Sunday, 30 April 2017 00:00

‹‹አሻም…ጋሽ አሴ!››

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

ያገር ፈርጦች…የታሪክ ሠነዶች… የብርሃን ፈለጎች… የጥበብ አለላዎች ---- በአደባባይዋ ሲኖሩ፤ ሀገር ዐውደ ዓመት… ዐውደ ዓመት ትሸታለች፡፡… ሣቅዋ ይጣፍጣል፤ እንባዋም ፍሬ ያፈራል!... ባንዲራዋም ይፀናል!
ኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲህ ያሉ ጥቂቶች አሏት፡፡ በአደባባይ ተናግረው፤ በጀርባ ምላስ የሚያወጡ ፌዘኞችዋ እልፍ ቢሆኑም፤… ታማኝ ሆነው የኖሩላት፣ በሕልማቸውና በእውናቸው ጫንቃቸው እስኪጎብጥ የተሸከሟት … እስከ ሞት የታመኗት አላጣችም፡፡
ጋሽ አሰፋ ጫቦ ከነዚህ ሕሩያን አንዱ ነው፡፡… ለዚህ ነው የሀገሬ ትዕምርት፣ የሰንደቅ ዓላማችን ቀለም የሚመሥለኝ፡፡… ለዚህ ነው ያገሬ ጥበብ ነው ብዬ፣ ቀና ብዬ በአክብሮት የማየው!... በመጣጥፎቼ ስጠቅሰው፤ ‹‹እጅግ የማከብረው ጋሽ አሰፋ ጫቦ›› የምለው ከልቤ ነው፡፡… እጅግ አከብረዋለሁ፡፡ እጅግ እወደዋለሁ፡፡…ለምን እንደሆነ ባላውቅም አክብሮቴ ውስጥ እስከሚደንቀኝ ድረስ የፍቅር ፍርሃት ነበር፡፡
የጋሽ አሴን ፅሑፎች አሣድጄ አነብብ ነበር፡፡ እርሱ ያለባቸውን መጽሔቶችና ጋዜጦች  ከአሮጌ ተራ እለቅማሁ፡፡ ለዛ ባለው አፃፃፍ፣ በድንቅ ትረካው፤ በብስለቱ፤ በመረጃውና በጨዋታ አዋቂነቱ እደመማለሁ፡፡…. ስለ ግጥም ሲፅፍ፤ ‹‹ሀገርህ ናት በቃ!›› በሚለው በነቢይ መኮንን ግጥም እንዳየሁት፣ ጋሽ አሴ፣ ባለ ሸጋ ብዕር ፀሀፊ ብቻ ሳይሆን ባለ ብዙ ዓይኖች ሃያሲም ነው፡፡ አንድ ቀን ፌስቡክ ላይ ሳገኘውም የነገርኩት ይህንን ነው፡፡ መጣጥፎቹን ጠቅሼ፤ ‹‹ጋሽ አሴ፤ አንተኮ ፖኤትሪ ነህ›› አልኩት፤ በርግጥም ባለ ብዙ አውታር ሙዚቃ፤ ጣፋጭ ቅኔም ነበር፡፡
‹‹ማንም እንዲህ ብሎኝ አያውቅም!---›› ሲለኝ፣ ፍርሃቴ መጣና ተለየሁት፡፡ ሁሌ ላናግረው እልና - እፈራዋለሁ፡፡ እንዲህ የምፈራውና የማከብረው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህሬ ጋሽ በቀለ አየለን ነው፡፡… ለምን እንደሆነ ግን ዛሬም አይገባኝም፡፡ ሰውነቴ ሁሉ ይርዳል!...
ጋሽ አሰፋ ግን ሀገር ነው፡፡ ጋሽ አሰፋ ትዕምርት ነው፡፡ ጋሽ አሰፋ ባንዲራ ነው፡፡.. ሁሌ ስሙንና ሥራውን ሣይ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ድቅን ይሉብኛል፡፡.. ባንዲራ ማለት ይህስ አይደል!
ጨረቃን ለመንካት ኮንሶ አድማሥ ላይ በሚል ሀሣብ የፃፈው ሳይሆን የሣለውን ፅሁፍ በረዥም ምላሱ ያላጣጠመ፤ በልቡ ከንፈር ያልሣመ ሰነፍ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ሰውየው ያገር ታቦት፤ የታሪክ ፅላት ነው፡፡ የአንድነት ጠበቃ፤ የኢትዮጵያዊነት መዝሙርና ቅኔ ነው፡፡ ስለዚህ ጋሽ አሰፋን ከአንድ ቤት ጣራ እንደተመዘዘ ቀንበጥ አላየውም፡፡ ይልቅስ ምሰሶውን ከደገፉት ዋልታዎች አንዱ እንደወደቀ እቆጥራለሁ፡፡… ክፍተት ይፈጥራል፡፡
ከሁለት ሣምንታት በፊት ‹‹የትዝታ ፈለግ›› የሚለውን መጽሐፉን እንደገና ሣገላብጥ፣ በሀገር ፍቅሩ እጅግ ተደንቄ ነበር፡፡ በተለይ የአንድነት ስሜቱና ፍቅሩ!... ትግሬ.. ኦሮሞ..አማራ..ጋሞ…ሲዳማ…ወላይታ…ለጋሽ አሰፋ ሁሉም ወገን ነው፡፡
ስለ ጨንቻ ሲያወራ፤ ስለ ኢትዮጵያዊነት.. እያወራ ነው፡፡ ስለ ጋሞ ከተረከ፣ ስለ መላው ኢትዮጵያ እያቀነቀነ ነው፡፡ የተገነጠለ መዝሙር የለውም፡፡ ሀገሩን እንደ ዳዊት ይደግማል፤ እንደ ፀሎት ያነበንባል፡፡ ለዚያ ነው ከምሥራቅ ምዕራብ አድማስ ላይ እንደተተከለ ቀስተ ደመና፣ ያገር ባንዲራ የሚመሥለኝ!
እንደ ገጣሚ ስስ፣ እንደ ህግ ሰው ብልህ፤ እንደ ታሪክ መርማሪ ጠንቃቃ፤ እንደ ካህን ማላጅ፣ እንደ ወጣት ፍም ልብ ነበር - ጋሽ አሴ!... ፅንፈኛ አይደለም፡፡ ሚዛናዊ ነው፡፡ ጥላቻን አጥብቆ ይሸሻል፡፡ ፈሪ አይደለም፤የልቡን ይናገራል፡፡… ልቡ ግን ለይቅርታ ቅርብ ነው፡፡
ከአፉ የማይለያትን ጨንቻ እንኳ ሲያሣየን፣በኢትዮጵያዊነት ቀለም ነክሮ፤ በባንዲራዋ ጠቅልሎ ነው፡፡ አሴ ሀገር እርቃንዋን ስትቆም፤ሃፍረትዋ ሲገለጥ አይወድድም፡፡ ለዚህ ነበር ሙግቱ፣ ለዚህ ነበር ህቅታው!
“የትዝታ ፈለግ” መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹..እኔ ጋሞ ነኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሁለቱ ተጣልተው ለማሥታረቅ ተቀምጬ አላውቅም፡፡ እረዳቸዋለሁ፡፡ የኔ ቢጤ በሺህ የሚቆጠሩ አውቃለሁ፡፡ የማላውቃቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሉ፡፡---”
ስለ ጨንቻ ኢትዮጵያዊነት ሲናገር፡-
‹‹የጨንቻ ነፍጠኛ ኦሮሞ፤ አማራ ነኝ አይልም፡፡ ኦሮሞ ነኝ የሚልም አይመሥልም፡፡ የጨንቻ ሰው ነው፡፡ የቤት ቋንቋው በአብዛኛው ኦሮምኛ ነው…››
በጨንቻ ስለኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ተናግሯል፡፡ ከትግሬነት ይልቅ፤ጋሞነት ውስጥ እንደተጠመቁ ይተርካል፡፡… በብሔራዊ አንድነት በእጅጉ ያምናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት፤ ብዙ ቀለም ያላቸው ዶቃዎች፣በአንድ ክር የተሰፉ መሆናቸውን አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ጋሽ አሴ እንዲህ ነው፡፡ ልቡን ላደመጠ፤ የደሙ መዝሙር፤ የነፍሱ ቅኝት አንድና አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት፣ፍቅርና መከባበር!
እንግዲህ ይህን የመሠለ አንበሳ ነው ያጣነው፡፡… ይህንን ግዙፍ ነው የተነጠቅነው፡፡ ፌስቡክ ይህን ያረዳኝ ቀን፤ ‹‹ውሸት በሆነ!›› ነበር - የልቤ ጩኸት፡፡ ደጋግሜ ሳገላብጥ ግን ከመራራው እውነታ ጋር ተጋፈጥኩኝ፡፡ የደራሲ ይታገሱ ጌትነት የፌስቡክ ግድግዳ ‹‹ውሸት በሆነ!›› ይላል፡፡ የጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ልጅም እንደዚሁ!... የኔም ልብ ግድግዳ ላይ የተንጠለጠለው ይኸው ነበር፡፡.. ግን ምኞት! ምኞት ብቻ! ያን ጊዜ እነዚህ ስንኞች ደም ለብሰው ከልቤ ፈሰሱ፡፡  
‹‹ድርሳን ተቀደደ››
አድማሳት መልካቸው… ወዘናቸው ጠፋ
ሀገር ቀለማቱን… ለዛዎቹን ደፋ፤
ድርሳን ተቀደደ…ታሪክ ተፋለሰ፤
ጥበብ ጌጡን አጣ…ፍትህ አለቀሰ፤
የዕውቀት ልቃቂቱ…ቁመናው ቀጠነ
ያገር ሰማይ ከፋው…ባንዲራው አዘነ፡፡
* * *
የነፃነት ቤዛ…ያድማሳችን ግርማ፤
የታሪክ መቀነት… የህዝባችን ዜማ፤
አይተን ሣንጠግበው… ነፍሳችን ሳትረካ፤
የልቡን ሣናነብ…ቀለሙ ሳይፈካ፤
መዝገቡ ተዘጋ…ድርሳኑ ዝም አለ፤
ታከተው መሠለኝ… ጓዙን ጠቀለለ፡፡
ወደ ጥልቅ ሐዘን - የገባሁት እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ወጣቶች በጋሽ አሴ ሞት ሲንገበገቡ አይቼ፣ በዚያ በጠረረ ሀዘን ውስጥ ሆኜ እንኳ አንዳች ተስፋ በውስጤ አቆጠቆጠ፡፡ ወጣቶች ይህን ሰው እንደ ባንዲራ አይተው፣ባጡት ነገር የሚቆጩ ከሆነ፣ ነገ ሀገሪቱ ባድማ አትሆንም፤ አደባባዮችዋ በታሪክ ሰነዶች ረሀብ አያዛጉም፤ ይልቅስ በአገር ፍቅር ስሜት ይቃጠላሉ … በሚል በዘመኑ ወጣቶች ላይ ያለኝ ተስፋ ደመቀ፡፡
በሀዘን ላይ ሀዘን የሆነብኝ፣ በሰው ሀገር ባይተዋር ሆኖ፣ መሞቱ ነው፡፡ በልቡ የሀገሩን ወንዞች ዜማ እያዜመ፣ የተራሮቹን ቁመና እየናፈቀ፣ በህዝቡ መካከል መመላለስ እየተመኘ በሰቀቀን መቅረቱ ውስጤን አደማው፡፡  
ጋሼ አሴ - አሜሪካን ለረዥም ዓመታት፣ ለዚያውም በበርካታ ግዛቶች እየተዘዋወረ ኖሯል፡፡ መኖር ብቻ አይደለም፣ ሁሌም እንደሚያደርገው ስለ አሜሪካ ያለውን አተያይና ለአገር ልጅ ይበጃል ያለውን እውነት እየነቀሰ ጽፎታል፡፡
“የትዝታ ፈለግ” ከሚለው መጽሐፉ ጥቂት እነሆ፡-
“አስፈራርቼ ማስቀረት አልችልም፡፡ ----- የቻለ ሁሉ ቢመጣ ደስታዬ ነው፡፡ ደስታዬ ባይሆን መምጣታችሁ ነውና ለእነ “ይምጡ በዝና” ትንሽ ምክር ለመስጠት ይፈቀድልኝ፡፡
ሀ) ስለ አሜሪካ እዚያ ኢትዮጵያ የተሰማው በአብዛኛው እውነት ነው፡፡ ትንሽ ተረትነትም የሚያጣ አይመስለኝም፡፡ አሜሪካ ትንግርት አገር ነው፡፡ የሞላው፣ የፈላው ነው፡፡ ያጣ፣ የነጣም አለበት፡፡ ለአንዳንድ ሕዝብ ክፍል የማጥ፣ የምጥ አገርም ነው፡፡ በአብዛኛው፤ “… ጥረህ፣ ግረህ … በላብህ … ትበላበታለህ፤ የዘር ርግማን (የአዳም) ቃል በቃል ሥራ ላይ የዋለው እዚህ ነው፡፡”
ጋሽ አሰፋ በመጽሐፉ ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ገጠመኝ፣ ብዙ ጥበብ አስፍሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ የቀድሞው ጦር እንዳይፈርስ በሽግግሩ ጊዜ ሽንጡን ገትሮ የተሟገተው እርሱ ነበር፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተሟግቷል፤ ኖሯል፣ አስተምሯል፡፡
አሁን አሜሪካን የሚኖረው የቅርብ ጓደኛዬ መለስ ባልቻ (ዶ/ር)፤ ማክሰኞ ጠዋት ፌስ ቡክ ላይ ብቅ ብሎ፤ “…. አቶ አሰፋ መሞታቸውን ቅድም ነው የሰማሁት፤ … አዘንኩኝ፤ እኔ ያለሁበት ከተማ ነበር የሚኖሩት፡፡” አለኝ፡፡
እኔም እጅግ ማዘኔን ነገርኩት፡፡ እናም አንድ ቀን በአካል እንደተገናኙ ነገረኝ፡፡ በፌስቡክ እንዳወራኝ፤ የተገናኙት “ከአሜን ባሻገር” የሚለውን የበዕውቀቱ ስዩምን መጽሐፍ ከፖስታ ቤት ሊያወጣ መጥቶ ነው፡፡ ጓደኛዬ፤”አሜሪካ ሀገር በዚህ ዕድሜ አንባቢ የሆኑ ኢትዮጵያዊ የት ተገኙ?” ብሎ ደነቀው፡፡ ሆኖም ጋሽ አሰፋ ጫቦ መሆኑን አላወቀም፡፡ እና ስደት እንደደበረው ነገረው፤”ሄጄ የሀገሬን ገበሬ ብረዳ ይሻለኝ ነበር” አለው፡፡
ጋሼ አሰፋም፤“ቢሆን መልካም ነበር፤ ካልሆነም በግሎባላይዜሽን አስብ!” አለው፡፡ አሰፋ ጫቦ መሆኑን ያወቀው የበዕውቀቱን መጽሐፍ የያዘውን ፖስታ አውጥቶ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ሲከተው፣ ከተጣለው ፖስታ ላይ ስሙን ካየ በኋላ ነው፡፡
 ጋሽ አሴ አሜሪካ ሆኖ ኢትዮጵያን ያረገዘ ሰው ነበር፡፡ ስለ ፍትህ የሚቃትት፣ ስለ አንድነት የሚዘምር! … ፅሁፎቹ ውስጥ የናፍቆት ዜማ፣ ነፍሱ ውስጥ ትዝታ አለ፡፡
ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ ስለ ህልፈቱ ልብ የሚቆነጥጥ ግጥም ፅፏል፡-
ናፍቆታል አገሩ፣ ጥያሜው ጠረኑ
በስጋው ተሰዶ፣ ይያት በአስክሬኑ፣
“አሻም!” በሉት ውጡ፣ አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ በትኑት፣ አፈሩን ዝገኑ …
የዕድሜ እንቆቅልሹ፣ የዘመን ትብትቡ
የትዝታው ፈለግ፣ ፍቅር የሀገር ሰቡ
ያንድነት ሀሣቡ፣ ያብሮነት ረሀቡ
ይፈታለት ህልሙ፣
ይውጣለት ህመሙ
….
ያውቀዋል አየሩን
ይረዳዋል ነፍሱ፣
ባያይ እንኳን ዐይኑ
ያውቃል ደመነፍሱ፣
ለመላ ነው ሞቱ፣
ለመግባት ከቤቱ፣
“አሻም” በሉት ውጡ፣ አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ በትኑት፣ አፈሩን ዝገኑ …
ይብረድለት ሱሱ
ቃናዋ ነው ምሱ፣
(ጥቂት ስንኞች ቀንሻለሁ!) ነፍሴን የነቀነቃት ግጥም ነው፡፡ እናም እንባ በሞላ ዓይን “አሻም” ብዬዋለሁ - ጋሽ አሴን! … እንደደከምክ …. ሀገር እንደራበህ … ሆያ ሆዬ በዓይንህ እንደመጣ፣ የ“መስቀል” ደመራ እንዳባባህ … በሰው ሀገር፣ በሰው አፈር አረፍክ!
“ጋሽ አሴ! …. አሻም ለድካምህ! … አሻም ለብርቱ ተጋድሎህ! … አሻም ለድንቅ ፍቅርህ! … አበባ በትኛለሁ … ሳቄን ቆርጥሜ ለእንባ ሰግጃለሁ … አንበሳዬ…!!

Read 1864 times