Sunday, 30 April 2017 00:00

የኮሚሽኑ ሪፖርት ገለልተኛና ተዓማኒ ነው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ፣ አማራና በደቡብ ክልል ጌድኦ ተከስቶ በነበረው ግጭትና ተቃውሞ ላይ ያቀረበውን የምርመራ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ በሪፖርቱ ላይ የገለልተኝነትና የሃቀኝነት ጥያቄዎች ተነስተውበታል፡፡ ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የኮሚሽኑን ሪፖርት አልተቀበለውም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ግጭቶችን ተከትሎ፣የደረሰው ጉዳትና ጥፋት በውጭ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም መንግስት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ፤ የውጭ ገለልተኛ አካልም ቢመጣም ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተለየ ሪፖርት አያቀርብም
ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ተቃዋሚዎች ግን በዚህ የጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ጨርሶ አይስማሙም፡፡
ለመሆኑ የህግ ባለሙያዎች፣ፖለቲከኞችና ጦማሪያን በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው? ኮሚሽኑ ገለልተኛና ተዓማኒ ነው ብለው ያምናሉ? ከመንግስት ተጽዕኖስ ፍጹም ነጻ ነው?
የምርመራ ሪፖርቱ ላይ ምን አስተያየት አላቸው? የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔርስ ስለሚመሩት ተቋም ምን ይላሉ?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በጉዳዩ ዙሪያ ያሰባሰባቸውን አስተያየቶች እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ ሁሌም ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው ብለን እናምናለን፡
፡ ሃሳቦች አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገኛኙ ድልድዮች ናቸው፡፡

             “የኮሚሽኑ ታማኝነት ለአስፈፃሚው አካል ሳይሆን ለህዝቡ ነው”
                 ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር (የኢሰመኮ ኮሚሽነር)

       ኮሚሽኑ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት መርማሪ ተቋማት መርሆዎችን ያሟላ ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለመንግስት አስፈፃሚው አካል ሳይሆን ለህዝቡ ነው። ተጠሪነቱ ለህዝቡ ወኪሎች፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ ገለልተኝነቱ ላይ እንዴት ጥያቄ ይነሳል?
ገለልተኝነት በዋናነት የሚለካው በስራና በተግባር ነው፡፡ መታየት ያለበት ያቀረብነው ሪፖርትና ምርመራውን ለመስራት የሄድንበት ርቀት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከ2008 ጀምሮ በርካታ የግለሰብና የቡድን መብቶች ጥሰት አቤቱታ ቀርበውለት፣ ፍትሃዊ የሆነ ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ያለ ማንም ጫና፣ በድፍረት ጠንካራ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በቂሊንጦ ቃጠሎ ላይ ጠንካራ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ጠንካራ ስራ ሰርቷል፡፡  አሁንም እየሰራ ነው፡፡
የኮሚሽኑ ታማኝነት ለአስፈፃሚው አካል ሳይሆን ለህገ መንግስቱና ለህዝቡ ነው፡፡ ሀገሪቱ ተቀብላ ላፀደቀችው ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተገዥ ነው፡፡ ገለልተኝነታችንን ደግሞ የሚመሰክረው ተግባራችን ነው፡፡ ዓለማቀፍ ተቋማት የሚባሉት ድርጅቶች የሚያወጡት ሪፖርት መሬት ወርደው ሳይሆን አየር በአየር የተገኘ መረጃ ነው፡፡
 የሰብአዊ መብት ጥሰት ደግሞ አየር በአየር በተገኘ መረጃ፣ በስሚ ስሚ አይጣራም፡፡ ሳይንሳዊ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ ጋ መሬት ወርዶ፣ በቦታው ተገኝቶ፣ የሚመለከታቸውን በሙሉ አካቶ ጠይቆ፣ መሰራት ያለበት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የትኛው ተቋም ነው መሬት ወርዶ ሳይንሳዊ ጥናት ያደረገው? የለም፡፡ ይሄው ኮሚሽን ነው በገለልተኝነት፣ ሳይንሳዊ ጥናት አድርጎ ሪፖርት ያቀረበው፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይም ያቀረባቸውን ምክረ ሀሳቦች ተፈፃሚነት ተከታትሎ፣ በድጋሚ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀርባል፡፡

-------------------

                         “ሪፖርቱ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተንፀባረቀበት ነው”
                         አቶ ወንድሙ ኢብሣ (የቀድሞ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያ)

      ፖለቲካ በህግ መመራት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የቀረበው ሪፖርት፣ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አላማ አንፃር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱ ሲቀርብ መከሰስ ያለባቸውን አካሎች ይጠቁማል። ይሄ ስህተት ነው፡፡ አንድ ሰው ወንጀል ከሰራና እንዲከሰስ ከተፈለገ የግድ የዚህ ኮሚሽን ሪፖርት አያስፈልግም። ምክንያቱም በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈፀመ ተብሎ ሲጠረጠር ፖሊስ ነው በደረሰው መረጃ መሰረት የሚያጣራው፡፡ ፖሊስ ያጣራውን መረጃ አጠናቅሮ ለአቃቤ ህግ ያቀርባል፤ አቃቤ ህግ ደግሞ የቀረበውን መረጃ መርምሮ ክስ መመስረት ሲያስፈልግ ይከሳል። ይሄ ነው ትክክለኛው የህግ አሰራር፡፡ ከዚህ አንፃር የኮሚሽኑ ሪፖርት ደረቅ ወንጀልን የተመለከተ ነው። ደረቅ ወንጀሎችን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማጣራት አይጠበቅበትም ነበር፡፡ ይሄ የፖሊስ ስራ ነው። አሁን የቀረበው ሪፖርት ይሄን መርህ የሳተ፣ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተንፀባረቀበት ነው፡፡
 ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች፣ የገለልተኝት ጥያቄ ሲነሳባቸውም ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ በቅርቡ በፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ድርድር በገለልተኛ አደራዳሪ መካሄድ አለበት ሲባል የኢህአዴግ ተወካዮች የሰጡት ምላሽ፤ ”እዚህ አገር ገለልተኛ የሚባል የለም፤ ወይ የተቃዋሚ ደጋፊ አሊያም የኢህዴግ ደጋፊ ይሆናል፤ ሁሉም የራሱ አቋም አለው” የሚል ነበር፡፡ ይሄን ተቋም ገለልተኛ ነው ብለን እንዳንቀበል፣ ይሄ የኢህአዴግ መከራከሪያ መነሻና ማስረጃ ይሆነናል፡፡
ከዚህ አንፃር የቀረበው ሪፖርት ገለልተኛ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዚህ የኢህአዴግ አቋም፣ ኮሚሽኑ ገለልተኛ አለመሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲስ ገ/እግዚአብሔርም ቢሆኑ የምርጫ ቦርድ ም/ሰብሳቢ የነበሩ ናቸው፡፡ በወቅቱ የተቃዋሚዎችን እሮሮና አቤቱታ በተገቢው ሁኔታ አያዳምጡም ነበር። ከዚህ አንፃር ገለልተኛ ናቸው ቢባል አያሳምንም፡፡
የኮሚሽኑ ኃላፊነት ድርጊቱን መርምሮ ማቅረብ ብቻ ነው። እሱ ግን ከዚያም አልፎ “እከሌ ጥፋተኛ ነው፤ መከሰስ አለበት” የሚል ድረስ ሄዷል፡፡ ይሄ በየትኛውም አለም አቀፍ አሰራር የማይደገፍ ነው፡፡ “ይሄ አካል ተጠያቂ መሆን አለበት” የሚለው የኮሚሽኑ ኃላፊነት አይደለም። ኮሚሽኑ የሚጠበቅበት ድርጊቱን ብቻ መግለፅ ነው፡፡
ግለሰቦችን ወይም ተቋማትን ተጠያቂ ማድረግ የኮሚሽኑ ኃላፊነት ስለመሆኑ በህግ አልተደነገገም። ለምሣሌ “ኦፌኮ”፣ “ሠማያዊ”፣ ወዘተ-- ይከሰሱ፤ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡ ይሄን ያለው በምን ስልጣኑ ነው? በአጠቃላይ እንደ ፖለቲከኛም እንደ ህግ ባለሙያም ሪፖርቱን ሳየው፣ ገደቡን ያለፈ ፖለቲካዊ ስሜት የተንፀባረቀበት ነው፡፡

--------------------

                       ‹‹ሪፖርቱ የቀረበው ገለልተኛ ባልሆነ አካል ነው››
                     ጎይቶም ፀጋዬ (ፖለቲከኛ)

      ሲጀመር ሪፖርቱ የቀረበው ገለልተኛ ባልሆነ አካል ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የሠብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲቋቋሙ የደነገገ ቢሆንም እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን ገለልተኛ አካል አልተቋቋመም፡፡ የተቋቋሙትም ቢሆን ሽባ እንዲሆኑ ነው የተደረገው፡፡ በመንግስት የተቋቋመው ኮሚሽንም ለስርአቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ናቸው የሚመሩት፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ ልክ እንደ ምርጫ ቦርድና የኢህአዴግ ተቋማት ነው የሚታየው፡፡ ይሄ የሆነው ስርአቱ ገለልተኛ የሆነ ተቋም እንዲኖር  ስለማይፈቅድ ነው፡፡
በሪፖርቱ የቀረበው የሟቾች ቁጥር እኛ እንደ ‹‹መድረክ›› ካለን መረጃ አንፃር እጅግ ጥቂት ነው፡፡ የኦፌኮ አመራሮች እስር ቤት ከመግባታቸው በፊት በርካታ መረጃ ይደርሰን ነበር፤ ሁሉንም እናውቅ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ወዲያው ሪፖርት ያወጡ ሲሆን ኮሚሽኑ 9 ወር ፈጅቶበታል፡፡ ይሄ የሚያሳየው በምክክር የወጣ ሪፖርት እንደሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለማመን መሞከራቸው ብዙም የሚደንቅ አይደለም፡፡ እነሱም ደጋግመው ሲገልፁት የነበረው ነው፤ በሪፖርቱ የተካተተው፡፡
ተጠያቂ መሆን የነበረባቸው የወረዳና የቀበሌ አመራሮች አልነበሩም፤ ዋናውን ትዕዛዝ የሰጠው አካል ነው መጠየቅ የነበረበት፡፡ የፀጥታ ሃይሉም ሆነ የወረዳ አመራሮች ያልታዘዙትን እንደሰሩ ተደርጎ መቅረቡ አሳዛኝ ነው፡፡ ዋናውን ትዕዛዝ ማን አስተላለፈ? ወታደሩን ማን አስታጥቆ ላከ? ሪፖርቱ ይሄን ለማየት አልደፈረም፡፡ እኔ በአጠቃላይ ተጠያቂ መሆን የነበረበት “ለምን ይሄ ቀውስ ተፈጠረ?” ከሚለው ጥያቄ በመነሳት፣ የላይኛው የመንግሥት አካል ነበር፡፡
ይሄን ጉዳይ በገለልተኝነት የተቋቋመ የሃገር ውስጥ ተቋም ቢመረምረው ይመረጥ ነበር፡፡ የውጭ አካላትም ቢሆኑ ምናልባት የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ሊያንፀባርቁ ይችሉ ይሆናል፡፡ የተሻለና የታመነ ውጤት ሊመጣ ይችል የነበረው ግን ገለልተኛ ሆኖ በተቋቋመ የአገር ውስጥ ጠንካራ ተቋም ነበር፡፡ አሁን ከቀረበው የኮሚሽኑ ሪፖርት ግን የውጭ ሃገር ተቋማት ሪፖርት ይመረጣል፡፡

----------------

                    “በሪፖርቱ አጠቃላይ ሲስተሙ መፈተሽ ነበረበት”
                 ዳንኤል ብርሃነ (ጋዜጠኛና ጦማሪ)

      ሪፖርቱ ካለፉት ጊዜያት ሪፖርቶች የተሻሉ ነገሮች አሉት፡፡ ባለፈው ጊዜ ዝም ብሎ ተመጣጣኝ ነው አይደለም የሚለውን ብቻ ለመመለስ ነው የሞከረው፡፡ የአሁኑ ግን ቦታዎችን እየለየ፣ የሃይል አጠቃቀሙን ለመለየት ሞክሯል፡፡ ይሄ አንድ ደረጃ መሻሻሉን ነው የሚያመለክተው፡፡ ምርመራው የተደረገበትና የቀረበበት ፍጥነት ግን ያን ያህል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ሪፖርቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው መሻሻል የታየበት ነው፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ሌሎች የውጭ ተቋማት መጥተው ቢመረምሩ ከዚህ የተለየ ውጤት አያመጡም ብለው በተናገሩት ሀሳብ አልስማማም። የውጭ ተቋማቱ ካላቸው አቅምና ልምድ አንፃር የተሻለ ሪፖርት ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል እነሱም የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ መሆን ያለበት በበጎ ፍቃድ ገለልተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ማቋቋም ነው፡፡ ከየፖለቲካ ፓርቲዎችና ከበጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች በተውጣጣ ቡድን አንድ ተቋም ቢቋቋም ከዚህ የተሻለ ውጤት ሊመጣ ይችል ነበር፡፡
በኮሚሽኑ  በቀረበው ሪፖርት ላይ “እዚህ ቦታ እርምጃው ተመጣጣኝ ነበር፤ አይደለም” የሚለው አገላለጽ ከፖለቲካ አቋም ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። ከፖለቲካ ስሜት የፀዳ ሪፖርት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የውጪዎቹም ቢሆኑ የራሳቸውን ፖለቲካ ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት ግን ሪፖርቱ ሳይሆን ሀገሪቷ እንዴት በጠንካራ መሰረት ላይ ትቁም የሚለው ነው፡፡
የፖለቲካ እርቅ፣ የፌደራሊዝሙ መጠናከር፣ የሀገሪቱ መረጋጋት ---- የሚፈጠርበትን ሁኔታ የሚያመቻች የመማሪያ እድል ይሆን ነበር፤ይሄ አጋጣሚ፡፡ ሆኖም ኮሚሽኑ በዚህ ደረጃ አይደለም ችግሩን ያጠናው፡፡ ፓርላማውም በዚህ ደረጃ ጉዳዩን እየተመለከተው አይደለም፡፡ እስካሁን ይሄን የሚያጠና ግለሰብም ሆነ ተቋም አለመኖሩ ለሀገሪቱ ብክነት ነው፡፡
ይሄ በጣም ይቆጫል፡፡ ምንድን ነው ብሄርተኝነትን ያባባሰው? እንዴት ነው ሀገራዊ አንድነት ማጠናከር የሚቻለው? ይሄን ለመመልከትና ለመፈተሽ የሚፈልግ ተቋም እስካሁን አላየሁም፡፡ በሪፖርቱ መቅረብ የነበረበት “የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ተመጣጣኝ አይደለም” የሚለው የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን አጠቃላይ ሲስተሙን የሚፈትሽ ሪፖርት ነው መሆን የነበረበት፡፡

---------------------------------------------------------------

                          ‹‹ኮሚሽኑ ከተሰጠው ስልጣን በላይ ነው የተንቀሳቀሰው››
                       ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ)

       የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ስልጣንና ተግባሩን የሚወስነው አንቀፅ 6 ላይ በዋናነት የተቀመጠው፣ ህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ ሠብአዊ መብቶች፣ በማንኛውም  አካል በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካሎች መከበራቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ስልጣኑና ተግባሩ አንፃር የሰሞኑን ሪፖርት ብንመለከተው፣ በሪፖርቱ መሠረት የ669 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በተመሣሣይ 1018 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ይሄን ሪፖርት ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አንፃር ስንመለከተው፣ አንቀፅ 15፤ ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው ይላል። በኮሚሽኑ ሪፖርት መሠረት ደግሞ 669 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በህይወት የመኖር መብታቸውን አጥተዋል፡፡ አንቀፅ 16 ደግሞ ስለ አካል ደህንነት ይገልፃል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት፣ 1018 ሰዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ አንቀፅ 17 ደግሞ በነፃነት ስለ መኖር ይደነግጋል፡፡ በኮሚሽኑ ሪፖርት መሰረት ደግሞ ብዙ ሰዎች ተፈናቅለዋል። እነዚህን ሰዎች በነፃነት የመኖር መብታቸውን አጥተዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች አሉ። እኔን ጨምሮ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ዜጎች፣ ለ2 ወራት ታስረን ቆይተናል፡፡ በቆይታችን ድብደባና የስቃይን ምርመራን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅሞብናል፤ ይሄ ደግሞ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 19፣ ስለተያዙ ሰዎች መብት የደነገገውን ይጥሣል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ፤ ”የኢሬቻ በአል መከበር አልነበረበትም፤ ችግር ሊፈጠር መሆኑን ሲያውቁ ማቋረጥ ነበረባቸው” ይላል፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 27፣ ማንኛውም ሰው ሃይማኖቱን ማክበር እንደሚችል ይደነግጋል፤ መከበር አልነበረበትም ማለት ራሱ የእምነቱ ተከታዮችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው፡፡
በሌላ በኩል በየትኛውም ደረጃ በፍ/ቤት እየታየ ያለ ጉዳይን ኮሚሽኑ የማየት ስልጣን የለውም፡፡ ከዚህ አንፃር የኦፌኮ፣ የOMN ሚዲያን ----- በሪፖርቱ ተጠያቂ ማድረጉ፣ የኮሚሽኑን ስልጣን የሚወስነውን የማቋቋሚያ አዋጁን ድንጋጌ ይጥሳል፤ስለዚህ ከተሰጠው ስልጣን በላይ ነው ሌሎችን ተጠያቂ እያደረገ ያለው ማለት ነው፡፡
በሃገሪቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማጋለጥ ሲኖርበት፣ እሱ ግን የመንግስትን ድርጊት አግባብነት ወደ ማረጋገጥ ነው የተሸጋገረው፡፡ በፀጥታ ሃይሎች የተወሰደውን እርምጃ ወደ ማረጋገጥ ነው የገባው፡፡ ይሄ ደግሞ ከስልጣንና ተግባሩ ውጪ መንቀሳቀሱን ያሳያል፡፡ መንግስትን ከማረም ይልቅ በህግ የተሰጠውን የስልጣን ገደብ ጥሶ፣ ሌሎችን ተጠያቂ ማድረጉ ራሱ የህግ ጥሰት ነው፡፡ “የኢሬቻ በአል መከበር አልነበረበትም” ሲልም ራሱን ችሎ የሠብአዊ መብት ጥሠት እየፈፀመ ነው፡፡ ይሄ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ገለልተኝነቱ አጠራጣሪ የሚሆነውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ መንግስትን ተጠያቂ ማድረግ አይፈልግም፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብ የተፈፀሙ ጥሰቶችን አውቆ፣ በመንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ አያደርግም፤ ስለዚህ ነው መንግስትም የወጪ ድርጅቶች ጉዳዩን እንዳያጣሩት የሚፈልገው፡፡ እንኳን የውጪ ድርጅቶች ይሄም ተቋም በትክክል እንዲያጣራ መንግስት አይፈልግም፡፡ ነገር ግን በውጪም ሆነ በሃገር ውስጥ ተቋማት ጉዳዩ ተጣርቶ፣ እውነታው ቢታወቅ ጥሩ ነው። የህግ ጥሰት እርማቶችን ለማድረግ ከተፈለገ፣ ገለልተኛ ተቋም ጉዳዩን ማጣራት አለበት፡፡
የ63 ፖሊሶች መሞት የሠብአዊ መብት ጥሰት ነው፤ ሲቪሎች መሞታቸውም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፤ ኮሚሽኑ ይሄን በእኩል ደረጃ መግለፅ ነበረበት፡፡ ግን “እዚህ ቦታ የተወሰደው ተመጣጣኝ እርምጃ ነው፤ እዚህ ደግሞ ያልተመጣጠነ ነው” የሚል ሪፖርት ነው ያቀረበው፡፡ ይሄን የመወሰን ስልጣን ፈፅሞ የለውም። ስለ ተመጣጣኝነት የመመስከር መብት የለውም። የደረሰን ጉዳት ብቻ ነው አጥርቶ ማቅረብ የነበረበት፡፡ የችግሩ መነሻ? ማን ፈፀመው? የሚሉትን ነው ዘርዝሮ ማቅረብ ያለበት። ከዚያ የሚወሰደው እርምጃ የመንግስት ድርሻ ነው የሚሆነው፡፡ ተመጣጣኝ እርምጃ ተወስዷል ሲል፣ ተጠያቂ የሚሆን አካል የለም ማለቱ ነው? ይሄ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡

Read 1149 times