Monday, 10 April 2017 11:23

10 በመቶ የሚሆነው ሞት በማጨስ ሳቢያ የሚከሰት ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በ2015 ከአለማችን አራት ወንዶች አንዱ በየዕለቱ ያጨስ ነበር

        ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝና በአለማችን በየአመቱ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 10 በመቶ ያህሉ የሚከሰቱት ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ መሆኑን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
በ195 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራውን ሰፊ ጥናት መሰረት ያደረገውንና ዘ ላሰንት በተባለው ሜዲካል ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፤ በ2015 ብቻ አንድ ቢሊዮን ያህል ያህል ሰዎች በየዕለቱ ሲያጨሱ እንደነበርና በአመቱ ከአለማችን አራት ወንዶች አንዱ በየዕለቱ ሲጋራ የሚያጨስ (የዘወትር አጫሽ) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሲጋራ ማጨስ ያለ ወቅቱ ለሚከሰቱ ሞቶችና ለአካል ጉዳተኝነት ምክንያት በመሆን ሁለተኛውን ደረጃ እንደሚይዝ የጠቆመው ጥናቱ፤ በ2015 አመት ብቻ በአለማቀፍ ደረጃ ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ6.4 ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ አክሎ ገልጧል፡፡
የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ገበያቸውን በተለይም ወደ አላደጉ አገራት ለማስፋት እየሰሩ ከመገኘታቸው ጋር በተያያዘ በማጨስ ሳቢያ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ጥናቱ፤ መንግስታት የትምባሆ ቁጥጥር ህግን ማጥበቅ እንደሚገባቸውም መክሯል፡፡

Read 1898 times