Monday, 10 April 2017 10:42

“መኢአድ” እና “ሰማያዊ” እስከ ውህደት የሚያደርሳቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን የሚገዳደር ግዙፍ ፓርቲ ለመፍጠር አቅደዋል
                        “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” ለሚለው የህዝብ ግፊት ምላሽ ነው ብለዋል
                              
     መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲ እስከ ውህደት የሚያደርሳቸውን በጋራ አብሮ የመስራት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ አንድ ውህድ ፓርቲ ሆነው ለመቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎችም ጋር በጋራ የመስራትና የመዋሃድ ዝግጅት ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ላለፉት አራት ወራት ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ 6 አባላት ያሉት ኮሚቴ፤ፓርቲዎቹ በጋራ የሚሰሩበትንና በቀጣይም ውህደት መፈፀም የሚያስችላቸውን ጉዳይ በጥንቃቄ ሲያጠና እንደቆየ የየፓርቲዎቹ አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡  
ፓርቲዎቹ አብረው ለመስራት የፈለጉት አላማቸው ተመሳሳይ በመሆኑና “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” ለሚለው የህዝብ ግፊት ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ የገለጹት አመራሮቹ፤ በመተባበር የሚፈልጉትን ውጤት ለማምጣት እንደሚተጉም አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ አንድነት፣በመሬት ፖሊሲ፣ በፌደራል መዋቅር እንዲሁም በሚከተሉት የሊበራል አስተሳሰብ ተመሳሳይ መሆናቸውን ያስረዱት አመራሮቹ፤ለጊዜው እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት አብረው እየሰሩ፣በሂደት በአባላቶቻቸው መካከል የአስተሳሰብ መቀራረብ በመፍጠር ወደ አንድ ውህድ ፓርቲነት ለመለወጥ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡  
አንድ ግዙፍ ጠንካራ ፓርቲ የመፍጠሩ ጉዳይ በመኢአድ እና በሰማያዊ ብቻ የሚወሰን አይደለም ያሉት አመራሮቹ፤ኢዴፓ እና መኢዴፓን ከመሳሰሉ በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ፓርቲዎች ጋርም ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡   የፓርቲዎቹን በጋራ አብሮ የመስራት ሂደት ሲያመቻች የቆየው ኮሚቴ፤ የሁለቱን ፓርቲዎች ታሪክ፣ መዋቅር፣ የፋይናንስ አቅም፣ ህዝባዊ ተቀባይነታቸውንና የውጭ ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነታቸውን በጥልቀትና በዝርዝር መፈተሹን ጠቁሞ፤ ወደፊት በግንኙነታቸው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም በዝርዝር ማጥናቱን አመልክቷል፡፡   
የፓርቲዎቹ አብሮ ዘላቂነት ምን ዋስትና አለው በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ አመራሮቹ በሰጡት ምላሽ፤ የፓርቲዎቹ አቋም በጥንቃቄ መጠናቱ ዋስትና ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ከዚህ ቀደም ተመስርተው ከከሸፉ የፓርቲዎች ህብረት፣ ቅንጅትና ግንባር ልምድና ተሞክሮ መወሰዱንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ግንኙነቶች ባለመጠናናት በችኮላ የሚፈፀሙ፣ መጠላለፍና ለግል ዝና መሯሯጥ የሚንፀባረቅባቸው እንደነበሩ በኮሚቴው ጥናት መለየቱን አመራሮቹ አስረድተዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም ከነበሩ መሰል የፓርቲዎች ግንኙነት የሚለየውም ግንኙነቱ ግለሰቦችን አሊያም አመራሮችን ሳይሆን አስተሳሰቦችን ያማከለ ብቻ እንዲሆን መታቀዱ ነው” ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ ሲሰሩ ከገዥው ፓርቲ ጋር በሚደረጉ ማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ ውይይትና ክርክር ጠንካራ ተገዳዳሪ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን በፖለቲካው ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ዘርፍ ነጥሮ የሚወጣ ፕሮግራም በጋራ እንደሚያዘጋጁም ታውቋል፡፡   
በሃገሪቱ ሰፊ መሰረት አለን የምትሉ ከሆነ፣ ምን ያህል አባላት እንዳሏችሁ ንገሩን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፤ ከፖለቲካ ስልት አንፃር የአባላት ብዛትን ለመግለፅ እንደማይችሉ፤ነገር ግን ሁለቱም ፓርቲዎች በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ 281 ወረዳዎች፣ 39 ዞኖች እንዲሁም በ5 ቀጠናዎች ፅ/ቤት ከፍተው እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በወጣቶች፣ መኢአድ ደግሞ በእድሜ በገፉ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው የአስተሳሰብ ግጭት አይፈጥርም ወይ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሰማያዊ አመራር አባል አቶ አበበ አካሉ፤ “አባት ልጁን ይተካል፤ ከነባር ፖለቲከኞች የሚገኘው ልምድ ለሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ለቀጣይ የፖለቲካ ጉዞአቸው ስንቅ ነው የሚሆነው›› ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ሌሎች ወደ ውህደት የሚመጡ ድርጅቶችን ጨምረው፣ በ2012 ለሚደረገው ሃገር አቀፍ ምርጫ ኢህአዴግን የሚገዳደር ግዙፍ ፓርቲ የመመስረት ውጥን እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

Read 2847 times