Sunday, 30 April 2017 00:00

በየቀኑ 400 ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ እየተመለሱ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      “ግብፅ በኤርትራ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳላት አናውቅም” - (የውጭ ጉዳይ ሚ/ር)

   የሳኡዲ መንግስት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ህገ ወጥ ያላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች ሀገሪቱን በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን አዋጅ ተከትሎ በየቀኑ እስከ 400 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ነው ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያውያኑ መዘናጋት አሳሳቢ የነበረ ሲሆን አሁን በተፈጠረው ግንዛቤ፣የምህረት አዋጁን በመጠቀም ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ ለሚመለሱ ዜጎች 21 ዓይነት የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መንግስት መፍቀዱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡  ከሳኡዲ በአጠቃላይ 100 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይመለሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን መንግስት ለተመላሽ ዜጎች ምን ያዘጋጀው የስራ እድል እንዳለ ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ “ጉዳዩ ለኛም ዱብእዳ ነው የሆነብን፤አዋጁ ይታወጃል ተብሎ አልታሰበም፤ነገር ግን ከክልሎች ጋር በመነጋገር የሥራ እድሎች በሚመቻቹበት ዙሪያ ምክክር ተደርጓል” ብለዋል፡፡ ከሳኡዲ ተመላሾች በአገር ውስጥ የተጀመረው የስራ እድል ማስፋፊያ ተቋዳሽ እንደሚሆኑም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዜጎችን ከሳኡዲ የመመለስ ጉዳይ ብሄራዊ ጉዳይ ተደርጎ መወሰዱን ጠቁመው ሁሉም የመንግስት አካላት በችግሩ ላይ እየተረባረቡ ነው ብለዋል። ችግሩ ድንገተኛ እንደመሆኑ ከድንገተኛነቱ ጋር የሚመጣጠን ስራ እየተሰራ ነው ሲሉም አክለዋል፤ ቃል አቀባዩ፡፡  በሌላ በኩል ግብፅ በኤርትራ 30 ሺህ የሚደርስ ጦር ለማስፈር እንቅስቃሴ ጀምራለች መባሉን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ መለሰ፤”መገናኛ
ብዙኃን ስለ ጉዳዩ ከሚያቀርቡት ዘገባ ውጭ ግብጽ በኤርትራ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳላት አናውቅም” ብለዋል።

Read 1948 times