Monday, 10 April 2017 11:13

ጥሞና - ወግ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

መሽቶ ይነጋል፡፡ ቃልኪዳኑ አይጓደልም፡፡ መለመላዬን ሆኜ ከተቸነከርኩባት ኩርማን ዞሮ መግቢያዬ አሻግሬ እያነጣጠርኩ ነው፡፡ የኮንዶሚኒየሙ ብርቅዬ እብድ፤ እሳት እያነደደ ያልጎመጉማል፡፡ እርሱ ምን አለበት… ጎበዝ፡፡ በደህና ጊዜ ተነካክቶ፡፡ ሸክሙ  እንደ ጤዛ ነው፡፡ ጓዙን አሽንቀጥሯል፡፡ ለነገሩ በዚህ ዘመን እብደት ዓይን አዋጅ ሆኗል፡፡ ጨርቅ አልጣልንም እንጂ… እኛም ከተነካካን ሰነበትን፡፡ ወደ ፍሬ ነገሩ ልዝለቅ፡፡
ሽቅብ ወደ ላይ ተመንድጌ ነው የዶከንኩት፡፡ አራት ደረጃዎችን ተሸጋግሬ፣ ከኮንዶሚኒየም ስቱዲዮ ላይ ፡፡ ደርሶ ወደ ላይ መሰቀል ይቀናኛል፡፡ ለነገሩ በምክንያት ነው፡፡ አንድም ለፈጣሪ ለመቅረብ፣ሁለትም ከግርግሩ ለመነጠል፡፡ የሀገሬ ባለቅኔ እንዲህ ብሎ ነው መሀላ ያስገባኝ፡-
ከሰው መንጋ እንነጠል፣
ለአንድ አፍታ እንኳን እንገለል፣
በእፎይታ ጥላ እንጠለል፣
 ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል፣
                           ፀ.ገ
በቀለስኩት የባይተዋር ደሴት ላይ ከሙሽራዋ ነፍሴ ጋር ገጥ ለገጥ ተሰይሜ ዝም ብያለሁ፡፡ ማጉረምረም ሲያሻኝ ድርሳን እገልጣለሁ፡፡ ደሞ ለማጉረምረም…፣ከድርሳን ወዲያ ላሳር፡፡
በቀን ጎዶሎ በተፈጠረ አጋጣሚ፣ድንገት ጥሞናዬ አጓጉል ሆነ፡፡ አንዲት ልብ አተንርክክ ጠይም ዓሳ መሳይ፣ ታቅፌ የኖርኳትን ሙሽራዋ ነፍሴን ለመቀናቀን ቀረበችኝ፡፡ ተካልቤ ነፍሴን ከዕቅፌ አበረርኳት፡፡ በወረት ፍቅር ጨርቄን ጣልኩ፡፡ የባይተዋሩ ግዛት በሰው መንጋ ተወረረ፡፡ አንገቴ ላይ ወፍጮ ታስሮ ከግርግሩ ባህር ተወረወርኩ፡፡ ከውብ ኮረዳ ጋር እህል ውሃ መግጠም ይህን ታህል ያብሰከስካል እንዴ ትሉ ይሆናል፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል፡፡
የኮረዳዋ የሠርክ ወሬ ቢታክተኝ የሥጋ ጥሜን ልቆርጥ ተነሳሳሁ፡፡ ከንፈሬን በከንፈሯ እያሟሸሁ፣ እንደ ጦር  የሾሉትን አጎጥጓጤዎቿን ለመቃረም ተንደረደርኩ፡፡ አፈጣጠኔ ሳያስበረግጋት አልቀረም፡፡ መዳፌን አፈፍ አደረገችው፡፡
“ቀዩን መስመር ያለፍክ አልመሰለህም”?! አለች መንቁሯን አሹላ ዓይኖቿን አጉረጠረጠችብኝ፡፡
አሁን ማን ይሙት፣ በቀይ ድንበርነት መሞሸር የሚገባው አመልማሎ ከንፈር ወይስ አጎጥጓጤ ? ከነፍሴ ጋር ስቃበጥ በድንበር ታግቼ አላውቅም፡፡ ሁለ ነገሬ የኩታራ ነበር፡፡ ወትሮስ ከነፍስ ጋር የተወዳጀ፣ምን ይሉኝታ፣ምን ክልከላ ይገባዋል?
የኮረዳዋ ገላ የማያውቁት ሀገር ሆነብኝ፡፡ ስለ ድንበሩ ላወጣ ላወርድ አቀረቀርኩ፡፡ ኤፍኤም ራዲዮ ላይ የሚለፈልፈው  ወሬ አስተናባሪ፣ እንደ እርጎ ዝንብ ማሀላችን ጥልቅ አለ፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በትዳር የፀኑ ጥንዶችን ቃል እየተቀበለ ነው
“የስኬት ምስጢሩን ወዲህ በሉን አባት” ወሬ አስተናባሪው ለአዛውንቱ አባወራ ጥያቄውን ሰነዘረ፡፡
“ምስጢሩ ለእኛም ግራ ነው የእኔ ልጅ”
“እንዴት ማለት” ግርታ በአኳተነው ቅላጼ ጥያቄውን መልሶ ወረወረ፡፡
“ማርን ቀምሶ ለማያውቅ ብላቴና ስለ ማር ጣዕም ከምታነበንብለት እንዲቀምሰው ጋብዘው፡፡ ያን ግዜ ሁሉ ነገር ያከትማል፡፡ የእኛም የስኬት ምስጢር ከኽይሁ ቁምነገር ጋር በአንድነት ይሰለፋል፡፡ ጎጇችን ውስጠ ወይራ ናት፡፡ ሳቅ ጨዋታዋ የሚደራው በዝምታ፣በስክነት ድባብ ውስጥ ነው፡፡” አሉና ለአፍታ ጥሞና ውስጥ ገቡ፡፡
ጎምቱው አዛውንት ለከላባው ወሬ አስተናባሪ ፈተና ሆኑበት፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በጥሞና የፀና ጎጆ፡፡ መንፈሳዊ ቅናት አንጨረጨረኝ፡፡ ወደ ዘነጋሁት የጥሞና ዓለም ለመመለስ አቆበቆብኩ፡፡ ተሳካልኝ፡፡ አንድ ሁለት እያሉ አርባ ደቂቃዎች እንደዋዛ ተዳመጡ፡፡ ያለፉት የእፎይታ ቅጽበቶች ኮረዳዋን የቁም እስር ቤት ውስጥ ከተዋት ኖሯል፡፡ አፍንጫዋን እንደነፋች በሩን በላዬ ላይ ጠርቅማ እብስ አለች፡፡ በዚያው የውሃ ሽታ ሆና ቀረች፡፡
 ሙያህስ፣ግብርህስ ካላችሁኝ፤ ይኸው እንካችሁ፣የታሪክ መምህርነቴን ዕወቁት፡፡ የታሪክን ሀሁ ለማስቆጠር በይፋ ያወጅኩት፣ ታሪክ ሠሪ ትውልድ ለመፍጠር ነበር፡፡ እንደው ድከም ብሎኝ ነው፡፡ ትውልድ በእኔ ዘበን ቀርቷል፡፡ ያ በፈረንጅ አፍ የሚያነበንብ፣ቀለምን እንደ ውሃ የጨለጠ ትውልድ፡፡ ለነገሩ እንደውሃ መጨለጥ ምን ይፈይዳል? ከአንጀት ካልተጠጋ፡፡ ያ ትውልድን የትርምስ፣የግርግር፣የእንኪያ ሰላንቲያ መቀመቅ አንድ ጊዜ እንደሆነ ውጦ አስቀርቶታል፡፡ ከጎሬው የከተተው አውሬ አልጮኽ ብሎ  ከለገመ  የክፍለ ዘመን እኩሌታ መገባደዱም አይደል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ የታሪክ ባለሟሎቻችን ፊት የሚሰጡት ለትናንትና ግርግራችን ብቻ ነው ፡፡ ከጥሞና ገበናችን ጋር ሆድ ጀርባ ናቸው፡፡ አክሱምን፣ላሊበላን ያነጹ ምጡቅ ጦቢያዊያን ጥሞና በዓይናችን እንደዞረ፣ በትርምስ ውስጥ እያዘገምን ዝንት ዘበንን ተሻገርን ጎበዝ፡፡
ታሪክን፣ታሪክ ያነሳዋል እንዲሉ፡፡ ታሪክ ባልሠራም፣ታሪክ ሠሪ ትውልድ ለዓይነ ሥጋ ማብቃት ቢሳነኝም፣በአንድ ነገር ግን  ተሳክቶልኛል፡፡ ከኑሮ ጋር ባለኝ ግብግብ ትልቅ ገድል በመፈጸም ላይ እገኛለሁ፡፡ እንደ እፉዬ ገላ እፍ ቢሉት ዕልም በሚል ወርሃዊ ገቢ ይህን ሁሉ ዘበን መወዝወዝ ቀላል አይምሰላችሁ፡፡ ኩርማን ደሞወዜን የጨበጠው መዳፍ ኦና ለመሆን የሚፈጅበት ቅጽበት አፍታ ነው፡፡ አንድአንዴ ይህም ሲበዛ ነው ብዬ ራሴን አጽናናለሁ፡፡ እንደውም ከዚህች ከማታወላዳ ዳረጎት ጋር  አብረው እንደ ጥቅማጥቅም ጅራፍ ቢጤ ለጀርባዬ ቢመርቁልኝ አይከፋኝም፡፡ ትውልድ ለመበደል ፊት ለፊት በኩራት የተሰለፍኩ ባለሟል መሆኔን አትዘንጉት፡፡
ለነገሩ እኔ ምንተዳዬ፣ ትችላለህ ታሪክ ፍጠር ብሎ ሰርተፍኬት የሸለመኝ አስኳላው፡፡ አስኳላው ይጠየቅልኝ፡፡ የምን ማፈግፍግ ነው፡፡ ግፋ ቢል፣ ዓሳውን መጎርጎር፣ከፋም ሲል ዘንዶውን ማውጣት፣ሌላ ምን መወስለት ያስፈልጋል፡፡ እናንተዬ ቀይ ድንበር አካባቢ እንደደረስኩ አፍንጫዬ  እየነገረኝ ነው፡፡ ያቺ ኮረዳ በደህና ጊዜ ድንበሩን አመላክታኛለች፡፡ ለካስ ለወግም ቀይ ድንበር አለው፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

Read 701 times