነር የአለም ፀሐይ ካሳ፣ የ91 ዓመቷ የእድሜ ባለፀጋና የመጀመሪያዋ የፋሺን ዲዛይነር ወይዘሮ ፅዮን አምዶም፣ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ዕሌኒ መኩሪያና በኢትዮ ቴሌኮም የሴቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ የአለም ስዩም ይገኙበታል፡፡ እናቷ እውቅ ሰዓሊ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓት የቴአትር መምህርና በ"የማለዳ ኮከቦች" የተሰጥኦ ውድድር ላይ  በዳኝነት የምትሰራው የእናቷ ውጤት በመሆኗ፣የዕለቱ ብቸኛ ወጣት ተሸላሚ መሆኗንም ማህበሩ ገልጿል፡፡ 

Read 852 times