Sunday, 30 April 2017 00:00

“ምንም አይል…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሙዚቃ ኦልዲስ አሉ አይደል…የሀሳቦች ኦልዲስስ ልክ ነዋ…ሲከፋን ‘ሪዋይንድ’ እናደርጋለና፡፡ ትናንት እንጠላው የነበረውን ነገር ሁሉ “ቢያንስ ያኔ አይተናል” ወይንም  “እባክህ እንትን ያላልንበት ዳገት የለም…” እንባባላለን፡፡
ምን እናድርግ!.. የሚያስከፋው ነገር እየበዛብን ሲሄድ ምን እናድርግ፡፡
“እሷን ስረግም ኖሬ ጭራሽ በገዛ እጄ ባለጭራና ቀንዷ ትምጣብኝ!”   
“ለካስ ሰው ካልሄደ አይታወቅም!” ምናምን የምንለው እኮ የሚያስከፉ ነገሮች ሲበዙብን ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…
“ኑሮ እንዴት ነው?” ስንባል…
“ምንም አይል…” እንላለን፡፡
“ምንም አይል ማለት ምን ማለት ነው?”
“ምንም አይል ማለት ነዋ!”
እናማ… “ምንም አይል…” የምትሰጠው ‘አገልግሎት’ ልክ የካርታዋ ‘ጆከር’ የምትሰጠውን አይነት ነው፡፡ እናላችሁ…
“ምንም አይል…” ስንል
“ባልጠጣሁት ቅቤ፣ ባልበላሁት ጮማ ለምን ብዬ  ‘አሪፍ ነው’ እላለሁ!    “ለማን ይድላው ብዬ ነው ቸገረኝ የምለው!…” ይባልና ስለ ኑሮ ስንጠየቅ “ምንም አይል…” እንላለን።
የምር እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምንም ነገር ለውጥ አላሳይ ሲላችሁ፣ ነገሮች ካቻምናም፣ አምናም፣ ዘንድሮም ያው ሲሆንባችሁ ግራ ይገባችኋል፡፡
ስሙኝማ፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘በስህተት’ ሊሆን በሚችል ቲቪ ዜና ታያላችሁ፡፡ የሆነ ስብሰባ ወሬ ለሠላሳ ሴኮንድ ያህል ታያላችሁ፡፡ ታዲያ…አለ አይደል… “ይሄን ዜና ልክ የዛሬ ስምንት ዓመት አላየሁትም እንዴ?” ትላላችሁ፡፡ ምን ይደረግ! ወሬው ያው፣ የተለጠፈው መፈክር ያው፣ ቋንቋው ያው!
“የእንትን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታወቁ፡፡” እንዴት ነው ነገሩ…የዚሁ መሥሪያ ቤት ሰዎች፣ ያኔ ገና ቡሽ ፕሬዝደንት እያሉ እንዲሁ ‘የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ቆርጠው’ ተነስተው አልነበር እንዴ! በስህተት የተደገመ ፊልም ነው እንዳንል…ጠረዼዛው ላይ ያለው ውሀ የቅርብ ምርት ነው፡፡
እናላችሁ… ልክ እንደ ‘ቦተሊካው’ ሁሉ፣ በየመሥሪያ ቤት ስብሰባ ላይ የሚናገሩት ሰዎች ሁሉ ኩንታል ጤፍ ሁለት መቶ ብር የነበረ ጊዜ የሚናገሩት እነኛው ሰዎች ይመስሏችኋል፡፡
“እሳቸው ያሉት ላይ ምንም የምጨምረው የለም…” ብሎ ለሠላሳ ሰባት ደቂቃ፣ ሠላሳ ሴከንድ ያወራው ሰውዬ፤ የዛሬ ስንት ዓመት እንዲሁ ሲል አልነበረም እንዴ! “እሳቸው ባሉት ላይ የምጨምረው የለም…” ያለውን ብዛት ቢቆጥር የሜሲን አምስት መቶ ሁለት የላ ሊጋ ጎሎች ብዛት ባያጥፍ ነው!
እናማ… “ምንም አይል…” ስንል ብዙ ነገሮች ግራ እየገቡንም ነው፡፡
የምር እኮ… “አሁን ቲማቲምም ምግብ ሆነችና በእሷም ድሀና ሀብታም ይለያሉ! ቼ ጉቬራ እኮ የፊልም ተዋናይ ከመሆን ይልቅ አብዮተኛ የሆነው እንዲሁ በደል ሲበዛበት ነው፣” እያለ መንደሩን ሲያምስ የነበረው… አለ አይደል… የሆነ ስብሰባ ላይ፣ “በእውነቱ ዋጋ ለማረጋጋት የተደረገው እንቅስቃሴ አስደሳች ነው፣ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት…” ምናምን ይላል፡፡  እንዴት ነው ነገሩ! የቼ ጉቬራ ጉዳይስ! (እኔ የምለው… የቼን ፎቶ በየመኪናቸው ላይ የሚለጥፉት ሰዎች፣ ራምቦ ምናምን እየመለሳቸው ነው እንዴ  ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…ለቴሌቪዥኑን ካሜራ ብቻ ሳይሆን ድንገት ቤት በጊዜ ገበተው (ቂ…ቂ…ቂ…) ዜና ለሚያዩት ለ‘ከባድ ሚዛኖቹ’… አለ አይደል… “አትርሱኝ፣ እዚህ ነኝ…” ለማለት የሚባሉት ነገሮች ስንት ጊዜ እንደሰማችኋቸው መቁጠር እንኳን ያቅታችኋል፡፡
“በእርግጥ የቲማቲሙ ዋጋ የጨመረ ቢሆንም የእድገት ምልክት ስለሆነ የሚያስደስት ነው ምናምን ነው…” ይላል፡፡
እናማ… “ምንም አይል…” ስንል ብዙ ነገሮች ግራ እየገቡንም ነው፡፡
ግራ ግብት ነው የሚለው፡፡ እንዴት ከዓመት ዓመት፣ እንዲሁ አንበሳ ሲሉት ጎፈር፣ ጎፈር ሲሉት አንበሳ እየሆነ የሚኖረው፣ ያሰኛችኋል፡፡
“ይቺን ከተማ እኮ መለማመጃ አደረጓትና አረፉት፣ ዶማ የያዘ ሁሉ የህንጻ ባለሙያ እየሆነ…“የሳጥን የሳጥን እኛስ እንሠራው አልነበር..” ምናምን ሲል ይቆያል፡፡ ከዛማ በሆነ በፈረደበት አንድ ስብሰባ ላይ ይገኛል፡፡ መድረክ መሪው ገና ተናግሮ ሳይጨርስ እጁን አሥር ጊዜ ያውለበልባል፡፡ የመናገር ዕድል ሲሰጠው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“በእውነቱ በጣም ደስ የሚል እንቅስቃሴ እየታየ ነው…! ይቺ ከተማ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ኒው ዮርክ እንደምትሆን ሳይታለም የተፈታ ነው…”
(ስሙኝማ፣ እግረ መንገዴን…ኮሚኩ ነገር ስንትና ስንት የሚጠቀሱ የአፍሪካ ከተሞች እያሉ ዘለን አሜሪካና አውሮፓ የሚወስደን ግራ  የሚገባ ነገር ነው፡፡)
እናላችሁ… “ኑሮ እንዴት ነው?” ስንባል… “ምንም አይል…” የምንለው ብዙ ነገር ግራ እየገባን ነው፡፡
ከዛ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ከሁሉ ቀድሞ ‘ሀሳብ ለመስጠት’ እጅ የሚያወጣው ያው ሰው ነው፡፡
“በእውነቱ አዲሱ ሥራ አስኪያጃችን ከመጡ በኋላ የድርጅቱ እንቅስቃሴ በጣም የሚያስደስት ነው…” ምናምን ይላል፡፡
እናማ… “ኑሮ እንዴት ነው?” ስንባል…
“ምንም አይል…” ስንል ብዙ ነገር ማለታችን ነው፡፡
‘አብሮ መኖር’ ችግር እየሆነብን ነው እያልን ነው!  
‘የአገሬ ልጅ’ እየተባለ መሳሳብ በዛ፣ እያልን ነው።
‘በማናውቀው መለኪያ… እንጀራ ልጆች የምንሆንባቸው ጊዜዎች እየበዙብን ነው’ እያልን ነው፡፡
‘የእኔ እምነት ተከታይ’ እየተባለ መሳሳብና መጠቃቀም በዛ እያልን ነው፡፡
አንተ እኮ እንትን ብትሆን ያልፍልህ ነበር አይነት
እኔ ስንተኛ ዜጋ መሆኔ ነው እያልን ነው፡፡
ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ
እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሰራ
የሚለው የአብሮ መኖር መለኪያዎች የአገር ልጅነት፣ የተመሳሳይ እምነት ተከታይነት ምናምን ያላበላሸው ዜማ እየቀረ ሲሄድ ስጋት ገብቶናል እያልን ነው፡፡
እኔ የምለው…የአብሮ መኖር ነገር ከተነሳ፣ ግብጾች ልባቸው እስኪጠፋ ‘ወደዱንሳ!’ ቢወዱን ነው እንጂ ታዲያ… “ስዞረው አደርኩት የግቢሽን አጥር..”. ምናምን አይነት ዜማ በዛብና! ቆይቶ ብቻ ፍቅሩ ቀርቶ… ነገርዬው፣ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ…” እንዳይመስልብን፡፡
እናላችሁ…የሆነ መሥሪያ ቤት አዲስ አለቃ ይመጣል፡፡ ሰውየው ገና ወንበሩ ላይ ቁጭ ከማለቱ የመሥሪያ ቤቱን ሠራተኛ በሆነ ባልሆነው ማስጠንቀቂያ፣ በማስጠንቀቂያ ያደርገዋል፡፡
“ይገርምሀል…የሆነ የሉሲፈር አበልጅ የሆነ አለቃ መጥቶብን መግቢያ፣ መውጫ አሳጠን!”
“ምን አደረገ?”
“ምን ያላደረገው ነገር አለ! የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ያልተጻፈበት ሰው የለም፡፡ በትንሽ በትልቁ ደብዳቤ እየጻፈ መፈረም ነው…ለእሱ ለራሱ እኮ ማስጠንቀቂያ ይጻፍለት ቢባል ውቅያኖስ ቀለም፣ ሰማይ ብራና ቢሆን አይበቃውም፡፡
እናማ… “ኑሮ እንዴት ነው?” ስንባል… “ምንም አይል…” ስንል ብዙ ነገር እያልን እንደሆነ ልብ ይባልልንማ! በቤታችን፣ በመሥሪያ ቤታችን፣ በማህበራዊ ግንኙነታችን የሚያስከፉን ነገሮች በዝተውብናል ማለታችን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2663 times