Sunday, 30 April 2017 00:00

አራቱ መስተፃርራን

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(18 votes)

  “--- ከተማችንም ገጠር አይሏት ሕንጻዎቿ እንደ ጡት አጎጥጉጠው፤ ወይ ሁነኛ የመንግሥት ባል አላገባች፣ ወይ እንደ ፈረሰች ከተማ ጨርሶ አልመነኮሰች - እንደ መንደር ምግብ ቤት ድስት አሥር ጊዜ ስትወጠወጥ ትኖራለች፡፡            የሀገሬ ህዳሴየሚጀምረው መቼ ነው ብለው ለሚጠይቁ፤ መልሱ - --”
                         
      ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ሕዝብ የሚሠሩ፣ በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ የማይመስሉ አራት መስተፃርራን አሉ፡፡ እርስ በርሳቸው የሚቀዋወሙ፡፡ አንዱ የሠራውን ሌላው ካላፈረሰ የሠራ የማይመስለው፡፡ ዋና ተልዕኳቸው የሌላውን ማፍረስ እንጂ የራሳቸውን መሥራት ያልሆነ። መዝገበ ቃላታቸው - ናደው፣ ደምስሰው፣ አፍርሰው፣ ቆፍረው፣ ጉረደው፣ ቁረጠው፣ ገልብጠው - በሚሉ ቃላት የተሞሉ፡፡
አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን
ያንን ካላጠፋሁ ከቶ ምንም ቢሆን
ዕረፍት አላገኝም እንቅልፍ አይወስደኝም
ቅን ነገር አይቼ እኔ አያስችለኝም፡፡  የሚለው መዝሙር፣ ብሔራዊ መዝሙራቸው የሆነ - አራቱ መስተፃርራን፡፡
እነዚህ አራቱስ እነማን ናቸው ቢሉ - ውኃና ፍሳሽ፣ ቴሌ፣ መንገዶች ባለሥልጣንና መብራት ኃይል ይባላሉ፡፡ አንዱ የሌላውን መኖር ቢያውቅም፣ አንዱ ግን ከሌላው ጋር ለመተባበር የማይፈልግ፡፡ የሀገር ወዳጅ እንዳንላቸው የሀገር ሀብት ሲያፈርሱ ምንም አይመስላቸው፤ የሀገር ጠላት እንዳንላቸው የምንሠራ ለሀገር ነው ይላሉ፡፡   
መንገዶች ባለ ሥልጣን ይመጣና አካባቢውን ቆፍሮ፣ ንዶ፣ ቤት አፍርሶ፣ ዛፍ ገንድሶ፣ አጥር ጠርምሶ፣ ምሶሶ ነቅሎ፣ መንገድ እሠራለሁ ይላል፡፡ አካባቢው ይታመሳል፣ ይተራመሳል። ለጥቂት ጊዜ ችግሩን ቻሉት እንባልና የአፈር እንጀራ እንበላለን፣ የአቧራ ውኃ እንጠጣለን፡፡ ልክ ጠጠሩ ተደላድሎ አስፓልቱ ሲነጠፍ፣ አካፋና አዷማ የያዙ ጎልማሶች አካባቢውን ይወሩታል፡፡ ያሠምራሉ፣ ይለካሉ፣ ይቆርጣሉ፡፡ ምንድን ነው? ስንላቸው ‹የቴሌ መሥመር ልንዘረጋ ነው› ይሉናል። ‹እስካሁን የት ነበራችሁ› ያልናቸው እንደሆን፣ መልሳቸውን የሚሰጡን ጉድጓዱን እየቆፈሩ ነው። ‹የተሠራ ሳናበላሽ፣ የተገነባ ሳንንድ አታውለን› ብለው ጸልየው የመጡ ናቸውና፣ ያሉትን ሳያደርጉ አይመለሱም፡፡ እኛም፤
የተመኘሁትን አንድ ቀን ሳላይ
ያልፍልኛል ስለው ሊያልፍብኝ ነወይ  
ያለችውን ሴትዮ እንጉርጉሮ እንዳንጎራጎርን እንከርማለን፡፡ የደኻ ምርኩዙ ተስፋ ነውና፣ ቴሌ ጨርሶ ሲሄድ ሠፈራችን ያልፍለታል ብለን ደግሞ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የተሠራውን አስፓልት ንደው፣ የተደለደለውን ጎድጉደው፣ በሬንጁ ምትክ አፈር፣ በአስፓልቱ ምትክ ጠጠር ሞልተው፣ የአህያ ሻኛ ቁስል የመሰለ የአስፓልት ላይ ቁስል ትተው ቴሌዎች ይሄዳሉ፡፡ እኛም፤
ለማይሰማው ስልክ ለሚቆራረጠው
እንደ ገላውዴዎስ መንገዴን ቆረጠው
--- እያልን እያዜምን እንቀራለን፡፡ እንደ ገላውዴዎስ የተባሉት ዐፄ ገላውዴዎስ ናቸው፡፡ መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ሐረር አካባቢ ከሐረሩ አሚር ከኑር መሐመድ ጦር ጋር በተደረገ ጦርነት ዐፄ ገላውዴዎስ ተገደሉ፡፡ ራሳቸውንም ቆርጠው ወደ ሐረር ከተማ ወሰዷቸው፡፡  
ቴሌ በቆፈረው ጉድጓድ እየተንገጫገጭን፣ ጉድጓዱ በያዘው ውኃም እየተንቦራጨቅን ኑሯችንን ስንገፋ፣ ሦስተኛው ፀር ይመጣል፡፡ ‹መንገዱ የፍሳሽ ማስወገጃ የለውም፤ አሮጌውም የውኃ መሥመር ይቀየራል› የሚል መፈክር ያሰማል፡፡ ምነው ሲሆን መንገዱ ሳይሠራ፣ ካልሆነም ቴሌ ሲቆፍረው አትመጡም ወይ? ያልናቸው እንደሆነ፣ ‹እኛ በወንድነት ከእነማን አንሰን ነው ሌላ በቆፈረው ጉድጓድ የምንሠራ። እኛም የራሳችን ቆፋሪ ክፍል አለን፣ የመቆፈሪያ በጀት አለን፣ የማስቆፈሪያ አበል አለን፡፡ እጃችን ሙቅ ይዟል እንዴ? እንንደዋለን እንጂ፡፡ እንኳን ይኼንን ኮረትና አፈር የለበሰ ጉድጓድ፣ ምን የመሰለውን አስፓልትም ዕጢ እንደሚወጣለት ሆድ ስንተረትረው ባያችሁ› ይሉናል፡፡
ገና እናፈርሳለን
ገና እንንዳለን
በጀቱ እስካለን፣ ዕቅድ እስካወጣን
ገና እንቆፍራለን፣ ገና እናፈርሳለን፡፡
የሚለውን መዝሙር እያቀነቀኑ፣ ያን የፈረደበት አስፓልት ይተረትሩት ገቡ፡፡ አማርኛ የሚናገሩ ደርቡሾች፡፡ ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር አገር ናት፣ መቼም ፈርዶባታል ብለን እኛም ዝም አልን፡፡ ዝምታችንም እንደ ፍርሃት ስለተቆጠረ ሦስቱ ጨረሱና አራተኛው መጣ፡፡ ‹ለአዲሱ መንገድ የኤሌክትሪክ ምሶሶ እንተክላለን› የሚሉ አፍራሾች፤ መቆፈሪያቸውን እንደ ሳንጃ ወድረው፣ አካፋቸውን እንደ ጦር አሹለው አሰፈሰፉ፡፡ የተስተካከለውን የእግረኛ መንገድ እንደተጣመመ ጥርስ እየነቀሉ፣ የተደላደለውን ጎዳና እንደ ወርቅ ፈላጊ እየፈነቀሉ የበልግ እርሻ አስመሰሉት፡፡ ይባስ ብለው ወደ ምሶሶ የሚገባው የኤሌክትሪክ ገመድ እንደ ፈልፈል በምድር ውስጥ ነውና የሚሄደው እኛም በተራችን መንገድ እንቆርጣለን - አሉና ተነሡ፡፡ እኛም፤
በመንደሩ መሐል አንድ ዋርካ ብትኖር
ያም መጥቶ ያም መጥቶ ይፈልጣት ጀመር
የሚለውን ነጠላ ዜማ ለቀቅን፡፡ ሠፈራችንን ከመልቀቅ ነጠላ ዜማ መልቀቅ ይሻላል ብለን። ይኼው ከተማችንም አራቱ መስተፃርራን እንደ አራቱ ወቅቶች እየተፈራረቁ ሲያፈርሷት፣ እርሷም ሳያልፍላት እኛም ሳያልፍልን እንኖራለን። በዚህ የጠላትነት አዙሪት ውስጥ መግባታችን የሚታወቀው ደግሞ ውኃና ፍሳሽ የዘረጋውን፣ መብራት ኃይል የቀበረውን፣ ቴሌ የደለደለውን እንደገና አፈርሰዋለሁ ብሎ መነሣቱን ስናይ ነው። መንገዱ ይሰፋል፣ ደረጃው ይሻሻላል ብሎ ባልተወለደ አንጀቱ ያ ሁሉ ብር የፈሰሰበትን አስፋልት ጅብ እንዳገኘው የአህያ ሆድ ዘረገፈው፡፡   
የአቦላን ተራራ ያክላል ጡትሽ
ወይ ባል አላገባሽ ወይ አልመነኮስሽ
እንዴው ልጃገረድ ይባላል ስምሽ
እንዳለው ክራር ገራፊ፡፡ ከተማችንም ገጠር አይሏት ሕንጻዎቿ እንደ ጡት አጎጥጉጠው፤ ወይ ሁነኛ የመንግሥት ባል አላገባች፣ ወይ እንደ ፈረሰች ከተማ ጨርሶ አልመነኮሰች - እንደ መንደር ምግብ ቤት ድስት አሥር ጊዜ ስትወጠወጥ ትኖራለች። የሀገሬ ህዳሴ የሚጀምረው መቼ ነው ብለው ለሚጠይቁ - መልሱ - እነዚህ አራቱ መስተፃርራን የታረቁ ጊዜ ነው፡፡        

Read 5845 times