Saturday, 15 April 2017 13:19

ተጠሪው

Written by  በአለማየሁ ጌትነት (ኢብታ)
Rate this item
(11 votes)

  እግዜሩ..! አልኩት መሸሸጊያ ጥግ መሰወሪያ ምታት በፈለኩ ጊዜ እግዜሩ..! አልኩት ከአፍላነት መደናግር ከጀማሪነት ስህተት መራቅ በሻትኩ ጊዜ ኸረ..! እግዜሩ! አልኩት ከፊቱ እጅግ በጠፋሁ እንዳይሰማኝ ባወኩ ጊዜ ዝም!!! አለ                      በጩኧት ጠራሁት! - በጩኧት ዝም አለ!
፠   ፠   ፠
ለእጄ ገንዘብን አደረኩ - ለኔ እግዜሬን አገኘሁ፤ እግዜሬ ቤት ገዛልኝ --እግዜሬ መኪና አስገኘኝ፤መኪና ሰዎችን ሰበሰበልኝ፡፡ .........ለእግዜሬ ታመንኩ፤ በእግዜሬ ታበይኩ፤ የደም መስዋት አቀረብኩ ......የክደት ቁርባን አደረኩ፤ የመጥለፍ ፍሬ አቃጠልኩ፤ በፊቱም ዘብ ቆምኩ ....ደስም አለው፡፡ ቤቴን ባረከ፤ እጄ በደም ዋኘ፡፡ ነፍሴ በአሻጥር ዋጀች፡፡ ፍጹም መንፈሱ ከኔ ሆነ ……..ግን እርግጠኛ ለመሆን ፈለኩ፤ ሳልፈልግ  ፈለኩ፡፡
 “አቤት!”  እንዳይለኝ  እየተመኘሁ  
 “እግዜሩ…!” አልኩት
 ዝም!!! አለ
 እንደገና ጠራሁት፤ “ደስታ ሆይ..!!” አልኩት
 ዝም!!!
 ልፈልገው ወጣሁ …በአመንዝራዋ ጣፋጭ አፍ …በደናግላን ጭን …በውቦች ከንፈር …በወይን ደንበጃን …በዳንኪራው ወለል ….በእጸ-ፋሪስ ሰረገላ  -----ማተርኩት ይሄ እግዜሬ፤ እግዜር ይስጠው፤ ለጥርሴ ሳቅ ለመንፈሴ ንቃት አመጣልኝ፡፡ …ይባረክ! …ዘላለም! በዳዊት መዝሙር በሰለሞን መሀልየ መሀልየ ይወደስ፡፡ . . .ግን ከቀናተኝነቱ መላቀቅ አልቻልኩም ፤ሳላመልከው ስውል ይጋጨኝ በቁሜ ከሲኦሉ ያሰምጠኝ ገባ፡፡
.....ወድያውም በድካም ድካምን ላብስ መድከሜ ተገለጠልኝ . . . .ፈራሁ!፡፡  በማመናቸው ውስጥ አለማመናቸው እንዳለ፣ ባለማመኔ ውስጥ ማመኔ አለ መሰል ፈራሁ፡፡ ….ስፈራ አለም ደከመችኝ ….ከባለጌ ወንበር ወረድኩ …..ከግዢ ገላ ተፈናጋሁ …..ከሱስ ደም ተቃባሁ ፡፡
. . .የፍቅር አምላክ ፍቅር መሆኑም ተከሰተልኝ።  . . . .ፍቅር ደግሞ በሷ ውስጥ አለ ወይም እሷ ፍቅር ናት!  እስካሁን አምላኬን በመሳቴ ውስጥ ውስጤን ጸጸት እያኘከኝ …መቅደስ ገላዋን …ጽላት ሀሳቧን አድርጌ አመለኩት፡፡ . . . ብዙ ሳመልካት ግን የደረደርኩት ጣኦት መናድ ጀመረ፡፡ ..በተናደ ቁጥር ደግሞ አንድ ሁለት እያለ የውሸት ደቀ መዝሙሩቹን ይዞ ሄደ፡፡
“ይሂዳ እኔ ምን ከዳየ!” …….እግዝሬ በሷ ውስጥ ሳለ!  ….ለምን ልጨነቅ?”
ሲናድ ሲቀንሱ - ሲናድ ሲቀንስ
ሲናድ ሲቀንሱ - ሲናድ ሲቀንስ
…..አምላኬ በጅ አዙር ገንዘብ ኑሮ ሳጣው አጣሗት።   . . . መናኛ ለበስኩ. . . . .በረንዳ ወረድኩ፤ እጎርሰው አጣሁ፡፡  ………የጸጸት ቤት የሀጢያት ምሳሌ ሆንኩ።  …..ከተሸጠው ቪላዬ ፊት፣ የፍሳሽ ቆሻሻ መውረጃ ጉድጓድ ላይ  ተጋደምኩ …በዚያ ፈረስ በሚያስጋልብ አልጋ ያልመጣ እንቅልፍ እዚህ  መጣ  ….ተኛሁ፡፡
“ልጄ!” አለኝ
“ስጠራህ የጠፋህ ሆይ፤ ከኔ ምን አለህ?” አልኩት
አሁንም “ልጀ..” አለኝ፤ በወፍራም የአባት ድምጽ፡፡
“ስፈልግህ ጠፋህ” አልኩት
“በተሳሳተ ቦታ ፈለከኝ አጣኸኝ ….አስፈለኩህ ተገኘሁ”
“ዘገየህ..!” አልኩት፤ በምሬት፡፡ “ዘገየህ፤ ሰይጣን እንኳ እንዳላስተው ሲሸሸኝ መጣህ ...በርኩሰት አሸዋ፣ በሀጢያት በረሃ፣ በጥፋት ተረተር ከተሸጎጥኩ፣ ከጉድ ወንዝ ከሰጠምኩ በኋላ መጣህ” አልኩት ዝም ብሎ በፍቅር አየኝ …እያነባሁ ቀጠልኩ፡፡
“የደስታ ፈጣሪ፣ ደስታ አይደለህምን?”
“ሰጥቶ የሚቀበሉኝ ‘ንጅ ተቀብለው እሚሸሸጉኝ አይደለሁማ”
“የሰላም ጌታ፣ ሰላም አይደለህምን?”
“እሚቀበሉኝ እንጅ ሚገዙኝ አይደለሁማ”
“የፍቅር አባት፣ ፍቅር አይደለህምን?”
“ሳይጠብቁ በሚሰጡ እንጅ በሚሸቅጡ ውስጥ የለሁማ!”
ከጥቂት ፋታ በኋላ፤ “ልጄ……!” አለኝ
በተራዬ ዝም፡፡
“ልጄ..! አንተ አሁንም ለኔ ልጄ ነህ! …….ንጹኅ ነህ!!”
ዝም!!
“ልጄ የዘሞተ ዝሙት አይደለም፤ የሳተ ስተት አይደለም፤ የከዳም ክደት አይደለም…”  .ድምጹ ቀረበኝ …..ውፍረቱ ቀጠነ ...ለስላሳ እጁ ይገፋኝ ገባ  ..ነቃሁ፡፡
“የደረሰብህን ሰማሁ” አለችኝ፤ ከሴት አዳሪዎቹ አንዷ ነበረች፤ “በጣም ያሳዝናል” ስትል አከለች፡፡ ፊቷ ላይ የሚታየው ሀዘን፣ ያኔ ፍቅርና ስራን ቀላቀልሽ ብዬ ሳባርራት እንኳን አይታይም ነበር፡፡
“ቤቴ ቤትህ ነው…… ቢያንስ በእግርህ እስክትቆም”  

Read 1772 times