Sunday, 30 April 2017 00:00

“ሰማያዊ” የኮሚሽኑን ውንጀላ አልቀበልም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

4 የኦሮሞ ፓርቲዎች፤ መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳሳቡ

በቅርቡ ለፓርላማ የቀረበው የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት፤ገለልተኛ አይደለም ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤በኮሚሽኑ የቀረበበትን ውንጀላ እንደማይቀበል ያስታወቀ ሲሆን 4 የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በበኩላቸው፤ የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደማይቀበሉት ገልጸው መንግስት፣ ህዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስበዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤”የችግሮች ሁሉ መነሻ የመንግስት አስተዳደር ጉድለት መሆኑ ሲነገር ነበር፤የኮሚሽኑ ሪፖርት ግን ኢህአዴግ በዚህ ጉድለት እንዳይጠየቅ የሚያደርግ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
ሰማያዊን በጥፋተኝነት ከመወንጀሉ በፊት ኮሚሽኑ ፓርቲውን ማነጋገር ነበረበት ያሉት አቶ የሸዋስ፤ያንን ሳያደርግ በፓርቲው ላይ ያቀረበው ውንጀላ ተቀባይነት የለውም፤ሪፖርቱም ተዓማኒ አይደለም ብለዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የባህርዳር 20 አመራሮች ታስረው ባሉበትና ጉዳያቸው በህግ ተይዞ ባለበት ሁኔታ ኮሚሽኑ ፓርቲውን የሚወነጅል ሪፖርት ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፤አቶ የሸዋስ፡፡
በተመሣሣይ 4 የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፡- የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር፣ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ እና የኦሮሚያ ነፃነት ብሄራዊ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤”ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ያቀረበው ሪፖርት ከሃቅ የራቀ ነው” ብለዋል፡፡ ሪፖርቱም በገለልተኛ አካል የተጣራ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት ድርጅቶች፤መንግስት ከሃላፊነት ለመሸሽ የሚያደርገውን ሩጫ ትቶ፣ ጉዳዩ በአለማቀፍ ገለልተኛ ወገኖች እንዲጣራና ለሞቱና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ተገቢው ካሣ እንዲከፈል ጠይቀዋል፡፡ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የወሰዱና ጉዳት ያደረሱ የፀጥታ ሃይሎች፣ትዕዛዙን የሰጡ የመንግስት ሃላፊዎች በህግ መጠየቅ አለባቸው ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶቹ፤መንግስትም ህዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስበዋል፡፡

Read 2957 times