Monday, 10 April 2017 11:18

“መሐረቤን ያያችሁ” መጽሐፍ ተመርቆ በገበያ ላይ ዋለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በወጣቱ ደራሲ ሙሉጌታ አለባቸው የተጻፈው “መሐረቤን ያያችሁ” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ መጽሐፍ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በሞዛይክ ሆቴል በተከናወነ ልዩ ፕሮግራም ተመርቆ በገበያ ላይ ውሏል፡፡
የስነ-ጽሁፍ ቤተሰቦች በተገኙበት ስነ-ስርዓት የተመረቀውና ማሕበራዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሀሳቦችን የሚዳስሰው “መሐረቤን ያያችሁ”፣ መቼቱን በ1980ዎቹ መጨረሻ የኢትዮጵያ ማሕበራዊ ሕይወት ላይ አድርጎ፣ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሳ ሲሆን በአዳዲስ የትረካ ቅርጾች የተዋቀረ ነው፡፡
የደራሲ አዳም ረታን “ሕጽናዊነት” የተባለ ልዩ የአጻጻፍ ስልት መጠቀሙን በመጽሃፉ መግቢያ ላይ የጠቆመው ደራሲው፤ በ215 ገጾች የቀረቡት አስራ ሁለት አጫጭር ትረካዎች እርስ በእርስ በቀጫጭን የትረካ መስመር እንደሚገናኙም ገልጧል፡፡
በሕጽናዊነት የአጻጻፍ ስልት ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔዎችን ሲያቀርብ የቆየው ደራሲው፤ “ይሄን ስልት መጠቀሜ ሕጽናዊነትን የማስቀጠል ደፋር ሙከራዬ ነው” ሲል አብራርቷል፡፡
ደራሲ አዳም ረታ በመጽሃፉ የጀርባ ሽፋን ላይ በሰጠው አስተያየት፤ “የሙሉጌታ አለባቸው ቋንቋ ውብ ነው፡፡ ይሕ መጽሐፍ ሊናቅ የማይችል የአንድ ወጣት የስነጽሑፍ ጀብደኛ ዘራፍ ነው” ብሏል፡፡
በአዲስ አድማስና በሌሎች ጋዜጦችና የህትመት ውጤቶች ላይ ለረጅም ጊዜያት አጫጭር ልቦለዶችን፣ ስነጽሁፋዊ ትንተናዎችን፣ መጣጥፎችንና የትርጉም ስራዎችን ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ሙሉጌታ አለባቸው፤ መጽሃፉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመጽሃፍት ቤቶችና በአዟሪዎች እየተሸጠ እንደሚገኝም በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡

Read 2324 times