Saturday, 15 April 2017 13:16

ባህላዊው የነጋ ቦንገር ባለ ኮከብ ሆቴል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

 የውጭ አገር እንግዶች ወይም ቱሪስቶች ስለ ኢትዮጵያ ሆቴሎች የሚናገሩት ቅሬታ አለ፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎችና ቅርሶች ባለቤት ሆና ሳለች፣ እንግዶች ከቻይና ወይም ከአውሮፓ በመጡ ዕቃዎች ባጌጡ ሆቴሎች ስለሚያርፉ፤ ስለ ኢትዮጵያ ምንም ትዝታ ይዘው እንደማይመለሱ በሚዲያም ሆነ በእርስ በርስ ግንኙነት ሲናገሩ ይሰማል ይላል የነጋ ቦንገር ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ነጋ፡፡
 በውጭ እንግዶች የሚነገረውን ቅሬታ ለማጥበብ ሆቴሉ በተቻለ መጠን የኢትዮጵያ ባህላዊ አሻራ እንዲኖረው አቅደው እንደሠሩት አቶ ዳንኤል ይናገራሉ። ሆቴሉን ኢትዮጵያዊ ባህል ለማጎናፀፍ አስበው ቢነሱም አንድ ችግር ገጠማቸው፡፡ የሆቴሉን ክፍሎች የውስጥ ዲዛይን በኢትዮጵያ ባህላዊ ሥነ-ጥበብ አርክቴክት የሚያስውብ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ አጡ፡፡
እንደ አጋጣሚ በዜግነት ግማሽ ግሪካዊና ግማሽ ኢጣሊያዊ የሆነ፣ በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባበኒ ተወልዶ ያደገ ባለሙያ አገኙ፡፡ ባለሙያው ኢስቴፋኒ ፌራሪ ይባላል፡፡ ቤተሰቦቹ ሳሪስ አካባቢ አንድ የዱቄ ፋብሪካ ነበራቸው፡፡ የእናቱ የቤተሰብ ስም ሳሪስ ይባላል። አሁን “ሳሪስ” እያልን የምንጠራው አካባቢ ስሙን ያገኘው ከእነዚህ ቤተሰቦች እንደሆነ አቶ ዳንኤል ይናገራል፡፡ አንድ ቀን የኢስቴፋኒ ፌራሪ እናት ወደ ሆቴሉ መጥተው፣ ሰገነቱ ላይ ቆመው ወደ ሰፈራቸው ተመለከቱና ቤታቸውን አይተው ቅዝዝ ብለው አለቀሱ፡፡ ‹‹ምነው?›› ሲባል፣ ‹‹ድሮ ልጆች ሆነን የተጫወትንበት ቦታ ትዝ ብሎኝ ነው›› አሉ፡፡
ኢስቴፋኒ አንድ ክፍል በኢትዮጵያዊ ባህልና ቁሳቁስ አስውቦና አስጊጦ እንዲሠራ ተደረገና ተገመገመ። ክፍሉን የተመለከቱት ሰዎች ‹‹ጥሩ ነው›› የሚል አስተያየት ሰለሰጡ፣ ሥራውን እንዲቀጥል ተደረገ፡፡
ይህ ባህላዊና ዘመናዊ ባህርይን የተላበሰው ሆቴል፤ ከ4 ወር በፊት በጊዜያዊ አቅም (በሶፍት ኦፒኒንግ) ሥራ የጀመረ ሲሆን በቅርቡ በይፋ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ እንደሚጀምር አቶ ዳንኤል ተናግሯል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የሆቴሉ 120 ክፍሎችና ኮሪደሩ (የክፍሎቹ መተላለፊያ) በኢትዮጵያዊ ባህልና ቁሳቁስ፡- በጂባ፣ በኬሻ፣ በገመድና በቃጫ የተሠሩ ናቸው፡፡ ሁሉም የክፍሎቹ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ፋብሪካ መመረታቸው ባህላዊ ያሰኘዋል፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ ምግቦች የሚስተናገዱበት ሁለት ባር፣ ምድር ቤት ናይት ክለብ፣ 25 ሜትር ርዝመት ያለው የመዋኛ ገንዳ (ስዊሚንግ ፑል)፣ ጂም፣ የስፓ አገልግሎት፣ የሳውናና ስቲም ባዝ የሚሰጥበት ማዕከል፣ በስተቀኝ 600 ሰዎች መያዝ የሚችሉ፣ እያንዳንዳቸው ከ100-150 ሰዎች የሚያስተናግዱ፣ (ከውጭ ድምፅ የማያስገቡ፣ እንደተፈለገውና እንደተሰብሳቢ ብዛት ሊሰፋና ሊጠብቡ የሚችሉ 4 አዳራሾች፤ ከሻይ ቡና ማስተናገጃ ስፍራ ጋር ያሉ ሲሆን፣ በስተግራ ደግሞ 500 ሰዎች ማስተናገድ የሚችልና ብፌ የሚዘጋጅበት ስፍራ ያለው የሠርግ አዳራሽ አለ፡፡
 ስብሰባ አዳራሹ ያለው 1ኛ ፎቅ ላይ ስለሆነ የተሰብሳቢዎችን ምቾት ለመጠበቅ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግል አሳንሰር (ሊፍት)፣ አልጋ ለያዙ እንግዶች፤ በአጠቃላይ ደግሞ 7 ሊፍቶች (አሳንሰሮች) ስላለው፣… ዘመናዊ ሊባል ይችላል፡፡
በ4875 ካሬ ላይ ያረፈው ይህ ሆቴል፣ ጣሪያው ረዥም ስለሆነ ሙቀት የለውም፡፡ ግቢውም በጣም ሰፊ ነው፡፡ ለሕፃናት መጫወቻና መዝናኛ የተሰጠው ትኩረት ግን አነስተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዥዋዥዌ መጫወቻ በስተቀር ሌላ መዝናኛ አላየሁም፡፡ ነገር ግን ቦታ ስላላቸው ሊሠሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡
የሆቴሉ ግንባታ ረዥም ጊዜ ነው የፈጀው። በቦታው ድንጋያማነት የተነሣ እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸው ስለነበር 8 ዓመት ነው የፈጀው። ‹‹ውጤቱ ግን አመርቂ ነው›› ይላሉ አቶ ዳንኤል። ምክንያቱም በሆቴሉ የተስተናገዱ እንግዶች የሚሰጡት አስተያየት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ‹‹አሁን ገና ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ገፅታ የያዘ ሆቴል አገኘን›› እንደሚሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ የአገራችን የሆቴሎች አሠራር ይመሳሰላል፡፡ ብዙዎቹ ከቻይናና ከአውሮፓ በመጡ ዕቃዎች ነው ውስጣቸው የሚጌጠው፡፡ ስለዚህ እንግዶች ኢትዮጵያ ውስጥ ይሁኑ ወይም ሌላ ቦታ የት እንዳሉ እንኳ አያስታውሱም። አሁን ግን የተነሱትን ፎቶግራፍ ሲያዩ ኢትዮጵያ መሆኑን ያስታውሳሉ። ብዙዎቹ በጣም ወደውታል፡፡ በተለይ የንግድ (ቢዝነስ) ሰዎች ከከተማ ወጥተው ማየት ስለማይችሉ፣ ኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት ማቴሪያል ይጠቀማሉ? አሰራራቸውስ እንዴት ነው? … የሚለውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚሁ ከተማ ውስጥ ሆነው በስሱ ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ እንደ ሌሎች ዕቃዎችን ከቻይና አምጥተን ብንገጣጥም ኖሮ፣ በ6 ዓመትና ከዚያም ባነሰ ጊዜ እንጨርስ ነበር፡፡ እኛ የተጠቀምናቸው ዕቃዎች እዚሁ አገር ውስጥ በፋብሪካ ስለተሰሩ ረዥም ጊዜ ወስደዋል” በማለት አስረድተዋል፡፡
ከዋና ዋና ምሰሶዎች፣ ከግድግዳውና … በስተቀር ኮሪደሮቹ (ማከፋፈያዎቹ) በእንጨት ነው የተሰሩት። ክፍሎቹ ደግሞ አገር ውስጥ በተመረቱ ዕቃዎች ነው ያጌጡት፡፡ የክፍሎቹ ኮርኒስ የተሰራውና የተጌጤው በጂባ፣ በኬሻ፣ በገመድና በቃጫ ነው፡፡ ኮሪደሮቹም እንደዚሁ፡፡ የክፍሎቹ መብራት ግማሽ ድረስ ሰፌድ በሚመስል ባህላዊ ማቀፊያ ስለተሸፈኑ አያንፀባርቁም። የክፍሉን መብራቶች እንግዳው እንደሚፈልገው ቦግ ወይም ደብዘዝ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ናቸው። ክፍሎቹ የተቀቡት ቀለም እውስጣቸው ካለው ዕቃ ጋር የሚጣጣም (ማች) የሚያደርግ ነው፡፡ የአልጋና የትራስ ልብሱ እንዲሁም ጌጦቹና የመስኮት መጋረጃው ሁሉ የሸማ ውጤቶች ናቸው፡፡ የክፍሎቹ ቁጥሮች እንኳ የተፃፉት በሚያምርና ደስ በሚል ባህላዊ ዘዴ ነው፡፡
ሁሉም ክፍሎች “ነጋ ቦንገር” የሚል ስም የተፃፈበት ሳሙና፣ ሻምፖ፣ ፎጣ አላቸው፡፡ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ቲቪ፣ ካዝና፣ ሚኒባር፣ ሚዛን፣ ፀጉር ማድረቂ፣ ሻወር፣ ሻይ ማፍያ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ በሆቴሉ ላደሩ እንግዶች ቁርስ፣ ዋይፋይ፣ ከአውሮፕላን ጣቢያ የሚያመጣና የሚወስድ ትራንስፖት በነፃ ያቀርባል፡፡
የሆቴሉ 120 ክፍሎች ዓይነት የአልጋ ደረጃዎች አሏቸው፡፡ ኪንግ፣ ቲውንና ስዊት ክፍሎች ኖርማል ሻወር አላቸው፡፡ ሱፒርየር ስታንዳርድና ኤክሲኩቲቭ ጃኩዚ አላቸው፡፡ እነዚህኞቹ ከተቀሩት የሚለዩት በስፋታቸውና ኤክስኪዩቲቩ እንደ አልጋ የሚያገለግል ታጣፊ ሶፋ ስላለው ነው፡፡
ሁሉም ክፍሎች ስቲምና ሳውና ባዝ አላቸው፡፡ ትናንሽ ሰፌዶችም ጌጦች ናቸው፡፡ የአልጋዎቹ እግሮች እንኳ አናታቸው ላይ የክርማ ጌጥ ተሰርቶላቸው ተሸፍነዋል፡፡ ሁሉም ክፍሎች በረንዳ (ባልኮኒ) አላቸው፡፡ ሐና ማሪያምና ፉሪን የሚያሳዩ ክፍሎች አሉ። መዋኛና መዝናኛውን ስፍራ የሚያስቃኙ ክፍሎችም አሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ሳሪስን ያሳያሉ፡፡  
‹‹ከደብረዘይት (ቢሾፍቱ) እንደመጣን ያረፍነው እዚህ ሳሪስ አካባቢ ነው፡፡ ብዙዎቻችን (ልጆች) ባደግንባትና አንዳንዶችም በተወለዱበት ስፍራ ይህን ሆቴል በመስራታችን በጣም ደስተኞች ነን›› ብሏል አቶ ዳንኤል፡፡

Read 1421 times