Saturday, 15 April 2017 12:38

መንግሥት የሠብአዊ መብቶች አያያዝን እንዲያሻሽል የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

‹‹ማዕከላዊ›› ላይ የሚቀርቡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አቤቱታ በገለልተኛ ቡድን እንዲጣራ ተጠይቋል

የአውሮፓ ህብረት የሠብአዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ስታቭሮስ ላምብሪኒዲስ፤ በኢትዮጵያ  ያለውን የሠብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር የተወያዩ ሲሆን መንግስት የሠብአዊ መብቶች አያያዝን  እንዲያሻሽል ተጠይቋል፡፡   
የህብረቱ ልዩ ተወካይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ለ3 ቀናት ባደረጉት የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረ  የሥራ ጉብኝት፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በወቅታዊ የሠብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በአንክሮ መምከራቸው ተጠቁሟል፡፡ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ የሠብአዊ መብት ጥሠት በመፈጸም አቤቱታ ይቀርብበታል የተባለውን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) የጎበኙት ልዩ ተወካዩ፤ በጸረ ሽብር አዋጁና በሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ወንጀሎች በተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሚደረገውን የምርመራ ሁኔታና የእስር አያያዝ በተመለከተ ተቋሙን ከሚመሩ ከፍተኛ አስተዳዳሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን በተቋሙ ላይ የሚቀርቡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አቤቱታ በገለልተኛ መርማሪ ቡድን እንዲጣራ ጠይቀዋል፡፡  
‹‹የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች ለማጠናከር ዝግጁ ነው›› ያሉት ሚ/ር ላምብሪኒዲስ፤‹‹ለዚህ ወሳኙ በሠብአዊ መብት አያያዝ ላይ ተጨባጭ መሻሻል ማምጣት ነው›› ብለዋል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናቱና የህብረቱ ልዩ ተወካይ ውይይት በዋናነት ያተኮረው ባለፈው ዓመት  በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በታሰሩ ግለሰቦች የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ላይ ሲሆን ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸው ለህብረተሰቡ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል - ላምብሪኒዲስ፡፡ የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎችም እንዲፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እንዲነሳ ልዩ ተወካዩ ጠይቀዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍጥነት  መነሳት መንግስት አቅጀዋለሁ ላለው የፖለቲካ ለውጥ ትልቅ ማሳያ እንደሚሆንም ሚስተር ላምብሪኒዲስ ገልፀዋል፡፡
በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ላይ ገደብ የሚያስቀምጡ የአዋጅ ክልከላዎችና ህጎች በድጋሚ እንዲፈተሹና ዜጎች አመለካከታቸውንና ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁባቸው መገናኛ ብዙኃን ያለ ፍርሃት በነጻነት የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ልዩ ተወካዩ ጠይቀዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራት እንዲጠናከሩ፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታም እንዲሻሻል በውይይቶቹ ላይ ተጠይቋል፡፡
ከመንግስት በኩል የፖለቲካ ማሻሻያዎች ለማድረግና ለወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር የተለያዩ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑ ለተወካዩ እንደተገለፀላቸው የአውሮፓ ህብረት ልኡክ በኢትዮጵያ፣ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ አንድም ተቃዋሚ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት ያልቻለበት እንደነበር የጠቀሱት ልዩ ተወካዩ ፤ በ2010 እና በ2012
የሚደረጉ ምርጫዎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሣትፎ የሚጠናከርበት እንዲሆን መክረዋል፡፡  
የአውሮፓ ህብረት የሠብአዊ መብቶች ጉዳይ ልዩ ወኪል በኢትዮጵያ፤ በአገሪቱ ወቅታዊ  የሠብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝን ጨምሮ የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ሊቀመንበር፣ ም/ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነርንና ሌሎች የገዥው
ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናትን  ያነጋገሩ ሲሆን ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ከሠብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው

መምከራቸው ታውቋል፡፡

Read 2361 times