Sunday, 30 April 2017 00:00

የአሰፋ ጫቦ ብቸኛ ሴት ልጅ - ስለ አባቷ ትናገራለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “የሁልጊዜ ምኞቱ፣ እዚህ መጥቶ ከኛ ጋር መኖር ነበር”

     ለመሆኑ እመቤት ከአባቷ ጋር የነበራት ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? አሰፋ ጫቦ ምን ዓይነት አባት ነው? ከልጁ ጋር ምን ያወጋል? ስለ ጤንነቱ ሁኔታ ምን ነግሯታል? ህልሙና ዕቅዱ ምን ነበር? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ
አንበሴ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ እመቤት አሰፋን በስልክ አነጋግሯቷል፡፡

     ከአባትሽ ጋር የነበራችሁ ግንኙነት እንዴት ነበር? ላንቺ ምን ዓይነት አባት ነው?
አባቴ በየሄደበት ሁሉ የኔን ስም ያነሳል፤ ግንኙነታችን በጣም ጥብቅ ነው፡፡ እኔ የሌለኝን ሁሉ እያሞጋገሰ ለሚያውቃቸው ሲያስተዋውቀኝ ነው የኖረው፡፡ እንደ አባት፣ እንደ ጓደኛ፣ እንደ ወንድም፣ እንደ እናት … በቃ ምን ልበልህ፤ በጣም ጥብቅ ግንኙነት ነው የነበረን፡፡
መቼ ነበር ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተያያችሁት?
ልክ ከዚህ ሀገር ሲወጣ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አባቴን በአካል አግኝቼው አላውቅም፡፡ በአካል መገናኘቱ እየናፈቀን ነው በተስፋ የኖርነው፡፡
እሱ ወዳለበት ሀገር ለመሄድ አልሞከርሽም?
አንድ ጊዜ ወደ እሱ ጋ እንድሄድ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ከዚያ በኋላም የኛ ዕድሜ ከ21 ዓመት እያለፈ ሲሄድ፣ ሁሉን ነገር ትቶ በቃ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ፣ እኛን ስለማግኘት ነበር የሚጨነቀውና የሚያስበው፡፡ እኛ እዚያ እንድንሄድ ሳይሆን እሱ ወደዚህ መምጣትን ነበር ሁሌ የሚያስበው፡፡ አሴ ለራሱም ለቤተሰቡም አልኖረም፤አንዴ ሲታሰር፣  አንዴ ሲሰደድ ነው የኖረው፡፡ እዚያም ሆኖ ትግሉ ሁሉ ከመፅሐፍ ንባብ ጋር ነበር፡፡ ተሳክቶለት በህይወት ባይመጣም፣ የሁልጊዜ ምኞቱ፣ እዚህ መጥቶ ከኛ ጋር መኖር ነበር፡፡
በምን መንገድ ነበር ስትገናኙ የነበረው?
በስልክና በደብዳቤ ነበር የምንገናኘው። በየቀኑ ይደውል ነበር፡፡ አንዳንዴ በቀን ሁለት ጊዜ ይደውላል፡፡ ረዥም ሰአት ያወራናል፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ለትንሽ አመታት ውስጡ ጥሩ ስሜት ስላልነበረው፣ (በአጠቃላይ ከፅሁፍ በራቀበት ጊዜ) ትንሽ ግንኙነታችን አስቸጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ የመጀመሪያ ልጁ ኤፍሬም አሰፋ በመሞቱና በሌሎች ምክንያቶች ትንሽ ስሜቱ ተጎድቶ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ለደቂቃ ሊያጣን አይፈልግምና ማታም፣ ጠዋትም ሌሊትም ይደውልልኝ ነበር፡፡ በጣም ረጅምና ብዙ ነበር የሚያወራኝ፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ምን ነበር የሚያወራሽ?
በቃ ፍላጎቱ ሃገሩ መግባት ነበር፡፡ ስለ ሃገሩ፣ ስለ ቤተሰቡ እናወራ ነበር፡፡ ከቤተሰብም የበለጠ ስለናፈቁት ወዳጆቹና ህዝቡ ያወራኝ ነበር፡፡  
በህይወት ሳለ መፅሐፍ ስለማሳተም ይናገር ነበር። አንቺ የምታውቂው ነገር አለ?
‹‹የትዝታ ፈለግ›› መፅሐፍ ታትሞ የወጣ ጊዜ የነበረው ደስታ የተለየ ነበር፡፡ ሁለተኛ መፅሐፉንም ፅፎ ጨርሷል፡፡ “ለማሳተም ፅፌ ጨርሻለሁ፤ ከአሳታሚዎቹ ጋር ያለውን ነገር መጨረስ ብቻ ነው የሚቀረኝ” ብሎኝ ነበር፡፡ እንደውም አሳታሚዎችን ‹‹ቶሎ አናግሪያቸው፤ ምነው ዘገየሽብኝ›› ይለኝ ነበር። እኔም ‹‹ቆይ እሺ አናግራቸዋለሁ›› እለው ነበር፡፡ ይገርምሃል እሱ ግን ይጣደፍ ነበር፡፡ ሁለተኛ መፅሐፉ ታትሞ ለማየት በጣም ይጣደፍ ነበር፡፡ ‹‹አልቋል እኮ! ምን እየሰራሽ ነው?! ምን ሆንሽ እሙ! ፍጠኝ እንጂ!›› ይለኝ ነበር፡፡ እኔ እንዲህ ሲጣደፍ በጣም ይገርመኝ ነበር፡፡ ለምንድን ነው እንደዚህ የሚያጣድፈኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ከህልፈቱ በኋላ ለዚህ ይሆን እንዴ የሚያጣድፈኝ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡
የመጀመሪያው መፅሐፍ ሲታተም፣ እኔ ውስጤ እረክቶ ነበር፡፡ ለብዙ ዓመታት ዝም ብሎ ይፅፋቸው የነበሩ ስራዎች፤ ተሰብስበው መታተማቸው አርክቶኝ ነበር፡፡ እሱም ታትሞ ሲያየው እጅግ በጣም ነበር የተደሰተው፡፡ ይሄኛው ታትሞ ቢያየው ደግሞ ምንኛ መልካም ነበር፡፡ እንግዲህ ያለቀው ፅሁፍ ይኖራል፤ ያለውን ነገር በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
እናንተ መርዶውን እንዴት ነበር የሰማችሁት?
አሴ ሆስፒታል እስከገባባት የመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እኔ እከታተለው ነበር፡፡ ይደውልልኝ ነበር፡፡ ያመመኝ ጉንፋን ነው ነበር ያለኝ፡፡ በጣም እንደምጨነቅ ስለሚያውቅ፣ ‹‹እናቴ እንግዲህ እንዳትጨነቂብኝ፤ በጣም ደህና ነኝ፤ ጉንፋን ነው ያመመኝ፡፡” አለኝ፡፡ በህይወቱ ከጉንፋን በስተቀር ራሱን እንኳ አሞት አያውቅም፡፡ በጣም ጤነኛ ሰው ነው፡፡
ከዚያ አንድ ቀን፤ “መድሃኒት ወስጄ ምግብ አልረጋልህ አለኝ፡፡ ምንም መብላት አልቻልኩም›› ብሎ ነገረኝ፡፡ ከመሞቱ 5 ቀናት በፊት ድረስ በየቀኑ ነበር በስልክ የምንገናኘው፡፡ ስለ ህመሙ ደረጃ ይነግረኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ ቀን ሲደውል “ላይብረሪ ውስጥ ነኝ” ብሎ ነግሮኛል፡፡ በሚኖርበት ዳላስ ውስጥ የታወቀ ላይብረሪ አለ፤ እዚያ መሆኑን ነገሮኝ ነበር፡፡ በዚያ ላይብረሪ በጣም ደስተኛ ነበር። በቆይታው ሁሉ ስለ ላይብረሪው ያወራኛል፡፡ በወቅቱ “ላይብረሪ ውስጥ ነኝ” ሲለኝ ግን አምስት ቀን ሙሉ ምግብ አልበላሁም ያለኝው ትዝ ብሎኝ፤ ‹‹ባልበላ ሆድህ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?›› ብዬው ነበር … ‹‹አሴ እባክህን ዛሬ እንኳ ላይብረሪው ቢቀርብህ ምናለበት! ሄደህ ለምን ትንሽ አትተኛም›› አልኩት፡፡ በቃ የመጨረሻ ንግግራችን ይሄ ነበር፡፡
 ከዚያ በኋላ በማግስቱ አልደወለልኝም። ሳይደውልልኝ ሲቀር እኔ መደወል ጀመርኩ፡፡ ስደውልለት ስልኩ ጥሪ መቀበል አልቻለም፡፡ ለካ እሱ ሆስፒታል ገብቷል፡፡ እዚያ ያለች አንዲት ዘመዳችንን አፈላልገን ጠየቅናት፤ ሆስፒታል መግባቱን ነገረችን፡፡ ‹‹ማንም ቤተሰብ እንዳይሰማ፤ ለልጄ እንዳትነግሯት አደራ! ቤተሰብ እንዳይረበሽብኝ፤እኔ ጤነኛ ነኝ ምንም አላመመኝም›› ብሎ ለሷ ነግሯት ነበር። ሆኖም እሱን ማግኘት ስላልቻልን እንዳመመው ተረዳን፡፡ እኛም በየቀኑ ዘመዳችን ጋ እየደወልን፣ ሁኔታውን እንከታተል ነበር፡፡ “ስለሚደክመኝ ነው የማላናግራቸው” ይለን ነበር፡፡ በእንዲህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው ባለፈው እሁድ ሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ህይወቱ ያለፈው። መርዶው የተነገረው ለኛ ሳይሆን ለሚቀርቡን ቤተሰቦች ነበር፡፡ ታናሽ እህቱ ቫቲካን አካባቢ አለች፤ እዚያ ኑ ተባልን፡፡ በዚህ መልኩ ነው ስለ ህልፈቱ መርዶው የተነገረን፡፡
የህልፈቱ መንስኤ በትክክል ታውቋል? የሃኪም ማረጋገጫ አግኝታችኋል? በማኅበረሰብ ሚዲያ የምግብ መመረዝ የህልፈቱ መንስኤ መሆኑ ሲናፈስ ነበር----?
ይሄ ሰው ታዋቂ ነው፡፡ እኔ አባቴ እንዲህ ታዋቂ ነው ብዬ ብዘረዝር፣ በኛ ባህል ያልተለመደ ነው፤ መኮፈስ ይመስላል፤ ሌላው ቢናገረው ነው የሚሻለኝ። የህልፈቱን መንስኤ በተመለከተ በእውነትና በመረጃ የተደገፈ ሲሆን ነው ጥሩ፡፡ ሁሉም የራሱን አስተያየት ከሚሰጥ፣ እኛም የራሳችንን መረጃ አሰባስበን፤ ወደፊት ትክክለኛው መረጃ ቢገለፅ ነው የሚሻለው፡፡
የቀብር አፈፃፀም ሥነ ስርዓቱ እንዴት ነው የታሰበው?
ታላቅ ወንድሙ፤እናትና አባቱ ባረፉበት አገሩ ሄዶ ቢያርፍ የሚል ሀሳብ አለው፡፡ እኔ ደግሞ አዲስ አበባ ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ ለሀገሩ ብዙ የለፋ የደከመ ሰው ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ግን  መጥቶ ያማከረን ትልቅ አካል የለም፡፡ ሊያናግረን የመጣ ሰው የለም። ውጪ ያሉት በጣም እየተረባረቡ ነው፡፡ እዚህ ግን ቢያንስ እንዴት እናድርግ ብሎ የመጣ አካል የለም። በእርግጥ ሁሉም ህዝብ አዝኗል፡፡ ብዙ የሀዘን መግለጫ ነው የሚደርሰን፡፡
አስከሬኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው መቼ ነው
ከእሁድ በኋላ ነው የሚሆነው፡፡ ወንድሜ እዚያ አለ፡፡ ትክክለኛ ቀኑን እሱ ነው የሚነግረን፡፡ ያኔ ለህዝቡ እናሳውቃለን፡፡  

Read 3583 times