Monday, 10 April 2017 11:01

የሕማማት ሳምንትና በዓለ ትንሣኤ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(3 votes)

በሀገራችን ከሚከበሩ ታላላቅ ብሔራዊ በዓላት ውስጥ አንዱ የትንሣኤ በዓል ነው። ሕማማት የክርስቶስን መያዝ፣ መገረፉን  መሰቃየቱንና መሞቱን (መሰቀሉን) የሚያመለክቱ ናቸው። ትንሣኤ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ ለሦስት ቀናት ከቆየ በኋላ በድል አድራጊነት መነሣቱን የምንዘክርበት ዕለት ነው።
ጌታችን መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት በአህያ ውርንጭላ  ተቀምጦና በሕዝብ ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕፃናትና ሽማግሌዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው አዳኝነቱን (አምላክነቱን) እየመሠከሩ በመከተል እንዳመሰገኑት  መጻሕፍት ያስረዳሉ።
ሰኞ በቤተ መቅደስ ውስጥ ተቀምጠው ዕቃ ሲሸጡና ሲለውጡ የነበሩትን ሸቃጮች አባርሯቸዋል። ቤተ መቅደስ የጸሎት እንጂ የመነገጃ ቦታ ያለመሆኑን አስተምሮአቸዋል። በዚሁ ዕለት ፍሬ አልባ የሆነችውን በለስ ረግሟታል። ሰኞ የተረገመችው በለስ፣ ማክሰኞ ደርቃ ተገኘች፡ በስምዖንም ቤት ባለሽቶዋ ማርያም (ማርያም እንተ ዕፍረት) ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ አምጥታ ቀብታዋለች።
ረቡዕ አይሁድ ጌታን ለመግደል  ቁርጥ  ውሳኔ አደረጉ። የጌታ ምክረ ሞት ተፈጸመ። እንዴትም እንደሚይዙት ከአይሁድ  ጋር ተስማሙ። በዚሁ ዕለት በጌታ ላይ የተደረገው የሞት ምክክር በመፈጸሙ የዓለም ድኅነት (ዓለም የመዳኛዋ ነገር) ታወቀ። ከዚህም የተነሣ ረቡዕ «ጾመ ድኅነት» ተባለ። ሐሙስ የመጨረሻውን የፋሲካ እራት ከደቀ መዛሙርቱ  ጋር በላ። ከእራት በኋላ መሥዋዕተ ኦሪትን ሽሮ መሥዋዕተ ወንጌልን ተካ ማለት ሥርዓተ ኦሪትን ለውጦ፣ አዲስ ሥርዓተ ቁርባንን ሠራ። ለእኛ አርአያ ይሆን ዘንድም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ። ትሕትናን አስተማረ። የሰው ልጅ ወደ ፈተና እንዳይገባ ተግቶ መጸለይ እንዳለበትም በጌቴሴማኒ እየጸለየ አሳየ። (ዮሐ 13,13-15)
ሐሙስ ማታም በይሁዳ ጠቋሚነት ተያዘና ተዘባበቱበት። ዓርብ ጠዋት የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች (ጸሐፍት ፈሪሳውያን) ኢየሱስ ክርስቶስን አሥረው ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት አቀረቡት። ሞት የሚገባው መሆኑንም ለገዢው ነገሩት። ጲላጦስም ጌታን መርምሮ ምንም ዓይነት በደል ስለ አላገኘበት «ንጹሕ እነ እምደሙ ለዝ ብእሲ» እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ ብሎ እጁን ታጠበ፡፡ ስለ ክርስቶስ ጻድቅነት መሠከረ። ይሁንና አይሁዶች የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተውና መስቀሉንም አሸክመው ወደ ቀራንዮ  በመውሰድ ግፍና በደል ይፈጽሙበት ጀመር፡፡ ነፍሰ ገዳዩ በርባን እንዲፈታላቸውና ንጹሑ የፋሲካ በግ ክርስቶስ ግን በስቅላት እንዲቀጣላቸው ስቅሎ ስቅሎ እያሉ ጮሁበት፡፡
ቀትር ሲሆን (በስድስት ሰዓት) ክርስቶስ ከፈያታውያን (ቀማኞች) ማለት የማናይና  ጸጋማይ ከተባሉ ሁለት ወንጀለኞች ጋር አብሮ ተሰቀለ። ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ዓለም በሙሉ ጨለመ ፤ፀሐይ ጠቆረች፤ ከዋክብትም ረገፉ (ሉቃ 23-44) ጨረቃ ደም ለበሰች። የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ። ደንጋዮችም ተፈረካከሱ፡፡መቃብር እየተከፈተ ሙታን በዐፀደ ሥጋ ተነሡ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸና፤ «አባት ሆይ፤ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ።» ብሎም በራሱ ሥልጣን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ።
በዚሁ ዕለት ወደ ማታ ዮሴፍ የተባለ የአርማትያስ ተወላጅ በንጹሕ ግምጃ ሸፍኖ የክርስቶስን ሥጋ ቀበረው። እናም ክርስቲያኖች የጌታን ፍቅርና ቸርነት ለማግኘት ሲሉ ከሥጋና ከቅባት ምግቦች ታቅበውና የሁዳዴን ፆም ሲጾሙ ሰንብተው በሰሙነ ሕማማት፤ በጸሎት በስግደት በጾምና በአክፍሎት ፈጣሪን ይለምናሉ። ካህናትም ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳናት ከመጽሐፈ ሊቃውንት ስለ ክርስቶስ ሕማምና ሞት የሚያወሱትን ምዕራፎች እያነበቡ ያስረዳሉ። በተለይም ዓርብና የቅዳሜ ሥዑር ዕለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሰባሰብ ከፍተኛ ስግደት ይሰግዳሉ፡፡ ይጸልያሉ። ቅዳሜ ጧት ላይ ካህናት በየቤቱ እየዞሩ ቄጠማ ያድላሉ። «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሐደ» (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ትንሣኤውንም ገለጠ) በማለት ስለ ዲያብሎስ መታሠርና ስለ ጌታችን መመርመር  ብሥራት ያበሥራሉ፡፡
ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ካህናት በያሬዳዊ ዜማ  “ፍጹመ ንጉሠ ኮነንዎ አይሁድ፡፡ ተካፈሉ አልባሲሁ ሐራ ሰገራት ወኮርእዎ ርእሶ በኅለት ረገዝዎ ገቦሁ በኲናት-- ” እያሉ ጸናጽል እያንሹዋሹና ከበሮ እየመቱ ያመረግዳሉ፡፡ ይኽም ፍጹም የሆነውን ንጉሥ አይሁድ በደሉት፤ እጀ ጠባቡንም ጭፍሮቹ እየቀደዱ ተካፈሉት፡፡ ራሱንም  በብረት መንዶ መቱት፤ ራሱንም በጦር ወጉት ማለት ነው፡፡ ምዕመናን  ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ ጧፍ እያበሩና ሊቃውንቱ «ትንሣኤከ ለዕለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ» በማለትም ሲዘምሩ ያድራሉ። «መነሣትህን ለአመንን ብርሃንህን ለእኛ ላክልን» ማለት ነው። «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ» ማለት እንኳን የሰው ልጅ ይቅርና ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካዋን አከበረች ይላሉ። እንደዚሁም “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሠይጣን አግዓዞ ለአዳም እምይዕዜእ ይኩን ፍስሐ ወሰላም» ማለት ክርስቶስ  በከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን  ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ ሰይጣንንም አሠረው። አዳምን ነፃ አወጣው። ከእንግዲህስ በኋላ ፍስሐና  ሰላም ይሁን» በማለት በከበሮና በጸናጽል፤ በእልልታና በጭብጨባ የክርስቶስን መነሣት ያበሥራሉ። ቅዳሴው በሚያራራውና በሚያማልለው  በእዝል ዜማ ሲከናወን ክብር ይእቲውና ዕጣነ ሞገር ቅኔውም እንዲሁ  በእዝል ዜማ ይቀርባል፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴው ከአበቃ በኋላ የክርስቶስ ፍቅር ያገበራቸው ምዕመናን አስቀድመው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰባሰቡ አክፋዮችንና የኔ ቢጤ ድሆችን ያገድፋሉ። ራሳቸውም ይገድፋሉ። እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ (ሽ) እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰህ (ሽ) እየተባባሉም መልካም ምኞታቸውን ይገልጣሉ። በየቤቱ እየዞሩም እርስ በእርስ ይገባበዛሉ።
በተለይ በገጠር  ወተት ያላቸው ሰዎች  እርጎና ወተት በቅርጥ ፤(ከቅል የተሠራ የወተት እቃ) በገምቦ፤ በቶፋ፤በቅል ይዘው በየቤቱ በመዞር የወተት ተዋጽኦ ያድላሉ፡፡ ወተት አልባዎችም የየላሞቹን ስም እየጠሩ “እነ ቡሬ፤ እነ ላሜ ቦራ፤ እነ ካሰች-- እንደ ከበደ መረጡ ከብቶች ሺ ይውለዱ፤ ሺ ይክበዱ ” እያሉ በመመረቅ ለባለ ወተቶች ምስጋና ያቀርባሉ፡፡
ከበደ መረጡ  በተወለድሁበት አካባቢ  ሁለት መቶ ላሞች በአንድ ጊዜ ወልደውለት “ጨጓራ ለበሰ” እየተባለ ይደነቅ የነበረ ሰው ነው፡፡ በልጅነቴ የአካባቢዬ ሰዎች ስለ ከበደ መረጡ  ሀብት እያወሩ ጨጓራ ለበሰ ሲሉ፤ “ከበደ ጨርቅ አጥቶ ነው ወይ ጨጓራ የለበሰ” ስላቸው እንደሣቁብኝ ትዝ ይለኛል፡፡ በኋላ እንደተረዳሁት፤ ከሁለት መቶ በላይ ጥገት ላሞች የነበሩዋቸው የበርጭ ጊዮርጊሱ ከበደ መረጡ በቁመታቸው ልክ ጉድጓድ አስቆፍረውና የጉድጓዱንም ግድግዳ በማር አስለስነው በውስጡ ከቆሙ በኋላ በቁመታቸው ልክ ወተት ይደፋባቸዋል፡፡ በወተት ባሕር ይዋኛሉ፡፡ በርካታ ሰንጋ አርደውም ለዝና እንዲሆን አገር ምድሩን ይጋብዛሉ፡፡ ከእርሳቸው በኋላ ግን በአካባቢው ጨጓራ የለበሰ ሰው የለም፡፡  
    ስቅለትንና የትንሣኤን በዓላት አስመልክቶ አገር ቤት የሚነገር አንድ አባባል አለ፡፡ ይኸውም አንድ ሰው ወላጅ እናቱ በሕማማት ሳምንት በጽኑ ታምማ ከሰነበተች በኋላ ጌታ በሞተበት በእለተ ስቅለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ትሞታለች፤ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓትም ትቀበራለች፡፡ ሕዝቡም “ይኽች ሴት በጣም ጻድቅ  ናት፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሲታመም ታምማለች፡፡ በሞተበት የስቅለት ቀንም ሞታለች፡፡ እናም  እንደ ክርስቶስ  ለሦስት ቀናት በከርሠ መቃብር ቆይታ ትነሣለች” እያለ በስፋት ያወራ ጀመር፡፡
ከሕዝቡ ምኞት ተነሥቶ የእናቱን ትንሣኤ ተስፋ ያደረገው ልጇም ከቅዳሜ ማታ ጀምሮ በኀዘንተኞች ታጅቦ በመቃብርዋ ላይ በመቆም ጧፍ  እያበራ ይጠባበቅ ገባ፡፡ ሰባት ሰዓት፤ስምንት ሰዓት፤ዘጠኝ፤ዐሥር ዐሥራ ሁለት ሰዓት አለፉ፡፡ እናቱ ግን እንደ አልዓዛር  ልትነሣለት አልቻለችም፡፡ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ ጠብቆ  ተስፋ የቆረጠው ልጅ እንደዚህ ብሎ አለቀሰ ይባላል፡-
“ስትታመም ታምማ ስትሞት አብራህ ሞተች፡፡
 አንተ ስትነሣ  የእኔ እናት የት ቀረች፡፡”
ይሁን እንጂ  ዕለተ ፋሲካና ዘመነ ፋሲካ  የደስታ እንጂ የለቅሶ  ጊዜ አይደለምና ማንም ቢሆን በፋሲካ ቀን ማልቀስ አይኖርበትም፡፡ የጨነቀ ነገር ሲመጣ ግን በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ ዓፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በፋሲካ ሰሞን በጀግንነት በወደቁ ጊዜ  ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ፡-
“ዛሬ በትንሣኤው በፋሲካው ቀን፡፡
ክርስቲያን ሲደሰት እኛ ተጨነቅን፡፡”
ብለው  ያለቀሱት ኀዘናቸው እጅግ መራራ፤ የቴዎድሮስ ሞትም የሀገር ሞት ስለ ሆነባቸው ነው፡፡ ይልቁንም ዕለተ ፋሲካ  ለአመኑት ሁሉ ትንሣኤያቸውና ዘመነ መርዓዊም (ዘመነ ጋብቻ) በመሆኑ ካህናቱ “ተፈስሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ፡፡ ወማዕዶታ ለሔዋን ዐፅመ ገቦሁ፡፡ ወኮነ አራቄ ለሐዲስ ኪዳን፡፡ በውኂዘ ደሙ አንጽሖሙ ለመሐይምናን” ማለት “የአዳም ፋሲካውና ከግራ ጎኑ ለተገኘቺው ሔዋን መሸጋገሪያ ድልድይ የሆንሺው ማርያም ደስ ይበልሽ፤ልጅሽ ለሐዲስ ኪዳን አስታራቂ ሆነ፤ በደሙ ፍሳሽም ሕዝቡን ከኃጢያታቸው አነጻቸው” በማለት ማኅሌተ ገምቦ እያወረዱ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል

Read 2410 times