Monday, 10 April 2017 10:55

ስለ ተክሌ አቋቋምና ዝማሜ

Written by  ታ. ገ
Rate this item
(8 votes)

 አቋቋም  “ቆመ”  ከሚለው የሰዋስው አንቀጽ የተገኘ ቃል ነው፡፡ የቃሉ አሰያየምም  “ ውስተ ዝንቱ መካን ቅዱስ ንቁም ንሰብሕ ወንዘምር” ያለውን የሊቁን የባስልዮስን ድርሰት መነሻ ያደረገ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የአቋቋም አመጣጥ ብዙ ታሪክ ያለው ሲሆን ይኽ ጽሑፍ ከተክሌ ጋር በተያያዘው ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ዝማሜ ማለትም የሥርዓተ ማኅሌት ቁመት ሒደት ነው፡፡ ቁመቱም በሰባት ዓይነት የተከፈለ ሲሆን እነርሱም ቁም ዜማ፣ ዝማሜ፣ ቁም፣ መረግድ፣ ጽፋት፣ አመላለስና ወረብ የተሰኙት ናቸው። በዚህ ረገድ ዝማሜ ቁም ዜማዉ በኅብረት  ከተዘለቀ በኋላ የድጓው መጀመሪያ ክፍል መሪ እየመራ፤ ተመሪ  እየተመራ ይባላል (ይመራል)፡፡ ቀጥሎም  ካህናት በኅብረት ሆነው  መቋሚያቸውን  ወደ ቀኝና ወደ ግራ፤ ወደ ፊትና ወደ ኋላ  እየወዘወዙ፤ አልፎ አልፎም መሬቱን እየመቱ (እየረገጡ)  ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስልት ነው፡፡    ወደ ቀኝና ወደ ግራ፤ ወደ ፊትና ወደ ኋላ  እየወዘወዙ በኅብረትና በተናጥል መዝመማቸውም ከጌታ  ሥቃይ ጋር የተያያዘ የራሱ ትርጉም አለው፡፡  
በተለምዶ ተክሌ የራሳቸውን  የአቋቋምና የዝማሜ ስልት ደረሱ ተብሎ ቢታመንም  የዝማሜው የመጀመሪያው ደራሲ ሊቁ አለቃ ገብረ ሐና ናቸው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን እኒህን ሊቅ የሚያውቃቸው በተሣላቂነታቸውና በቧልተኝነታቸው (በአሽሙረኛነታቸው) ነው እንጂ በባለቅኔነታቸውና በዜማ ሊቅነታቸው አይደለም፡፡
ወደ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለሥራ ጉዳይ ሔጄ በነበረበት ጊዜ  በደቡብ ጎንደር  በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምሥክር የሆኑት ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴ እንዳስረዱኝ፤ አለቃ ገብረ ሐና የራሳቸውን አቋቋም የደረሱት  ጣና ገዳም ውስጥ ሱባኤ ገብተው በነበረበት ጊዜ  ነው፡፡ የጎንደርን ቀለም በየዱሩ እየዞሩ በመዘመር ላይ ሳሉ መልአክ ተገለጠላቸውና፤ “እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሌላ ከፍተኛ ጥበብ አለ፡፡ ውዝዋዜን በዚህ ሸምበቆ እየመሰልክ ሥራው” በማለት ምልክቱን  ይነግራቸዋል፡፡ ይኽም የሆነው  ፎገራ ውስጥ  ናበጋ ቅዱስ  ጊዮርጊስ  ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ምክንያቱም አገሩ የሸምበቆ ተክል የበዛበት ስለሆነ ነው፡፡ ሸምበቆውን ነፋስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እያላተመ ሲያወዛውዘው የሚታየው ትርእይት አፍዝዞ የሚያስቀር በመሆኑ፣ አለቃ ገብረ ሐናም በትርእይቱ ተመስጠው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተመሩ፣ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆነውን የዝማሜ ስልት በሸምበቆ ተምሳሌት ለማፍለቅ ችለዋል፡፡
ዝማሜ ማለትም ልክ ነፋስ ሸምበቆን እያስጎነበሰና እያሥነሳ እንደሚያስደንሰው በዚያው ስልት  መቋሚያን ወይንም ዘንግን  ወደ ግራና ወደ ቀኝ  እያዟዟሩ፤ መሬቱን እየረገጡ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት የዜማ ስልት ነው፡፡   
አለቃ ገብረ ሐና የዝማሜን ጥበብ ከሸምበቆ መንጋ (ሠራዊት) ቀስመው  ከሠለጠኑበት በኋላ ቤት ዘግተው፤ ማንም ሰው ሳይሰማቸው  ለልጃቸው ለአለቃ ተክሌ በኅቡዕ አስተምረዋቸዋል፡፡ ተክሌም ከወላጅ አባታቸው የተማሩትን የአቋቋም ስልት እያራቀቁትና እየተካኑበት ስለሔዱና በደብረ ታቦር ኢየሱስ  ደብር ወንበር ዘርግተው በስፋት  ስለአስተማሩት በዘርፉ ብዙ ሊቃውንትን አፍርተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ተክሌ ራሱን የቻለ የአቋቋም ስልት ሆኖና  በራሳቸው ስም  ተሰይሞ ለመታወቅ ችሏል፡፡
በሌላ በኩል  ያገኘሁት ምንጭ እንደሚያትተው፤ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ ም ገጽ 123) ይኽ አቋቋም
(የተክሌ ለማለት ነው) ከአለቃ ገብረ ሐና በፊት የጎንደሮች ጊዮርጊስ የቤት ባህል ነበር፡፡ በተለይም በዝማሜነቱ በጣም ተወዳጅና መሳጭ ስለነበር አለቃ ገብረ ሐና ከደብሩ በመገኘት ብዙ ጊዜ ካዳመጡ በኋላ የራሳቸውን ማስተካከያ አክለውበት  በተለይም ዝማሜውን ልዩ ጣዕም እንቅስቃሴ፤ ልዩ የዘንግ ውዝዋዜ እንዲኖረው በማድረግ  አሳምረው አዘጋጅተውታል፡፡ ይኽንን አቋቋም ያዘጋጁበት ቦታም በጎንደር ከተማ ደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ አካበቢ  ከቤተልሔም በስተሰሜን  ምሥራቅ አጠገብ በነበረው ቤታቸው  ሆነው ነው፡፡ በዚህ ቤታቸው አጠገብ የሸምበቆ ተክል በብዛት ስለነበረ ነፋስ ሸምበቆውን ሲወዘውዘው እያዩ ከዘንጋቸው ጋር አዋሕደው ውዝዋዜውን አዘጋጅተውታል፡፡ በኋላም የደከሙበትን ሙያ  በሥውር ለልጃቸው ለአለቃ ተክሌ አስተምረዋቸዋል፡፡
ርእሰ መምህራን መርሻ እንደሚሉት፤ በደብረ ታቦር በስፋት የሚታወቀው የተክሌ ዝማሜ ነው። ይኸውም ልክ እንደ ሸምበቆ ነው፡፡ ውዝዋዜው  ውበት አለው፡፡ ድጓው አንድ ሲሆን የሚለየው በጣዕመ ድምጹ ነው፡፡ በውዝዋዜው፤ በውስጠ ጉሮሮውና በርዝመቱ ከሌላው የቤተልሔም (ላይ ቤትና ታች ቤት)፤ የቆማ ፋሲለደስ፣ የጎጃም አጫብር፣ከትግራይ አክሱሜ፤ በሸዋ ከነበሩት ወንጨሬና ተጉለት፣ በሰሜን ወሎ ዋድላ ዋድሌ ተብለው ከሚታወቁት (ዛሬ  የጥንቱን ዜማቸውን ትተው የቤተልሔም ዜማ ከሚጠቀሙት) የዜማ ስልቶች የተለየ ነው፡፡ ቀለሙ በትክክል እንደወረደ ነው፡፡ ዓይነቱም እንዳለ ሌላ ድምጽ ባልሰሙ መምህራን  ሲቃኝ በእጅጉ ያማልላል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተክሌዎች ከቤተ ልሔም የዜማ ስልት ጋር በድጓ ሲገናኙ በዘንግ ግን ይለያያሉ። ቤተ ልሔም  የሚባለው የድጓ ዜማ ሲሆን  የተክሌ ዝማሜ የዘንግ ዝማሜ  ይባላል፡፡ ግን ከበሮ ምቱን፤ ጸናጽሉን ብዙ ሰው አይወድደውም፡፡ ዘንጉ ግን በእጅጉ ሳቢና በመላ ኢትዮጵያ  ተወዳጅ ነው፡፡  በከበሮና በጸናጽል  ጎንደር በዓታ ይልቃል፡፡ የጸናጽል ዋነኛ ተጠሪዋም ጎንደር በዓታ ናት ይላሉ፤ የተክሌ ዝማሜ ሊቁ ርእሰ መምህራን መርሻ፡፡ እርሳቸው እንዳወሱት፤ አዲስ አበባ  በሚደረግ አጠቃላይ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ  እንዲዘምም ዘንግ የሚሰጠው  ለደብረ ታቦር ተክሌ ነው፡፡ ጸናጽል ለጎንደር በዓታ፤ ቅኔ ደግሞ ለጎጃም ይሰጣል፡፡ በዚህ ረገድ እርሳቸውም ለሁለት ጊዜያት ያህል  በሲኖዶስ ስብሰባ ተሳታፊ በነበሩበት ሰዓት  ዘንግ እየተሰጣቸው ዘምመዋል። ምክንያቱም ተክሌ ምሥክር እያለ ዘንግ ለሌላ ስለማይሰጥ ነው፡፡
ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴ በተክሌ አቋቋም የመምህራን ሐረግ (ተዋረድ)  ስድስተኛ ሰው ናቸው፡፡ ይኸውም የመጀመሪያው አለቃ ገብረ ሐና ሲሆኑ እርሳቸው በሥጋም፤ በአቋቋም ጥበብም አለቃ ተክሌን ወለዱ፡፡ አለቃ ተክሌ  አለቃ መኮንንንና ሌሎችን፤ አለቃ መኮንን አለቃ ቀለመ ወርቅንና ሌሎችን፤ አለቃ ቀለመ ወርቅ አለቃ ማኅተምን፤ አለቃ ማኅተም ርእሰ  መምህራን መርሻ መብራቴን የቀለም አባት ሆነው ወልደዋል፡፡
ርእሰ መምህራን መርሻ እንዳወጉኝ፤ በመጀመሪያው ላይ አለቃ ተክሌ ገብረ ሐናን  ፈተና ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይኸውም አለቃ ተክሌ  በክብረ በዓል ቀን ወደ ጎንደር ሔደው  ፎገራ ወረዳ ናበጋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዝማሜ ጊዜ በበርካታ  ሊቃውንቱ መኻል  ሲዘምሙ ሊቃውንቱ በመገረም፤ “ይትበሀላችን ያልሆነውን እንግዳ ነገር ከወዴት አመጣኸው” ብለው  ከማኅሌት ገብተው እንዳይቆሙ ይከለክሏቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ወደ ወሎ ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄደው ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡
አለቃ ተክሌ ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በነበሩበት ወቅት  የደብረ ታቦር ገዥ የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ  የተማረ ሰው ይወድዳሉ መባልን ስለሰሙ ወደ ደብረ ታቦር ይመለሳሉ። በጊዜው የደብረ ታቦር ኢየሱስ፤ የመንበረ ብርሃን እናቲቱ ማርያምና ዓፄ ዮሐንስ ያሠሩት የኅሩይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አድባራት አስተዳዳሪ  የነበሩት አለቃ ወርቅነህ  አለቃ ተክሌን  ተቀብለው ወደ ራስ ጉግሳ ያቀርቧቸዋል፡፡
ራስ ጉግሳም ጣዕም፤ ለዛና ስልት ያለውን ድምጽ ሲሰሙ በእጅጉ ስለተመሰጡ“ ተክሌ መልአክ ነው እንጂ ሰው አይደለም” ብለው፤ ቀለብ ሰፍረው፤ ደመወዝ ቆርጠው፤ ልብስ አልብሰው  ደብረ ታቦር ኢየሱስ  ተመድበው እንዲያስተምሩ አደረጉዋቸው። በዚያም አለቃ ተክሌ ወንበር ዘርግተውና ደቀ መዛሙርትን አብዝተው ትምህርቱን ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡ በርካታ ሊቃውንትንም በየቦታው አውጥተዋል፡፡ የደብረ ታቦር ኢየሱስ  መምህርና አስተዳዳሪ ሆነው የሠሩት አለቃ ተክሌ ከቀለም ልጆቻቸው በስተቀር  ከአብራካቸው የተከፈለ ዘር አልነበራቸውም፡፡ በመጨረሻም  ርእሰ መምህራን መርሻ  በተወለዱባትና መንበረ ማርያም ተብላ በምትጠራው ደብር ውስጥ ስለ ዐረፉ መካነ መቃብራቸው በዚያው ይገኛል፡፡  
ርእሰ መምህራን መርሻ በ1952 ዓ.ም የተወለዱት እዚያው ደብረ ታቦር  መንበረ ማርያም (እናቲቱ ማርያም) በተባለው ቦታ ነው፡፡ ከንባብ እስከ ዳዊት፤ ከጾመ ድጓ እስከ ድጓ  ያለውን ትምህርት እዚያው ደብረ ታቦር እናቲቱ ማርያም ከአለቃ ማኅተም ዘንድ ተምረዋል፡፡ ቅኔንም በዚያው በደብረ ታቦር ዙሪያ በአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ከየኔታ  ኪዳነ ማርያም ፤ እንደገናም ከጉራምባ ኪዳነ ምሕረት ቅኔ ቤት ገብተው ተቀኝተዋል፡፡
ትምህርታቸውን በማስፋፋትም ድጓ እዚያው ደቡብ ጎንደር በክምር ደንጋይ  እንዝና ማርያም ከየኔታ ሲራክ ወረቴ  ዘንድ ተምረዋል፡፡ ከዚያ መልስ  የተክሌን አቋቋም ለ25 ዓመታት ከአለቃ ማኅተም  ለመማር ችለዋል፡፡ በእርሳቸው ገለጻ መሠረት፤ የተክሌ አቋቋም  ጸናጽሉ፤ ቀለሙ አይያዝም፡፡ በቶሎም አይገባም፡፡ ጩኸቱ፤ የቀለም ወዙ እስከ ሚገባ  በጣም ያደክማል፤ ለሚማረውም፤ ለሚያስተምረውም ብዙ ሰዓት ይፈጅበታል፡፡ የተክሌ አቋቋም ምሥክሩ አለቃ ማኅተም፣ ጥር 10 ቀን 1991 ዓ.ም  ሲሞቱ  ወንበሩ እስከ ሚያዚያ 10 ቀን 1991 ዓ ም ድረስ ክፍት ሆኖ ቆየ፡፡
ይኽንን የተረዳው ሀገረ ስብከቱም  ማንን እንተካበት ብሎ ከአሰበና አለቃ ማኅተምም “ቀለሙን አስፋፍቶ የያዘው መርሻ ነውና እኔን እንዲተካኝ” ብለው ተናዝዘው ስለነበር፣  ከሚያዚያ 20 ቀን 1991 ዓ ም፡ ጀምሮ  የተክሌ አቋቋም ምሥክር ሆነው ተሾመዋል፡፡  ከዚያ ይዞም  600 መምህራንን አስተምረው ምሩቃኑ  በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣በወሎ (በመርሳና በደሴ) ወንበር ዘርግተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡   

Read 5285 times