Sunday, 30 April 2017 00:00

ወዳጄ አሰፋ ጫቦ እና እኔ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

ዛሬ ስለ አሰፋ ጫቦ መሞት ሐዘን ላይ ነን!
አሰፋ ጨቦ የጨንቻ ሰው መሆኑን በአካል አግኝቼ ያወኩት ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት ውስጥ ከታሰርኩ በኋላ ነው - በ1971 ዓ.ም እኔ ከደርግ ጽ/ቤት ተዛውሬ (ተመርቄ) ስመጣ … ታላቅ ዕድል ነው ልበል፡፡ ይሄ ጉዳይ ለአዘቦት ሟች (Average Mortal) ብዙ አይገባም ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደ ስቃዩ ሳይሆን በመንግሥት አካብዴ መዋቅር፡-
1ኛ) - ደርግ ጽሕፈት ቤት
2ኛ) - ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት
3ኛ) - የፖሊስ ጣቢያዎች
4ኛ) - የከፍተኛ እሥር ቤቶች
5ኛ)  - የቀበሌ እሥር ቤቶች
6ኛ) - የግለሰብ ቤቶች ናቸው፡፡
ቅደም ተከተል ማረፊያ ቤቶች ናቸው፡፡
አንዳንዴ ይዘበራረቃሉ እንጂ ዋና ማጎሪያ የሚባሉት የቀበሌ እሥር ቤቶች ናቸው፡፡
አሰፋ ጫቦ ውጪ ሆኜ እንደሰማሁት፤ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) መሥራችና መሪ ነበር፡፡ በአካል ግን ያገኘሁት ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት ነው፡፡ እሱ ሰባት ቁጥር የግል እሥር ክፍል (Solitary Confinement) ሆኖ ነው፡፡ ያኔ ሰባት ቁጥር ውስጥ የነበሩት የኢህአፓ አመራር ቡድን አካል የነበረው ፍቅሬ ዘርጋው፣ የኦኤልኤፍ አመራር አባል የነበረው መኮንን ገላን፣ የኢህአፓ መሪና መስራች የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ የአርሲው ፈረቀሳ አማኞች ዋና ኃላፊ በመባል የሚታወቁት ቀኛዝማች ታየ፣ በሲአይኤ ኤጀንትነት ተጠርጥሮ ታሥሮ የነበረው ዶ/ር ካሳሁን መከተ፣ የቤተ መንግስት መሀንዲስ ነበር የተባለ፣ ደስታ የተባለው አቶ ጥላሁን፣ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ክፍል የቆየ ወዘተ … ብዙዎች አደገኛ እስረኞች ተብለው እዚሁ ሰባት ቁጥር ታስረው ነበር። ከነዚህ መካከል፤ ፍቅሬ ዘርጋው ተገድሏል፡፡ መኮንን ገላን ቆይቶ ተፈትቷል፡፡ የኢህአፓው ብርሃነ መስቀል ተገድሏል፡፡ የአርሲው ፈረቀሳ ዋና ኃላፊ ቀኛዝማች ታየ ተገድለዋል፡፡ ሲአይ ኤ ነው ተብሎ የተጠረጠረው ዶ/ር ካሳሁን ተገድሏል!  የቤተ መንግስቱ መሀንዲስ አቶ ጥላሁን ተፈቷል፡፡ ደስታ ተስፋዬ በትግራይ ጉዳይ ታሥሮ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ተለቆ፣ ታሞ ሞቷል፡፡
አሰፋ ጫቦ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ታሥሮ፣ ከጊዜ በኋላ በተለምዶ ላይ ግቢ በሚባለው እሥር ቤት ተዛውሮ፣ እዚያው ከ10 ዓመት በላይ ቆይቶ በኋላ ተፈታ፡፡
ማዕከላዊ በነበረ ጊዜ ከእነ አሰፋ የግል እሥር ቤት - 7 ቁጥር ፊት ለፊት ነው፤ የእኔ ክፍል ያለው -  3 ቁጥር ነው፡፡ ፊት ለፊት በመሆናችን በቀን ተቀን እይታ የመገናኘት ዕድል ስለነበር ሀሳብ ለሀሳብ የምንግባባ ዓይነት ሆንን፡፡ በመጀመሪያ እንዳለ ልቀበለው ከብዶኝ ነበር፡፡ አንደኛ ኢጭአት ነው፡፡ ኢህአፓና ኢጭአት ይግባባሉ ብሎ መገመት መቼም የዋህነት ነው፡፡ እሥር ቤት ግን አንድ አስማት አለው፡፡ ቀስ በቀስ ሰውና ሰው እንጂ ድርጅትና ድርጅት መሆንን መርሳት ይመጣል፡፡ የዕለት - ሰርክ ውይይታችን፣ የግል አቋማችን፣ የፖለቲካ ብስለታችን የትምህርት ደረጃችን፣ የአዕምሮ ስፋታችንና ሆደ ሰፊነታችን ዋና ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከአሠፋ ጫቦ ጋር እንድንቀራረብ ያደረገን እናቱም አባቱም ይሄው ነው። የእኛ መቀራረብ ቅር ያላቸው እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም እሥር ቤት አመል ለአመል የሚስማሙበትና የሚቻቻሉበት ሥፍራ ነው፡፡ ወዳጄ አሰፋ ጫቦ፤ ወፍራም ድምፅ ስላለውና ጮክ ብሎ ስለሚያወራ ከበር ጥግ እስከ ሽንት ቤቱ ጥግ የሚሰማ ነው፡፡ ግልፅነትና የማን - አለብኝ አነጋገሩ፣ የጨንቻ ልጅነቱ ይሁን ራሱ ያዳበረው ማንነቱ እስከ ዛሬም እርግጠኛ ያልሆንኩበት ጉዳይ ነው፡፡ እርግጠኛ የሆንኩበት አንድ ነገር ግን፣ እሥር ቤትም ጮክ ብሎ ነው የሚያወራው፤ ውጪም ጮክ ብሎ ነው የሚያወራው፡፡ እንዲያውም አሜሪካ ሆኖ በፃፈልኝ አንድ ደብዳቤ፤
“እናቴን አንዴ እንዲህ ብዬ ጠየኳት፡፡ የሆነ ነገር ስናገር ሰው ይቀየመኛል፡፡ ለምን ይመስልሻል? ብዬ ብጠይቃት፤”
“ክፍት አፍ ስለሆንክ ነዋ” - አለችኝ - ብሎኛል፡፡
አሰፋ አስተያየት ሲሰጥ፣ ፍጥጥ ግልጥጥ ያለ ነው፡፡ በአዕምሮው ያጠራቀመው የረጅም ጊዜ የንባብ ዕውቀት ያለው ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ሌላ ሰው ለተናገረው ሀሳብ የሚለው ነገር አያጣም፡፡
አንድ ቀን ሁለታችንም ተፈተን፣ አዲስ አበባ ደጎል አደባባይ ተገናኘን፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ቡና ከጠጣን በኋላ፤
“ወዴት እየሄድክ ነው አሴ?” አልኩት፡፡
“እሥር ቤት እያለሁ መጥተው ያልጠየቁኝን የጥንት ወዳጆቼን እየዞርኩ ልጠይቃቸው አስቤያለሁ” አለኝ፡፡
“እንዴ አሴ … አሥራ አንድ ዓመት ያህል ታሥረህ ስትማቅቅ ያልጠየቁህን ሰዎች አሁን ማግኘት ምን ይጠቅምሃል?” አልኩት
“አይ ነቢይ! Why should I add more enemies. I had enough!” (በቂ ጠላቶች ነበሩኝ፡፡ ለምን አሁን አዲስ እጨምራለሁ!) አለኝ፡፡
አሰፋ ቀጠለና፤
“አንተስ ወዴት ትሄዳለህ?” አለኝ፡፡
“መጽሐፍ ሲራክ የዱሮ የእሥር ቤት ጓደኛዬ፣ ቢራ ልጋብዝህ ብሎ ፓርላማ ፊት ለፊት ካለው የዓርበኞች ማህበር ነው የቀጠረኝ”
“ምን ገንዘብ አግኝቶ ነው የሚጋብዝህ?”
“ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ለረዥም ጊዜ ስለ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያኖናትና ገዳማት ፕሮግራም ያቀርብ ነበር፡፡ አሁን ክፍያው ደረሰለት መሰለኝ፡፡ እንዲያውም እሱ ራሱ በቃሉ፤ “እስቲ በዚህ በዚህ እንኳን ትንሽ እንተንፍስ ብዬ ነው፤” ነው ያለኝ!”
ይሄኔ አሰፋ እንደ መሳቅ አለና፤
‹አሃ! መጽሐፈ ደግሞ ምን ነካው? ወደ ኋላ ነው እንዴ የሚተነፍሰው?!›› አለ
(ይቀጥላል)
ወዳጄ አሴ ሆይ!
አፈር ሳትቀምስ፣ አንድ ዕውነት ልንገርህ
ዕንባ ቢቀድመኝም፣ ብዕሬን ልችርህ፡-
አልሞት ብለህ ከርመህ
ሰው መኖር ያለውን፣ አንተ ክደህ ርቀህ
በብዕርህ ጉልበት፣ ቆየህ ነብስ ዘርተህ
ያነበበህ ያውቃል፣ የገባው የልብህ!
መቼም አልቀረና፣ ላንተ ይሁን ያለው
በዕለቱ ሆነ እሄው፤ በድንገት ሆነ ዕጣው
ያለቀንህ መሞት፣ ተፅፏል ማለት ነው!
የምትወደው አፈር፣ በቀኑ ሊያቅፍህ ነው
አገር ሰፊኮ ነው፣ አዋቂውን ያቃል
እንደራስህ ክብደት፣ ፀንቶ ይይዝሃል!
በል እረፍ እንግዲህ፣ እረፍትም ያሻሃል!!
ተለያይተን ኖረን፣ ስደት አራርቆን
ይኼው ሞት አይሞቴ፣
አንድያውን ለየን!
(ሚያዚያ 19 2009 ከአሴ ጋር በድንገት ለመለያየታችን)
(ይቀጥላል)

Read 5487 times