Saturday, 01 April 2017 14:54

ፅንስ ማቋረጥና ጥርስ መንቀል ለየቅል

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በርእስነት ያስቀመጥነው አባባል የዚህ አስተያየት አቅራቢ ነው፡፡ ይድረስ ለላንቺና ላንተ አምድ ዝግጅት ብለው ያደረሱን አስተያየት ከዚህ የሚከተለው ነው፡፡
“ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ‘በህብረተሰብ’ አምድ ላይ ‘ፅንስ ማስወረድ ጥርስ የመንቀል ያህል ቀሏል’ በሚል ርዕስ ስለፅንስ ማቋረጥ ፅሁፍ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ፅሁፉ ጥንቃቄ የጐደለውን የፅንስ ማቋረጥ በመከላከል ረገድ ያለውን ሁኔታና መሻሻል ያለበትን ጉዳይ አስነብቧል፡፡ የጽሁፉ ርእስ አመራረጥም ምንጭ ካደረጋቸው ሰዎች የተገኘ ለመሆኑ በተለያየ መንገድ ተገልጾአል፡፡ ነገር ግን ምንጮች ያሉት አባባል  መነፃፀር የሌለባቸውን ጉዳዮች ያነጻጸረ ነው፡፡ በመሰረቱ ፅንስ ማቋረጥና ጥርስ ማስነቀል ለየቅል ስለሆኑ በምንም መመዘኛ የሚነፃፀሩ ጉዳዮች አይደሉም። በሙያነታቸው አንዳቸው ከሌላኛው የማይበልጡ ወይም የማያንሱ የተከበሩ ሙያዎች ናቸው፡፡ በሕክምናው ዘርፍ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ የሙያና የአሠራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥበብ ያላቸው ናቸው፡፡ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት የራሱ የሆነ የሰለጠነ ባለሙያና ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ተቋምና የአገልግሎት መስጫ መሣሪያዎችና መድሃኒቶች ያስፈልጉታል፡፡ ጥርስ ማስነቀልም በመጣጥፉ ውስጥ እንደቀረበው ቀላልና በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይሆን ልክ እንደ ፅንስ ማቋረጡ የራሱ ባለሙያና ግብአቶች የሚያስፈልጉትና በጥንቃቄ የሚካሄድ መሆኑን አንባቢ ልብ ሊለው ይገባል። ይህንኑ የብዙቼንን ችግር የጥቂቶች እንደሆነ በማስመሰል ዘግናኝና ሰቅጣጭ በሆኑ ቃላትና አገላለጾች ማቅረብ ችግሩንም ሆነ የችግሩ ተጠቂዎችን አሳንሶ ወደማየት ሊያመራ ይችላል። ለምሣሌ አገልግሎቱን የሚሰጠውን ተቋም ‘ቤቢ ስቶፕስ’ የአገልግሎቱ ፈላጊዎችን ደግሞ ‘ነጠላ ዜማዋን ከምትለቅ ብናስፈነጥረው አይሻላት አገልግሎት ሰጪዎችንና ተቀባዮችን አውራጆችና አስወራጆች’ ብሎ ማቅረብ ለድርጊቱ ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው ያስመስላል፡፡ በዚህ እትም እንደተገለጸው በደላሎች አገናኝነት የጽንስ ማቋረጥን ተግባር ዛሬም በየመንደሩ የሚፈጽሙ ሰዎች ካሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ምስክርነቱን የሚሰጡላቸው ሰዎችም ይልቁንም ጉዳዩን ወደ ህግ አቅርበው እርምጃ እንዲወሰድ ቢያደርጉ የዜግነት ድርሻቸውን የሚወጡ ይመስለኛል፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና ተከሰተ ብለው ባልተጠበቀ መንገድ ጽንሱን ለማቋረጥ የሚሄዱ ካሉ... እነሱም ቢሆኑ በህግ በተደገፈ በባለሙያና በጤና ተቋም ደህንነቱ የተጠበቀ ያውም በነጻ ጽንስን ማቋረጥ ስለሚችሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ መጣል እንደሌለባቸው አስተያየን እለግሳለሁ፡፡ የላንቺና ላንተ አምድ አዘጋጆች በዚሁ አጋጣሚ በአሁኑ ወቅት የጽንስ ማቋረጥ ሂደት ምን እንደሚመስል ባለሙያ አነጋግራችሁ ብታስነብቡን ጥሩ ይመስለኛል፡፡
        ቤተልሔም ተሾመ
የዚህ አምድ አዘጋጅ በደረሳት ጥቆማ መሰረት በአሁኑ ወቅት በጽንስ ማቋረጥ ዙሪያ ያሉት እውነታዎች ምን ይመስላሉ? ስትል በአይፓስ ኢትዮጵያ ዶ/ር አብዩት በላይን እና አቶ ደረጀ ወንድሙን አነጋግራለች፡፡ ዶ/ር አብዮት በላይ በአይፓስ ኢትጵያ ከፍተኛ ጤና አማካሪ ሲሆኑ አቶ ደረጀ ወንድሙ ደግሞ በዚሁ መስሪያ ቤት የፖሊሲ አማካሪ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ይፀንሳሉ ተብለው ከሚገመቱ ሴቶች መካከል 38 ከመቶ ያህሉ ሳያቅዱ ወይም ያለፍላጐታቸው እንደሚፀንሱ በአለን ጉት ማኸር ኢንስቲትዩትና አጋሮቹ እ.ኤ.አ. 2014/ በፅንስ ማቋረጥ ላይ የተካሄደ አንድ አገር አቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡ በዕድሜ ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሆኑ 1000/ ሴቶች መካከልም 28ቱ ፅንስ ለማቋረጥ እንደሚገደዱ ይሄው ጥናት አስረድቷል፡፡ በጥናቱ መሠረት በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው በዓመት በአማካይ 345/ ያህል ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንስ ለማቋረጥ ሞክረው ለድህረ ውርጃ ህክምና የመጡ ሴቶችን ያስተናግዳሉ፡፡ በተለይም በጠና ታመው ለድህረ-ውርጃ ህክምና ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ 100000/ ሴቶች መካከል 628ቱ እንደሚሞቱ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ለሴቶች ሞት ምክንያት ከሚሆኑት ዋና ምክንያቶች መካከል ጥንቃቄ የጐደለው ፅንስ ማቋረጥ አንዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር የተያያዙ የሴቶችን ህመምና ሞት ለመቀነስ የተሻሻሉና ፅንስ ማቋረጥን የሚመለከቱ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎችን አዛብቶ ማቅረብም ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሣሌ አስተያየት ሰጪዋ በተገለጸው እትም ላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ የመጨረሻ አንቀጽ ውስጥ ‘አንዲት ሴት ውርጃን መፈፀም የምትችልባቸውን ምክንያቶች ያሰፈረው ሕጉ ሴቲቱ ውርጃ ለመፈፀም የምትፈልግበትን ምክንያት እንድትገልጽ አትገደድም ሲል ውርጃን በግልፅ መፍቀዱንም መከልከሉንም የማያሳይ አንቀጽ አክሎበቭል’ የሚለው አገላለጽ ብዥታን ይፈጥራል፡፡
መንግሥት ከወሊድና ከእርግዝና ጋር የተያያዙ የእናቶችን ሕመምና ሞት ለመቀነስ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕጉ ውስጥ ፅንስ ማቋረጥን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በ1997 ዓ.ም. እንዲሻሻሉ አድርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በ1998 ዓ.ም. በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዝርዝር የቴክኒክና የአፈፃፀም መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ የፅንስ ማቋረጥ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛው ዓላማ ጥንቃቄ በጐደለው የፅንስ ማቋረጥ የተነሳ የሚደርሰውን አላስፈላጊ የእናቶችን ህመምና ሞት ለመቀነስ ሲሆን በተጨማሪም የሚከተሉትን ምክንያቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ እነሱም በርካታ ሴቶች በቤተሰብ ዕቅድ መረጃና አገልግሎት ባለማግኘት ላልተፈለገ እርግዝና የሚጋለጡ በመሆኑ ፅንስ ማቋረጥን በሕግ መከልከል ጥንቃቄ የጐደለውን ፅንስ ማቋረጥ የሚያባብስ በመሆኑ ፅንስ ማቋረጥን ለመቀነስ መፍትሄውበሕግ መከልከል ሳይሆን ሴቶችና ወንዶች ስለአካላቸው ተገቢ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ እና የቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራምን ማስፋፋት መሆኑን በመገንዘብና ጥንቃቄ የጐደለውን ፅንስ ማቋረጥ ለማከም የሚወጣው ወጪ በሴቷም ሆነ በጤና ተቋማት ላይ ጫና የሚያሳድር መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
ስለ ተዋልዶ ጤና የተሟላ መረጃ የሌላቸውና አስተማማኝ የእርግዝና መከላከያ የማያገኙ ሴቶች ላልታቀደ እርግዝና የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ፅንስ ማቋረጥ በሕግ ቢፈቀድም ባይፈቀድም ፅንስ ለማቋረጥ የወሰኑ ሴቶች ያጋጠማቸውን ያልቭቀደ እርግዝና ከማቋረጥ ወደኋላ አይሉም፡፡ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች በማይኖሩበት ወይም በመከላከያዎቹ መጠቀም በህዝቡ አመለካከት የማይደገፍ ከሆነ ወሊድን ለማዘግየት ወይም ለመከላከል የሚፈልጉ ሴቶች ፅንስ ማቋረጥን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈጽሙ ጥናቶች ያመለክቭሉ፡፡ በሌላ በኩል ፅንስ ማቋረጥ በከፍተኛ ደረጃ ይፈፀምባቸው የነበሩ ያደጉ አገሮች የእርግዝና መከላከያ በማስፋፋታቸውና በተሳካ ሁኔቭ ሥራ ላይ በማዋላቸው ፅንስ ማቋረጥ እየቀነሰ መምጣቱን ከጥናቶች መገንዘብ ተችሏል። በመሆኑም ፅንስ ማቋረጥን በሕግ መፍቀድና አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ሴቶች ፅንስ በማቋረጥ እንዲተማመኑና እንደወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙበት ሊያደርግ አይችልም፡፡ ፅንስ ማቋረጥን ለመከላከል መፍትሄው በሕግ መከልከል ሳይሆን ሴቶችና ወንዶች ስለአካላቶቻቸው በደንብ እንዲገነዘቡ ማድረግና የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በማስፋፋት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ነው፡፡ ሴቶች የእርግዝና መከላከያን በአጥጋቢ ሁኔቭ በሚጠቀሙበት ጊዜ የፅንስ ማቋረጥ ክስተት ይቀንሳል፡፡
በአንዳንድ አገሮች ፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊ መደረጉን ተከትሎ የፅንስ ማቋረጥ ክስተት የጨመረ መስሎ እንደሚታይ የሚጠቁሙ አሃዛዊ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ድርጊቱ ጨምሮ ሳይሆን ቀደም ሲል በሕገወጥ መንገድና በድብቅ ሲሠራ የቆየው የፅንስ ማቋረጥ ተግባር በህጋዊ መንገድ በግልጽ መከናወን በመጀመሩና ሳይደበቅ ሪፖርት በመደረጉ ነው፡፡
ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝና ሲገጥማቸውና ፅንስ ለማቋረጥ ሲወስኑ ደህንነቱ የተጠበቀ ሕጋዊ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት ካላገኙ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ምርጫቸውን ለመፈጸም ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም ፅንስ ማቋረጥን በሕግ ባልገደቡ አገሮች የክስተቱ መጠን በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ድርጊቱን በሕግ በከለከሉ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የጐደለው የፅንስ ማቋረጥ ተግባር እንደሚካሄድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም የፅንስ ማቋረጥ ዕድልን በሕግ በፈቀዱ አገሮች ውስጥ ጥንቃቄ በጐደለው የፅንስ ማቋረጥ ምክንያት የሚሞቱ ሴቶችን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏል። በዚህ ረገድ የአገራችን ኢትዮጵያ ልምድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለምሣሌ ያህልም ከጤና ጥበቃ በተገኘ መረጃ መሠረት በ1998 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጥንቃቄ በጐደለው ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር 32 በመቶ የነበረ ሲሆን ሕጉ ከተሻሻለ ከ10 ዓመት በኋላ ግን ይህ አሃዝ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
የጤና ጥበቃ የአፈፃፀም መመሪያው የጤና ባለሙያው በቅን ልቦናው ሙያውን ተግባራዊ እንዲያደርግ ሰፊ ሥልጣን የሰጠው እንደማንኛውም ሌላ ህመም ሲሆን የግል አመለካከቱ ሳያግደው ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ያመለክታል እንጂ ሴቶች ስለጠየቁ ብቻ አገልግሎቱን ያገኛሉ ማለት አይደለም፡፡ ሕጉ በመደፈር ወይም ከቤተዘመድ ጋር በተደረገ ግንኙነት ለተከሰተ ፅንስ ማስረጃን ለማቅረብ በሚወስደው ጊዜ መራዘም ምክንያት ሴቶች ጥንቃቄ በጐደለው መንገድ ውስብስብ ወደሆነ የጤና ችግር ውስጥ እንዳይገቡ በማሰብ በተለየ ሁኔታ እንዲታይ አድርጓል። ይኸውም በመደፈር ወይም ከዘመድ ጋር በተፈፀመ የግብረ-ስጋ ግንኙነት አረገዝኩ ያለች ሴት የደፋሪውን ወይም የዘመዷን ማንነት ለመግለጽ እንደማትገደድ በሕጉ መብት ተሰጥቷታል። በተመሳሳይ ሁኔ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆናቸው ወጣት ሴቶች የዕድሜያቸው ትክክለኛነት የሚገልጽ ማስረጃ ለማቅረብ እንደማይገደዱ በሕጉ ተመልክቷል፡፡

Read 14302 times