Print this page
Saturday, 15 April 2017 13:35

የፓርቲዎች ድርድር - ዕድሎቹ፣ ተስፋዎቹና ፈተናዎቹ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በ8ኛው የኢህአዴግና ተቃዋሚዎች የድርድር ቀጠሮ ላይ ከመድረክ፣ሠማያዊ ፓርቲና መአህድ በስተቀር “ያለ
አደራዳሪ ድርድር የለም” በሚል ከድርድሩ ለመውጣት ዳር ዳር ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ወደ ድርድሩ የተመለሱ
ሲሆን “ድርደሩ ከተደራዳሪ ፓርቲዎች በተመረጠ ቋሚ ኮሚቴ ይመራ” በሚል ሃሳብ ከስምምነት ላይ መደረሱ
ታውቋል፡፡ ድርድሩ የሚካሄድበት አዳራሽም አፍሪካ ህብረት፣ ኢሲኤ እና ፓርላማ አዳራሽ በአማራጭነት ቀርበው
በኢህአዴግ ጥቆማ መሠረት፣ ፓርላማ አዳራሽ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ሎጂስቲክስም መንግስት ያሟላል ተብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ ሚዲያን በተመለከተ አዲስ ውሳኔ ላይ የደረሱ ሲሆን እስካሁን ከነበረው አሰራር በተለየ ከአንዳንድ ልዩ
ጉዳዮች በስተቀር ሁሉም ድርድሮች ለሚዲያዎች ዝግ ሆነው እንዲካሄዱ ተስማምተዋል፡፡ “ድርድር ያለ አደራዳሪ አይሞከርም” ብለው በጽናት ሲሞግቱ የቆዩ ፓርቲዎች ምን አቅደው ወደ ድርድሩ ተመለሱ? ከድርድሩ ምን ውጤት ይጠብቃሉ? ለድርድር ሊያቀርቡ ያቀዷቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ምንድን ናቸው? ድርድሩ የመክሸፍ ዕጣ ሳይገጥመው ለውጤት ይበቃ ይሆን? ፓርቲዎቹ ስለ ተደራዳሪው ኢህአዴግ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ
አንበሴ፤በእነዚህ አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ ተቃዋሚዎችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡

                  • ተቃዋሚዎች ከድርድሩ ውጤት አንጠበቅም አሉ
                  • ሁሉም ድርድሮች ለሚዲያ ዝግ እንዲሆኑ ተወስኗል
                  • የፖለቲካ እስረኞችና አሳሪ ህጎች የድርድሩ አካል ይሆናሉ ተባለ


            “በድርድሩ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ የለንም”
              አቶ ዘመኑ ሞላ (የመኢዴፓ ዋና ፀሐፊ)

     እኛ አሁንም “ድርድር ያለ አደራዳሪ አይሆንም” የሚለው አቋማችን እንደተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን ገና በረቂቅ ደንብ ላይ ተለይተን መውጣቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ፣ የፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ በመወሰኑ፣ በድርድሩ ቀጥለን፣ ኢህአዴግን በትላልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ለመፈተን ወስነናል፡፡ እርግጥ ነው ኢህአዴግ አሁንም ግትር ነው፡፡ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በረቂቅ ደንብ ላይ ባለመግባባት፣ ዋናውን የህዝብ አጀንዳ ወደ ጎን መግፋት፣ ተገቢ አይሆንም በሚል ነው የገባነው እንጂ አሁንም ተስፋ ይኖራል ብለን አይደለም፡፡ ረቂቅ ደንቡን አልፈን፣ ዋና አጀንዳ አቅርበን፣ ኢህአዴግ ተለውጫለሁ ታድሻለሁ የሚለው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ መፈተሽ አለብን ብለን ነው የገባነው፡፡
እንደ ፓርቲያችን ውሳኔ፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ጉዳይ በድርድሩ በዋናነት ማንሳት እንፈልጋለን፡፡ ቀዳሚው ጥያቄ መሆን ያለበት ይሄ ነው፡፡ ትልቁ አጀንዳችን የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጉዳይ ነው፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እነዚህ ሰዎች ከእስር ቤት መውጣት አለባቸው የሚል አቋም አለን። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ብለን አናምንም፡፡ በሌላ በኩል የዲሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበቡ፣ ማናቸውን አሳሪ ህጎች እንዲለወጡ እንፈልጋለን፡፡ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ ያለ ከፍተኛ ጫና አለ፤ ይሄ እንዲስተካከል እንፈልጋለን፡፡ አሳሪ የንግድ ህጎች አሉ፤ እነዚህን ማስነሳት እንፈልጋለን፡፡ እነዚህን አቅርበን ኢህአዴግ ምን ያህል በሚናገረው ልክ ታድሷል ተለውጧል የሚለውን ማጋለጥ እንፈልጋለን፡፡ ብዙ አሳሪ አዋጆችና መመሪያዎች እንዲፈተሹ አጥብቀን ሀሳብ እናቀርባለን፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች ይዘን እንቀርባለን፡፡ በዚህ ድርድር ከኢህአዴግ ብዙ ነገር ይጠበቃል። አጀንዳችንን ይዘን እንገባለን፤ እንፈትሻለን፤ ውጤት ካጣን ለህዝብ አሳውቀን የራሳችንን ውሳኔ እንወስናለን፡፡ መፈተን እንፈልጋለን፤ ብዙ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ ግን የለኝም፡፡

-----------------------------

                           “ሦስተኛ አማራጭ አቅርበን ተቀባይነት አግኝቷል››
                           ዋሲሁን ተስፋዬ (የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ሃላፊ)

       ድርድሩ በተደጋጋሚ ስንጠብቀው የነበረ ነው፡፡ ስለዚህ በቀላሉ የምንመለከተው አይደለም፡፡ አሁን በድርድሩ ለመቀጠል ስንወስን “ድርድሩን በዙር መምራት” የሚለውን ሃሳብ ተቀብለን አይደለም፡፡ “በገለልተኛ አደራዳሪ መካሄድ አለበት” የሚለውን የፀና አቋማችንን እንደያዝን በሂደቱ ለመቆየት ወስነን ነው፡፡ እኛ ውጤት የሚመጣው ድርድሩ “በገልልተኛ አካል ቢካሄድ ነው” የሚልም እምነት አለን፡፡ ግን በዚህ አንድ ጉዳይ ከኢህአዴግ ጋር ስለተለያየን፣ አጠቃላይ የድርድሩን ሂደት አቋርጦ መውጣት ተገቢ ነው ብለን አላመንም፡፡ ስለዚህም በድርድሩ ሂደት ለመቀጠል ወስነናል፡፡
ኢዴፓ ድርድሩ እንዴት ይመራ በሚለው ላይ ሦስተኛ አማራጭ አቅርቧል፡፡ “በዙር የሚለው ድርድሩ ወጥነትና ውጤት እንዳይኖረው ስለሚያደርግ፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች በቋሚነት ተመርጠው የአደራዳሪነት ሚና ይውሠዱ፤ ከእነዚህ ፓርቲዎች የሚመረጡ ቋሚ አደራዳሪዎች ይሁኑ” የሚል ሃሳብ አቅርበን፣ ሰፊ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ. ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህኛው አማራጭ ለመቀጠልም ተስማምተናል፡፡
ድርድር በመርህ ደረጃ ሰጥቶ መቀበል ነው። አንድ ችግር ገጠመን ብለን አጠቃላይ ውጤቱን ሳንገመግም ድርድሩን አቋርጦ መውጣት ተገቢ ነው ብለን አላመንም፡፡ አማራጫችንን እያቀረብን እንሄዳለን፡፡ አጠቃላይ ውጤቱንም ገምግመን የደረስንበትን ለህዝብ እናሳውቃለን፡፡ የድርድሩን አጠቃላይ ሂደት፣ትርፍና ኪሣራ መጨረሻ ላይ እንገመግማለን፡፡ በዚህ ሞዳሊቲ ላይ ብቻ ጥሎ መውጣቱ ግን ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለን።
ከድርድሩ የሚጠበቀው ነገር ግልጽ ነው፤ የሃገሪቱን ችግሮች ይፈታል ብለን እናምናለን። ተቃዋሚዎች አላሰራ ያላቸው መሰናክል ተቀርፎ፣በመጨረሻ ህዝቡ በምርጫ ካርድ የሚፈልገውን አካል ወደ ሥልጣን የሚያወጣበትና የሚያወርድበት መደላድል እንዲፈጠር ነው የምንፈልገው፡፡ ይሄን ችግር እንዲፈጠር ያደረጉ ህጎችም ሆኑ ሌሎች መሠናክሎች ላይ ተደራድሮ መደላድሎችን የመፍጠር አላማ ነው ያለን፡፡ ለዚህ የሚያበቃ ድርድር ይካሄዳል የሚል እምነት አለን፡፡
የዲሞክራሲ ምህዳሩን አጥበውታል ከሚባሉ ጉዳዮች ዋነኞቹ፡- የፀረ ሽብር ህጉ፣ የሚዲያ ህጉ፣ የመያድ ህግ ሲሆኑ ሌሎችም አሣሪ ህጎች አሉ፡፡ የድርድሩ አንድ አካል ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲና ሌሎች ተቃዋሚዎች በምርጫ በእኩል ደረጃ እንዳይወዳደሩ ካደረጋቸው አንዱ የፋይናንስ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ እንዲስተካከል እንደራደራለን። መንግስት ለተቃዋሚዎች የፋይናንስ ድጓማ እንደሚያደርግ በአዋጅ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በኢህአዴግ እምቢተኝነት ግን እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡
በእኩል ደረጃ ላይ እንዳንቀመጥ ያደረገን አንዱ ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ  ገንዘብ አለው፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ አንድ እጩ እንኳ ለማቅረብ የሚበቃ ገንዘብ የላቸውም፡፡ ከውጪ ሃይሎችና መንግስታት እንዳይወስዱም በህግ ተከልክለዋል፡፡ ሁሉም የገቢ ምንጮች ተዘግተውባቸው፣ እንዴት ነው በእኩል ሜዳ መወዳደር የሚችሉት፡፡ በዚህ ላይ ሰፊ ድርድር እናደርጋለን የሚል ተስፋ አለን፡፡
የምርጫ ስርአቱን ማስተካከል ሌላው ለድርድር የሚቀርብ አጀንዳ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ አገር ችግር የምርጫ ህጉን በማሻሻል ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች ችግርም መቀረፍ አለበት፡፡ በአለም ላይ ምርጥ የተባለውን የምርጫ ስርአት  ብናመጣም፣ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች እስካልተስተካከሉ ድረስ ለውጥ የሚመጣበት መንገድ የለም፡፡ አሁን በኛ ሃገር ያለው የምርጫ ስርአት እኮ በሌሎች ሃገሮች ውጤታማ ሆኖ እየሰራ ነው፤ዋናው የምርጫ አስፈፃሚዎች ጉዳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ እኛ ከድርድር አናፈገፍግም፤ ይሄን ስንል ግን ውጤት በማያመጣ ድርድር ውስጥ እንቆያለን ማለት አይደለም፡፡ አቋማችንን እየገለፅን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡

---------------------------------------

                               “ውይይቱ ውጤት ያመጣል የሚል ተስፋ የለንም”
                            አቶ ጥላሁን እንደሻው (የመድረክ አመራር)  

       ድርድር፣ ምክክር፣ ውይይት የሚባሉ ነገሮች እየተደበላለቁ፣ ጉዳዩ አንድ መልክ ሊይዝ ባለመቻሉ ነው መድረክ ከሂደቱ ራሱን ያገለለው፡፡ ምክክር ከሆነ ሁሉም በጉባኤ ተሰብስቦ የየራሱን ምክረ ሀሳብ የሚሰጥበት ነው፤ ውይይትም እንደዚያው ነው፡፡ ድርድር ግን ከነዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ ድርድር ሲባል የራሱ ባህሪ ያለው ነው፡፡ ከሁለት ወገን ተከፍለው የመሃል አደራዳሪ ኖሮ “አንተ ይሄን ታሻሽላለህ፤ እኔ ይሄን አሻሽላለሁ” የሚባልበት ነው፡፡ 22 የየራሳቸው አጀንዳ የያዙ ሰዎች ተሰባስበው፣ የየራሳቸውን ሀሳብ የሚሰጡበት ውይይት እንጂ ድርድር ሊባል አይችልም፡፡
እኛ ኢህአዴግን ወደ ድርድር እንዲገባ እየጠየቅን ነበር፡፡ አገሪቱ ካለችበት ችግር አንፃር ጊዜው የምክክርና የውይይት ሳይሆን የድርድር ነው የሚል አቋም አለን፡፡ በውይይቱ ቆይታችን ኢህአዴግ ወደ ድርድር እንዲመለስ ስንጥር ነበረ፡፡ ግን መጀመሪያውኑ ምክክር ብሎ ባመጣው ሀሳብ ነው እየገፋ ያለው፡፡ በሁለት አካላት መካከል የሚደረግ የድርድር መልክ አልያዘም፡፡ ይህ ባልሆነበት የሚደረግ ሂደት ሁሉ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ውይይትና ምክክር ብቻ የሚፈልግ ከሆነ፣ የጋራ ምክር ቤት ተብሎ ላለፉት 8 ዓመታት ከሌሎች ጋር ሲወያይ ከርሞ ምን ውጤት መጣ? የሀገሪቱ ችግር በዚህ ውይይት መቼ ተፈታ? የበለጠ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ፣ ኢህአዴግን መቶ በመቶ የምርጫ አሸናፊ ነው ያደረገው፡፡ የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ እየተደረገ አይደለም እንዴ ሀገሪቱ ወደ ማጥ ውስጥ የገባችው? አሁንም ያንኑ መልክ ይዞ የሚመጣ ውጤት የለም፡፡  
ሞዳሊቲ ሲዘጋጅ የድርድር ነው የውይይት የሚለው ነው ያላግባባን፡፡ እነሱ የሚፈልጉት የውይይት ነው፤ እኛ ደግሞ የድርድር ሞዳሊቲ ነው የምንፈልገው፡፡ ስለዚህ እየተዘጋጀ ያለው ሞዳሊቲ ስለማያስኬደን ተውነው፡፡ ሞዳሊቲው ለኛ አካሄዱን ለማወቅ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሌሎቹ እንደሚሉት ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ሞዳሊቲው ጥርት ብሎ መቅረብ አለበት፡፡ እኛ የምንፈልገው የድርድር ሞዳሊቲ እንጂ የውይይት አይደለም፡፡
ወደ ዋና አጀንዳ መግባት የምንችለው፣ የምናካሂደው ድርድር መሆኑን ስናረጋግጥ ነው፡፡ አሁን በተያዘው አቅጣጫ ግን የሚካሄደው ድርድር ሳይሆን ውይይት ነው፡፡ አሁን ይሄን ተቀብለው በሂደቱ የቀጠሉ ፓርቲዎች፣ ከዚህ ቀደም የምርጫ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ተጀምሮ በነበረ ድርድር ላይ ተሳትፈው ነበር፡፡ አንድ የአምባሳደሮች ቡድን ባመጣው የምርጫ አካሄድ ተሞክሮዎች ላይ እንድንወያይበትና እንድንደራደርበትም አድርጎ ነበር፡፡ ቡድኑ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፣ የምርጫ አስተዳደርና የምርጫ ታዛቢዎች የሚሉ 3 ዋነኛ ጉዳዮች አቅርቦልን የነበረ ሲሆን መድረክ ሶስቱም ያስፈልገናል ሲል እነዚህ ፓርቲዎች ናቸው “ሁለቱን አንፈልግም፤ የምንፈልገው የምርጫ ሥነ ምግባር ጉዳይን ብቻ ነው” ብለው ከኢህአዴግ ጋር የተፈራረሙት፡፡
የምርጫ አስተዳደሩ ገለልተኛ ሳይሆን፣ የምርጫ ታዛቢ ገለልተኛ ሳይሆን የስነ ምግባር ደንብ  የምትለዋን ብቻ ፈርመው፣ የሀገሪቱን ችግር ያባባሱት እነሱ አይደሉም እንዴ? በዚህ ፊርማቸው የኢህአዴግን የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ፣ እየተወያየን ነው ብለው ቆይተዋል፤ ግን ምን ውጤት አመጡ? የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ችግ የሚፈታ፣ አንድ ተጨባጭ ነገር ለምን አልሰሩም? እነዚሁ ፓርቲዎች ናቸው አሁንም ያሉት፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንደሚባለው፣ ለውጥ ይመጣል ብለን ተስፋ አናደርግም፡፡ ለሀገሪቱ ጥሩ ነገር እንዲመጣ ግን እንደ ማንኛውም ዜጋ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡ ግን ካለፈው ልምዳችን በመነሳት ስንገመግም፣እነዚህ ፓርቲዎች ውጤት የሚያመጣ ውይይት ያደርጋሉ የሚል ግምት የለንም፡፡  

---------------------------------  

                “ችግሮችን በስር ነቀል ደረጃ ይፈታል የሚል እምነት የለንም”
                         አቶ መላኩ መሠለ (የኢራፓ አመራር)

                       እኛ በመጀመሪያ ድርድሩ በኢትዮጵያ ህዝብ መስዋዕትነትና ተጋድሎ የተገኘ በመሆኑ ከፍተኛ ዋጋ እንሰጠዋለን፡፡ ህዝብ እያነሳ ያለውን ጥያቄና የሀገራችንን ጥልቅ ችግሮች ስር ነቀል በሆነ ደረጃ በሚፈታ መልኩ እንዲካሄድ ፍላጎት አለን፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ድርድሩ በገለልተኛ አካሎች እንዲመራ የፈለግነው፡፡ ይሄን አቋም ይዘንም ነው ወደ ድርድሩ የገባነው፡፡ በገለልተኛ አካል ያልተመራ ድርድር፤ ውጤታማ እንደማይሆንና ምንም መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል አሳውቀናል። እኛ በሂደቱ በትዕግስት እንጓዛለን እንጂ ለሀገሪቱ ፋይዳ ቢስ መሆኑን አበክረን ገልፀናል፡፡  መንግስት ሊፈታቸው የሚፈልጋቸው ጥያቄዎችና እኛ  የያዝናቸው ጥያቄዎች በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ የተለያዩ መሆናቸውን ገምግመናል። የራሱን የአፈፃፀም ጉድለቶች ለማረም ብቻ ወደ ድርድሩ እንደመጣ ገምግመናል፡፡ እኛ የውጭ ፖሊሲዎችን ጨምሮ በነፃነት፣ በሉአላዊነት፣ በድንበር ጉዳይ ---- በጣም ከባድ፣ በላይኛው የመንግስት መዋቅር ያሉ የፖለቲካ ችግሮችን ሳይቀር ነው በአጀንዳነት ለማንሳት የምንፈልገው። የዚህ መነሻችን ደግሞ ህዝቡ ሲያስተጋባቸው የነበሩ ችግሮች ሲሆኑ ኢህአዴግ ከሠማይ በታች በማንኛውም ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ማለቱ መበረታታት ሰጥቶን ነው የገባነው፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን  ሃሳቦቻችንን ተቀብሎ ማሻሻያ ያደርግባቸዋል የሚል ተስፋ ሰንቀን ነው የገባነው፡፡ ድርድር ሰጥቶ መቀበል በመሆኑና አሁን በሃገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት ካለን ጉጉት የተነሣ፣ “ድርድር ያለ አደራዳሪ አይሆንም” የሚለው ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ መቀጠሉን ወስነናል። ልዩነታችንም እንዲታወቅልን አሣስበናል፤ ምክንያቱም በቀጣይ በሂደቱ ላይ የማይመቹን ነገሮችን ቢያጋጥሙን የራሳችንን ውሳኔ እንድንወስን አመቺ እንዲሆንልን ነው፡፡ ኢራፓ ከምስረታው ጀምሮ በሠላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለው፡፡ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል የሚል አቋምም ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ ይሄን አቋም ለመንግስትና ለሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ሁሉ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡
ይሄ ድርድር ሲከፈትም አምነንበት ገብተንበታል፡፡ ወደ ድርድሩ ስንገባ የምናቀርበው አጀንዳ ህገ መንግስትን የማሻሻልና የማዳበር፣ መከላከያ ሰራዊታችን ገለልተኛ የሚሆንበትን ጉዳይ፣ የአጎራባች ሀገራት ድንበሮች እስከ ገቢ ያሉ የሉአላዊነት ጥያቄዎችን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታትና አሳሪ ህጎችን ማስለወጥ እንፈልጋለን፡፡ ግን አሁን ባለው አካሄድና በተያዘው መስመር ሂደቱ የሀገሪቱን ችግሮች በስር ነቀል ደረጃ ይፈታል የሚል እምነት የለንም፡፡

---------------------------------

                         “በድርድር እንጅ በምክክር ውጤት አይመጣም”
                        አቶ የሸዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር

       ድርድር ከተባለ አደራዳሪ መኖር እንዳለበት እናምናለን፡፡ አሰራሩም እንደዛ ነው፡፡ አደራዳሪ ከሌለ ድርድር አይኖርም፡፡ አደራዳሪ ከተመረጠ በኋላ ነው አጀንዳ ማቅረብ የሚቻለው፡፡ ይሄ እንዲሆን ነበር ጥረታችን፡፡ ግን ገዥው ፓርቲ ይሄን አልተቀበለም። ይሄን አለመቀበሉ ደግሞ በቀጣይ ሰጥቶ መቀበልን በሚጠይቀው ድርድር ላይ ለሚፈጠሩ ነገሮች እንደ ምልክት ነበር የወሰድነው፡፡ የህግ ማሻሻያዎች፣ የሚሰረዙ ህጎች እንዲሁም የተቋማት ሪፎርምን ሁሉ እንጠይቃለን ብለን ነበር ያሰብነው፡፡ ገለልተኛና ነፃ አካል አልፈልግም ያለ አካል እንዴት ትላልቅ ጥያቄዎችን ሊያስተናግድ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ ተገደናል፡፡ አሁንም አደራዳሪ ካለ፣ የሀገሪቱን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን፡፡
ድርድርነቱ የቀረው ገለልተኛ አደራዳሪ አያስፈልግም ሲባል ነው፡፡ አሁን በሚደረገው ስብሰባ ወይም ውይይት ‹‹ይቅናቸው›› የሚል መልካም ምኞት ቢኖረኝም፣ በዚህ ሂደት እንዴት ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ አይገባኝም፡፡ ይሞክሩት ግን ውጤት የሚመጣ አይመስለኝም፡፡ ምክክር እንዲህ ብታደርግ ጥሩ ነው የሚል ሃሣብ የሚቀርብበት ነው፤ ድርድር ግን ይሄ መደረግ አለበት እየተባለና የማሻሻያ ውሣኔ ሃሣቦችና የመፍትሄ ሃሣቦች የሚቀርቡበት መድረክ ነው፡፡ በድርድር እንጅ በምክክር ውጤት አይመጣም፡፡

----------------------------------

                        “ከዚህ ድርድር ምንም የተለየ ነገር አንጠብቅም”
                      አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት)

      ድርድር ያለ አደራዳሪ የሚለው አሁንም የፓርቲያችን ፅኑ አቋም ነው፡፡ ይሄን ልዩነት አስመዝግበን ነው በድርድሩ የቀጠልነው፡፡ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ከሆነ ዝሆን የሚያክል ችግር አስቀምጦ መርፌ የምታክል ቀዳዳ ሳትበግረን አማራጮችን አቋርጠን ማየት አለብን ስንል፣ 6ቱ በጋራ የተሰባሰቡ ፓርዎችን ለብቻ ያለ አደራዳሪም ቢሆን እንዲያደራድሩን ሀሳብ አቅርበናል፡፡ የኛ ትልቁ ሀሳብ የሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲኖር ነው። እኛ በፍፁም በዙር የሚለውን አንፈልግም፡፡ “ቋሚ አደራዳሪዎች ከፓርቲዎች ይመረጡ” የሚለውና ተቀባይነት ያገኘው ሀሳብ፣ ከመጥፎ ሀሳቦች መካከል የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የተሻለው መጥፎ ነው እንጂ መኢአድ የሚምንበት አይደለም፡፡ ሁሉንም ከመዝጋት መሃል መንገድ ድረስ እንምጣ ብለን ነው፡፡
ከዚህ ድርድር ምን ትጠብቃላችሁ ከተባለ ምንም አንጠብቅም፡፡ የማንጠብቅበት ምክንያት የፈለግነውን ያክል ለውጥ የሚያመጣ አካሄድ ስላላየን ነው። ምንም ሳትጠብቁ ለምን ገባችሁ ከተባለ፣ ይሄን እንድናደርግ የሚያስገድደን የፖለቲካ ስትራቴጂ ስላለን ነው፡፡ ምንም ጥቅም እንደሌለው እያወቃችሁ ለምን ገባችሁ ልንባል እችላለን? መልሳችን ወደ ውይይቱ ሳንገባ ከዚህ መንግስት ጋር ምንም ልንባባል አንችልም፡፡ ለዚህች ሀገር ከዚህ መንግስት ውጪ ከሌላ ሀገር መንግስት ጋር ተነጋግረን መፍትሄ ማምጣት አንችልም፡፡ ግን የጠበቅነውን ያክል ውጤት እናገኝበታለን ብለን አንጠብቅም፡፡
መኢአድ በውይይቱ እንዴት እንደሚቀጥል ሂደቶች እየታዩ የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡ አጀንዳውን እያየን ሂደቱን እንፈትሻለን፡፡ እንደ አደራዳሪ ሁሉ ገዢው ፓርቲ የቀረቡ አጀንዳዎችን የሚገፋ ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ የመቀጠሉ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ አጀንዳው ወንዝ የማያሻግረን ከሆነ እዛው ላይ ይቆማል፡፡ የአሁኑን ውሳኔ በግሌ አላመንኩበትም ግን የድርጅት ጉዳይ ስለሆነ የድርጅቴን ሀሳብ አከብራለሁ።
የምጠብቀውም የተለየ ነገር አይኖርም። ኢህአዴግ የምርጫ ምህዳሩን አሰፋለሁ እያለን ነው፤ ይሄን በድርድሩን ሂደት ሳያሳየን የምርጫውን መስፋት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ድርድሩ በአደራዳሪ ቢሆን ለዚህች ሀገር የበለጠ ውጤት ሊመጣ ይችል ነበር የሚል እምነት አለን፡፡ 3ኛ ወገን የበለጠ የሚጠቅመው ለኢህአዴግ ነበር፡፡ ግን አቋሙን መቀየር አልቻለም፡፡
በዚህ ድርድር ላይ ግብ ብለን የያዝናቸው በመጀመሪያ ከመኢአድ አባላት 65 በመቶ የሚሆኑት እስር ቤት ናቸው፡፡ ተነጋገረን ውጤት እናመጣለን የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ አሁንም በዚህኛው ሂደት እንሞክረዋለን፡፡ በህዝቡ ላይ የተጫነው የዲሞክራሲ እጦት፣ የኃይል አገዛዝ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ይቀንስለታል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ ግባችን ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ሁሉ ማመቻቸት ነው፡፡ መንግስት ህገ መንግስቱን እስከ መቀየር እደራደራለሁ ብሏል፤ ይሄ ጥሩ ተስፋ ነበር፡፡ አፋኝ ህጎች ከተነሱ በህጉ ውስጥ ሆኖ መስራት ይቻላል የሚል እምነት አለን፡፡ ግባችን በነዚህ ዙሪያ ነው፡፡ ግን አሁን የገለልተኛ አደራዳሪ አለመኖር፣ ተስፋችንን  በሙሉ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡  

Read 2334 times