Monday, 10 April 2017 10:44

የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ተማሪዎች በአዲስ አድማስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ተመራቂ ተማሪዎች ትናንት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ
ዝግጅት ክፍልን የጎበኙ ሲሆን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ገጣሚ ነቢይ መኮንን ስለ ጋዜጣው አመሰራረት፣ አሰራርና
የወደፊት ራዕይ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርጎላቸዋል፡፡ “ጋዜጠኝነት አበባና የእርግብ ላባ አይደለም፤ ብዙ እሾህ ያለበት፣ እግራችሁ ላይ ሲተከል እየደማችሁ እየነቀላችሁ የምትጓዙበት መንገድ ይሆናል” ሲል ምክሩን ለተማሪዎች የለገሰው ነቢይ መኮንን፤ በስራው ዓለም ሲሰማሩ ስለሚገጥማቸው መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ከልምዱ አካፍሏቸዋል፡፡ መምህራኑና ተመራቂ ተማሪዎች በጉብኝታቸው ወቅት ለአዲስ አድማስ አጭር ጥያቄዎችም
እንደሚከተለው ምላስ ሰጥተዋል፡፡

                    “የግል ፕሬሱ መቀጨጩ በሀሳብ ገበያ ላይ ጫና መኖሩን ያመላክታል”
                          ፍሬዘር እጅጉ

      አሁን በኮሌጅ ደረጃ የሚሰጠው የጋዜጠኝነት ትምህርት ብቁ ጋዜጠኞች ያፈራል ብለህ ታስባለህ?
ብዙ ጋዜጠኞችን ያዘጋጃል ብዬ አስባለሁ፡፡ መሰረታዊ ሙያው የሚፈልጋቸውን ዕውቀቶችና ክህሎቶች በካሪኩለሙ ውስጥ የተካተተ ስለሆነ በተገቢው መንገድ ጋዜጠኝነትን ለመተግበር ብቁና ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኞች የሚፈጠሩት ትምህርቱን ከተማሩ በኋላ በስራ ስነ ምህዳር ውስጥ ሲያልፉና የተማሩትን በተግባር ሲያውሉ ይመስለኛል፡፡
ምንድን ነው በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት (ሚዲያ) ሙያ የጎደለው ትላለህ?
በግለሰብ ደረጃ (በጋዜጠኞች)
የጋዜጠኝነት ሙያዊ  ትምህርትና ስልጠና (ዕውቀት) አለመያዝ
የክህሎት ማነስ
ተግባቢነት የሌለው ትምህርት ዝግጅት
በተቋም ደረጃ
ለገንዘብ/ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት
ግልፅ የሆነ ህዝብን የሚወግን አሰራር ደንብ አለመኖር
ሙያዊ ስልጠናዎችን በበቂ ሁኔታ አለመስጠት
በሀገር ደረጃ
የሚዲያ ስነ - ምህዳር የሀሳብ ልዩነቶችን ሁሉ ለማስተናገድ በሚቻልበት ደረጃ
በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ጋዜጠኝነት ሳይሆን ልማታዊ ባህርያት ያለውን ጋዜጠኝነትን ብቻ ለመተግበር መሞከር፡፡
የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ልማታዊም ሆነ የዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የያዘ ስርዓት እንደሆነ ሁሉ ከዚሁ ስርዓት የሚወጣ የሚዲያ ፍልስፍና የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቅ መሆን የሚገባው ሲሆን የልማታዊ ጋዜጠኝነትን እሴቶችን ብቻ መተግበር ለልማታዊ መንግስት እንጂ ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማይጣጣምና የማይገጥም ነው፡፡ ስለዚህም በሀገር ደረጃ የተቀመጠውን የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፍልስፍና ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመች በምርምር የተገዛ የሚዲያ ስርዓት ማዋቀር ተገቢ ይሆናል፡፡
የልማታዊ ጋዜጠኝነት አይነቶች
የአገራችን የግሉ ፕሬስ ከመፋፋት ይልቅ መቀጨጩ ምንድን ነው የሚጠቁመው?
ዜጎች በህይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ጠቃሚና መሰረታዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን የመረጃ እጥረት እንደሚኖራቸው እገምታለሁ፡፡ የምግብ እጥረት ሆነ ሌሎች ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ነገሮች እጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ችግር እንደሚያጋጥም ሁሉ ዜጎችም የመረጃ እጥረት በአጋጠማቸው ጊዜ ችግር እንዳጋጠማቸው መቁጠሩ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ (የትራዲሽናል ሚዲያ ህትመት)
የትራዲሽናል ሚዲያ (የህትመት) የግል ፕሬሱ መቀጨጩ በ market place of ideas (በሀሳብ ገበያ) ላይ ጫና መኖሩን አመላካች ይሆናል፡፡ ጥቂት ወይም አንድ የሀሳብ ምርት ብቻ ወደ ሀሳብ ገበያው ተመርቶ እየተቀላቀለ መሆኑን የሚያሳይ ይሆናል፡፡
ሚዲያው እንዲፋፋና ተገቢ ሚናውን እንዲወጣ ከመንግስት ምን ይጠበቃል?
ከመንግስት የሚጠበቀው በዋናነት መንግስት የሚከተለውን የሚዲያ ፍልስፍና በሰከነ መንገድ መመርመር ነው፡፡ ሌላው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን መሳ ለመሳ የሚያስተናግድ የሚዲያ አሰራር መፍጠር ወይም መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር በዕውቀት የሚመራ ሙያ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ የሚዲያ ተቋሞች ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች አቅማቸውን ለማሳደግ ተከታታይ የሆነ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሄ ቸል ሊባል የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ስራቸውን በተግባር የሚያውሉት ባወቁት መጠን ስለሆነ፣ ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠት ዘለቄታ ያለው የተሻለ ዘገባ እንዲሰሩ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይና ተወዳጅ ዝግጅቶች እንዲጨምሩ ያደርጋል፡፡ ለሌሎች ሀገሮች ለ30 እና 40 ዓመታት ሳይቋረጡ የቀጠሉ ብዙ ዝግጅቶች አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች እንዲኖሩ ካስፈለገ፣ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት ማሳደግ ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡
ከግል ፕሬስ የምታደንቃቸው? የምትወዳቸው የህትመት ውጤቶች ጥቀስልን፡፡ ከአሁንም ከተዘጉትም?
ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያስ?
የአገራችን ሚዲያ ዕጣ ፈንታ ምን ይመስልሃል? ተስፋ ይታይሃል?
መሻሻል ይገባዋል፡፡ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ሙያ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ ከሚያስተምሩ መምህራንና ተመራማሪዎች ጋር በህብረት ሳይንሳዊ መንገዶችን ተከትሎ፣ መሻሻል ያለባቸውን ለማሻሻል፣ በጠንካራ ጎን መወሰድ ያለባቸውን እንዲሁ ወስዶ በምርምር የታገዙ ስራዎች ከተሰሩ ትልቅ ተስፋ ይታየኛል፡፡ መጀመሪያ ሀገር መከተል ያለበት የሚዲያ ፍልስፍና አሰራር ላይ ሙያዊ ጉዳዮችን ለማካተት ምላሽ መስጠት ይፈልጋል፡፡ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ሰፊ ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ለሀገራችን ሚዲያ ችግር ምላሽ እንደሚኖረው እርግጠኛ መሆን ይችላል፡፡
በምሳሌነት የምትጠቅሰው የውጭ ሚዲያ ይኖራል፡፡ ከእነ CNN, BBC, Fox News በነገራችን ላይ ከአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ጀምሮ Mainstream Media የሚሏቸው እነ ABC, CNN, ሚዛናዊነት … ሃቀኝነት፣ እውነታ … የሚሉትን ዘንግተው በአድሏዊነት በመዘገብ የዓማኒነታቸውን አጥተዋል፡፡ ታዝበሃቸዋል? ምን? አስተያየት አለህ?  
የሃቅ ስህተት ከሌለበት መገናኛ ብዙኃን አንድ ጉዳይ በተለያየ መንገድ ሊዘግቡ ይችላሉ፡፡ እስከ አሁን በምርምር የተደገፉ አድሏዊነት እንደነበረባቸው የሚያረጋግጥ የምርምር ውጤት አላየሁም፡፡ ለአሜሪካ የፕሬዚዳንት ምርጫ ሁልጊዜ ሀገር አቀፍ ምርምሮች ይካሄዳሉ፡፡ በ1930ዎቹ የተደረጉ ከመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብና ተፅዕኖ አንፃር የተከናወኑ ምርምሮች የተለያዩ የኮሚዩኒኬሽን ቴዎሪዎችና ሞዴሎች እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ በቅርቡ መሰል ሳይንሳዊ ጥናቶች ውጤት ላይ ተንተርሶ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በግለሰብ ከተከታተልኩት የCNN ሆነ BBC ዘገባዎች የሃቅ መፋለስ ተገኘባቸው የሚል ዘገባም አላየሁም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሃቅን አፋልሰዋል፣ ቁጥር አዛብተዋል የሚል ዘገባ ሲያቀርቡ፣ ከነማስረጃው ነው፡፡ በእርግጥ “ሚዲያው የአሜሪካ ህዝብ ጠላት ነው” ብለው ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ይህ ግልፅ የሆነ በመንግስትና በሚዲያው ያለ የሻከረ ግንኙነት ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ Against establishment ናቸው፡፡ ሚዲያዎቹ ደግሞ የ establishment አካል መሆናቸው ይገመታል፡፡ የግጭቱ /የሻካራ ግንኙነቱ መነሻ ይሄ ይመስለኛል፡፡ ነገር ያለ ጥርጥር በማስረጃ አድሎ አድርገዋል ብሎ መናገር ግን ግራ ቀኝ ሳይመለከቱ ብያኔ እንደ መስጠት ይመስለኛል፡፡  

-----------------

                       “የሚዲያው እጣ ፈንታ በመንግሥት እጅ ላይ ነው”
                      በለው አንለይ

      አሁን በኮሌጅ ደረጃ የሚሰጠው የጋዜጠኝነት ትምህርት ብቁ ጋዜጠኞችን ያፈራል ብለህ ታስባለህ?
በከፊል አዎ፡፡
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት (ሚዲያ) ሙያ የጎደለው ምንድን ነው ትላለህ?
የዳበረ የትምህርት ካሪኩለም፣ የሚዲያ ነፃነት፡፡
የአገራችን የግሉ ፕሬስ ከመፋፋት ይልቅ መቀጨጩ ምን ይጠቁማል?
መንግሥት በነፃው ሚዲያ ላይ ያለውን አቋም፣ በማቴሪያልና በእውቀት የተደራጁ ት/ቤቶችና መምህራን እጥረት መኖሩን፡፡
ሚዲያው እንዲፋፋና ተገቢ ሚናውን እንዲወጣ ከመንግስት ምን ይጠበቃል?
መንግስት አፋኝና ገዳቢ ህጎችን ከማውጣት ተቆጥቦ፣ ሚዲያው ለአገር ዕድገትና ዲሞክራሲ ያለውን ሚና መገንዘብ፡፡
ከግል ፕሬስ የምታደንቃቸውን፤ የምትወዳቸውን፣ የህትመት ውጤቶች ጥቀስልን…፡፡ ከአሁኑም ከተዘጉትም?
አዲስ አድማስ
ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያስ?
- -
የአገራችን ሚዲያ ዕጣ ፈንታ ምን ይመስልሃል? ተስፋ ይታይሃል?
የሚዲያው ዕጣ ፈንታ በመንግስት እጅ ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለው፣ ነፃው ሚዲያ አሁን ካለበት ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል፡፡
ከውጭ ሚዲያስ … በምሳሌነት የምትጠቅሰው ይኖራል፡፡ ስለውጭ ሚዲያ ምን አስተያየት አለህ?
የውጭ ሚዲያዎችን እከታተላለሁ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ምርጫ ወቅት የሚሰሩትን ዘገባም ተከታትያለሁ፡፡ በዘገባቸው የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፣ የሀሳብ ነፃነታቸውን ነው፡፡ በአገራቸው ጉዳይ የሚያምኑበትን ሀሳብ ነው ያንሸራሸሩት፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት በማራመዳቸው የተዘጋ ሚዲያዎችም ሆነ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፡፡   

--------------

                       ‹‹ህልሜ የህዝብ ዓይንና ጆሮ መሆን ነው››
                         ሰናይት ዘውዱ

     ሰናይት ዘውዱ አለባቸው፤ ዕድሜ-20-፤ Journalism and Mass Communication፤ 3ተኛ ዓመት
ጋዜጠኝነት ለመማር ምን አነሳሳህ?
ልጅ እያለሁ ጀምሮ ነገሮችን ጠይቆ የማወቅ፣ ለወሬ የመቸኮል  ባህሪያቶች ነበሩኝ፡፡ ጋዜጠኝነት ደግሞ ለዚህ ቅርብ የሆነና ለብዙሀኑ ድምፅ መሆን የሚያስችል ሙያ ስለሆነ ከሁሉም ዘርፎች እሱን መረጥኩ፡፡
ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚማርክህ - የሚስብህ ምንድን ነው?
ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚማርከኝ፣ በድፍረት ነገሮችን የመጠየቅ ችሎታ ነው፡፡
ከኮሌጅ ስትወጣ የተማርከውን በትክክል የምትተገብረው ይመስልሃል?
ከሚባለው በላይ፤ ምክንያቱም በጣም ፈልጌው የተማርኩት ሙያ ስለሆነ!!
በአገራችን የጋዜጠኝነት ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
የጋዜጠኛ ፈተና እንደተማርኩት፤ ከተራ ዛቻ እስከ መታሰርና መገደልም ሊደርስ ይችላል፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
የወደፊት ህልሜ እውነትን ብቻ መሰረት አድርጋ የምትሰራ፣ ህዝብንም የምታገለግል፣ የህዝብ አይንና ጆሮ መሆን የምትችል ምርጥ ጋዜጠኛ መሆን፡፡
ከኤፍ ኤም ሬዲዮ የምታዳምጠው?
ኤፍኤም 97.7 (የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ Community radio) እና ኤፍኤም 103.4
ከቴሌቪዥን ጣቢያ አዘውትረህ የምታየው?
አማራ ቲቪ፡፡
ከጋዜጣ የምትወደው - ዘወትር የምታነበው?
ጋዜጣ አንባቢ አይደለሁም፡፡
ከውጭ … ሚዲያ ጋዜጠኛ .. የምትወደውና የምታደንቀው?
ከአገር ውስጥስ የምታደንቀው ጋዜጠኛ አለ?
         - - - - -
ብዙዎቹን አላደንቃቸውም ግን በአንፃሩ የስፖርት ጋዜጠኛውን ማንደፍሮ ታደሰን አደንቀዋለሁ፡፡
የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
ከመንግሥት ሚዲያዎች በተሻለ የህዝብን ችግር ይረዳሉ፡፡
ስለ መንግስት ሚዲያዎችስ?
የመንግስት አገልጋዮች ናቸው፣ የህዝብን ችግር ብዙም ጠልቀው አይገቡበትም፡፡
የኮሌጅ ቆይታህሽ እንዴት ነበር?
ደስ ይላል፡፡ የሚከብድም የሚቀልም ነገር ነበረው፤ ሁሉንም እንደ አመጣጡ ተወጥቼዋለሁ፡፡

------------------------

                    ‹‹ህዝብን ማገልገል ይማርከኛል››
                     ዳንኤል ኢሳያስ

      ዳንኤል ኢሳያስ፤ ዕድሜ-21፣ ዲፓርትመንት Journalism and Communication- ( 3ተኛ ዓመት)
ጋዜጠኝነት ለመማር ምን አነሳሳህ?
ከልጅነቴ ጀምሮ ያለኝ የሙያው ፍቅር ነው፡፡
ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚማርክህ - የሚስብህ ምንድን ነው?
ህዝብን ማገልገል፡፡
ከኮሌጅ ስትወጣ የተማርከውን በትክክል የምትተገብረው ይመስልሃል?
አዎ ይመስለኛል፡፡
በአገራችን የጋዜጠኝነት ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
መገለል፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነት፣ ሀሳብን በነፃነት መግለፅ አለመቻል፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
ጥሩ ጋዜጠኛ መሆን፡፡
ከኤፍኤም ሬዲዮ የምታዳምጠው?
ፋና 103.4፣ ሻሸመኔ፣ ደቡብ ኤፍኤም 100.9
ከቴሌቪዥን ጣቢያ አዘውትረህ የምታየው?
ኢቢኤስ፣ ጄቲቪ
ከጋዜጣ የምትወደው - ዘወትር የምታነበው?
የለም !
ከውጭ … ሚዲያ… ጋዜጠኛ .. የምትወደውና የምታደንቀው?
ሮበርት ማራዋ (የስፖርት ጋዜጠኛ)
ከአገር ውስጥስ የምታደንቀው ጋዜጠኛ አለ?
ሚሚ ስብሀቱ!
የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
በአሁኑ ሰዓት አሪፍ ደረጃ ላይ ናቸው ብዬ አስባለሁ፤ በብዛትም እየተከፈቱ ይገኛሉ፡፡
ስለ መንግስት ሚዲያዎችስ?
አስተያየት የለኝም፡፡
የኮሌጅ ቆይታህ እንዴት ነበር?
በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው፤ ብዙ ነገሮችን ያወቅንበት ጊዜ ነበር፡፡

------------------

                       “ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን እሻለሁ”
                         ምንበላ ሞላ

      ምንበላ ሞላ፣ ዕድሜ     - 25፣ ጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን 3ተኛ ዓመት (ተመራቂ)
ጋዜጠኝነት ለመማር ምን አነሳሳህ?
እኔ ጋዜጠኝነትን ለመማር ያነሳሳኝ ዋናው ነገር አሪፍ ጋዜጠኛ ሆኜ፣ ድምፅ ለሌላቸው አናሳ ህዝቦች ድምፅ ለመሆን ነው፡፡ በተጨማሪም ተደብቀው የኖሩ ነገሮችን ለማውጣትና ለህዝብ እንዲታይ ለማድረግ ነው፡፡
ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚማርክህ - የሚስብህ ምንድን ነው?
ራሴን መስዋዕት አድርጌ ሌሎችን መጥቀም፣ ድምፅ ለሌላቸው ድምጽ መፍጠር፡፡ ሌላው የሚስበኝ ዜና ማንበብ ነው፡፡
ከኮሌጅ ስትወጣ የተማርከውን በትክክል የምትተገብረው ይመስልሃል?
አዎ፤ አቅሜ በፈቀደው መጠን የተማርኩትን እተገብራለሁ፡፡
በአገራችን የጋዜጠኝነት ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
ብዙ አይነት ፈተናዎች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ሀሳብን በነፃነት እንዳትገልፅና የፈለግኸውን መናገር እንዳትችል ትገደዳለህ፤ ይህ አንዱ ፈተና ነው፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
የወደፊት ህልሜ በተማርኩት ትምህርት፣ አሪፍ ጋዜጠኛ ሆኜ አገሬን ማገልገል ነው፡፡
ከኤፍ ኤም ሬዲዮ የምታዳምጠው?
ፋና በጣም አዳምጣለሁ፡፡
ከቴሌቪዥን ጣቢያ አዘውትረህ የምታየው?
ሾቢዝ ወይም ስለ ታላላቅ ሰዎችና ስራዎቻቸው
ከጋዜጣ የምትወደው - ዘወትር የምታነበው?
አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ
ከውጭ … ሚዲያ … ጋዜጠኛ .. የምትወደውና የምታደንቀው?
መለሰ ነጋሽን አደንቃለሁ፡፡
ከአገር ውስጥስ የምታደንቀው ጋዜጠኛ አለ?
ተመስገን በየነን አደንቃለሁ፡፡
የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
የግል ሚዲያዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ እድል አላቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ስለ መንግስት ሚዲያዎችስ?
የመንግስት ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ መንግስት ጣልቃ ይገባባቸዋል፡፡ እናም መንግስትን ሁልጊዜ መደገፍ አለባቸው፡፡ አንድ ቀን ምናልባት … መንግስትን ቢተቹ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡
የኮሌጅ ቆይታህ እንዴት ነበር?
የኮሌጅ ቆይታዬ ጥሩ ነው፡፡ ትምህርቴን በአግባቡ እየተከታተልኩና ጊዜዬን በአግባቡ እየተጠቀምሁ አሳልፌአለሁ፡፡

-----------------

                       “የራሴን የሚዲያ ተቋም የመክፈት ትልቅ ህልም አለኝ”
                         ደረጀ ሽፈራው

       ደረጀ ሽፈራው ለገሠ፣ ዕድሜ - 22፣ የትምህርት ዘርፍ - ጋዜጠኝነት (3ኛ ዓመት)
ጋዜጠኝነት ለመማር ምን አነሳሳህ?
መጀመሪያ ጋዜጠኛ የመሆን እቅዱም ህልሙም አልነበረኝም፤ ነገር ግን እንደ እድል ሆኖ የጋዜጠኝነት ዲፓርትመንት ደርሶኝ በመማር ላይ እገኛለሁ፡፡ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በጣም ነው የወደድኩት፡፡ አሁን ከማንኛውም ትምህርት በላይ በፍቅር የምወደው የትምሀርት ዘርፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚማርክህ ወይም የሚስብህ ምንድን ነው?
ከሚማርኩኝና ከሚስቡኝ ነገሮች መካከል ብዙ ነገር የምታውቅበት አጋጣሚና እድል መኖሩ፤ ብዙ የማንበብ እድሉን ለማግኘት መቻሉ፤ ለህዝቡ የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ነገሮችን ማድረሱ፤ ከብዙው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከኮሌጅ ስትወጣ የተማርከውን በትክክል የምትተገብረው ይመስልሃል?
በትክክል! በተለይ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም ፕሬስ ላይ በትክክል የተማርኩትን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብዬ እገምታለሁ - እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ፡፡
በአገራችን የጋዜጠኝነት ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለአድማጭ አለማድረስ፣ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን ሚዛናዊ ባለማድረግ  የሚነሳ ተቃውሞ፤ የሀቀኝነት ችግር፣ የታማኝነት ጉድለት፣ ግልፅ አለመሆን፣ ለዘገባ (ለዜና ሽፋን) ስጦታ (ገንዘብ) መቀበል ወዘተ …
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
በሚዲያ ዘርፍ ታዋቂና ፕሮፌሽናል ፕሮግራመር መሆን በጣም ያስደስተኛል፡፡ እንዲሁም የግሌን የሚዲያ ተቋም የመክፈት ትልቅ ህልም አለኝ፡፡
ከኤፍኤም ሬዲዮ የምታዳምጠው?
ፋና 96.7፣ ሸገር 102.1
ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች አዘውትረህ የምታየው?
EBC, JTV, ENN, … ብዙ ናቸው፡፡
ከጋዜጣ የምትወደው - ዘወትር የምታነበው?
አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር አልፎ አልፎ፡፡
ከውጭ … ሚዲያ … ጋዜጠኛ .. የምትወደውና የምታደንቀው?
በብዛት ቢቢሲ ላይ ያሉት ጋዜጠኞች ይመቹኛል፡፡
ከአገር ውስጥስ የምታደንቀው ጋዜጠኛ አለ?
ተመስገን በየነ ዜናዎችን ሲያቀርብ ያስደስተኛል፡፡
የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
ከመንግስት ሚዲያዎች በተጨማሪ ጥሩ information የሚያደርሱበት ሌላኛው የሚዲያ ዘርፍ በመሆናቸው እንደ ጥሩ ጎን እደግፋቸዋለሁ፡፡
ስለ መንግስት ሚዲያዎችስ?
በአብዛኛው የመንግስት ሚዲያዎች በበላይነት የቆሙት ለህዝብና ለራሱ ለመንግሥት ነው፡፡
የኮሌጅ ቆይታህ እንዴት ነበር?
በጣም ጥሩ ነው፡፡

Read 2551 times Last modified on Monday, 10 April 2017 10:51