Monday, 03 April 2017 00:00

የቼስ ስፖርት እንዲስፋፋ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የማዘጋጀት ጥረቶች መቀጠል አለባቸው
• በትምህርት ቤቶች፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በወጣት ማዕከላት መዘውተር አለበት፡፡


በጅማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ዞን 4.2  የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና ነገ ይፈፀማል፡፡ የጅማ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አህጉራዊ ሻምፒዮናው በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዳቸው በኢትዮጵያ የቼስ ስፖርት እንዲስፋፋ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ በሻምፒዮናው የተሳተፉ ተወዳዳሪዎችን በጅማ ከተማ ተገኝተን እንዳነጋገርናቸው የጅማ ከተማ የውድድር መስተንግዶ እንዳስደሰታቸው፤ ይህን ተመክሮ ተጠቅሞ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ጥረቶች መቀጠል እንዳለባቸው፤ በትምህርት ቤቶች፤በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በወጣት ማዕከላት ስፖርቱ መዘውተር እንደሚኖርበት፤ የቼስ ስፖርት ስልጠናዎች በየትምህርት ቤቱ በተለይ ለታዳጊዎች በተደጋጋሚ መሰጠት እንዳለባቸው፤ እና የተለያዩ ክለቦች ተመስርተው ውድድሮች በሳምንቱ የእረፍት ቀናት እየተካሄዱ መጠናከር እንደሚኖርባቸው መክረዋል፡፡ በዞን 4.2  የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና የሚያሸንፉት  ተወዳዳሪዎች በቼስ  ዓለም አቀፍ የማስተርስ ማእረግ ከመጎናፀፋቸውም በላይ፤ በባቱም፤ ጆርጂያ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና አፍሪካን በመወከል እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
 የኬንያ ቼስ ፌደሬሽንን በመወከል የሚወዳደረው ሪኪ ሳንግ፤ በአህጉራዊው ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉ አገራትና የተወዳዳሪያቸው ብዛት እንዳስደሰተው ለስፖርት አድማስ ገልጿል፡፡ የጅማ ከተማ የእንግዳ አቀባበል፤ የጅማ ዩኒቨርስቲ ድጋፍ እና የተማሪዎቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጅማ ቼስ ማህበረሰብ አስተዋፅኦ የሚመሰገን ነው ብሏል፡፡
በኬንያ በቼስ ስፖርት ያሉ ተመክሮዎችን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ ሪኪ ሳንግ ምላሽ ሲሰጥ፤ በኬንያ ስፖርቱን ባንኮች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ክለቦችን በማቋቋም ይደግፉታል ብሏል፡፡ 16 ክለቦች የሚሳተፉበት ዓመታዊ የቼስ ሊግ መኖሩን፤ እድሜያቸው ከ6 ዓመት እስከ 8 ዓመት የሚሆናቸውን ታዳጊ ህፃናት በቼስ ስፖርት ስልጠናዎች የሚያሳትፉ አገር አቀፍ ተቋማት መኖራቸውን፤ በየትምህርት ቤቶች በተለያዩ ግዚያት ውድድሮች የሚካሄድባቸውን ልምዶች የጠቀሰው ሪኪ ሰንግ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተመክሮ የሚሆኑ ናቸው ብሏል፡፡ በተለይ ስለ ኬንያ የቼስሊግ ተጨማሪ ማብራርያ ሲሰጥ 16 ክለቦች በክፍያ ተመዝግበውሲወዳደደሩ እያንዳንዱ ክለብ በስሩ 8 ተወዳዳሪዎችን በማስመዝገብ መሆኑን አስገንዝቦ፤ ሊጉ ጥሩ ሽልማት የሚገኝበት እና ተወዳዳሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ከሙያቸው ባሻገር እያዘወተሩት የሚገኝ አዝናኝ የስፖርት መድረክ ነው ሲል ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡
በ2016 በአዘርባጃን ተደርጎ በነበረው 42 የዓለም ቼስኦሎምፒያድ አፍሪካውያን ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ያመለከተው ሪኪ ሳንግ ያስታውሳል በጅማ ከተማ የተካሄደው የዞን ሻምፒዮና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች በማዘጋጀት በስፋት እንዲሰሩ ያነቃቃል፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ዓለም አቀፍደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እና በአህጉራዊ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት በመንተራስ ተጨማሪ የቼስ ውድድድሮችም በሚቀጥሉት 5እና10 ለ ዓመታት ማስተናገድ ትችላለች ሲል ተናግሯል፡፡ ሌላው የኬንያ ቼስ ተወዳዳሪ በስፖርቱ ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ፒተር ጊልሬዝ ናቸው፡፡ ሚስተር የቼስ ስፖርት ዕድሜ፣ ፆታ እና ሙያ የማይለይ ሁሉንም የሚያሳትፍ ስፖርት በማለት ገልፀውታል፡፡
በኬንያ ቼስ ፌደሬሽን ተወካይነት በዞኑ ሻምፒዮና ላይ ከተሳተፉት መካከል የ21 እና የ14 ዓመት ወንድምና እህት ይገኙበታል፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ሳንዲያ ዴሽፓንዴ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት ልጆቻቸቸው በዝንባሌ የጀመሩት ስፖርት በአህጉራዊ ደረጃ በሚካሂዱ ሻምፒዮናዎች እንዲሳተፉ እና በተወዳዳሪነት ዓለም በሚዞሩበት ደረጃ ስላደረሳቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ ላለፉት 6 ዓመታት በልጆቻቸው ደጋፊነት በተለያዩ አገራት ዞረው ከፍተኛ የህይወት ልምድ አግኝቻለሁ ይላሉ፡፡ የቼስስፖርት ልጆቼን ጎብዝ እና ውጤታማ ተማሪዎች አድርጓቸዋል የሚሉት ወይዘሮ ሳንዲያ፤ በክፍል ደረጃቸው ሁልግዜም የላቀውጤት ከማስመዝገባቸውም በላይ በስነምግባራቸው በስነስርዓታቸው የተሻለ ስብእና አትርፈውበታል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ቤተሰቦች ልጆቻቸው የቼስ ስፖርት በትምህርት ቤታቸው፤ በመኖርያቸው እና በመዝናኛ ስፍራዎቻቸው እንዲያዘወትሩ ማበረታታት አለባቸው ሲሉ መክረዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የቼስ ፌደሬሽን ማስተር ማዕረግ ያለው ኡጋንዳዊው ሃሩና ናዙቡጋ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው የጅማ ከተማ ገና ለመጀመርያ ጊዜ ባስተናገደችው አህጉራዊ ሻምፒዮና ገና ከጅምሩ የታየው ስኬትወደፊት በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሻምፒዮናዎች በጥሩ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን ገልጿል፡፡
ብዙዎች ቼስን እንደ ጨዋታ ይመለከቱታል ግን ትክክል አይደለም ያለው ሃሩና፤ ቼስ የዓዕምሮ ስፖርት ብቻ ሳይሆን የላቀ አስተሳሰብና እውቀት ለመቅሰም የሚያግዝ፤ በስነምግባር እና በሞራል የታነፀ ስብእና ለማግኘት እና የአኗኗር ዘይቤን ለመፍጠር፤ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ውድድር እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል ሲል ይናገራል፡፡
በስፖርቱ አይነት ትልቁ የሚባለው የቼስ ኦሎምፒያድ ወደ አፍሪካ ቢመጣ ያስደስታል ያለው ሃሩና፤ ይህን ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ወደ አህጉሪቱ ለማምጣት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው የቀድሞው የሊቢያ መሪ ጋዳፊ እንደነበሩ አስታውሶ፤ ወደፊት ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ወይም ኢትዮጵያ የተለያዩ የቼስ ውድድሮችን በአህጉራዊ   እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማዘጋጀት እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል፡፡
ለ20 ዓመታት በቼስ ተወዳዳሪነት የቆየው ደሳለኝ ፈቃዱ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት የዓለም ቼስ ፌደሬሽን እጩ ማስተር የነበረበትን ደረጃ በዞኑ ሻምፒዮና እየተወዳደረ እንደሆነ ይገልፃል የዓለም ቼስ ፌደሬሽን ማስተር ያላቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡ በጀርመን፤ በራሽያ፤ በቱርክ እና በአዘርባጃን በተካሄዱ የቼስ ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው ደሳለኝ፤ ስፖርቱ በስፋት እንዲካሄድ የመገናኛ ብዙሃናት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብሏል። የቼስ ኦሎምፒያድን ለማስተናገድ ብዙ ወጭ እና በጀት ሊጠይቅ ይችላል ለዚያ የሚሆን በቂ አቅም በቼስፌደሬሽን መፈጠር ይኖርበታል የሚለው ደሳለኝ፤ ሌሎች የዓለም የቼስ ፌደሬሽን ውድድሮችን በማጥናት ለዓለም አቀፋዊ መስተንግዶ መነቃቃት መፈጠሩን መጠቀም ያፈልጋል ሲልም ተናግሯል፡፡
የዓለም ቼስ ፌዴሬሽን በየክፍለ አህጉራቱ  በበላይነት የሚመራቸው ከ7 በላይ ዓለም አቀፍ የቼስ ውድድች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውድድሮች መካከል የቼስ ኦሎምፒያድ፣ የቼስ ዓለም ዋንጫ፣ የቡድንና የግል የዓለም ቼስ ሻምፒዮናዎች፣ የሴቶችና የታዳጊዎች የዓለም ሻምፒዮናዎች ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን (FIDE) ከ92 ዓመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን፣ 185 አባል አገራት ያሉትና ዋና መስሪያ ቤቱን በግሪክ አቴንስ ያደረገ ነው፡፡  ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት ከእነዚህ ዓለም አቀፍ የቼስ ውድድሮችን አንዳንዶቹን ለማስተናገድ ጥረቶች መኖር አለባቸው። በተለይ የዓለም የቼስ ኦሎምፒያድ እና የቼስ የዓለም ዋንጫ፣ የዓለም ሻምፒየንሺፕ ስፖርቱን በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋፋት የሚያግዙ ናቸው፡፡    በየሁለት ዓመቱ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ስር የሚዘጋጀው የቼስ ኦሎምፒያድን ኢትዮጵያ ማተናገድ ብትችል ስኬታማ ሊሆን ይችላል፡፡ በ2016 እ.ኤ.አ 42ኛውን ቼስ ኦሎምፒያድ አዘርባጃን በባኪ ከተማ ያስተናገደች ሲሆን በ2018 ደግሞ 43ኛውን የዓለም ቼስ ኦሎምፒያድ ጆርጅያ ባቱሚ በተባለች ከተማዋ የምታስተናግደው ይሆናል። በ2020 እ.ኤ.አ  ላይ 44ኛውን የቼስ ኦሎምፒያድ ቱኒዚያና ደቡብ አፍሪካ ለማስተናገድ ጥረት እያደረጉ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ምናልባት በ2022 ለሚደረገው 45ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ ቼስ ፌደሬሽን ትኩረት አድርጎ  ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በጅማ ከተማ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሊስተናገድ የበቃው ዞን 4.2  የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና መነሻ ሊሆን ይችላል። በዓለም አቀፍ የቼስ ፌዴሬሽንስር የሚካሄደው የቼስ ኦሎምፒያድ ለ15 ቀናት  ከ150 በላይ አገራት የወከሉ ከ1500 በላይ የቼስ ተወዳዳሪዎችን የሚያተናግድ ግዙፍ የስፖርት መድረክ ነው፡፡

Read 1265 times