Print this page
Saturday, 15 April 2017 13:29

ለሕዝብ ያልታወቀ - ከሕዝብ የራቀ

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(11 votes)

 ‹‹ማስገደድና ማዘዝ ሥልጣንን እንጂ አቅምን አያመለክቱም››
                
        መቅደላ ላይ ጀግናው ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የሠዉበትን ቦታ ለማየት ጎብኚዎች ተራራውን ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ እልፍ ብሎ ደግሞ አንድ የመቅደላ ገበሬ በትሩን ተደግፎ ቆሞ የሚሆነውን በአግራሞት ያያል። ይህንን የታዘበ ጋዜጠኛ ካሜራውን አነጣጥሮ፣ መቅረጸ ድምጹንም ወድሮ ጠጋ አለውና ‹ዐፄ ቴዎድሮስ የተሠዉበት የመቅደላ አካባቢ ነዋሪ በመሆንዎ ምን ይሰማዎታል?› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ገበሬውም በትሩን ተደግፎ ባሻገር መቅደላን እያየ ‹ተወኝ ባክህ፤ ካላጣው ቦታ እዚህ መጥቶ ሞቶ እህሌን ያስጠቀጠቅብኛል› አለና መለሰለት ይባላል፡፡
ይሄ ገበሬ በመቅደላ ዙሪያ የሚኖር ገበሬ ነው፡፡ ለእርሱ ከመቅደላ አምባ በላይ የእርሻ ቦታው የመኖርና ያለመኖር ጉዳዩ ነው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ መቅደላን ለመጎብኘት በመሄዱ ገበሬው ያገኘው ትሩፋት የለም። እንዲያውም ተጓዡ መንገድ ፍለጋ በእርሻው ላይ ሲሄድ ሲመጣ የሚያደርሰው ጉዳት ያሳስበዋል፡፡ ለእርሱ ያ ሁሉ ወጭ ወራጅ ‹ዓለምኛ› ነው፡፡ ቤሳ ቤስቲኒ ጠብ አያደርግለትም። ለምን እንደሚወርዱ፣ ለምንስ እንደሚወጡ የነገረው የለም፡፡ እርሱ የወረዳ ካቢኔ፣ የፓርቲ ካድሬ፣ የዞን መስተዳድር፣ የክልል ባለ ሥልጣን፣ የ‹ወርክ ሾፕ› ተሳታፊ፣ የመስክ ጎብኚ፣ የኮንፈረንስ ተካፋይ አይደለ፡፡ ማን ይነግረዋል፡፡ እርሱ ‹ሕዝብ› ነው።
መብት ዕድልን ካላስቀደመ ዋጋ የለውም፡፡ የማወቅ መብት የማወቅ ዕድልን ማስቀደም አለበት፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት የፍትሕ አካላትን በቅርበትና በነጻነት የማግኘትን ዕድል ማስቀደም አለበት። ሐሳብን በነጻነት የመግለጥ መብት ነጻና ገለልተኛ ሐሳብ የመግለጫ መንገዶችን በቅርበት የማግኘት መብትን ማስቀደም አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶች በሌሉበት የመማር መብት፣ የማምለኪያ ቦታዎች በሌሉበት የማመን መብት፣ አመቺና ተደራሽ የመጓጓዣ መንገዶችና ዘዴዎች በሌሉበት የመዘዋወር መብት፣ ደመና እንጂ ዝናብ አይሆኑም፡፡
የሀገራችን ሰው ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› የሚለው ብሂል አለ፡፡ በጥንቱ ባህል ግብዣ ላይ ቁርጥ ሥጋ ሲቀርብ የሰላ ቢላዋ ከሌለ፣ ሥጋው ለዓይን እንጂ ለሆድ ምግብ ሊሆን አይችልም፡፡ የአዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1898 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ፈረስ የሚያስጋልብ ዳስ ተጥሎ፣ ሥጋው ቅጠል በተረበረበ አልጋ ላይ ተጋድሞ፣ ተጋባዡ ዓላማ እንዳየ ወታደር ተሰድሮ ይረበረብ ነበር ይባላል፡፡ ምን ዋጋ አለው። የቀረበው ሥጋና የመጣው ቢላዋ አልጣጣም ብሎ ብዙው ተጋባዥ ሥጋ አግኝቶ ቢለዋ ሳይደርሰው ቀረ፡፡
ይህን ያየ ተጋባዥ ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› ሆነበትና የዳሱ ማገር የተሠራበትን ሸንበቆ እየሳበ፣ እንደ ቢላዋ እየጠረበ ሥጋውን ይቆርጠው ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከተ ገጣሚ፤
ብርንዶው ባንድ አልጋ
ጮማውም ባንድ አልጋ
በማገር ይበላል እንዲህ ያለ ሥጋ፡፡ ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡ አንድ ነገር ለሕዝብ ተብሎ መሠራቱ፣ መቅረቡና መገዛቱ ብቻ ጠቃሚ አያደርገውም፡፡ ሕዝቡ ያንን ነገር የሚያውቅበት፣ ዐውቆ የሚወስንበት፣ ወስኖ የሚያስከብርበት ዐቅም እንዲያዳብር መደረግ አለበት። የሐኪሙ ፍቱን መድኃኒት ከማዘዝ በላይ የበሽተኛው የመድኃኒቱን ጥቅምና አጠቃቀም ተረድቶ መውሰዱ የበለጠ አስፈላጊ ነው፡፡ ደርግ በወደቀ ጊዜ ገበሬው ለምን የገበሬ ማኅበርን ደን እንደቆረጠ አንድ ባለሞያ የተናገሩት እዚህ ላይ ቢጠቀስ ሸጋ ነው፡፡ ‹‹የዚያ ዘመን አብዮተኞች ሕዝቡ በታሪኩም በተረቱም ሰምቶት የማያውቀውን ኮሙኒዝም የሚባል ዛር አመጡበት፡፡ የት እንዳለ፣ ምን እንደሚመስል፣  ግብሩ ምን እንደሆነ፣ ማርከሻው በምን እንደሆነ የማይታወቅ ዛር ነው ይዘውበት የመጡት። በሥዕል አያውቀውም፣ በተረት አልተነገረውም፣ በዘፈን አልሰማውም፣ በድርሳንም በተአምርም አንብቦት አያውቅም፡፡ ጠበል ላይም ሲለፈልፍ አልሰማም፡፡ ለዚህ ለማያውቀው ዛር ሲባል ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡ ውትድርና ዘምቷል፣ ዛፍ ተክሏል፣ እርሻ አርሷል፣ መዋጮ ገፍግፏል፡፡ በመጨረሻ ደርግ ሲወድቅ ኮሙኒዝምን ቢፈልግ ቢፈልግ አላገኘውም፡፡ ያገኘው ዛፉን ነው፡፡ ዛፉ ኮሙኒዝም መሰለውና ቆረጠው፡፡ የዛፍ መትከልን አስፈላጊነትና ጥቅም ከማስረዳት፣ ከማሳመንና አምኖ እንዲሠራበት ከማድረግ ይልቅ ‹ባይገባውም ዋናው ዛፉ ነው› ተብሎ በቅጣት የተሠራው ሥራ ዛፉ ኮሙኒዝ እንዲሆን አደረገው›› ነበር ያሉት፡፡
ማስገደድና ማዘዝ ሥልጣንንና ጉልበትን እንጂ ዐቅምን አያመለክቱም፡፡ በአእምሮ ዐቅማቸው የማይተማመኑ ሁሉ ሐሳብን፣ ዕውቀትንና ተዋሥኦን ይፈሩታል፡፡ ተናግረው እንደማይሰሙ፣ ተንትነው እንደማያሳምኑ፣ ተከራክረው እንደማይረቱ ልባቸው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ከሰውነት ተርታ ይወርዳሉ፡፡ እንስሳነት ሜዳ ላይ ይገኛሉ። እንደ እንስሳትም ጉልበትና ሥልጣንን ብቻ ይጠቀማሉ፡፡ መመሪያቸው ‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው› ነው፡፡ የዱቄቱ ጥራት ግን እንደተፈጨበት ቦታ እንደሚወሰን አያውቁም። በሚሸረክት ወፍጮ የተፈጨ ዱቄት እንዴት ዳቦ ይሆናል? ንጽሕና በሌለው ወፍጮ የተፈጨ ዱቄትስ እንዴት ጤና ይሆናል፡፡ ውጤት ያለ ሂደቱ ብቻውን ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡
እስኪ ሁለት ነገሮች እናንሳና የመቅደላውን ገበሬ የሚያስታውሰንን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ በየስብሰባውም፣ በየሚዲያውም፣ በየሰሌዳውም ‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ› ይባላል፡፡ ለመሆኑ ይህ ዕቅድ የት ነው ያለው? እንደ ግማደ መስቀሉ ተቀብሮ? ወይስ እንደ ታቦተ ጽዮን ተሠውሮ? ለመሆኑ ስንት ገጽ አለው? የተጻፈውስ በምን ቋንቋ ነው? ‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅዱን ለማሳካት እንዲህና እንዲያ እናደርጋለን› የሚሉት ሰዎች ምን ያህል አንብበውታል? ምን ያህልስ ተረድተውታል? ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ልባቸውን ሞልተው ደረታቸውን ነፍተው ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የሚናገሩት ጋዜጠኞችስ እውነት አንብበውታል? አንድ ቅጅስ በእጃቸው ይገኛል? ወይስ ‹ሳያዩ የሚያምኑ› የሚለው ለዚህም ይሠራል? በየመድረኩ የሚያስፎክሩ ሰዎችስ ‹ዕድገት›ና ‹ትራንስፎርሜሽን› ስለሚሉት ሐሳቦች ተመሳሳይ ግንዛቤ አላቸው?
የአዲስ አበባ መሪ ዕቅድስ? የዕቅዱ ባለቤት ሕዝብ ነው፤ በዕቅዱ ላይ ከሁለት መቶ ሺ ሕዝብ በላይ ተሳትፎበታል ተብሏል፡፡ ሕዝቡ ግን በእጁ ቅጅው አለው? መጠየቅ ይችላል? በዕቅዱ መሠረት ተፈጽሟል፣ በዕቅዱ መሠረት አልተፈጸመም ለማለት የሚያስችለው መዝገብ በእጁ አለ? በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ወጣቶች አንብበው ሊረዱት፣ መምህራንም ከዚያ አውጥተው የቤት ሥራ ሊሰጡበት የሚችሉበት ቅጅ አለ?  
በሌላው ዓለም የሆነ እንደሆነ የማወቅ መብትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚታወቅበት መንገድ ወሳኝ ነውና ‹የሕዝብ ቅጅ (Popular Version)› የሚባል ኅትመት ይዘጋጃል፡፡ የሕዝብ ቅጅ የሚባለው ሞያዊ በሆኑ ቃላት የተሞላውን፣ ውስብስብ የሆነውንና እልፍ በሆኑ ገጾች የተዘጋጀውን መዝገብ ሦስት ነገሮችን አሟልቶ እንዲዘጋጅ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ፣ ዋና ዋና ሐሳቦችንና ጉዳዮችን ይዞ፣ በተመጠኑ ገጾች የሚዘጋጅ ነው፡፡ የሕዝብ ቅጅ፡፡ የኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚጎድለው አንዱ ዋነኛ ነገር ይሄ ነው፡፡ ዕቅዱ የሚታሰብ እንጂ የሚነበብ አልሆነም። ዕቅዱ ስለ እርሱ የምንሰማለት እንጂ እርሱን ራሱን የምንሰማው አልሆነም፡፡ ዕቅዱ መኖሩን በእምነት እንጂ በመንካት ልናረጋግጠው አልቻልንም፡፡ ስለ ዕቅዱ እናውቃለን እንጂ ዕቅዱን አናውቀውም፡፡ ለምን?
የሕዝብን የማወቅ መብት የሚያስከብር የሕዝብ የማወቂያ መንገድ አልተዘጋጀምና፡፡ የመቅደላው ገበሬ ከመቅደላ አምባ ይልቅ የእርሱ እርሻ ነገር ያሳሰበው፣ መቅደላ ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ የሚነግረው ስላላገኘ ነው፡፡ ለተራራው ቅርብ ቢሆንም ለጉዳዩ ግን እጅግ እንዲርቅ ተደርጓል፡፡ የሁለቱ ሀገራዊ መዛግብት ዕጣ ፈንታም እንዲሁ ነው፡፡ ስለ ፈጣሪ የሚነግሩን ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን ለሕዝብ በሚገባው ቋንቋ በቀላሉ ሕዝብ እጅ እንዲደርሱ፣ ጳጳሱና ምእመኑ፣ ዑለማውና ሙእሚኑ እኩል እንዲጠቅሱዋቸው በተደረገበት ዘመን፤ ለሀገር የወጣ ዕቅድ ምነው እንደ ሰማይ ራቀ፣ እንደ ነፍስ ረቀቀ?  

Read 5765 times