Saturday, 15 April 2017 13:26

የ “ሥጋ ነገር …”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በአለማቀፍ ደረጃ በሥጋ ፍጆታቸው አርጀንቲና፣ ኡራጋይ፣ ብራዚል፣ አሜሪካና አውስትራሊያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ቬትናም፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ቱርክና ኢንዶኔዢያ  የሥጋ ተመጋቢነት ባህል ስለሌላቸው ዝቅተኛ የስጋ ፍጆታ የሚጠቀሙ የዓለም ሀገራት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
አብዛኛው አፍሪካዊ ሥጋ የመብላት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም በአቅም ውስንነት ፍላጎቱን ማሟላት እንደማይችል ይኸው የፋኦ ጥናት የሚጠቁም ሲሆን አንድ ዴንማርካዊ በአመት 145 ኪ.ግ ሥጋ ሲመገብ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በአማካይ 8.9 ኪ.ግ ሥጋ ብቻ  በዓመት ይመገባል ይላል፡፡
ዜጎቻቸው ሥጋ መመገብ ብርቃቸው ካልሆነባቸው ሀገራት ኩዌት፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ ተጠቃሾች ሲሆኑ አንድ ሰው በአማካይ ከ110 ኪ.ግ እስከ 120 ኪ.ግ ሥጋ በዓመት ይመገባል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ13 ቢሊዮን እስከ 33 ቢሊዮን ዶላር የሥጋ ሽያጭ በማከናወን የሚታወቁ ኩባንያዎችም የሚገኙት በእነዚህ ሥጋ የዘወትር ቀለባቸው በሆኑ ሃገራት ነው፡፡
45 በመቶ ቻይናውያን  ከ5 እና 6 አመት በፊት የነበረው ሥጋ የመመገብ ፍላጎታቸውና አቅማቸው ወደ 80 በመቶ እያደገ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
የአሜሪካውያን የሥጋ ፍላጎት በአንፃሩ በ5 አመት ውስጥ በ9 በመቶ ያሽቆለቆለ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በማህበረሠቡ ፅዩፍ የሆነው የፈረስ ሥጋ በሱፐር ማርኬት ከሌሎች ሥጋዎች ጋር እየተቀላቀለ ለሽያጭ ይቀርባል የሚለው አሉባልታ ነው ተብሏል፡፡
በአለም ሃገራት ሥጋ የመመገብ ባህል ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የአሣማ ሥጋ ነው፡፡ በአመት እስከ 3 ትሪሊዮን አሣማዎች የሚታረዱ ሲሆን አብዛኛው የአለም ህዝብም ይመገባቸዋል ተብሏል፡፡ በዓለም ላይ በዓመት ከ60 ትሪሊዮን ዶሮዎች በላይ የሚታረዱ ቢሆንም ከአሣማ አንፃር ተመጋቢዎቻቸው ውስን ናቸው፡፡ ከ300 ሚሊዮን ከብቶች በላይ እየታረዱ በየአመቱ ለሥጋ ተመጋቢዎች እንደሚቀርቡም የፋኦ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እንደ አዲስ እየተለመደ የመጣው የባህር እንስሳትን እና የተለያዩ ጥቃቅን ነፍሳትን የመመገብ ባህል መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

Read 4049 times