Monday, 03 April 2017 00:00

እንግሊዝ የስኮትላንድን አዲስ የመገንጠል ዕቅድ አልተቀበለቺውም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የስኮትላንድ ፓርላማ አገሪቱ ከብሪታኒያ ለመገንጠል የሚያስችላትን ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ ለማድረግ የያዘቺውን አዲስ ሃሳብ ባለፈው ማክሰኞ በአብላጫ ድምጽ መደገፉን ተከትሎ፣ የእንግሊዝ መንግስት የመገንጠል ዕቅዱን እንደማይቀበለው ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አገሪቱ ከብሪታንያ ለመገንጠል የሚያስችላትን ህዝበ ውሳኔ በመጪው አመት መጨረሻ ለማከናወን የሚያስችላትን ፈቃድ ከእንግሊዝ ለማግኘት ማሰቧን የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጂን የገለጹ ሲሆን የእንግሊዝ መንግስት ግን በዚህ እቅድ ዙሪያ እንደማይደራደር አስታውቋል፡፡
የስኮትላንድ ፓርላማ ለሁለተኛ ጊዜ የመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ይደረግ በሚለው የሚኒስትሯ ሃሳብ ላይ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት፣ ሃሳቡን 69 ለ59 በሆነ አብላጫ ድምጽ ቢያሳልፈውም የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ግን፣ ዕቅዱን እንደማይቀበሉትና ድርድር እንደማያደርጉበት አስታውቀዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ቃል አቀባይ፤ “የመንግስት የወቅቱ ዋነኛ ትኩረት አገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ለመውጣት የጀመረቺው እንቅስቃሴ ነው፤ የስኮትላንድ የመገንጠል ጥያቄ የወቅቱ የመንግስታችን አጀንዳ አይደለም” ማለታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የስኮትላንድ ህዝብ እንግሊዝ ከአውሮፓ ጋር የሚኖራትን ቀጣይ ግንኙነት በተመለከተ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን ባላገኘበት ሁኔታ ይህንን እጅግ ቁልፍ ውሳኔ እንዲያሳልፍ መጠየቅ ፍትሃዊ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡
ስኮትላንድ በ2014 ከብሪታኒያ ለመገንጠል ያካሄደቺው ህዝበ ውሳኔ የብዙኃኑን ድጋፍ ባለማግኘቱ አገሪቱ ሳትገነጠል መቅረቷ ይታወሳል፡፡

Read 3784 times