Sunday, 30 April 2017 00:00

በአገሪቱ የሚገኙ 239 ወረዳዎች በወባ በሽታ ሥጋት ላይ ናቸው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

     የወባ በሽታ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እየገደለ ነው
የወባ በሽታ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት እያጠፋ ሲሆን በሽታው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለሚገኙ 239 ወረዳዎች ትልቅ ሥጋት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተከበረው ዓለም አቀፍ የወባ ቀን ላይ እንደተጠቆመው፤ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ የቆየው የወባ በሽታ፣አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት እየዳረገ  ነው ተብሏል፡፡   
ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤አገሪቱ እ.ኤ.አ ከ2010-2015 የወባ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ህመምንና ሞትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በ2030 ወባን ከአገሪቱ ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፣ከመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከህብረተሰቡ በርካታ ሥራዎች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡
“End Malaria for Good” በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሞኑን በተከበረው 10ኛው ዓለም አቀፍ የወባ ቀን በዓል ላይ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሱዋክ ቱት እንደተናገሩት፤ በቀላሉ ሊከላከሉት፣ ሊቆጣጠሩትና በህክምናም ፈውስ ሊያገኙበት በሚችሉት የወባ በሽታ፣በክልሉ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየርና በሽታው በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብና የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡

Read 1234 times