Sunday, 30 April 2017 00:00

ዓፄ ናዖድ፤ ደራሲውና ባለቅኔው ንጉሥ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

    ዓፄ ናዖድ የዓፄ በእደ ማርያም ልጅ፤የዓፄ እስክንድር ወንድም (በእናት አይገናኙም) የዓፄ ልብነ ድንግል አባት ናቸው፡፡ እናታቸው የዓፄ በእደ ማርያም ሦስተኛ ሚስት የነበሩት ግራ ባልቲሓት (የግራዋ እመቤት) ሬሽ ገዜት  (ራስ ገዚት) ናቸው። ራስ ገዚት  የለባሽ በተባለው ቦታ በመጀመሪያ የወለዱት ቴዎድሮስ የተባሉትን፤ ቀጥለው ደግሞ ናዖድን ነው፡፡ ናዖድ በወንድማቸው በዓፄ እስክንድር ዘመነ መንግሥት በአገዛዙ ላይ እንዳይሸፍቱና እንዳያውኩ ስለተሠጋ በነበረው ልማድ መሠረት የነገሥታት ልጆች ወደሚታሠሩበት አምባ ግሸን ወይንም አምባ ነገሥት ተግዘው፣ በዘበኛ እየተጠበቁ በዚያው ይኖሩ ነበር፡፡
አጋጣሚውም መልካም  ሆነላቸውና በአምባ ግሸን ተራራ ላይ ዜማ፤ ቅኔ፤ ብሉያትንና ሐዲሳትን ለመማር ችለዋል፡፡ ከሊቅነታቸውም የተነሣ የልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትና የቅኔ ደራሲ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ልክ እንደ ዓፄ  ናዖድ  ሁሉ በእንደዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ  ተጠቅመው ብዙ ነገሥታት ሊቅነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ሊቅነታቸውን ከአስመሰከሩት ሊቃውንት ውስጥ የዓፄ  ናዖድ አያት  ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብ፤ አባታቸው ዓፄ በእደ ማርያም (አምባ ግሸን ሳይገቡ ቅኔ የተማሩ)፤ ወንድማቸው ዓፄ እስክንድር (አምባ ግሸን  ለጥበቃ ሳይላኩ በደቀ እስጢፋ አማካይነት) ባለቅኔ የሆኑ፤ ቀዳማዊ ዓፄ ተክለ ሃይማኖት ፤ዳግማዊ ዓፄ ዮሐንስ፤ ፈጻሜ ነገሥት ተክለ ጊዮርጊስ ለአብነ ያህል  ተጠቃሾች ናቸው፡፡   
ታዋቂው ጸሐፌ ታሪክ  አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ (የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ይኵኖ አምላክ እስከ ዓፄ ልብነ ድንግል፤ 1951፤ 252) እንደሚነግሩን፤ መጽሐፍ ተምረው፤ ቅኔ ተቀኝተው፤ ድርሰት ደርሰው የምናገኛቸው ነገሥታት በአባቶቻቸው፤ በወንድሞቻቸው፤ በቅርብ ዘመዶቻቸው ዘመነ መንግሥት አገር እንዳያውኩ  እየተባለ በአምባ ግሸንንና (ወሎ) በኋላም በወኅኒ አምባ (ጎንደር) በግዞት መልክ ለረጅም ጊዜ ሲቀመጡ የመማሪያ ሰዓት እያገኙ፤ ከነገሡ በኋላ ደግሞ  የተማሩትን እየሠሩበት ስለተገኙ ነው፡፡
በመጨረሻም ወንድማቸው የዓፄ እስክንድር ዘመን ሲያልፍ፤ ከአደጉበትና ከሚወድዱት  ከአምባ ግሸን ማርያም  ወርደው፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑት ዓፄ ናዖድ በአምባ ግሸን በነበሩበት ዘመን የሀገራችንን መንፈሳዊ ትምህርት በየደረጃው ስለተማሩ ታሪከ ነገሥት መልክዐ ማርያምን የደረሱ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
ይኽ መልክዐ ማርያም በመላ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ውስጥ በየዕለቱና በየበዓላቱ ቀን ለካህናቱ በነፍስ ወከፍ እየታደለ የሚደገምና ምዕመናኑ የሚጸልዩበት የጸሎት መጽሐፍ ነው። የመልክዐ ይዘት እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከእግር ጥፍርዋ እስከ ራስ ጸጉርዋ ያላትን የሰውነት ክፍል በግእዝ ግጥም ከብሉያትና ከሐዲሳት  ታሪክ ጋር በተገናዘበ መልኩ  የሚያሞግስና የሚያመሰግን መንፈሳዊ  ድርሰት ነው፡፡
ይኸም ሰላም ለዝክረ ስምኪ ሐዋዝ ከሚለው ጀምሮ ለዘኢያፈቅረኪ እግዝእትየ ድረስ በቁጥር 63 ነው፡፡ እያንዳንዱ የምስጋና ግጥም አምስት ቤት አለው፡፡ ለምሳሌ
“ ሰላም ሰላም ለዝክረ ስምኪ ሐዋዝ፡፡
እምነ ከልበኔ ወቁስጥ ወእምነ ሰንበልት ምዑዝ።
ማርያም ድንግል ለባሲተ ዓቢይ ትእዛዝ፡፡
ይስቅየኒ ለለጽባሑ ወይነ ፍቅርኪ አዚዝ፡፡
ከመ ይሰቅዮ ውኂዝ ለሠናይ አርዝ፡፡”
ሲተረጎም፡- እመቤታችን ማርያም ሆይ  እጅግ ለሚያምረው የስም አጠራርሽ ሰላም ይሁን፡፡ (ሰላምታ ይገባሻል) ከልበኔና ቁስጥ፤ ሰንበልትም ከሚባሉ የሽቶ ዓይነቶች  ስምሽ የተወደደ መዓዛ አለውና፡፡ ድንግል ሆይ፤ ከፈጣሪ ዘንድ ታላቅ ክብርን የተጎናጸፍሽ ነሽ፡፡ መልካም ተክል በመስኖ ውኃ እንደሚለመልም የፍቅርሽ ወይን በየቀኑ ነፍሴን  ያጠጣው (ያርካው፤ ያለምልመው) የሚል ነው፡፡
ልክ እንደ አባታቸው ዓፄ በእደ ማርያም፣ እመቤታችንን ያፈቅሩ የነበሩት ዓፄ ናዖድ በዘመነ መንግሥታቸው ዜማ፤ ቅኔና ልዩ ልዩ መንፈሳውያን መጻሕፍት ሲማሩባት የነበረቺውን የግሸን ዐምባ ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ብዙ ደንጋይና እንጨት አሰባስበው ሥራ መጀመራቸው ለድንግል ማርያም የነበራቸውን የተለየ ፍቅርና እምነት ያሳየናል፡፡ ዓፄ ናዖድ ለእመቤታችን የነበራቸው ክብርና ፍቅር፤ እምነት መልክዕ በመድረስና ቤተ ክርስቲያን በመሥራት ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ በቁጥር 25 የሆኑ ልዩ ልዩ ቅኔዎችንም ተቀኝተውላታል፡፡
ቅኔ በባሕርዩ በቃል ተነግሮና ሳይመዘገብ እንዲሁ ባክኖ የሚቀር ከፍተኛው የፍልስፍና ክፍል ቢሆንም ዓፄ ናዖድ ከብሉይና  ከሐዲስ ኪዳን፤ ከውዳሴ ማርያም መጻሕፍት ጋር በተያያዘ መልኩ ቅኔ ተቀኝተው ለእመቤታችን ያቀረቡት በረከተ ቅኔ ተመዝግቦ የተገኘው እንግሊዝ አገር  ሎንዶን መጻሕፍት ቤት  በተለይ ስለ አባ ኖብ ገድል (ግብጻዊ መነኩሴ) በሚያትተው ክፍል ውስጥ ነው፡፡ አባ ኖብ
የተባሉት አባት የኖሩት በ4ኛው ምእት ላይ ሲሆን  ለክርስትና ሃይማኖት ሲሉ  ከኢ-አማንያን ጋር ብዙ የተዋጉና መሥዋዕት የሆኑ አባት ናቸው። መምህር አፈወርቅ ተክሌ (መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፡ 2005፤, 434) እንደጻፉት፤ ገድለ አባ ኖብን የደረሱት አባ ወልደ ክርስቶስ የተባሉ  አባት ናቸው፡፡
በዓፄ ናዖድ የተደረሱት 25 ቱም ቅኔዎች በአጠቃላይ በይዘት ደረጃ የሚያንጸባርቁት  የእመቤታችንን፤ የኢየሱስ ክርስቶስን፤ የቅዱስ ሚካኤልን፤ የቅዱስ ገብርኤልንና የነቢያትን፤  የጻድቃንና ሰማዕታትን ክብር ነው፡፡ ከቅኔዎቻቸው ውስጥ  የሚከተለው ሥላሴ  ለአብነት ያህል ተጠቅሷል፡፡ ቅኔውን የደረሱትም የእመቤታችን የልደት ቀን በሆነው ግንቦት አንድ ቀን (የግንቦት ልደታ ነው፡፡)
በእርግጥ የቅኔያቱ ምሥጢርና መንገድ በኋለኛው ዘመን በጎንደርና በጎጃም፤ በሸዋ፤ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች እንደታየው በሰምና ወርቅ መንገድ እጅግ የረቀቀ  አይደለም፡፡ እንዲሁ ጽድቃጽድቅ ቅኔ  ነው፡፡ ቅኔዎችን  የተቀኙት ተጉለት  ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን  መጋቢት አንድ ቀን የእመቤታችን  በዓል ቀን ነው፡፡ ድርሰቶቹን ያበረከቱት በመንግሥት ሥራ ተጠምደው በነበረበት ጊዜ ስለሆነ በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል። ቅኔዎቻቸውም ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። ከሥራዎቻቸው ውስጥ አንድ ሥላሴ  በማሳያነት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሚ፡አዳም፡ ዘአዕይንትኪ፡ ርኅራኄ፡፡
እምስርቀተ (እምሥርቀተ ለማለት ነው) ፀሐይ፡ይበርህ፡ዘሥነ፡ ገጽኪ፡ሡራኄ፡፡
ወመላትሕኪ፡ ይጼኑ፡ እምርሔ፡፡
ለክብረ፡ ልደትኪ፡ ዮም፡ አቄርብ፡ ስባሔ፡፡  
በሰጊድ፡ ወበእማሔ፡፡
ምስለ እሊአየ፡ በውህዋሄ፡፡
ውዳሴኪ፡ እሰብክ፡ ኵለሄ፡፡ (ተክለ ጻድቅ፤ 1951፤ 298)
ትርጉም፡- ዓይንሽ እንዴት አስደሳችና ውብ ነው!  የተዋበው ፊትሽ ከፀሐይ ብርሃን ይልቅ የበለጠ ያንጸባርቃል፡፡ የጉንጭሽ መዓዛ ከሽቶ የበለጠ ይመስጣል፡፡ ዛሬ ለልደትሽ ቀን  ክብር እንዲሆን  በመስገድና እጅ በመንሳት፤ ልዕልና (ክብር) በመስጠት  ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
ምሥጢር፡- ከላይ የቀረበው ሥላሴ  የሚያመለክተው፣ ዓፄ ናዖድ ለቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ከፍተኛ እምነት ነው፡፡ ቅኔው የተመሠረተውም  መኀልየ መኀልይ ዘሰሎሞን ላይ (4፡3-4)   ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
ከመ፡ፍሕሶ፡ቀይሕ፡ከናፍርኪ፡ንባብኪ፡አዳም፡፡ከመ፡ቅርፍተ፡ሮማን፡መላትሕኪ፡እንበለ፡ አርምሞትኪ፡፡ ወከመ፡ ማሕፈደ፡ ዳዊት፡ ክሳድኪ።” መኃልየ፡ መኃልይ፡ ዘሰሎሞን፡4፡3-4፡፡
የአማርኛ ትርጉሙ፡- “ ከንፈሮችሽ  እንደ ሱፍ አበባና እንደ ሶሪ ላባ ቀያዮች ናቸው፡፡ ንግግርሽ እንደ ሮማን  ፍሬ ይጣፍጣል፡፡ ጉንጭሽ  ከእርጋታሽ ጋር ያስደምማል፡፡ አንገትሽ  እንደ ዳዊት ሰገነት  የረዘመ ነው፡፡ ” የሚል ነው፡፡
በመሆኑም ቅኔዎቹ  ከአንድ ዘመን ወደሌላው ዘመን በሚሸጋገሩበት ወቅት የፊደላትና የቤት አመታት (በመጨመርና በመቀነስ) ችግር ቢኖርባቸውም የጥንቱ ዘመን የአቀኛኘት ስልት፤ የቋንቋውና የሰዋስው ሥርዓቱ፤ የቅኔ አደራደሩና ምሥጢሩ ከአሁን ጊዜው የቅኔ ስልት ጋር ሲነጻጸር  ምን እንደሚመስል ለማመዛዘን ይረዳል፡፡ ዓፄ ናዖድ ለ23 ዓመት ያህል ገዝተው  ያረፉት ነሐሴ 7 ቀን በ1500 ዓ፡ ም ነው፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ በዙፋናቸው የተቀመጡት ልጃቸው ዓፄ ልብነ ድንግል ናቸው፡፡

Read 4888 times