Monday, 10 April 2017 11:21

1 ሚ. አፍሪካውያን በሊቢያ በኩል የስደት ጉዞ ላይ ናቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አይሲስ በሊቢያ አግቷቸው የነበሩ 28 ኤርትራውያን ተለቀቁ

    የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሆኑ 1 ሚሊዮን ያህል ስደተኞች በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በማሰብ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የስደት ጉዞ ላይ እንደሚገኙ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ብቻ 590 ያህል አፍሪካውያን ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው መሞታቸውን የጠቆሙት በሊቢያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የቀድሞ ሃላፊ  ጆ ዎከር ከዚንስ፣ 1 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን ስደተኞች ለሞት በሚያጋልጠው በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016፣ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ጣሊያን የገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር 181 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በዚሁ የስደት መስመር ጣሊያን የገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች 22 ሺህ ያህል እንደሚደርሱም  አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ አሸባሪው ቡድን አይሲስ በሊቢያ ሲርጥ ውስጥ አግቷቸው የነበሩና ቡድኑ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ አካባቢውን ለቅቆ ከሄደ በኋላ የትሪፖሊ መንግስት ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል በሚል አስሯቸው የቆዩ 28 ኤርትራውያንና ሰባት ናይጀሪያውያን ስደተኞች መለቀቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ወደ አውሮፓ ለመግባት በስደት ጉዞ ላይ የነበሩ ሴቶች እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ የአይሲስ ታጣቂዎች ሴቶቹን በማገት ለወሲብ ሲጠቀሙባቸው እንደነበርም ገልጧል፡፡
ስደተኞቹ ባለፈው ረቡዕ ከእስር መለቀቃቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የተቀበላቸው ሲሆን  የህከምና ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ መጠለያ እንዲገቡ መደረጉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1382 times