Sunday, 30 April 2017 00:00

የአሰፋ ጫቦ የቀብር ሥነ ስርአት በኢትዮጵያ ይፈፀማል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አስከሬኑ እስከ ሰኞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል

ባለፈው እሁድ ሚያዚያ 15፣በሚኖርበት አሜሪካ፣ዳላስ፣ በሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ያለፈው አንጋፋው የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ሊቅ አሰፋ ጫቦ አስከሬን፣በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባና የቀብር ሥነ ስርአቱም በትውልድ አካባቢው አሊያም በአዲስ አበባ እንደሚፈፀም ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የአሰፋ ጫቦ ትክክለኛ አሟሟት እስካሁን ያልተረጋገጠ ሲሆን ቤተሰቦቹም ለጥቂት ቀናት ታሞ ሆስፒታል መግባቱን እንጂ የሞቱን መንስኤ የሚያረጋግጥ ተጨባጭ የህክምና ማስረጃ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው እሁድ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ህይወቱ ማለፉን በቅርብ ዘመዳቸው በኩል እንደተረዱ፣ብቸኛ ሴት ልጁ እመቤት አሰፋ ለአዲስ አድማስ ገልጻለች፡፡  
ህይወቱ ከማለፉ ጥቂት ቀናት በፊት በየቀኑ በስልክ ይነጋገሩ እንደነበር የጠቀሰችው ወ/ሮ እመቤት፤አባቷ ከጉንፋን በቀር በሌላ በሽታ ታሞ እንደማያውቅ ጠቁማ፣የአሁኑ ህመሙም  ለከፋ ችግር እንደማይዳርገው ነግሯት እንደነበር አስታውሳለች፡፡
የህልፈቱ መርዶ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ የሚገኙ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ሲሆን ነዋሪነቱን በአሜሪካ ያደረገው የመጨረሻ ልጁ አለማየሁ አሰፋ፣ እስከ ሰኞ ድረስ አስከሬኑን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቀብር ሥነ ስርአቱ በትውልድ ሀገሩ ጨንቻ ወይም አዲስ አበባ የሚፈጸም ሲሆን እርግጠኛ ቦታው ሲወሰን ይፋ እንደሚያደርጉ
ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ75 ዓመት ዕድሜው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አሰፋ ጫቦ፤ሦስት ወንድና አንድ ሴት ልጅ እንዲሁም ዘጠኝ የልጅ ልጆች እንዳፈራ ለመረዳት ተችሏል፡፡

Read 4959 times