Sunday, 30 April 2017 00:00

የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ወደ 7.7 ሚሊዮን አሻቀበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

ለጋሽ አገራት ለአደጋው ምላሽ እየሰጡ አይደለም

    በሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ተረጂዎች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 77.8 ሚሊዮን ማሻቀቡን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ ለአዲስ አድማስ ያስታወቁ ሲሆን መንግስት እያቀረበ ካለው እርዳታ ውጭ ለጋሽ ድርጅቶች በሚፈለገው መጠን ለአደጋው ምላሽ እየሰጡ አይደለም ብለዋል፡፡
 ኮሚሽኑ ባለፈው ጥር ወር 5.6 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ እንደሚፈልጉ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ2 ሚሊዮን በላይ በመጨመር የተረጂዎች ቁጥር ወደ 77.8 ሚሊዮን ማሻቀቡ ታውቋል፡፡  
የተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን የጨመረው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን ተጨማሪ1.5 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፤በደቡብ ክልል 203 ሺ እንዲሁም በአማራ 304 ሺህ ተጨማሪ ተረጂዎች መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቁጥሩ በተጠቀሰው መጠን ሊጨመር የቻለው ከድርቁ ጊዜ መራዘም ጋር በተያያዘና በአንዳንድ አካባቢዎች ከመስከረም እስከ ህዳር ባለው ወቅት ውርጭ መከሰቱን ተከትሎ፣የሠብል ወድመት በመድረሱ እንደሆነ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤በደቡብ ክልል ደግሞ ከድርቁ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናከር ጋር ተያይዞ የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩን አስረድተዋል፡፡ በአማራ ክልል ከ3 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ የሆኑት ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሳይሆን በውርጭና በጎርፍ እንዲሁም በበረዶ ዝናብ ሳቢያ ሰብላቸው በመውደሙ እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ አመልክቷል፡፡
ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በዚሁ ስሌት መሰረት ለተረጂዎች እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ፤የአሜሪካ መንግስት ከለገሰው የ114 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ወጪ ጎልቶ የሚጠቀስ ሌላ እርዳታ ከለጋሽ መንግስታት አለመገኘቱን ጠቁመው መንግስት ችግሩን በራሱ አቅም ለመወጣት እየጣረ ነው ብለዋል፡፡   
በመጋቢት ወር ይጠበቅ የነበው የበልግ የዝናብ ሁኔታ ምን ያህል እንደነበር በግንቦት ወር መጨረሻ ተገምግሞ በሰኔ ወር የተረጂዎች ቁጥር ላይ ክለሳ የሚደረግ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ ጠቁመዋል፡፡
አገሪቱ በ50 ዓመት ውስጥ አይታው አታውቅም የተባለው ድርቅ የተከሰተው በ2007/2008 ሲሆን በወቅቱ አለማቀፍ ተቋማት የተረጂዎችን ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን አድርሰውት ነበር፡፡  መንግስት በበኩሉ፤10.1 ሚሊዮን መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።  

Read 3089 times