Monday, 10 April 2017 10:28

“ሂውማን ራይትስ ዎች” የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን በሠብአዊ መብት ጥሰት ወነጀለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 የሠብአዊ መብት ጥሰቶቹ በተባበሩት መንግስታት ልዩ መርማሪ እንዲጣሩ ጠይቋል
                         
      ዓለም አቀፉ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ ”ሂውማን ራይትስ ዎች”፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ፖሊስን በሠብአዊ መብት ጥሰቶች ወነጀለ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 5 ቀን 2016 በሶማሌ ክልል ጁማክ፣ ዱባድ በተባለ መንደር ውስጥ አንድ የክልሉ ልዩ ሃይል አባል ከአንድ ግለሰብ ጋር ተጣልቶ መቁሰሉን ተከትሎ፣ የልዩ ሃይሉ አባላት በወሰዱት ግብታዊ እርምጃ 7 ሴቶችን ጨምሮ 21 የመንደሪቷ ነዋሪዎች ያለ አግባብ በጅምላ መገደላቸውን የ”ሂውማን ራይትስ ዎች”ን ሪፖርት ጠቅሶ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ድረ-ገፅ አስታውቋል፡፡
ግጭቱ የተነሳው የጫት ነጋዴ የሆነ ግለሰብና አንድ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባል በፈጠሩት ጸብ መሆኑን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ይሄን ተከትሎም ሰኔ 5፣ የክልሉ ልዩ ኃይል በተሽከርካሪ በመታገዝ፣ መንደሯን መክበቡንና በገበያ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች ላይ በቀጥታ ተኩስ መክፈቱን እንዲሁም ለማምለጥ በሞከሩት ላይም መተኮሱን የዓይን እማኞች መግለጻቸውን ጠቁሟል፡፡
በወቅቱ መንግስት ጉዳዩን እንዲያጣራና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ቢጠየቅም እስካሁን ምንም አይነት ማጣራት አለማድረጉን፣ የተጎጂዎች ቤተሰቦችም ምንም አይነት ካሣ አለማግኘታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል - ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦችን በእማኝነት በመጥቀስ፡፡  
የክልሉ ልዩ ኃይል በተደጋጋሚ ህገ ወጥ ግድያዎችን ጨምሮ አስገድዶ መድፈርና የማሰቃያ ምርመራ በማድረግ ከፍተኛ የሠብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚፈጽም የጠቆመው “ሂውማን ራይትስ ዎች”፤ ከህዳር 2016 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሶማሌ ክልል ያሉ ነዋሪዎችን ጨምሮ ድንበር በመሻገር በጎረቤት ሶማሊያ እንዲሁም በአዋሣኝ የኦሮሚያ ክልልም ህገ ወጥ ጥቃቶችን እየፈፀመ ነው ብሏል፡፡ በመንደሪቱ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ ጨምሮ በልዩ ሃይሉ ላይ የሚቀርቡ የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎችን የተባበሩት መንግስታት ልዩ መርማሪ ቡድንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋማት እንዲመረምሩት የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈቅድ “ሂውማን ራይትስ ዎች” ጠይቋል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች ለተፈጠረው ግጭት አንዳንድ ወገኖች የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን ተጠያቂ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በግጭቱ በዋናነት የመንግስት ሹመኞች እንዳሉበት በመጥቀስ መንግስታቸው በእነዚህ ሹመኞች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሰይድ ባለፈው ሳምንት ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በየጊዜው በኢትዮጵያ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ስለሚያወጡት ሪፖርቶች በሰጡት አስተያየት፤ “ሪፖርቶቹ ርዕዮት አለማዊ ዘመቻ ማካሄጃ ናቸው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

Read 2342 times