Saturday, 15 April 2017 13:26

“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ሁሉም ነገር እየተንጠራራን እንኳን ልንነካው እያስቸገረን፣ ሁሉም ነገር የዓይን አዋጅ ብቻ እየሆነብን… በዓል በመጣ ቁጥር “ገበያው እንዴት ነው?” ምናምን የሚል ነገር ሁሉ እየቀነስን ነው፡፡ ገበያው ምንም ሆነ ምን…የብዙዎቻችን ኪስ መስፈርቱን አያሟላማ! የበግ ቅርጫ እያሰብን ባለበት ዘመን … “ስማ የከብት ገበያ እንዴት ነው?” መባባል ፌዝ ነገር እየሆነ ነው፡፡
ለክፉም ለደጉም እንኳን አደረሳችሁማ!
ስሙኝማ…የዛሬዋ ምሽት ስንት ‘አድቬንቸር’ የሚሠራባት ምሽት ነበረች! (‘ነበረች’ የተባለው አሁን የዓመቱ ቀናት በሙሉ እንደዛ እየሆነ የመጡ ስለሚመስለን ነው፡፡)
እናማ…“አቦ እባካችህ…ቤት እንለውጥ!” እየተባለ በአንዷ ምሽት አሥራ አምስት መሽታ ቤቶች እየተዞረ ሲጠጣ የሚያድርበት ምሽት ነበረች፡፡ (እዚህ አገር እኮ የበዓል ዋዜማ ልክ የምጽአት ቀን ዋዜማ ይመስላል፡፡ አለ አይደል… “ነገ ለምታልቅ ዓለም ሲያምርህ የኖረው መጠጥ ሁሉ ዛሬ ጠጣ!” የምንባባልበት ነው የሚመስለው!”
እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
እናላችሁ…ዘንድሮ ግን ይሄ ጠጥቶ የማሽከረከር ምርመራ ነገር በዙዎችን ትንሽ አደብ እንዲገዙ ሳያደርጋቸው አይቀርም፡፡ ያድርግልንማ! ግን ደግሞ…
“ግፋ ቢል ገንዘብ መቀጣት ነው፣ ጓንታናሞ አይቆለፍብኝ!” በአእምሮው ሳይሆን በኪሱ የሚያስብ መአት ይኖራል፡፡ (ኪስ ሞልቶ አእምሮ ባዶ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡)
ጠጥቶ የማሽከርከር ነገር ካነሳን አይቀር… ይቺን ቀልድ ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ውስኪውን ሲገለብጥ ያመሻል፡፡ እናላችሁ…ሲበቃው መኪናውን እያሽከረከረ ሲሄድ ያስቆሙትና የትንፋሽ ምርመራ ይደረግለታል፡፡ ምንም! ምንም አይነት የአልኮል ምልክት አልተገኘበትም። ሰውያችን ግራ ይገባዋል፡፡ ግማሽ ጠርሙስ  ሊሆን ምንም የማይቀረው ገልብጦ ባዶ! የከሰከሰው ገንዘብ ትዝ ይለውና ምን ቢል ጥሩ ነው…“የሰጡኝ የተወጋ ውስኪ ነው ማለት ነው…” አለና አረፈው፡፡
እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
ስሙኝማ… የዛሬዋ ቀን እኮ ስንት ‘አድቬንቸር’ የሚሠራባት ቀን ነበረች — እንደ ዛሬ የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ሁሉ ገና ቤት አለመግባቱ የሚታወቀው እኩለ ሌሊት ሲደርስ ባልነበረበት ዘመን ማለት ነው፡፡ ከተማውን ሲያስሱ የሚያነጉ ወዳጆቻችን እንደሚነግሩን፣ በየስፍራው የሚታየው ‘የታዳጊዎች አብዮት’ ያስደነግጣል ነው የሚባለው፡፡ እኔ የምለው…‘ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች’ የምትለው ነገር ማስታወቂያ ማሳመሪያ ሆና መቅረቷ ነው! ደግሞላችሁ… የመጠጡ ነገር እንዳለ ሆኖ “ሌላ ሌላውማ ለማን ይነገራል…” የሚባለውን ነገር ህጻናቱ ገና በባዮሎጂ ክፍለ ጊዜ ያልደረሱበትን ‘እውቀት’ በተግባር እያዩት ነው እየተባለ ነው፡፡
እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
እናላችሁ… የዛሬዋ ምሽት… “እማዬ አስቀድሼ ነው የምመጣው…” የምትባል የማምሻ ምክንያት ስለነበረች ‘ህጣናቱ’ ሁሉ “ዓዳም ሔዋንን አወቃት” የሚለውን ነገር በተግባር ‘የሚያረጋግጡበት’ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ…“እማዬ…” ምናምን የሚለው መጠሪያ በሆነ የውስጥ መመሪያ ‘ህገ ወጥ’ ሆኗል እንዴ! አሀ… በሚዲያም የምንሰማው “ማማ…” “ማሚ” ምናምን ብቻ እየሆነ ነዋ! (የኮሪያዎቹ ፊልም ላይ ‘እታበባ’ የምትለው አጠራር ጥሩ ምርጫ ነች፡፡ “ሲስ”… “ብራዘር” የሚሉ ነገሮች በበዙበት ዘመን…“እታበባ” እና “ወንድም ጋሼ” “ወንድም ዓለም” አይነት አጠራሮችን መስማት አሪፍ ነው። ‘በተቀመጥንበት ሰለጥንና’ ግራ ገባን እንዴ! የጃፓኑ የቅርቡ የኤሌክትሪክ ባቡር የእኛ የመሰልጠን ፍጥነት ቢለካ የትና የት ጥለነው እንደሄድን ይታወቅልን ነበር፡፡ ‘መጨረሻውን ያሳምርልን’ እንጂ…ከልክ በላይ ፍጥነትም ሞተር ‘ፉዞ’ ያደርጋል! “አባቱን አያውቅ፣ አያቱን ናፈቀ…” አይሁንብንማ!)
ስሙኝማ…በቀደም በአንድ የከተማችን አካባቢ በሚኒባስ ታክሲ እየተጓዝን ሳለ መንገዱ ላይ ‘ጫማውን እንኳን ማሰር ያዳግተዋል የሚባልለት ጩጬ’… የሆነች እኩያው የምትሆን ልጅን ልክ ብራድ ፒት አንጀሊና ጆሊ ላይ ያደርግ እንደነበረው (በደጉ ጊዜ!) …. ‘ግጥም’ አድርጎ ትንፋሿን ሲያሳጥረው አየን፡፡ እናማ… አንዲት እናት ድምጻቸውን ለስለስ አድርገው…
“አፈር ብላ፣ አፈር ያስበላህ…” ይላሉ፡፡
ታዲያላችሁ… ይሄኔ በጣም የሚገርመው ነገር…አለ አይደል… ምናልባት ለአራተኛው የልጅ ልጃቸው ልደት “ምን ልግዛላት…” እያሉ ሊያሰሉ የሚችሉ ሰውዬ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ቢስማትስ፣ ምን አዲስ ነገር አለው!…” አሉና አረፉት፡፡ በዛ ሰዓት…
“ይቺ ሚጢጢ ልጅ የእሳቸው ልጅ ብትሆን ኖሮ እንዲህ ይሉ ነበር!” ያሰኛችኋል፡፡
እናማ… ታክሲው ውስጥ “ቢስማትስ!” እና  “ገና አራስ ልጆች ናቸው እኮ!” ምናምን በሚሉ ነገሮች የተነሳው ክርክር ቢጤ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚችል ነው፡፡ የምር… “ህጻናቱ በአጉል መንገድ ላይ ገብተው ህይወታቸውን እንዳያበላሹ መምከር ይችላሉ” የሚባሉ ሰዎች… “ልጆቹ እንደፈለጉት ቢሆኑ ዘመኑ ነው…” ሲሉ ስትሰሙ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይቺ “ዘመኑ ነው…” የሚሏት ነገር እኮ ጉድ እያደረገችን ነው!
እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ የፍስክ ወቅት ሲመጣ… አለ አይደል…
“ቅባት እንዳታበዙ፣”
“ጮማውን በልክ አድርጉት፣”
ምናምን የሚባል ነገር አለ፡፡    
ቆይማ…ጮማው በልክ የሚሆነው መጀመሪያ ሲኖር አይደል እንዴ! ቅባት የሚበዛው መጀመሪያ ሲኖር አይደል እንዴ!
የምግብ ነገር ካነሳን አይቀር እግረ መንገዴን…በበፊተኛው ጊዜ…
ጮማውን በካራ አንተ ብቻ በልተኽ፣
ጠጁን በብርሌ ብቻህን ጠጥተኽ፣
የት ትገባ ይሆን ሆድህን አንዘርጠኽ…
ተብሎ ይዘፈን ነበር፡፡ አሁን ግን እንደዛ ብሎ የሚገጥም የለም፡፡ ልክ ነዋ… ‘አንዘርጠኽ’ የሚለውን ቃል የሚያውቀው ሰው ጥቂት ነዋ! ደግሞ ‘የሚገባበት’ አይጠፋማ!
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… አንዳንድ ጊዜ በቴሌቪዥን ስለሆነ ምግብ አዘገጃጀት የሚያቀርቡትን ታዩና… አለ አይደል… ሆድ ሊብሳችሁ ይችላል፡፡ ልክ ነዋ… ለአንድ ጊዜ የሚሆነውን ምግብ ለመሥራት የሚያስፈልገው ወጪ እኮ የአሥራ አምስት ቀን በጀት ሊሆን ይችላል! ያን ሁሉ ገንዘብ ማውጣት ብንችል እኮ…መጀመሪያ ነገር ቴሌቪዥን ፊት አንገሸርም ነበራ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… የምር በዝቅተኛ ወጪ አሪፍ ምግብ እንዴት እንደሚሠራ ቢያሳዩ አሪፍ ነው፡፡
እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
አሀ…ተከናንቦ የሚወጣው ሁሉ ዓላማው የነፍስ አይደለማ! አንዳንዶች ክንብንቧን የሚጠቀሙባት እንደ ጭምብል ነበር፡፡
“የወንፈሌው ጥጥ ተው አትንቀጥቀጥ…” የለ፣
“ዛሬ በዓል ነውና ቅጠልም አልበጥስ…” ብሎ መቀኘት የለ…‘ሁሉም ምቹ፣ ሁሉም ዝግጁ’ ይሏችኋል ዛሬ ነው፡፡
እግረ መንገዴን…አንድ ጊዜ ያወራናት ከዓመታት በፊት የሆነ ነገር ትዝ አለችኝማ…የሆነ አፓርትመንት ህንጻ ላይ በከፊል ሀበሻ የሆነ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር በገዛ ቤቷ ተኝቷል፡፡ ከከተማ ወጥቷል የተባለው አቶ ባል ድንገት ከች ብሎ በር ያንኳኳል፡፡
“በል ቀስ ብለህ በጓሮ በር በኩል ሂድ…” አይባል ነገር፣
“አልጋው ስር ግባና ትንፍሽ እንኳን እንዳትል…” አይባል ነገር፣
“ጓዳ እንስራው ስር ተሸሸግ…” አይባል ነገር… ‘ፈረንጅ ቀመሱ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሰውዬ ግራ ይገባዋል፡፡ እና አጅሬው ምን ይሁን! የነበረው ‘መውጫ’…በመስኮት ከአራተኛው ፎቅ መዝለል!  ዘለላታ፡፡ ለሰባት ነው ለምናምን ወር ተኛ፡፡ ለሦስት ደቂቃ ‘እነሆ በረከት’  ሰባት ወር በጄሶ! ‘መስዋእትነቱ’ በዛ! ቅዳሜ ስዑርን ቢጠብቅ ኖሮ ይህ ሁሉ ባልደረሰበት፡፡ …ቂ…ቂ…ቂ… እናማ…“የደስታ ልኩ የት ድረስ ነው?” ያሰኛል!
እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ፡፡
 ከችግር የጸዳ በዓል ያድርግልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2872 times