Saturday, 01 April 2017 00:00

ካርሎስ ቀበሮው ለ3ኛ ጊዜ በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ካርሎስ ቀበሮው በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀውና ከአለማችን ቀንደኛ ገዳዮች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ኢሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ፣ ከ43 አመታት በፊት በፓሪስ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ባለፈው ማክሰኞ ለ3ኛ ጊዜ የዕድሜ ልክ እስራት ቅጣት እንደተጣለበት አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1974 የተከሰተውንና 2 ሰዎች ለሞት፣ 34 ሰዎች ደግሞ ለመቁሰል አደጋ የተዳረጉበትን የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ክስ ተመስርቶበት ፓሪስ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበውና ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ የተከራከረው ካርሎስ፤ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ተጨማሪ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበት ዘገባው ገልጧል፡፡
ካርሎስ ችሎቱ ከመሰየሙ ከሰዓታት በፊት፣ “ይህ እጅግ የሚገርምና ከአራት አስርት አመታት በፊት ተፈጸመ በተባለ ወንጀል ላይ የሚከናወን ወለፈንዲ የሆነ የፍርድ ሂደት ነው” በማለት ችሎቱን ያጣጣለ ቢሆንም፣ የዕድሜ ልክ እስራት ፍርዱ መወሰኑንና ይህን ተከትሎም ጠበቆቹ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ማስታወቃቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ከ23 አመታት በፊት በፈረንሳይ ልዩ ሃይል ክትትል በካርቱም በቁጥጥር ስር የዋለው ቬንዙዋላዊው አደገኛ ገዳይ ካርሎስ በ1970 ዎቹ እና 80 ዎቹ በፈጸማቸውና ባስፈጸማቸው በርካታ የግድያ ወንጀሎች ለሁለት ጊዚያት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ከዚያ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ የ67 አመቱ ካርሎስ፣ ከሳምንታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ሙያህ ምንድን ነው በሚል ከችሎቱ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “ብቁ አብዮተኛ” ሲል ምላሽ የሰጠ ሲሆን ዕድሜውን ሲጠየቅም፣ “17 ነው፤ ደስ ካላችሁ 50 አመት ጨምሩበት” ሲል ማላገጡን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1647 times