Print this page
Monday, 10 April 2017 10:36

ኮሚሽኑ በኦሮሚያና አማራ ክልል ግጭት ላይ የምርመራ ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀርባል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሠብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ተጠቁሟል
                            
      የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ከሐምሌ 2008 ጀምሮ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ስለደረሰው ጉዳት ያደረገውን የምርመራ ውጤት ሪፖርት የፊታችን ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚያቀርብ ሲሆን በቂሊንጦ ስለደረሰውና የ23 ታራሚዎችን ህይወት ስለቀጠፈው የእሳት አደጋ የምርመራ ውጤቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በሁለቱ ክልሎች ቀደም ብሎ ተከስቶ የነበረውን ተቃውሞና ግጭት አስመልክቶ  የምርመራ ውጤት ሪፖርቱን ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ከሐምሌ 2008 በኋላ በድጋሚ ያገረሸው ተቃውሞና ግጭት ያስከተለውን ጉዳትና የግጭቱን መንስኤ በተመለከተ ለሁለተኛ ዙር ምርመራ 10 ቡድኖችን አዋቅሮ ወደ ክልሎቹ በመላክ፣ ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡   
የምርመራ ውጤቱ ሪፖርት ተጠናቅሮ መጠናቀቁንና ማክሰኞ ዕለትም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚቀርብ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁሟል፡፡ በሁለቱ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በተከሰቱ ግጭቶች ከ1ሺ የማያንሱ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳት፣ በርካቶችም ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡  
በሌላ በኩል ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ አስመልክቶ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ያደረገውን ምርመራ ውጤት ባለፈው ረቡዕ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የአደጋውን መንስኤ በተመለከተ አስነሽዎቹ በወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ እስረኞች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ አደጋው ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማስቆም ይቻል እንደነበር የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ አደጋውን ሊያስከትል የሚችል ረብሻ አስቀድሞ ተፈጥሮ እንደነበር አመልክቷል፡፡  
ለዚህ ደግሞ መነሻው በማረሚያ ቤቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸው ነው ያለው ኮሚሽኑ፤ የታራሚዎች አያያዝ ችግር በሰፊው እንዳለ ጠቁሞ፣ በቀጣይ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በማረሚያ ቤቱ መገኘት የሌለባቸው አደንዛዥ እፆችን ጨምሮ የሲጋራ መለኮሻ ላይተርን የመሳሰሉ ተቀጣጣይ ነገሮች መገኘታቸውን በምርመራው ማረጋገጡን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ እስረኞችም ተገቢ ባልሆነ መልኩ በአንድ ክፍል ውስጥ ተፋፍገው እንደሚኖሩ ጠቁሟል፡፡

Read 5289 times