Monday, 10 April 2017 10:58

ከሆሳዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ

Written by  ከዳዊት አላዛር
Rate this item
(4 votes)

  “---እስራኤላውያን፣ ከግብጽ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፣ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ኹኔታ ያመለክታል፡፡ ይህን መሠረት አድርጎ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲኹም ቂጣ፣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ውኃ የሚያስጠማ በመኾኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡”
                    ጾም፤ በቀጥተኛ ትርጉሙ፦ ሰውነት ከሚፈልጋቸውና ለሰውነት ከሚያስጎመጀው ነገር መታቀብ፥ መወሰን ማለት ነው፡፡ ጾም፣ ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና ስላለው፣ ሃይማኖት ባለበት ኹሉ ጾም አለ፡፡ በሃይማኖታዊ ትርጉሙ፦ ፈጣሪን መለመኛ፣ ከኃጢአት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለኾነ በጾም ወራት፣ ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የኾኑ፣ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን፤ ሥጋንና ቅቤን፣ ወተትና ዕንቁላልን ማራቅ ታዟል፤ ባልና ሚስትም በአልጋ አይገናኙም፡፡ ጾም፥ ከምግብ በመከልከል ብቻ ሳይኾን፣ ከጸሎትና ከምጽዋት ጋር ተዛምዶ፣ ዓይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር የተቆጠበ እንደኾነ ደግሞ ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡
በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ባህልና ትውፊት ውስጥ ያሉ፣ የምዕራብም ኾኑ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከሐዋርያት የወረሱት የጾም ሕግና ሥርዓት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም፣ ይኸው የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፤ በሥርዓቷም፣ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት ያሉ ሲኾን፣ ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ ያለ ኹሉ እንዲጾማቸው ሕግ ሠርታለች፡፡
ጾመ ኢየሱስ የመጀመሪያው ነው፤ ዓቢይ ጾም ወይም ሁዳዴ ይባላል፡፡ ስያሜው፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የማዳን ሥራው መጀመሪያ አድርጎ የጾመው በመኾኑና ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች ድል የተነሡበትና ድል የሚነሡበት መኾኑን ያመለክታል፤ የሚቆየውም፣ ለ56 ቀናት ማለትም ለስምንት ሳምንታት ነው፡፡ የየሳምንታቱ እሑዶች፣ የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በሠራላቸውና የክርስቶስን ቤዛነት በሚዘክሩ መዝሙሮች ስም ይጠራሉ፡፡
የመጨረሻው ሳምንት - ሕማማት ነው፡፡ በደመ ክርስቶስ በተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማይታሰብበት ዕለት ቀርቶ ሰዓት እንኳ ባይኖርም፥ የዐቢይ ጾም መዝጊያ ሳምንት የኾነውና ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት - ሰሙነ ሕማማት ከፍተኛውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ የክርስቶስ መከራው፣ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት፤ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የፍዳና የኩነኔ ወቅት የሚታሰብበት ስለኾነ ሰሙነ ሕማማት፣ የሕማማት ሳምንት ተብሏል፡፡
ቤተ ክርስቲያን፣ በሰሙነ ሕማማት ሳምንት ለየት ያለ የአገልግሎት ሥርዓት ሠርታለች፡፡ ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ቅዳሴ አይቀደስም፡፡ የዘወትር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የኾነው፥ ጥምቀተ ክርስትና፣ ሢመተ ክህነት፣ ሥርዓተ ፍትሐት፣ ሥርዓተ ማሕሌት፣ ሥርዓተ ተክሊልና ሌሎችም የተለመዱ አገልግሎቶች አይካሔዱም፡፡ በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም፡፡ በአጠቃላይ፣ የጌታችንን ሕማሙን፣ ሥቃዩን፣ መከሠሡን፣ መያዙን፣ ልብሱን መገፈፉን፣ በጲላጦስ ዐደባባይ መቆሙን፣ መስቀል ላይ መዋሉን፣ ሐሞት መጠጣቱንና ሌሎችንም ለበደለኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ፡፡
እነዚኽ፣ ሥርዓታዊና ምስጢራዊ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎቶች፣ ከሆሳዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ የሚፈጸሙ ሲኾኑ፤ ካህናትና ምእመናን በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ አብዝተው በመጾም፤ ከሐሜት፣ ከነገረ ዘርቅና ከኃጢአት ርቀው፣ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ፤ ግብረ ሕማማት የሚባለውን መጽሐፍ ሲያነቡና ሲሰሙ፣ ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ፥ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት/በዘጠኝ/፣ በሠርክ/ዐሥራ አንድ/ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ሰሙነ ሕማማት የተለየ ሳምንት ነውና፣ እንኳን ሥጋዊ ደስታና ሣቅ ጨዋታ መንፈሳዊ ደስታም የተከለከለ ነው፡፡
የሰሙነ ሕማማት ዜማ፥ ከሰኞ እስከ ረቡዕ - ግዕዝ፣ ሐሙስ - አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ - ዕዝል ነው፡፡ በእነኚኽ ዕለታት፣ ከኹሉም በፊት የሰዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል፡፡ የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር/መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፡፡ ድጓው ከአራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋራ እንዲስማማ ኾኖ ነው የሚቃኘው፡፡ ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡-
ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ዐማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም
ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም፤
ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳዕየ እብል በአኮቴት
እየተባለ፣ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ ዐሥራ ኹለት ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡
ከዚያ በመቀጠል፡-
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ /በዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ
እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ። በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ ይጀምራል። በመጨረሻ ተኣምረ ማርያም እና ተኣምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ፣ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ፣ ምእመናንም፣ አቤቱ ይቅር በለን፤ እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡
ከዚያም ኹለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል። ዜማውን በቀኝ በግራ በመቀባበል፣ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል፡፡ እንዲኽ በማለት፡-
ኪርያላይሶን/አምስት ጊዜ/ በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን/ሁለት ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል
ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን ዐማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን
በዚኽ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻ በግራ በቀኝ በማስተዛዘል 41 ጊዜ ይደገማል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት፣ የጌታችን ኅቡእ ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡ ምንባባቱ ከመለያየታቸው በቀር በኹሉም ዕለታት ሥርዓቱ ተመሳሳይ ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት ያለው ዓርብ፣ የስቅለት ዓርብ ይባላል፤ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ ዕዳ በደሉን ተሸክሞ የተንገላታው የዓለሙ ኹሉ መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ ኾኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ነው፡፡ ስቅለት፣ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን፣ የጌታን የመከራውንና የሕማሙን ነገር የምናስታውስበት በመኾኑ የሚከበረውም በስግደት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በንባብና በትምህርት ነው፤ ስግደቱም ከሰሞኑ ኹሉ የበለጠ ነው፡፡
በመኾኑም በስቅለት ዓርብ፣ መሪው ዕዝል ይመራል፤ ሕዝቡ ይከተላል፤ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ፥ “ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት = ሲነጋም ሊቃነ ካህናት ተማከሩ” የሚለው ዜማ፣ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል። ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንዳለፈው ይቀጥላል፡፡ ይህም ቀኑን በሙሉ ሲከናወን ውሎ በዐሥራ አንድ ሰዓት፣ ካህናት በአራት ማዓዝን ቆመው እግዚኦታ ያደርሳሉ፡፡ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጸናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡
ምእመናንም፣ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጢአት እየተናዘዙ በካህናት አባቶች ንስሐ ይቀበላሉ፤ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይኸውም፣ በአንድ በኩል የክርስቶስ ግርፋት ተሳታፊዎች መኾናቸውን ለመግለጥ ሲኾን፣ በሌላ በኩል የተግሣጽ ምሳሌ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው፤ የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው፤ እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ለማለት ነው፡፡
ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው፣ በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር፣ አቅሙ ተመዝኖ የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፤ በታዘዘውም መሠረት ይፈጽማል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፣ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ፣ በካህኑ ኑዛዜ ወደየቤቱ ይሰናበታል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፤ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል፣ ጌታ በደሙ ቀድሶ፣ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት ዓርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ አድርጎ የሰጠበትን የትንሣኤውን ብርሃን እስክናይ ድረስ፡፡
ከዓርብ ስግደት መልስ፣ እስከ እሑድ /የትንሣኤው ሌሊት/ ድረስ ኹለት ቀን የሚያከፍሉ ምእመናን፣ ምንም ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ ይህም አክፍሎት ይባላል፡፡ የማያከፍሉ ግን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው ይሰነብታሉ። ብዙ ጊዜ የሚቀመሰውም፣ ከጸሎተ ሐሙስ የተረፈውን ጉልባንና ዳቦ ነው፡፡ ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና በጸሎተ ሐሙስ የሚበላ ንፍሮ ነው። እስራኤላውያን፣ ከግብጽ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፣ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ኹኔታ ያመለክታል፡፡ ይህን መሠረት አድርጎ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲኹም ቂጣ፣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ውኃ የሚያስጠማ በመኾኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡
ቅዳሜ ጠዋት፣ ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፤ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም፣ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሀደ = በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፤ ትንሣኤውን ገለጸ፤ የምሥራች” እየተባለ እየተዘመረ ቄጤማው ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፤ ምእመናኑም እየሠነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን በመልበስ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው በየሰበካቸው፣ ቄጤማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፤ ምእመናንም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡
ቄጤማው በራስ ላይ መታሰሩ፥ አይሁድ በጌታችን ጭንቅላት ላይ የእሾህ አክሊል ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡ ጥንተ አመጣጡና ምስጢሩ ግን፣ ከአባታችን ኖኅ ታሪክ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት፣ የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጤማ ባፏ ይዛለት በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች፦ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ ኃጢአት - ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤ በክርስቶስ ሞት ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ በማለት፣ አዳምና ልጆቹ፥ ከለምለሚቱ ሥፍራ ከተድላ ገነት መግባታቸውን ለመግለጽ፥ ምእመናን ቄጤማ ይዘው፣ ቄጤማ አስረው ይታያሉ፤ ትንሣኤውንም ለሚናፍቁ ትልቅ ብሥራት ነው፡፡
የሰሙነ ሕማማት ቅዳሜ፣ “ሰንበት ዐባይ” ትባላለች፤ ጌታችን፣ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለበት ዕለት ናት፡፡ ኹለተኛም፣ ይህች ዕለት ስዑር ቅዳሜ፤ የተሻረች ቀዳሚት ሰንበት ትባላለች፡፡ ስዑር መባሏ በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፤ “ቅዳሜ ሹር” እንዲሉ፤ አንድም፣ በዚኹ ቀን በሚባለው ዕዝል ውስጥ፥ ስኢሮ ሞተ፤ ሞትን ሽሮ ተነሣ፤ ይላል፤ ሞትም የተባለው ዲያብሎስ ያመጣው ሞተ ነፍስ ነውና፣ የተሻረ የተባለው ዲያብሎስ ነው፡፡
በአዳም ከሲኦል መውጣትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት፣ ቤተ ክርስቲያን የምታሰማን የምሥራች ከደስታ ኹሉ የበለጠ ነው። ምንም እንኳን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ቢኾንም፣ አዳም ከሲኦል ወጥቶ ወደ ገነት መግባቱ የታወቀው፤ የክርስቶስ ትንሣኤው የተመረመረው በቀዳም ስዑር ስለኾነ፣ የትንሣኤው ብሥራት በአፈ ካህናት ለሕዝበ ክርስቲያን ይነገርበታል፡፡ የኀዘኑ  ዜማዋና የኀዘኑ ልብሷ ተለውጦ፣ የጸናጽል የከበሮ ድምፅ ታሰማለች፡፡
ቅዳሜ ምሽት፣ የአብያተ ክርስቲያናቱ ቅጽርና ዙሪያው ነጫጭ በለበሱ ምእመናን መልቶ ሲታይ ያስደንቃል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ ደወሎች ሲደወሉ፣ መዘምራኑ የማሕሌቱን፣ ቀሳውስቱ የሰዓታቱን ሥርዓት ማከናወን ይጀምራሉ፡፡ ማሕሌቱ ተቁሞ ቆይቶ በምልጣኑ ሳዓት ዲያቆኑ ከዳዊት መዝሙር፣ ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምነዋም… ብሎ በሚስረቀረቅ ዘለግ ባለ ድምፅ በሰበከ ጊዜ፣ የሕዝቡ ደስታ በጣም የበዛ ይኾናል፤ በውስጥም በውጭም ያለው ሕዝብ በእልልታና በጭብጨባ ተቀባብሎ ያደምቀዋል፡፡
ከዚኽ በኋላ፣ የትንሣኤውን ነገር የሚያነሣው ወንጌል ተነቦ፣ መሪው መስቀሉን ከዲያቆኑ ተቀብሎ፦ ዮም ፍሥሓ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን እስመ ተነሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና ዛሬ በክርስቲያን ሰንበት በዚኽች በእሑድ ፍሥሓ ኾነ፤ ደስታ ተደረገ፤ ብሎ መርቶ መዘምራኑ ይህንኑ ተቀባብለው ይዘሙታል፤ ያሸበሽቡታል፡፡
ከዚኽ በኋላ፣ ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ = ትንሣኤህን ለምናምን ኹሉ ብርሃንህን ላክልን፤ የሚለውን እስመ ለዓለም የተባለውን ቀለም አለዝበው በወረቡት ጊዜ፣ ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን፣ ከሰም የተሠራ የጧፍ መብራት ይታደልና ዑደቱ ሊደረግ ይጀምራል፤ ከጧፉ ውጋጋን የተነሣም ምሽቱ ሰዓተ መዓልት ኾኖ ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎም፣ ሦስት ጊዜ ከተደወለ በኋላ ቅዳሴ ለመግባት ሲዘጋጁ ይታያል፤ መንፈቀ ሌሊት ሲኾን ቅዳሴ መቀደስ ይጀመራል፤ ድርገትም በወረዱ ጊዜ በጣም ብዙ ሰው ሥጋወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅቶ ይቀርባል፡፡
ከቅዳሴም በኋላ፣ ኹሉም ወደየቤቱ ተመልሶ በትንሣኤው በዓል ከየቤተሰቡ ጋራ ደስ ብሎት የሚገባውን ያደርሳል፡፡ በበነጋውም በየቤተ ዘመዱ እየሔደ፣ እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ፤ እንኳን አብሮ ፈታልን፤ እየተባባለ ይጠያየቃል፤ እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልን፤ ማለት፣ ሁለት ወር ሁዳዴ ሲጾም ሰንብቶ በጌታ ትንሣኤ ምክንያት ጾሙ ስለቀረለት ነው፡፡
በተጨማሪም፣ የአክፋይ ወይም ገብረ ሰላመ እየተባለ፣ ምእመናን፣ ከማዕዶት እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ዕለታት ተከፋፍለው ለሰበካቸው ካህናት፥ ጠላ በመንቀል፣ እንጀራ በአገልግል በመውሰድ ያበላሉ፤ በየቤታቸውም እየጠሩ ይጋብዛሉ፤ እንዲኹም ዘመድ ዘመዱንም ሲጠይቅ ይሰነብታል። ይህም፣ ጌታችን ከተነሣ በኋላ እስኪያርግ ድረስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት ቀን ግብር አግብቶ መግቧቸው ነበርና ያንን ያሳስባል፡፡

Read 1573 times