Saturday, 15 April 2017 12:37

ለበዓሉ በአዲሱ የትንፋሽ መርመሪያ ከፍተኛ የትራፊክ ቁጥጥር ይደረጋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“የትንፋሽ መመርመሪያው ውጤት እያመጣ ነው”
   የአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ፅ/ቤት፣በአዲሱ የትንፋሽ መመርመሪያ በመጠቀም ለበአሉ ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ላይ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የፅ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ፤ አዲሱ የትንፋሽ መመርመሪያ መሳሪያ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው፣በትንሳኤ በዓልም ከወትሮው በተለየ ከዋዜማ አንስቶ ጠንካራ ክትትልና ፍተሻ እንደሚደረግ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
መሳሪያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በርካታ አሽከርካሪዎች ግንዛቤ እያገኙ በመሆኑ ከአልኮል ነፃ ሆኖ ማሽከርከር እየተለመደ መምጣቱን የጠቆሙት ም/ኢንስፔክተሩ፤ቁጥጥሩ በሙከራ ደረጃ ላይ እያለ በርካታ አሽከርካሪዎች ጠጥተው ይያዙ እንደነበርና አሁን ግን ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህም አሽከርካሪዎች ግንዛቤ እያገኙ መሆኑን መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡ የአደጋው መጠን በምን ያህል ቀነሰ የሚለውን ለመገምገም ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅ ገልጸው፤በአጭር ጊዜ የተገኘው ውጤት ግን አበረታች ነው ብለዋል- ም/ኢንስፔክተሩ፡፡ ለበዓሉ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥር ተጨምሮ፣ በአዳዲስ አካባቢዎች ሁሉ እንደሚመደቡና ቀንም ማታም የአልኮል ቁጥጥሩ እንደሚደረግ ም/ኢንስፔክተር አስታውቀዋል፡፡ አልኮል ከመጠን በላይ ጠጥቶ የተገኘ አሽከርካሪ፣አብሮት ያልጠጣ ሰው ካለ፣መኪናውን እንዲያሽከረክር እንደሚደረግ፣ይህ ካልሆነም መኪናው ለ12 ሰዓት ያህል ፖሊስ ጣቢያ ይቆምና አሽከርካሪው የክስ ወረቀት ተሠጥቶት፣ ቅጣቱን ከከፈለና መንጃ ፍቃዱ ከተሰጠው በኋላ መኪናውን እንደሚወስድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለማንኛውም የትራፊክ መንገድ መዘጋጋትም ሆነ የወንጀል ችግሮች በ991 የነፃ መስመር ወይም በ0111 110111 ቢደወል ፖሊስ ፈጣን ምላሽ ይሰጣል  ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ትራፊክ ጽ/ቤት፤ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው ተመኝቷል፡፡ 

Read 2462 times