Print this page
Wednesday, 04 April 2012 08:57

የታላቁ ህዳሴ ግድብና የባለስልጣናቱ ቡድን ልምምድ

Written by  ግሩም ሰይፉ እና ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(0 votes)

“የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን ይገነባል” በሚል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ የተጀመረበትን አንደኛ አመት ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዝግጅቶቹ አንዱ በመንግስት ባለስልጣኖች እና በዲፕሎማቶች መካከል ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ ነው፡፡ ባለስልጣኖቹ ወደቡድኑ ከመቀላቀላቸው በፊት የጤና ምርመራ አድርገዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የመንግስት ባለስልጣኖች ለነገው ጨዋታ ልምምድ በሚያደርጉበት ሜዳ ተገኝተን ነበር፡፡

የቡድኑ አሰልጣኝ አቶ አጥናፉ አባተ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ስኮትላንዳዊ ኤፌም ኦኑራና እና የቤልጂየሙ ቶም ሴንት ፌይት ረዳት አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ የባለስልጣናት ቡድኑ ልምምድ ያደረገው ከአዲስ አበባ ስታዲዬም አጠገብ በሚገኘው ዘመናዊ የአትሌቲክስ መለማመጃ ሜዳና ትራክ ላይ ነው፡፡ አሰልጣኝ አጥናፉ አባተ በሰጡት አስተያየት “በኢትዮጵያ እንኳን ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ታላላቅ ስታድዬሞችም እንደሚገነቡ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለውናል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ፈንቴና የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ ወደ ልምምድ ሜዳው ቀድመው የገቡ የቡድኑ ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ የስፖርት ኮሚሽነሩ አብዲሳ ያደታና የኤነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑም በሰዓታቸው ተገኝተዋል፡፡ አሰልጣኙ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚሰጥ ከባድ ልምምድ ሲያሰሯቸው የነበረ ሲሆን በቦታው ተገኝተን እንደተመለከትነው “በቃኝ” ብሎ ያቋረጠ አንድም ባለስልጣን አልነበረም፡፡

“ቀለሜዋ ስለነበርኩ ወደ ስፖርት ብዙ አልቀረብኩም”

ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ - የማዕድን ሚ/ር

የመንግስት ሃላፊዎች ቡድን የስነልቦና አማካሪና በሞራል ድጋፍ ሰጪ ሆኜ እሳተፋለሁ፡፡ ሥራዬ በርቱ ማለት ነው - ለቡድኑ አባላት “እኛ የመንግስት ባለስልጣናት በከፍተኛ የስራ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን በእንዲህ አይነት መድረክም መስራት እንችላለን፣ ዋናው ነገር ልምምዱ ነው፤ ጊዜ ሰጥቶ መስራት ከተቻለ ውጤታማ እንሆናለን” ብያቸዋለሁ፡፡ ኳስ ተጫውቼ አላውቅም፡፡ ድሮ በትምህርት ቤት ቀለሜዋ ስለነበርኩ ስፖርቱ ላይ ብዙም አልሳተፍም ነበር፡፡ አንዳንዴ ቮሊቦል እጫወት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ገጣሚ ባለመሆኔ ለቡድኑ ማበረታቻ የሚሆን ግጥም አላዘጋጀሁም፡፡ ግን “እንበርታ ይቻላል” እያልኩ እደግፋቸዋለሁ፡፡

“ስሮጥ እንደበረሮ ነው”

ወይዘሮ ዘነቡ ታደሠ - የሴቶችና የህፃናት ሚ/ር

ስፖርት አስተማሪ አልነበርኩም ግን የስፖርት ፍላጎት አለኝ፡፡ ልጅ ሳለሁ በጣም እጫወት ነበር፡፡ በረኛ ነበርኩ፡፡ አሁን ለመሰረትነው ቡድንም በረኛ ነኝ፡፡ ለበረኛነት ቁመቴም የሰጠ ነው፡፡ ስሮጥም አይታችሁኛል እንደበረሮ ነው፡፡ መሃል አጥቂም ተከላካይም መሆን እችላለሁ፤ በአጠቃላይ ሁለገብ ነኝ፡፡ ለቡድኑ ድጋፍ መስጫ ግጥም አዘጋጅቻለሁ፡፡

ገበረ ለትውልድ እጅ ሰጠ ላገር

አፈር ተሸክሞ ድንበር ላይሻገር!

ሚሊዮኖች መዘዙ ቢሊዮን አዋጡ

ከቤት ሊያሳድሩት ሊያደርጉት በቅጡ!

የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበቱ

ይኸው ዛሬ ደግሞ ሊከበር ዓመቱ

አጀበ ልደቱን አመራሩ አርቲስቱ!!

ለድጋፍ የገጠሙት ግጥም

“ጐል ለማግባት ተስፋ አደርጋለሁ”

አቶ መላኩ ፈንቴ - የገቢዎች ሚኒስትር

ወደ ስፖርቱ የገባሁት ከረጅም አመታት በኋላ ነው፡፡ ከ15 ዓመት በኋላ ማለት ነው፡፡ በልጅነትና በትምህርት ቤት ኳስ ጨዋታ አዘወትር ነበር፡፡ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ ተውነው፡፡ በቡድናችን  በርከት ያሉ የቆየ ልምድ ያላቸው የሚመስሉ ኳስ ተጨዋቾች አሉ፡፡ አቶ ምህረት፤ አቶ ተፈራ እና አቶ ብርሃንን የኳስ አያያዝ ስመለከት፣ የድሮ ልምድ እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ ለማጥቃት እና ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ሳየው፣ በቡድናችን ጥንካሬ እንድተማመን አድርጎኛል፡፡ ድሮ ኳስ ስጫወት የምሰለፈው በተለይ በአጥቂ ቦታ ነበር፡፡ ዛሬ እንዳያችሁኝ ድሮ አልደክምም ነበር፡፡ በጣም ፈጣን ሯጭ ነበርኩ፡፡ ጎል ለማግባት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጎል ካገባሁ ለግድቡ በሰጠነው ክብር ያህል ደስታዬን ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡

“እሸነፋለሁ ተብሎ አይገባም”

አቶ ምህረት ደበበ - የኢትዮጵያ መብራት ሀይል ኮርፖሬሽን የስራ አስፈፃሚ

በወጣትነት ትምህርት ቤት ስንማር ህይወታችን እጅግ ከስፖርት ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ እግር ኳስ፤ አትሌቲክስ እና ቅርጫት ኳስ እናዘውትር ነበር፡፡ እኔ በተለይ የምወደውን እግር ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ስማር ከሲ ቡድን ተነስቼ ዋና ቡድን ደርሻለሁ፡፡ እግር ኳስን መጫወት ከትምህርት ጋር ትንሽ ሃሳብን ይሻማ ስለነበር፣ ቤተሰቦቼ ወደ ትምህርት እንዳዘነብል ተቆጥተው አስተውኝ፡፡ ሊሴ ገብረማርያም እና ከዚያም በዩኒቨርስቲም ኳስን እጫወት ነበር፡፡ በውጭ አገር ትምህርት ላይም በኮሌጆች ውድድር ተሳትፌያለሁ፡፡ አትሌቲክስ እና ጅምናስቲክ ዛሬም እስራለሁ፡፡ ሜዳ ቴኒስም እጫወታለሁ፡፡ ማየት አዘውትራለሁ፡፡ ሁሉም የቡድናችን አባላቶች የእግር ኳስ የጀርባ ታሪክ አላቸው፡፡

እኔ አማካይ በመሆኔ ብዙ ግብ  የማስቆጠር እድል ላይኖረኝ ይችላል፡፡ ግን ለቡድናችን ብዙ የግብ እድሎች ለመፍጠር አስባለሁ፡፡ ጎል እንዳይገባብንም እከላከላለሁ፡፡ የተቃራኒ ቡድን አቅም አይታወቅም፡፡ አምልጠህ ኳስ ማግኘት ከቻልክ ደግሞ ታገባለህ፡፡ እግር ኳስና ማኔጅመንት መጨረሻው ውጤት ማምጣት ነው፡፡ ጐል ማግባት ነው፡፡

በኳስ ዓለም አሸንፋለሁ ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ግን እሸነፋለሁ ተብሎም አይገባም፡፡ ስለዚህ ዋና አላማችን ለማሸነፍ ነው፡፡ ከተሸነፍንም በፀጋ መቀበል ነው፡፡ ቢቻል ደግሞ እኩል ለእኩል መውጣት ነው፡፡ ስለተጋጣሚያችን ያለውን ነገር አናውቅም፡፡ ምናልባትም በአካል  ብቃት የተሟሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

“ለህዳሴ ግድብ ያልሆነ ጉልበት…”

አቶ አለማየሁ ተገኑ - የውሀና ኢነርጂ ሚ/ር የቡድኑ አምበል

ያደረግነው ልምምድ ጥሩ ነው፡፡ እንዳያችሁት ሁለቱም የቡድናችን ተጫዋቾች በልምምዱ ላይ ሲሾሩ ትንፋሻቸውን ይዘው ሲጫወቱ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ያንድ ቡድን ትልቁ ሃብት ነው፡፡ የቡድናችን የልምምድ አሠራርና የሞራል ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፡፡ በሁሉም ተጨዋቾች የላቀ አቅም አለ፡፡ ሜዳ ከገባን በኋላ የቡድን ስሜቱ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደተመለከታችሁት የቡድናችን አባላት ለልምምዱ በሰዓቱ ነው የተገኙት፡፡ አንዱ ትልቁ ነገር ሰዓት አክባሪነት ነው፡፡ ይሄ “አፍሪካን ታይም” እየተባለ የሚነገረው ጊዜን አለማክበር እኛ ጋ  መቅረት አለበት፡፡ ትራንስፎርሜሽኑ ይህንንም ማሳሰብ አለበት፡፡ የኛ ቡድን ሰዓቱን ከማክበር አኳያ ዲስፕሊኑ የተሟላ ነው፡፡ በቡድናችን ጥሩ ስብስብ እተማመናለሁ፡፡ ወጣቶች አሉበት፤ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉም አሉ፣ ዕድሜያቸው የገፋም ይገኛሉ፡፡

ኳስ ድሮ ትንሽ ትንሽ እጫወት ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ባንድ ቡድን ውስጥ ገብቼም እጫወት ነበር፡፡ ያለኝን ትንፋሽና ጥሩ የመሮጥ አቅም ያዳበርኩት ከዚሁ ነው፡፡ ድሮ ትምህርት ቤቴ ከወላጆቼ  ቤት 30ኪ.ሜ ርቀት ነበረው፡፡ በትውልድ ስፍራዬ ጊምቢቾ የተባለ በሰሜን ሸዋ የሚገኝ ት/ቤት ስለነበር፣ ስሄድ በርምጃ ሳይሆን በሩጫም ነው፡፡ የት/ቤቱ ስም ጤቲ ደንሶ የተባለ ሲሆን ኳስ ተጫዋች ልሆንበት የሞከርኩበት ቡድን ደግም “አሞራ” ይባል ነበር፡፡ በቢሾፍቱ የሚገኝ ነው፡፡ ለአሁኑ የባለስልጣኖች ቡድን አምበል ሆኜ የተመረጥኩት በአጋጣሚ ነው፡፡ ስራን ከማስተባበር ጋር የተገናኘ በመሆኑ ቡድኑን በአምበልነት የመምራት ችግር አይኖርብኝም፡፡

አባይ ህዝባችንን ወደ አንድ አመለካከት ያመጣ ነው፡፡ ወንዙን የተደፋፈርንበት ወር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብን ሆ ብሎ የመነሳት መንፈስን የፈጠረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ነው፡፡ በእግር ኳስ ጉልበታችን አንድም ሳናስቀር የግድቡ ግንባታ መጀመር አንደኛ አመትን እናከብራለን፡፡ ለህዳሴ ግድብ ያልሆነ ጉልበት መኖር የለበትም ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ በአባይ ስም እግር ኳስን ለመጫወት ጉልበታችንን አሟጥጠን እንጠቀማለን፡፡

 

 

Read 2448 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 09:04