Saturday, 15 April 2017 12:42

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳውዲ ዜጎችን ለማስመለስ ኮማንድ ፖስት አቋቋመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል

    በሳኡዲ ከሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጥቂቶቹ ብቻ የመኖሪያ ፍቃድ እንዳላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሌላ ሀገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሳኡዲ አረቢያን ለቀው እንዲወጡ የታወጀውን አዋጅ ተከትሎ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵውያን ተመላሾችን ጉዳይ የሚከታተል ኮማንድ ፖስት አቋቋመ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ያለ ችግር ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሚኒስትር ዴኤታ በሆኑት አክሊሉ ገ/ሚካኤል የሚመራ ቡድን፣ ከሳኡዲ ባለስልጣናት ጋር መምከሩን አስታውቀዋል፡፡ “ከህገ ወጥ የውጭ ሀገራት ነዋሪዎች ነፃ የሆነች ሳውዲ አረቢያን ማየት” በሚል መነሻ በወጣው አዋጅ፤ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሀገር ዜጎች ከሀገሪቱ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወደ 100 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በሣኡዲ አረቢያ እንደሚኖሩ የሚገመት መሆኑን የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከነዚህ ውስጥ ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው ጥቂቶቹ ብቻ መሆኑን ጠቁሞ፣ የአዋጁ ጊዜ ሊጠናቀቅ የአንድ ወር ከ15 ቀናት ጊዜ ብቻ የቀሩት ቢሆንም እስካሁን 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን ብቻ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ እንደተመዘገቡ አስታውቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥም 200 ያህሉ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ይህ ቁጥር የ90 ቀኑን እድል ተጠቅመው ወደ ሃገር ቤት ይመለሳሉ ተብሎ ከሚጠበቀው አንፃር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሠው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ጉዳዩ አሳስቦኛል ብሏል፡፡ የሣኡዲ አረቢያ መንግስት ህገ ወጥ የሚላቸው፣ በህገ ወጥ መንገድ የሣኡዲን ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞችን፤ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው
በመዘዋወር፣ በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ የስራ እና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁና ያላሳደሱ እንዲሁም የስራ ፈቃድ ቢኖራቸውም የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውና ለኡምራና ሃጂ ሄደው በዚያው የቀሩ ሰዎችን መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ90 ቀን የጊዜ ገደብ ሃገሪቱን ለቀው መውጣት ያልቻሉ ህገ ወጦች፤ የቤት ለቤት አሠሣ ተደርጎ በፖሊስ ተይዘው ይታሠራሉ፤ ከፍተኛ ቅጣትም ይጣልባቸዋል ተብሏል፡፡
ህጉን አክብረው በ90 ቀን ውስጥ የሚወጡ ግን አሻራ የማይሠጡ በመሆኑ ህጋዊ ሆነው ተመልሰው ወደ ሣኡዲ የሚሄዱበት እድል እንዳላቸው ከአዋጁ ዝርዝር መረዳት ይቻላል፡፡ ከ3 ዓመት በፊት በተመሳሳይ የሣኡዲ መንግስት የ90 ቀን ገደብ አስቀምጦ እድሉን ተጠቅመው መውጣት ባልቻሉት ላይ በወሰደው እርምጃ
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ 2.5 ሚሊዮን የተለያዩ ሃገር ዜጎች በሃይል መባረራቸው አይዘነጋም፡፡ ሣኡዲ አረቢያ በዋናነት ይሄን አዋጅ ልታወጣ የቻለችው 70 በመቶ የሃገሪቱን ገቢ የሚሸፍነው የነዳጅ ዘይት ዋጋ በየጊዜው በመዋዠቁና በአካባቢው እያንዣበበ ባለው የሽብርተኝነት ስጋት መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪ መረዳት ተችሏል፡፡ በአገሪቱ 9 ሚሊዮን የተለያዩ ሃገራት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ሲኖሩ፣ 2 ሚሊዮን ያህሉ ህገ ወጥ ናቸው ተብሏል፡፡





Read 4199 times