Saturday, 15 April 2017 13:28

ኢትዮጵያ ግድብ እንዳትሰራ፣ “ከጦርነት ያላነሰ ነው” ዘመቻ! ከግብፅ ዘመቻ የባሰ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

  ስለዘመቻው፤... ሁለት ሚኒስትሮች፣ የኤልፓ ስራአስኪያጅ፣ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣን ተናግረዋል -  “የብርሃን አብዮት” በተሰኘው የኢቢሲ ዘጋቢ ፊልም። ግን የግብፅ ዘመቻ አይደለም።
ታዲያ የማን ዘመቻ? (ይሄ ጥያቄ በኢቢሲ አልተነሳም)። ዘገባው እንዲህ ይላል።
“አምርረው ነው የዘመቱብን - የግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ!”  
እነማን? (ኢቢሲ አልጠየቀም። ጥያቄውን ዘንግቶት ይሆናል!) ዘገባው ቀጠለ።
“በእነዚህ ኃይሎች፣ የግድብ ግንባታው ተቋረጠ። ለ2 ዓመት ተስተጓጎለ!”
የትኞቹ ሃይሎች? (ኢቢሲ ይህን አልጠየቀም። አሁንም ረሳው?) ዘገባው ተጋመሰ።
“እነዚህ አካላት፣ በኢትዮጵያ ላይ የ6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አድርሰዋል!”
የትኞቹ? በምን ሰበብ? (የጠየቀ የለም። ጥያቄዎቹ አልተፈለጉም!) ዘገባው ቀጥሏል።
“ዘመቻው፣ ከጦርነት ያላነሰ ስራ ነው። ጦር ሰራዊት ሆነው ነው የገጠሙን!”
በኢትዮጵያ ግድቦች ላይ፤ ከጦርነት ያልተናነሰ ዘመቻ! የኢቢሲ ዘገባ ውስጥ፣ “እነማን ዘመቱብን? በምን ምክንያት?” የሚሉ ጥያቄዎች፣ በጭራሽ አልተነሱም። እነዚህን ጥያቄዎች እየፈራና እየሸሸ፣ ለ40 ደቂቃ የዘለቀው የኢቢሲ ዘገባ፤ ዋናውን ጉዳይ እያድበሰበሰና እየሸፋፈነ ተጠናቀቀ።
ከጨለማ እንዳንገላገልና መብራት እንዳናገኝ፣ እንደምቀኛ የጠመዱንና የዘመቱብን ጠላቶች እነማን እንደሆኑ፣ ኢቢሲ በግልፅ ለመናገር አልደፈረም።
ኤሌክትሪክ እንድናጣ፣ ከድህነትም እንዳንወጣ፣ ከየአቅጣጫው ክፉ ጋሬጣ የበዛብንና የበረታብን፣ በምን ሰበብ ወይም በምን ምክንያት እንደሆነስ ይታወቃል? ኢቢሲ፣ ትንፍሽ አላለም።

ለምን? ምንን ለመደበቅ
ዘመቻው ምን ላይ እንዳነጣጠረ፣ ኢቢሲ በተደጋጋሚ ገልጿል። በኢትዮጵያ ግድብ እንዳትሰራ ለመከልከል፣ ካሁን በፊት የተጀመሩ ግድቦችንም ለማስቆም የሚካሄድ ዘመቻ ነው። የውጭ ኃይሎችና ጠላቶች፣ ለአፍታ ባልተቋረጠ ዘመቻ፣ ብዙ ኪሳራ እንዳደረሱብን በመግለፅ ነው የጀመረው የኢቢሲ ዘገባ። የጥፋት ዘመቻን እና የኢትዮጵያ የግድብ ግንባታን፣... ፍልሚያውንና ውጣውረዱን፣ መዘዙንና ውጤቱን እንድንመለከትም ይጋብዘናል። ለአስር ዓመታት የተጓተተው፣ ግዙፉ የጊቤ3 የኃይል ማመንጫ ግድብ፣... የትንቅንቁና የጦርነቱ ዋና ማሳያ መሆኑን በመተረክ፣ ርዕሰ ጉዳዩን ለማብራራት ይሞክራል - የአቢሲ ዘገባ። ትኩረትን የሚስብ፣ አስገራሚና አጓጓ ትረካ ይመስላል - አጀማመሩ። በዚያ ላይ፣ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ፣ በቀጥታ ከመንካት አልፎ፣ የሞትሽረት ጥያቄ በመሆኑ ደግሞ፣ ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ ርዕሰ ጉዳይ ነው ቢባል አይበዛበትም። የድህነት ወይም የመሻሻል ጥያቄ ነው።
ያለ ኤሌክትሪክ ሃይል፣... ከድህነት የወጣ፣ ወደ ብልፅግና የተራመደ፣ የስልጣኔን ብርሃን ያየ አገር የለም ብለዋል - ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉት አቶ ዘሪሁን አበበ። እውነት ነው። ግድብ መገንባትና ኤሌክትሪክ ማመንጨት፣ ለኢትዮጵያዊያን የድህነትና ከተመፅዋችነት የመገላገል ጥያቄ ነው። አለበለዚያ፣ መዘዙ ብዙና መራራ ይሆንብናል።... አለበለዚያ፣ የአምናው አይነት ቀውስን መቋቋምና መፍትሄ ማበጀት ከአቅማችን በላይ ይሆንብንና፣ ሁለት ሦስቴ ሲደጋገም፣ አገሪቱ... ‘እንዳልነበረች እስክትሆን ድረስ’፣ ውጥንቅጧ ይወጣል። በአጭሩ፣... ጉዳዩ የሞት ወይም የሽረት፤... የስራ አጥነት ስደት ወይም የስራ እድል ፈጠራ፤... የትርምስ ወይም የማንሰራራት፤ ብርቱ ጉዳይ  ነው። የግድብ ግንባታና የኢኮኖሚ እድገት፣ ኑሮን የሚያሻሽል የሕይወት መንገድ የመሆኑን ያህል፤ የግድብ ግንባታን የሚያዳክም የሃብት ብክነት ደግሞ የሞት መንገድ ነው - ቃልበቃል።
እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት፣ ‘ሞት’ ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ፣ ከጎረቤት አገራትና ከአለም ዙሪያ ካልተረዳን፣ ከነ ሶሪያና የመን፣ ከነ ኮንጎና ሊቢያ ካልተማርን፤ የራሳችንን ቤት መመልከት እንችላለን። አምና የተከሰተው ቀውስ፣ ‘በደብል ዲጂት ፍጥነት’፣ ቁልቁ ወደ ገደል እያንደረደረ፣ የእንጦሮጦስን አስፈሪ አፋፍ አሳይቶናል። ቀልድ አይደለም፣ ሰዎች።
ኤሌክትሪክን የሚያሳጣ፣ ኢኮኖሚን የሚያዳክም፣ ኪሳራን የሚያስከትል፣ ሃብትን የሚያባክን፣ ማንኛውም አይነት ዘመቻ፣... የውጭ ሃይሎችም ሆነ የአገር ውስጥ ዘመቻ፣ የኤንጂኦ ቅስቀሳም ሆነ የባለስልጣናት ውሳኔ... ቀልድ አይደለም። አፍታ ሳይቆይ የሚጠፋ አየር ላይ የተንሳፈፈ ብናኝ፣... የማይጨበጥ የማይዳሰስ የሸለብታ ቅዠት፣... ውጤት የማያስገኝና መዘዝ የማያመጣ፣ ጉዳት አልባና እርባና ቢስ፣... ጊዜያዊ ቧልትና አላፊ ጨዋታ አይደለም። የቢሊዮን ብሮች ሂሳብ፣ የሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የኑሮ ጉዳይ፣ የአገር ህልውና ጥያቄ ነው። የሞትሽረት ጉዳይ ስለሆነም፣ በግድብ ግንባታ ላይ የሚካሄደውን ዘመቻ፣ በቁጭት ብቻ ሳይሆን በጥብቅ መመርመር ይኖርብናል። በዚህ ዙሪያ፣ ለበርካታ አመታት በአዲስ አድማስ ተከታታይ የታተሙ ፅፉፎችንና ትንታኔዎችን ማስታወስ ይቻላል። ኢቢሲ፣ አሁን ገና ባንኖ፣ ዘገባ ለመስራት መሞከሩ ጥሩ ነው። ግን፣ ምን ዋጋ አለው? ጀማምሮ፣ አድበሰበሰው። ለምን?

የአካባቢ ጥበቃ ጥቃት - ከአገር ውስጥ እና ከውጭ
ፀረግድብ ዘመቻ የሚካሄድብንና የቢሊዮን ብሮች ኪሳራ የሚደርስብን፣ በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችና ተቋማት አማካኝነት ነው። የዘመቻው ሰበብ፣ “አካባቢያችን እና መላው ዓለም፣ ጋራና ሸንተረሩ ሁሉ... የሰው እጅ ሳይነካቸው፣ እንደ ጥንቱ ተጠብቀው መቆየት አለባቸው” ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ፣ ግድብ ከተገነባ፣ የጥንቱ ሸንተረርና ነባር ሸለቆ ይለወጣል። ያልነበረ ‘መጤ’ ኃይቅ ይፈጠራል። ይሄ ትልቅ ጥፋት ነው። ሰዎች፣ አካባቢያቸውን እንዳይለውጡና እንዳይነኩ ለመከላከል፣... የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ዋናው ዘዴ፣ የሰውን አቅም ማዳከም ነው። የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት የሚያገለግሉ አቅሞችን ማኮላሸትና ማዳከም። ለምሳሌ፣ ግድብ በመገንባት ፋንታ፣... በእጥፍ የሚበልጥ የገንዘብ ወጪን የሚፈጁ፣ በእጥፍ የሚያንስ መናኛ ኤሌክትሪክን የሚያመነጩ የነፋስ ተርባይኖች በመትከል፣ አላማቸውን ያሳካሉ - ኤሌክትሪክ ሃይልን የማሳጣት፣ በኪሳራና በሃብት ብክነት አቅምን የማዳከም አላማ።
በሌላ አነጋገር፣ የግድብ ግንባታን ለማስቆም የሚካሄደው ዓለማቀፍ ዘመቻ፤ ለአገራችን እጅግ አጥፊ የመሆኑን ያህል፤... በዚያው ልክ እዚሁ አገራችን ውስጥ፣ በባለስልጣናት ውሳኔ፣ የነፋስ ተርባይኖች ለመትከል የሚባክነው ሃብትና የቢሊዮን ብሮች ኪሳራም፣ እጅግ አጥፊ ነው። ተመሳሳይ ናቸው። ይውሃ ግድብን ማፍረስ እና የነፋስ ተርባይኖችን መትከል፣... ተመሳሳይ ጥፋቶች ናቸው - ከተመሳሳይ “የአካባቢ ጥበቃ” አስተሳሰብ የሚመነጩ ጥፋቶች። ኢቢሲ፣ ይህንን ተመሳሳይነት ጥፋትና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሸፋፍኖ ለማለፍ ነው የሞከረው። ግድብን በሚቃወሙ አለምአቀፍ ተቋማት አማካኝነት፣ የ10 ቢሊዮን ብር ካሳራ ደርሶብናል። የነፋስ ተርባይኖችን ለመትከል ውሳኔ በሚያስተላልፍ የአገራችን ተቋማት ደግሞ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶብናል። ሁለቱም ያስቆጫሉ። ኢቢሲ ነገር በማድበስበስ መከራውን የሚያየውም፤ ይህንን ለመሸፋፈን... በአገር ውስጥ የመንግስት ተቋማት አማካኝነት የደረሰብንን ኪሳራ ለመሸፋፈን ለመደበቅ ይመስላል።
የጊቤ3 ግድብ፣ ለኢትዮጵያ የሚኖረውን ትርጉም ለመገመት አይከብድም። የአገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅም በእጥፍ ገደማ የሚያሳድግ ግዙፍ ግድብ ነው። ይህንን በመቃወም የተካሄደው ዘመቻ፣ ፈፅሞ ሚስጥር አይደለም። በአለም ዙሪያ በአደባባይ፣ በግላጭ የተካሄደ ዘመቻ ነው - በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች። ኢቢሲ ግን፣ ይህንን በግልፅ ለመናገር አልደፈረም። በደፈናው፣ “የውጭ ሃይሎች” ዘመቻ እንዳካሄዱ ነው የሚነግረን። “የእነዚህ ሃይሎች” ዘመቻ፣ አፍሪካን፣ አውሮፓንና አሜሪካን እንዳዳረሰም ይጠቅሳል። ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የአለም ባንክ፣ ለግድብ ግንባታ፣ ብድር መስጠት እንዲያቆም አድርገውታል። የአውሮፓ ሕብረት ባንክም እንዲሁ፣ ለጊቤ3 ግንባታ ብድር ለመስጠት ቃል ከገባ በኋላ፣ ቃሉን እንዲያጥፍ አስገድደውታል። ከዚያም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ብድር ለመስጠት ገንዘብ መድቦ ጫፍ ከደረሰ በኋላ፣ እጁን ጠምዝዘውታል። ምናለፋችሁ፣ የግዙፉ ግድብ ግንባታ ለሁለት ዓመታት እንዲቋረጥ፣ ከዚያም ለበርካታ ዓመታት እንዲጓተት ያደረገ ሰፊ ዘመቻ ነው የተካሄደው።
የዘመቻው መዘዝ ብዙ ነው። ግን፣ የጉዳቱን ክብደት ለማወቅ፣ መዘዞች በሙሉ መዘርዘር አያስፈልግም። የግድብ ግንባታ ሲቋረጥና ለ10 ዓመታት ሲጓተት፤... የኤሌክትሪክ እጦት እየተባባሰ፤ በኢኮኖሚ ላይ በየእለቱ ኪሳራ እየደረሰ፣ ምርት እየተስተጓጎለ፣ ስራ አጥነትና ድህነት እየተራዘመ... ወዘተ... እያልን መቁጠርን እንተወው። ከሥራአጥነትና ከኑሮ ችግር ጋር፤... ብጥብጥንና ትርምስን በማባባስ በኩል፣ ምን ያህል የጥፋት ጓዝ እየጎተተ ወደ ቀውስ እንደሚገፋፋም፣ ለጊዜው ሳንዘረዝር እንለፈው።
እነዚህን ሁሉ ትተን፣... የግድብ ግንባታው፣ ለሁለት ዓመት ስለተቋረጠ ብቻ፣... በአገሪቱ ላይ በቀጥታ የደረሰው ኪሳራ፣ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን በማየት፣ የጉዳቱን ግዙፍነት መገንዘብ እንችላለን። ለዓመታት መጓተቱም፣ ተጨማሪ የቢሊዮን ብሮች ኪራሳ ያመጣል። እነዚህ ቀጥተኛ ኪሳራዎች ብቻ፣... ከ10 ቢሊዮን በላይ ይሆናሉ። ይሄ፣... በየትኛውም አገር ቢሆን፣ አሳዛኝ ኪሳራ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ ደሃ አገራት ግን፣ ክፉኛ ያንገበግባል።

10 ቢሊዮን ብር ምን ያህል ነው?
በንፅፅር ተመልከቱት። አገሪቱን እያናወጠ ወደ ትርምስ አፋፍ አድርሷት የነበረውን፣... የአምናውን አስፈሪ ቀውስ ታስታውሳላችሁ። የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣ ለአስፈሪው ቀውስና ነውጥ ሰበብ ሆኗል ተብሎ ሲነገርም ሰምታችኋል። የሚሊዮን ወጣቶች የስራ አጥነት ችግርን በከፊል ለማቃለል፣ በመንግስት የተመደበው “አገር አድን ገንዘብ” ስንት ነው? የ10 ቢሊዮን ብር ብድር! አገርን ከአደጋ ለማዳን፣ ከገደል አፋፍ ለመመለስ፣ ከክፉ ትኩሳት ለማገገም ይረዳል ተብሎ የተመደበ ትልቅ ገንዘብ ነው - 10 ቢሊዮን ብር።
ለ60ሺ ወጣቶች፣ ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር ያገለግላል ተብሎ በሃዋሳ የተገነባው የኢንዱስትሪ መንደር፣ በ5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው። በ10 ቢሊዮን የዚህን እጥፍ መገንባትና፣ ከ100ሺ ለሚበልጡ ወጣቶች፣ በዘመናዊ ኢንዱስትሪ፣ ኑሮን የሚያሻሽል፣ ብሩህ ራዕይን የሚያጎናፅፍ፣ አስተማማኝ የስራ እድል መክፈት ይቻላል።
በ10 ቢሊዮን ብር፣ ከድሬዳዋ ያልተናነሰ ነዋሪዎችን የሚያስተናግዱ 50ሺ ኮንዶሚኒዬም ቤቶችን መገንባት ይቻላል። እንግዲህ አነፃፅሩት። በአዲስ አበባ፣ በየዓመቱ ተገንብተው ለነዋሪዎች የሚደርሱ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች፣ በአማካይ 10ሺ ገደማ ናቸው።
ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ በከፍተኛ አገራዊ ወኔ፣ ከመንግስት ሰራተኞችና ከነጋዴዎች፣ በአምስት አመታት ያልተቋረጠ ቅስቀሳ፣ እስካሁን በመዋጮና በቦንድ ግዢ የተሰበሰበው ገንዘብ፣ 10 ቢሊዮን ብር አይሞላም። 10 ቢሊዮን ብር ብዙ ነው።
እንደ ተከዜ ግድብ፣ እንደ ገቢ2 ወይም እንደ በለስ፣... በአስተማማኝነቱ የሚጠቀስ፤ እስከ 400 ሜጋዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣... በዓመት ከ1700 በላይ ጊጋዋት አወር የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመርት ግድብ መገንባት ይቻላል። በዓመት፣ 800 ጊጋዋትአወር የሚያመነጭ ግድብ ለመስራት፣ በአማካይ 5 ቢሊዮን ብር ቢፈጅ ነው።
ከ800 ጊጋዋት አወር በላይ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ያቃታቸው የአገሪቱ የነፋስ ተርባይኖች ግን፣ ከ770 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቶባቸዋል። አሁን ባለው ምንዛሬ፣ 17 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ አሁን ባለው ምንዛሬ፣ በ5 ቢሊዮን ብር አማካይ ወጪ ግድብ ብንገነባ ኖሮ፣ እንደነፋስ በየደቂቃው ከቁጥጥር ወጭ የማይንገራገጭና የማይዋዥቅ፣ ከ800 ጊጋዋት አወር የሚበልጥ አስተማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማምረት ይቻላል - በየዓመቱ።
በዛሬ ምንዛሬ ሲታሰብ፣ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት የፈሰሰባቸው፣ በመቀሌና በአዳማ ናዝሬት የተተከሉት የነፋስ ተርባይኖችስ? ከ800 ጊጋዋት አወር በላይ፣ ብዙም ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም የላቸውም። ይህም አስተማማኝ አይደለም። ነፋስን መገደብና ማጠራቀም፣ ፍጥነቱንና መጠኑን መቆጣጠር አይቻልም። ሳይታወቅ ነፋሱ ፀጥረጭ ብሎ፣ ተርባይኑ ይደነዝዛል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ እያዘገመ ለመሽከርከር ያምጣል - ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ባያደርሰውም። ፍጥነቱ ሊጨምር ይችላል። ወይም፤ ድንገት ይጦዛል። እንደአውሎነፋስ ይዞርበታል። የነፋስተርባይኖች ቁሳቁስ፣ በብዛት የሚበላሹትም፣ በዚህ የነፋስ ተፈጥሮ ሳቢያ በሚከሰተው የእንቅስቃሴ ውጣውረድ፣ በሚዋዥቀው የሃይል መጠንና በሚዛባው ቅደምተከተል (ፌዝ) ነው። የኢቢሲ ዘገባ ላይ ግን፣ የነፋስ ተርባይኖችን እያሳዬ፣ “አንዴ ከተተከሉ በኋላ፣ ተጨማሪ ወጪ አይጠይቁም” ሲል ነግሮናል። እንዴት ተቀልዷል!
ጉዳዩ፣ ኑሮን የማይነካና ከቢሊዮን ብሮች ኪሳራ ጋር የማይገናኝ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ፣ “የአላዋቂ አስቂኝ የውሸት ወሬ” ብለን ልናልፈው እንችል ነበር። ኢቢሲ፣ “ተጨማሪ ወጪ የለውም” እያለ፣ አይን ያወጣ ሃሰት፣ ለወራት ሲሰብክና ሲያሳይ መክረሙ፣ ለ‘እውነት’ ደንታ እንደሌለው ይመሰክራል። ነገር ግን፣ ይባስኑ አሳፋሪና አሳዛኝ የሚሆነው፣ እንዴት መሰላችሁ? በዚሁ መስክ፣ ለሙያቸው ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡ የኤሌክትሪክ መሃንዲሶች፣ የእለት ተእለት ስራቸውን የሚያከብሩ የኤሌክትሪክ ቴክኒሺያኖች፣... ኢቢሲን መገሰፅና ማረም አለመቻላቸውን ስናይ ነው።

የጥገናና የመለዋወጫ ወጪ
የነፋስ ተርባይኖች፣ በብዙ የሃብት ብክነት ከተተከሉ በኋላም፣ ኪስን የሚያራቁቱ ፈታኝ ሸክሞች ናቸው። ከነፋሱ ጋር ደቂቃ በደቂቃ፣ ፋታ የለሽ ክትትልን ይጠይቃሉ። በሚዋዥቀውና በሚዛባው ኃይል ሳቢያ የሚበላሹና የሚቃጠሉ መሳሪያዎችን ለመጠገንና ለመቀየርም፣ በየጊዜው ገንዘብ ይጠይቃሉ። ለዚህም ነው፣ ከግድቦች ጋር ሲነፃፀር፣ የነፋስ ተርባይኖች የጥገና ወጪ፣ በእጥፍ የሚበልጠው። ይህንንም እውነት፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም፣  ከገለልተኛ ምሁራን ጥናት ብቻ ሳይሆን፣ በግድብ ግንባታ ፋንታ የነፋስ ተርባይኖችን የማስፋፋት ዘመቻ እያካሄዱ ከሚገኙ ተቋማት ጭምር ማረጋገጥ ይቻላል - ለምሳሌ ከአለም ባንክ። ...Operation and maintenance (O&M) cost accounts for 15–25 percent of the cost of delivered electricity, PhD. Carlos Alvarez, world Bank, April 12, 2016፣ www.worldbank.org።
የበርካታ አገራትን መረጃ በማሰባሰብ የተደረገው ሰፊ ጥናትም፣ የነፋስ ተርባይኖችን የጥገናና የመለዋወጫ ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል -  ለ1ሜጋዋት በዓመት ከ25000 ዶላር በላይ ነው ወጪው። ጥገናና መለዋወጫ ብቻ፣ በአገራችን የሚገኙ የ324 ሜጋዋት የነፋስ ተርባይኖች፣ በዓመት 8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው። ደግሞም፣ የጥገናና የመለዋወጫ ወጪ፣ ከአገር አገር ያን ያህል ልዩነት የለውም።
ምክንያቱም፣ የጥገናና የመለዋወጫ ኮንትራት፣ ለተርባይን አምራቾች የሚለቀቅ ነው። በአመት 8 ሚሊዮን ዶላር፣ በዛሬ ምንዛሬ፣ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል። (IEA Wind Task 26: Wind Technology, Cost, and Performance Trends in Denmark, Germany, Ireland, Norway, the European Union, and the United States በሚል ርዕስ ጁን 2015 የወጣውን ጥናት፣ ገፅ 148 ላይ መመልከት ይቻላል።

Read 2071 times