Sunday, 30 April 2017 00:00

አዋሽ አንተርናሽናል ባንክ፤ በአርማው ላይ ማሻሻያ አደረገ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      በ2025 በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ 10 ምርጥ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን እየተጋ መሆኑን የሚገልፀው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ትናንት በሂልተን ሆቴል ባደረገው የብራንድና የንግድ ስያሜ ትውውቅ፤ ለ22 ዓመታት ሲጠቀምበት በነበረው የብራንድና የንግድ ስያሜ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ፡፡
የባንኩ የቢዝነስና ኦፕሬቲንግ ሞዴል መቀየሩን፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት በአዲስ መልክ መዋቀሩን፣ አዲስ የደንበኞች አመዳደብና አገልግሎት አሰጣጥ መዘጋጀቱን የጠቀሱት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፤ በባንኩ ሎጎ ወይም አርማና ቀለሞች ላይ ማሻሻያ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው ኅብረተሰብና የባንኩ የቅርብ ባለድርሻ አካላት ባንኩን የሚጠሩት ‹‹አዋሽ ባንክ›› በማለት ስለሆነ የባንኩ ሕጋዊ የመዝገብ ስሙ ‹‹አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ›› ሆኖ እንዲቀጥል፣ የንግድ ምልክት ስያሜው ‹‹አዋሽ ባንክ›› ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የኮርፖሬት ቀለሞች በሁለት ሙሉ ቀለም ማለትም ጥልቅ ሰማያዊና ብርቱካናማ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ አዲሱን ብራንድ የማስተዋወቅ ሥራ  በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በተለያዩ ጋዜጦች እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በ486 መሥራች ባለአክስዮኖች፣ በ23.1 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል፤ በ1987 ዓ.ም የተመሰረተው አዋሽ ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ3,600 በላይ፣ የባንኩ ካፒታል 2.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅላላ ሀብቱ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፣ ተቀማጭ ገንዘብ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ፤ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፤ በቅርንጫፎች ብዛትም ከ293 በላይ መድረሱን አቶ ፀሐይ

ሺፈራው አስታውቀዋል፡፡
አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት በጠቅላላ ሀብት፣ በካፒታል መጠን፣ በተቀማጭ ገንዘብ፤ በብድር፣ በትርፍ፣ በቅርንጫፎች ብዛትና በተለያዩ መስፈርቶች

የግል ባንኩን ኢንዱስትሪ እየመራ ነው ተብሏል፡፡

Read 4550 times