Sunday, 30 April 2017 00:00

የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም በአማርኛ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  በአርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ ደራሲነትና ዳይሬክተርነት፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰርነት፣ በጥቂት ባለሙያዎች ተሳትፎ፣ በኢትዮጵያ
የመጀመሪያው የአማርኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም ተሰርቶ፣ የትንሳኤ በዓል ዕለት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ለእይታ በቅቷል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከረዥም ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያስብበት እንደነበር የሚናገረው ደራሲና
ዳይሬክተር ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ እግዚአብሔር የፈቀደው ጊዜ ይህ ወቅት በመሆኑ የሁዳዴ ፆም ሲገባ ተጀምሮ፣ በ55 ቀናት ተጠናቆ ለእይታ መብቃቱ እንዳስደሰተው ይገልጻል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አርቲስት ፈለቀ አበበን ፊልሙ በተቀረፀበት ባልደራስ ፈረስ ቤት መዝናኛ አግኝታው፣ በፊልሙ ሥራ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

                    *ደራሲና ዳይሬክተር፡- አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ
                    *ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰር፡- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ
                    *ለዕይታ የቀረበው፡- ሚያዝያ 8 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በኢቢኤስ
                    *ቀረጻው የተከናወነው፡- በኢትዮጵያ

     የኢየሱስን ታሪክ በአማርኛ መስራት ያሰብከው መቼ ነበር?
ሀሳቡ ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተሞከሩ ፕሮጀክቶችም ነበሩ፡፡ ያው እግዚአብሔር የፈቀደው አሁን በመሆኑ እውን ሆኗል፡፡ በነገራችን ላይ ያለመገጣጠም ጉዳይ ሆኖ እንጂ ፍላጎቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነበር፤ አሁን ተሳክቷል፡፡
የሜል ጊብሰን “ዘ ፓሽን ኦፍ ክራይስት”ን ጨምሮ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ ፊልሞች ተሰርተዋል፡፡ ያንተ ፊልም በአማርኛ ከመሰራቱ ውጭ ምን የተለየ ነገር ይዟል?
በጣም ጥሩ! እኛ ለመስራትና ለማሳየት የሞከርነው ኢትዮጵያ በመፅሐፍ ቅዱስ ካሏት በርካታ ነገሮች ጥቂቱን ነው፡፡ ይህም ከብሉይ ኪዳን እስከ አዲስ ኪዳን ያለውን የሚያስዳስስ ነው፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግም ከአዳም እስከ ስቅለት ያለውን ታሪክ አካትተን ሰርተናል፡፡ እንደ እድል ሆኖ ኢትዮጵያ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ በመፅሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ጥቂት አገሮች አንዷ ስለሆነች ከልጅነታችን ጀምሮ የሚነገሩን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ንግሥት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፣ ንጉሥ ዳዊት “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” አለ፤ የሚሉት ነገሮች እጅግ የምንኮራባቸው ናቸው፡፡ ዳዊት በበገና የዘመረልሽ እያልን ስንዘምር የነበረውን፣ በምስል ወደ እይታ የማምጣት መጠነኛ ሙከራ ነው ያደረግነው፡፡
መጠነኛ ሙከራ ለምን ሆነ? የገንዘብ? የጊዜ? ወይስ ምንድን ነው የገደባችሁ?
የጠቀስሻቸው ሁሉ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በእኔ አረዳድ ግን አሁን የሰራነው እግዚአብሔር በፈቀደው መጠን ነው፡፡ ለአሁን የተፈቀደልን ይሄን ያህል ነው፡፡ ሲፈቀድ ደግሞ በትልቅ ፕሮዳክሽን እንሰራለን፡፡ አሁን ጉዳዩን መነካካታችን፣ዓይን ገላጭ መሆናችን ለሌሎች መነቃቃትን ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
 በገፀ ባህርያቱ ዙሪያ ብንነጋገርስ?
በጣም አሪፍ፤ እንቀጥል፡፡
ኢየሱስን ሆኖ የተጫወተውን ገፀ ባህሪ ኢትዮጵያዊ ለማስመሰል የቆዳው ቀለም ጠይም መሆኑ ቢያስመሰግናችሁም ፀጉሩን ሉጫ ማድረጋችሁ “ፊልሙ ከፈረንጅ ተፅዕኖ አልወጣም” የሚል ትችት አስከትሎባችኋል፡፡ እንደውም ፀጉሩ ድሬድ መሆን እንደነበረበትና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ከባህታዊያን ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ያንን የሚያመለክት ቢሆን ጥሩ ነበር የሚሉ ወገኖች  አሉ። አንተ ምን ትላለህ?
ይሄንን ሜክአፕ አርቲስቷ ብትመልሰው አሪፍ ነበር፡፡
ገጸ ባህርይውን ፈጥረህ ያሳደግከው አንተ ነህ ብዬ ነው፡፡ “የፊልም እግዜሩ ዳይሬክተሩ” ይባል የለ---
እውነት ነው! እንግዲያውስ በመፅሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር አምላክ “ኑ በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር” አለ፤ ሰውንም በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው” ነው የሚለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር መልክ ጥቁር አይደለም ነጭም አይደለም፤ በአጠቃላይ ቀለሙ አልተነገረም። ሁላችንንም የሰው ልጆች በመልኩና በአምሳሉ ነው የፈጠረን፡፡ በመሆኑም የኢየሱስን መልክ እንደዚህ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስችል መደምደሚያ ለመስጠት እንቸገራለን፡፡ እርግጥ ከአይሁድ ዘር መምጣቱ፣ ከዳዊትና ከአብርሃም ዘር መምጣቱ ተገልፆልናል፡፡ እኛም በሙከራችን ጠይም የሆነን ኢየሱስ አሳይተናል፡፡ ፀጉሩን እንደ ቆዳ ቀለሙ ከቀየርነው በሰው ውስጥ ያለውን ምስል በአንዴ እናጠፋዋለን፡፡ ምክንያቱም በህዝቡ በአማኙ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሰረጸ ምስል ስላለ ማለቴ ነው፡፡ ከፈረንጅ ተፅዕኖ ደግሞ በደንብ አላቀነዋል። የፀጉሩ አንድ ነገር ነው፡፡ በጭብጦቹ ግን በደንብ ነው ኢትዮጵያዊ ያደረግነው፡፡
ከጭብጦቹ በጣም አዲስ ነው፣እስከ ዛሬ በተሰሩት የኢየሱስ ፊልሞች ላይ ትኩረት አላገኘም የምትለው ካለ?
ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኢትዮጵያዊቷ ንግስት፣ ስለ ንግስት አዜብ መናገሩን ብዙ ሲጠቀስ አይሰማም፡፡ በእኛ ስራ ግን ሲናገር አሳይተናል። በሌላ በኩል የፊልሙ መነሻ ከጊዮን ወንዝ ነው የሚጀምረው፡፡ እንደሚታወቀው የጊዮን ወንዝ ከኤደን ገነት ምንጮች አንዱ ነው፤የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከባል ነው የሚለው፡፡
ይህ ቃል የሚገኘው ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ ነው፡፡ እኛ ከዚህ ጀምረን ኢየሱስን ወደ እኛ ለማስጠጋት ሞክረናል፡፡ የጸጉሩን ጉዳይ ግን እኔም እቀበለዋለሁ፡፡ ከጠይም መልኩ ጋር የባህታዊያን አይነት ፀጉር ቢኖረው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ለመዝለል አልፈለግንም፡፡ በኪነ - ጥበብ አይን መልኩና ፀጉሩ ባልኩሽ መልኩ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ በምዕመናን አይን ግን የተለመደውን የኢየሱስ መልክ መቶ በመቶ መቀየር ትንሽ ይከብዳል።  ጉዳዩን ጠቅለል ስናደርገው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ ከነበረው ስጋዊ መልኩ ይልቅ መንፈሳዊ ክብሩ ይልቃል፣ የሚል አመለካከት አለኝ፡፡
ፊልሙ ወደ አንድ የእምነት ተቋም ያጋደለ ነው የሚል አስተያየት ከሰዎች ሰምቻለሁ፡፡ የእናንተ ምልከታ እንዴት ነበር? የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን አማክራችኋል? ወይስ ጥናት ሰርታችሁ ነበር?
እንደ ጥያቄ የትኛውም አይነት ጉዳይ ሊነሳ ይችላል፡፡ እንኳን የኢየሱስን ታሪክ ያህል ትልቅ ሀሳብ ተነስቶ በአለማዊ ጉዳይ ላይ በተሰሩ ፊልሞችም ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት ጥያቄዎች እንዳይነሱ ከኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰራችን ከኢቢኤስም ጋር ተነጋግረናል፡፡ ወደ አንዱ ሀይማኖት ያጋደለ እንዳይሆን ማለቴ ነው፡፡ እናም ትረካው ሲጀምር አባትየው ለልጁ ስለ መፅሀፍ ቅዱስ ሲያስረዳው ይሰማል፡፡
እስቲ እሱን አብራራልኝ?
ገና ሀይቁ ጋር ትረካው ሲጀምር፤ ከታሪክ እንደተረዳነው መፅሀፍ ቅዱስ የኦሪት 39፣ የአዲስ ኪዳን 27፣ በድምሩ 66 መፅሀፎች አሉ ይባላል፡፡(ይሄ ብዙ ጊዜ ፕሮቴስታንቶች የሚቀበሉት ነው) ከዚያ ደግሞ “ኤፖክራፊ” የሚባል አለ፤ 13 ሀዋሊዶች ነበሩ፤ ዤሮም የሚባል ሰው 13ቱ እንዲጨመሩ ሲያደርግ 79 ሆኑ፡፡ ይህ የሆነው በጣም ብዙ ዓመት ቆይቶ ነው፡፡ ይሄ ካቶሊኮች የሚቀበሉት ነው፡፡ በኋላ መፅሐፈ ኩፋሌና መፅሐፈ ሔኖክ ሲጨመሩ 81 ሆኑ፤ ይሄኛው ኦርቶዶክስ የሚቀበለው ነው፡፡ ይህንን አብራርተን ነው የጀመርነው፡፡ ምን ለማለት ነው፤ የእኛ ቁርኝትና ስራ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር እንጂ ከሃይማኖት ተቋማቱ ጋር አይደለም፡፡ ከዚህ ጥያቄ ለመዳን ነው በማብራሪያም የጀመርነው። ስራችን ለሁሉም ሀይማኖት ክፍት እንዲሆን በጣም ተጠንቅቀናል፤ ጊዜም የወሰደብን ለዚህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፊልሙ ስምንት ጊዜ ነው የተፃፈው፡፡
ምንም እንኳን ፊልሙን ለመስራት የረጅም ጊዜ ሀሳብ ቢኖርህም የዚህን ፊልም ፕሮዳክሽን ለማጠናቀቅ ግን 55 ቀናት ብቻ እንደወሰደ ሰምቻለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ሀሳቡ በውስጥህ ስለነበረ ነው? ወይስ የራሱ የኢየሱስ ፊልም ስለሆነ እገዛው ታክሎበት ነው?
ምንም ጥያቄ የለውም ሁልጊዜ የእግዚአብሔር ስራ ሲሰራ እኛ ምክንያት ነን እንጂ እሱ ራሱ ቀድሞ ስራውን ሰርቶ ጨርሷል፡፡ የእግዚአብሄር ስራ ሲሰራ ሁሌም ቢሆን ስራውን የሚሰራው፣ የሚያቃናው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እኔ ነኝ የሰራሁት ወይም እየሰራሁ ያለሁት ብሎ ለቅፅበት መታበይ አደጋ ያመጣል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኑን ስሰበስብ የነገርኳቸው፤ ”ይህን ስራ የሚሰራው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙናል፤ በመጨረሻ ግን ይሳካል፤ ሆኖም እኔ እየሰራሁ ነው ወይም እየሰራ ነው ብላችሁ መናገር አይደለም እንዳታስቡት፤ ስራውን የሚሰራው እግዚአብሔር ነው” ብያቸው ነበር፡፡ እንዳልሺውም ስራውን የሰራው እሱው ነው።
ፊልሙን የሰራችሁት የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሳችሁ እንደመሆኑ በቦታም በአልባሳትም ሆነ በቁሳቁስ ደረጃ ብዙ የተቸገራችሁ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ይሆን የሮማዊያን ወታደሮች የያዙት ጋሻ ከካርቶን የተሰራው ነው የተባለው? ከሌላ ነገር መስራት አይቻልም ነበር?
እውነት ነው ከካርቶን ነው የሰራነው፡፡ የተፈቀደልንም ይሄው ነው፡፡
የተፈቀደልን ይሄው ነው ስትል ምን ማለትህ ነው?    
ቅድም እንደነገርኩሽ በተፈቀደልን መጠን ነው የሰራነው፡፡ ምናልባት የሮማዊያን ወታደሮች ጋሻ ትዝ ያለኝ ወደ ቀረፃ ልገባ ስል ይሆናል፡፡ አስቀድመን አላሰብነው ይሆናል፡፡ ዞር ስል አርት ዳይሬክተሩ አለ፤ ጋሻ እፈልጋለሁ አልኩት፡፡ ካርቶን አጠገቡ አለ።  ከካርቶን ጋሻ ሰርቶ ሰጠኝ፤ አለቀ፡፡ እኛ በዚያ ቦታ እንፈልግ የነበረው ጋሻ ማሳየት እንጂ ጋሻው ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስ ወይም ከአሉሙኒየም ተሰራ የሚለው አልነበረም ጉዳያችን፡፡ ተመልካችም እኛ ከሰራነው በላይ ሞልቶ እንደሚመለከተን እርግጠኞች ነን እንጂ የኢየሱስና የመፅሐፍ ቅዱስ ስራዎች እኮ በጣም በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች፣ እጅግ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ፣ በጣም በትልልቅ ባለሙያዎች በአለም ላይ ሲሰሩ ነው የኖሩት፡፡
ፊልሙ ራሱን የቻለና ወጥ የሆነ የማጀቢያ ሙዚቃ የለውም፡፡ መንፈሳዊ ፊልም ሲሰራ ማጀቢያ ሙዚቃ መስራት ያስቸግራል እንዴ?
እውነት ነው፡፡ አይደለም እንዲህ ለተጣደፈ ፕሮዳክሽን በደንብ ታስቦበት ለሚሰሩ ፊልሞች ሳውንድ ትራክ ስኮሪንግ መስራት ከባድ ነው። ነገር ግን መዘንጋት የሌለብን ባየነው የመፅሐፍ ቅዱስ ፊልም ውስጥ የሰማናቸው የሙዚቃ ድምፆች ለቦታው ተስማሚ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ተውሰን ያመጣናቸውና እኛ ያልፈጠርናቸው ቢሆኑም፡፡ በእኛ ፊልም ላይ ኢየሱስ ሲሰቀል የሰማነው ድምፅ በሌላ ፊልም ኢየሱስ ሲሰቀል የሰማው ድምፅ ነው፡፡ በዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ድምፆችን ከተለያዩ ፊልሞች ሰብስበናል፤ ለዚህ መሳካት በተለይ ኢቢኤስ ቴሌቪዥንና ኤዲተሩ ኤርሚያስ ይልማ ያሳዩት ትጋት ከፍተኛ ነው፤ምስጋና ይገባቸዋል። እንዳልሽው እግዚአብሔር ሲፈቅድ፣ በራሳችን የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች አጅበን የምንሰራው ትልቅ ፕሮዳክሽን ይኖረናል፡፡
ከራስህ ውጭ አንድም የተለመደ ፊት በፊልሙ ውስጥ አላካተትክም፡፡ ለምንድን ነው?
ሆን ብዬ ነው ያንን ያደረኩት፡፡
እንዴት?
ተመልካቹ በፊልሙ ውስጥ መፅሐፍ ቅዱስን እንዲያይ ነው እንጂ ተዋናይ እንዲያይ አልፈልግም። አንተስ ራስህን ለምን አካተትክ ካልሺኝ፣ ሙሴን እንደገና ከመስራት ባለፈው ዓመት እስራኤል ሄደን የሰራነው ስላለ፣ ያንን ላለማጣት ሲባል ተነጋገርንና “ሙሴን አንዴ ጀምሬዋለሁ ልቀጥል” በሚል ነው እንጂ አልኖርም ነበር፡፡
እነዚህኞቹስ ተዋንያን አይደሉም እንዴ? ከመታየት ያመልጣሉ?
ምን መሰለሽ ---- ትህትና ክብረትን ትዕቢትን ውድቀትን ትቀድማለች ይላል፤ መፅሐፍ ቅዱስ። የእግዚአብሔርን ስራ እየሰራን፣ የራሳችንን ክብር የምንፈልግ ከሆነ ችግር ነው፡፡ በጣም ትህትና ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስን ሆነው ቢጫወቱ የምፈልጋቸው በጣም ምርጥ ምርጥ ታዋቂ አክተሮች አሉ፡፡ አስቤያቸውም ነበር፡፡ እነዚህን አክተሮች ባመጣቸው ግን እከሌ ኢየሱስን እንዴት እንደተጫወተው ሰው ሲያስተውል፣ ዋናውን ጉዳይና መልዕክት ይረሳዋል፡፡ አዲስ ፊት ሲሆን ሰው ተዋናዩን ስለማያውቀው ትኩረቱን መልዕክቱ ላይ ያደርጋል የሚለውን በማሰብ እንጂ አብረውኝ የተሰማሩት አዳዲስ ቢሆኑም በጣም አሪፍ አሪፍ ልጆች ናቸው፡፡ በጣም ኮርቼባቸዋለሁ፡፡
በፊልሙ ላይ በጣም የተወደደው አንተና ወንድ ልጅህ ሙሴና ህፃኑን ሆናችሁ የተወናችሁበት ትዕይንት ነው፡፡ “ሙሴ ልጁን ሲያስተምረው፣ህፃኑም ሲጠይቅ የእውነት እንጂ ፊልም አይመስልም” የሚል አስተያየት ሰምቻለሁ፡፡ የዚህ ትዕይንት ፋይዳ ለኢትዮጵያውያን ልጆች ትልቅ ነውም ተብሏል፡፡ እስኪ ስለዚህ ትዕይንት በጥቂቱ አውጋኝ …
 ይህን ትዕይንት በሚመለከት መግቢያው ላይ መዝሙረ ዳዊት ባልሳሳት ቁጥር 7-8 ይመስለኛል “የሰማነውንና ያየነውን አባቶቻችንም የነገሩንን ከሚመጣው ትውልድ አልሰወሩም፤ ለልጆቻቸው ያስታውቁ ዘንድ” ብሎ ነው ፊልሙ የሚጀምረው፡፡ እንደ ትውልድም ስትመለከቺ፤ ብዙ ጊዜ በሚዲያም ስትሰሚ፣ የእውቀት ሽግግር ችግር አለ፡፡ እኛ ደግሞ ለ1 ሺህ 625 ዓመታት ከመንበረ ማርቆስ በሚመጡ ግብፃዊያን ጳጳሳት ነው ከይቅርታ ጋር ስንገዛ የኖርነው፤ ስለዚህ የእውቀት ሽግግር አንድ ቦታ ላይ ተገድቧል፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ ደግሞ በዓለም ላይ በብዛት የሚሰራጭና በብዛት የማይነበብ መፅሐፍ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህ ልጆቻችን በራሳቸው መፅሀፍ ቅዱስን ገልጠው እንዲያነቡ የሚያደርግ አቅም መፍጠር ይችላል፤ ከአባት ወደ ልጅ የሚደረግ ውይይት ማለት ነው፡፡
እዚህ ፊልም ላይ የተነሱ ጥያቄዎች አብዛኞቹ ልጆች የሚጠይቋቸው ናቸው፡፡ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው ምዕመንም ጥያቄዎቹን ይጠይቃል። የልጁ ጥያቄ ለፊልም አይመስልም የተባለውም እውነት ነው፤ ልጄ በረከት መፅሐፍ ቅዱስ ያነባል፣ ጥያቄ ይጠይቃል፣ ስለዚህ ፊልሙ ላይ በዚያ መጠን የእውነት ማስመሰሉ፣ ቤት ውስጥ የዕለት ከዕለት ተግባሩ ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በመፅሀፍ ቅዱስ አንዳንድ እውነት የማይመስሉ ነገሮች አሉ አይደል፤ ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ሲጳራን ማግባቱን አይነት ታሪኮች? ይህን እውነታ መግለጥ የሚቻለው ለአንድ ልጅ በማውራት ነው፡፡ ለዛ ነው ቅርፁን የመረጥነው። በዚያ ላይ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ባለቤት ወ/ሮ ማክዳ፤ ቅርፁን በምን መልኩ እናስኪደው በሚለው ላይ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ “ልክ ለልጆች እንደሚተረክ ሆኖ ቢቀርብ ጥሩ ነው” ብለው ሀሳቡን ያመጡት እሳቸው ናቸው፤ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ፊልሙ የኢትዮጵያ ልጆችንና ምዕመናንን ታሳቢ አድርጎ የተሰራ ቢሆንም የአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው የተጠቀማችሁት፡፡ ለምን ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ወላይትኛና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በሰብታይትል አልተጠቀማችሁም የሚል አስተያየትም ሰምቻለሁ፡፡ ምን ትላለህ?
በጣም አሪፍ ሀሳብ ነው፡፡ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰሩ እንደነገርኩሽ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ነው፡፡ ይሄን ጉዳይ ቢያስብበት መልካም ነው፡፡ ከኢቢኤስ ጋር ይሄኛው ሁለተኛው ስራችን ነው፡፡ ባለፈው እስራኤል ሄደን የሙሴን ታሪክ ሰርተናል። ሁለቱም የተሰሩት ከኢትዮጵያ ጉዳይ አንፃር ነው፡፡ እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያላት ቦታ ትልቅና የሚገርም ነው፡፡ ወደፊት የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንም ሆነ ሌሎች ታሪኮችን ስንሰራ ተደራሽነቱ ለብዙ ብሔረሰብ ልጆች እንዲሆንና ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው እያወቁ እንዲያድጉ እንጥራለን፡፡ ያ ካልሆነ “እናቷን አታውቅ አያቷን ናፈቀች” አይነት እንዳይሆን ወይም የራሳችንን ሳናውቅ የውጭን ከማሳደድ ስለሚያድነን በጣም ጥሩ ጥያቄ አንስተሻል፡፡ ይሄ መልዕክት ፕሮዱዩሰሮቹ ዘንድ የሚደርስ ይመስለኛል፡፡
ቀረፃው የት የት ነው የተካሄደው?
መጀመሪያ ያደረግነው ስክሪፕቱን ከመፃፍ ጎን ለጎን ቦታ መምረጥ ነበር፤ ስንመርጥ ደግሞ ለሀሳቡ የሚሄዱ ቦታዎችን ነው የመረጥነው፡፡ አብዛኛው ቦታ አዲስ አበባ ሲሆን ሁለት ክልሎች ላይ ቀረፃ አድርገናል፡፡ የጣናውን የጊዮን ወንዝ ታሪክ ስላለ፣ ባህር ዳር ሄደን ነው የሰራነው፡፡ ጢስ አባይም ጣናም ላይ ቀርፀናል፡፡ በሌላ በኩል አጠገባችን ሆነው ብዙ ትኩረት የማንሰጣቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እንጦጦ ደብረ ኤሊያስን ብትወስጂ፣ ብዙ ኢየሩሳሌምን የሚመስሉ ነገሮች አሉት፡፡ ገፈርሳ ወንዝ ዮርዳኖስ ወንዝን ይመስላል፤ የገፈርሳ ትንሽ ሰፋ ይላል እንጂ ይመሳላሉ፡፡ ዮርዳኖስን ገፈርሳ ወንዝ ላይ ነው የቀረፅነው፡፡ ሌላው አሁን እኔና አንቺ እያወራንበት ያለው ባልደራስ ፈረስ ቤት መዝናኛ የሚገርም ነው፤ እኛ መጀመሪያ ፈረስ ፍለጋ ነበር የመጣነው፤ ውስጥ ስንገባ ግን አዳራሹና ወንበሮቹ የድሮ መሆናቸውን ስንመለከት፣ እግዚአብሄር ያዘጋጀልን ቦታ እንደሆነ ነው የተሰማን። የመጨረሻውን እራት የቀረፅነው እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ የሳባና የሰለሞንን፣ የንጉስ ዳዊትንና የሄሮድስንም የቀረፅነው እዚሁ ነው፡፡ በሁለቱ አዳራሾች እያቀያየርን ነው የሰራነው፡፡  
መተሀራም ቀረፃ አካሂዳችኋል አይደል?
አዎ! በዚህ ፕሮዳክሽን እስራኤልና ግብፅ ለመሄድ ቪዛ አግኝተን ተሰረዘ፤ ምክንያቱም ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነበር፤ እንደገና ደግሞ የእግዚአብሄር ፈቃድ አልሆነም፤ እዛ ሄደን እንድንቀርፅ፡፡
በምን አረጋገጣችሁ የሱ ፈቃድ አለመሆኑን?
በጣም ጥሩ! እዚያ ሄደን ሰርተን ቢሆን ኖሮ፣ አሁን እኔና አንቺ ይህን ፊልም የመጀመሪያው የአገር ውስጥ ፕሮዳክሽን እያልን አናወራም ነበር። ኢትዮጵያዊ ፊልም የሚለውን ትንሽ ይሸረሽረው ነበር፤ ስለዚህ ግመል ያለበትን ትዕይንት መተሃራ ቀርፀን ተመለስን፡፡
በመተሀራ ጉዟችሁ በጣም አስደንጋጭ ክስተት ተፈጥሮ፣ ጭንቀት ውስጥ ገብታችሁ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ ንገረኝ? እንዴትስ ተወጣችሁት?
ፊልሙን ስንሰራ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ፈተና ነበር፤ የዚህኛው ግን በጣም አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከዚህኛው በፊት ቀረፃ ላይ እያለን ሜክአፕ አርቲስቱ እላዩ ላይ ቤንዚን ቀድቶ እሳት ሲለኮስ፣ ሙሉ በሙሉ እጁ ተቃጥሎ፣ በፈጣሪ እርዳታ ነው የተረፈው፡፡ ጠባሳው አሁንም አለ፡፡ ይሄኛው ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ምንድን ነው የሆነው? አልባሳቱን የሰራችው ዲዛይነር ሰላም ደምሴ (ኮኪ) መፅሐፍ ቅዱስ አንብባ፣ የተለያዩ ፊልሞችን አይታ፣ ጥናት አድርጋ ነው በዛን ጊዜ ይለበሱ የነበሩ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ መቀነቶች፣ ካፖዎች ብቻ ብዙ ነገር በማዳበሪያ ኮትተን፣ መኪና ላይ ጭነን ከሄድን በኋላ ናዝሬት ለምሳ ስንቆም ማዳበሪው መኪናው ላይ የለም፡፡ ሁሉም ሰው አይን ውስጥ እንባ ሞላ፤ ምግብ ቀርቧል፡፡ በተለይ ኮኪን ማየት አትችይም፡፡ እኔን ደሞ አስቢኝ፤ ወታደሮቹን ይዞ እንደሚዘምት የጦር መሪ ውሰጂኝ፤ሁሉም ከኔ ነው መፍትሄ የሚጠብቀው፡፡
ማዳበሪያው የት ገብቶ ነው ------ ከዚያስ?
ያኔ እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ቀና ትያለሽ፤ ለምን ይሄን ሸክም ሰጠኸኝ አልኩኝ፤ በጣም ነበር የከፋኝ፡፡ ነገር ግን ወዲያው መፍትሄ መጣ፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እግዚአብሄር ሙሴን ወደ ፈርኦን ሂድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ፈርኦን እምቢ ብሎ ልቡን እንደሚያደነድንና ህዝቡን እንደማይለቅ እግዚአብሄር ያውቃል፤ እግዚአብሔር ያንን ያደረገው በሱ ፈቃድና ሀይል ብቻ ህዝቡ ከግብፅ እንደሚወጣ ለማሳየት ነው፡፡ ለእኛም ያሳየን ይሄንን ይሆናል፤ ስራውን የምሰራው እኔ እንጂ እናንተ አይደላችሁም ለማለት ይመስለኛል፡፡ እናም የናዝሬት ልብስ ሰፊዎች ስራቸውን አቋርጠው የምንፈልገውን በ40 ደቂቃ ውስጥ ሰፍተው ሰጡን፡፡ ከዚያ ወደ መተሃራ ተጉዘን እሱን ቀረፃ ጨርሰን ስንመለስ፣ በህይወቴ ውስጥ ወደ አንድ ነገር ስሸጋገር ታውቆኛል፤ እጅግ የበዛ የአገር ፍቅርና የእግዚአብሔር ኃይል በእለቱ በውስጤ ተገልጿል፡፡ የናዝሬት ልብስ ሰፊዎች የሰፉበትን ልንከፍል ስንል፣ እምቢ አንቀበልም አሉ፡፡ ጨርቁን ገዝተን ሰጠናቸው፤ የአገልግሎት አልጠየቁንም፤ እንዲያውም “የበረከቱ ተካፋይ እንሁን” ነው ያሉት፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ይህቺ ናት፤ የተባረከችና የተባረከ ህዝብ ያለበት፡፡
ምን ያህል ወጪ ወጣበት ፊልሙ?
እውነት ለመናገር ወጪው ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም፤ ይህንን የሚያውቀው ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰሩ ኢቢኤስና ወኪሉ ታጠቅ ክፍሌ ነው። ታጠቅ ግን በጣም ተባባሪ፣ ለስራው ፍቅር ያለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ስራዎች እንዲሰሩ የሚፈልግ ልጅ ነው፤ ቤት ድረስ አንኳኩቶ “እባካችሁ አሪፍ ስራ እንስራ” የሚል የሚገርም ልጅ ነው፡፡ የኔን ንጭንጭ ችሎ፣ ለዚህ መብቃታችን ደስ ይለኛል፤ አመሰግነዋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስራ ስትሰሪ አለመገደቡ፣ የተለየ አሪፍ ባህሪው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ይሄን እሰራለሁ ብለሽ ካሳመንሽ በቃ ይደረጋል፤ ባህር ዳር ልንሄድ ነው ሲባል ለሁሉም የቡድኑ አባላት የአውሮፕላን ትኬት ገዝተው ያቀርባሉ፤በጣም በፍጥነት ለጥያቄሽ መልስ ይሰጣሉ፤ ይሄ በጣም የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡
በዚህ ፊልም ምክንያት ሶስት የውጭ አገር ጉዞዎችን ሰርዘሀል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
እውነት ነው! አንዱ ቡርኪና ፋሶ፣ ዋጋድጉ የሚካሄደው ፔስፓኮ ፊልም ፌስቲቫል ላይ መታደም ነበረብኝ፡፡ ‹‹ፍሬ›› የተሰኘው ፊልሞችን በፌስቲቫሉ ላይ እጩ ነው፡፡ እንደማልሄድ ቀድሜ አሳውቄ ስለነበር፣ እዚያ አገር የታተመ መፅሄት ‹‹የማይገኘው ሰለብሪቲ›› ብሎ መፅሄቱ ላይ አውጥቶኛል፡፡ ‹‹ፍሬ›› ፊልምን ስንሰራ CNN ላይ ቃለ ምልልስ ነበረኝ፤ በዚህ ቃለ ምልልስ “ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ሺህ ዘመን ታሪክ ያላት ስለሆነች በፊልም ሙያችን ለዓለም አውጥተን የምናሳየው ብዙ ታሪክ አለን” ብዬ ነበር፤ ስለዚህ ከቡርኪናፋሶ  ስቀር፣ ያንን አንዱን እያደረግኩት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላው ግብፅ፣ አንዱ ደግሞ እስራኤል ነው ጉዞው የተሰረዘው፡፡
በፊልሙ ውስጥ ብዙ ገፀ ባህሪያት አሉ፡፡ የተወኑት ግን ከስድስት አይበልጡም፡፡ ነገሩ እንዴት ነው?
ይሄ የሚገርመው የፊልሙ ክፍል ነው፡፡ አንድ ሰው እንደ አስር ገፀ ባህሪ እየተጫወተ ነው የሰራነው፡፡ ሜክአፕ አርቲስቷ፣ ኮንቲኒቲ፣ ዲዛይነሯ፣ ሜክአፕ አርቲስቱና ረዳቱ፣ ፕሮዳክሽን ማናጀሩ ---ሁሉም ተውነዋል፡፡ ግን የእግዚአብሔር ስራ ስለሆነ እሱ ሀይልና ብርታትን፣ እውቀትን ይሰጣል፤ ተወጥተነዋል፡፡
በመጨረሻ ይህ ሀሳብ እንዲከናወን ዓለም ሳይፈጠር እቅድ ለነበረው፣ ምንም ለማይሳነው እግዚአብሄር ምስጋና ይድረሰው፡፡ በስራችን ውስጥ ያለ ምንም ማሰለስ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ለሰጡን፣ በስራው ላይ ለተሳተፉት በሙሉ የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ረዳት አዘጋጅ ተብለው የተጠቀሱት፡- የፊልሙ ቡድን አባላት በሙሉ ናቸው፡፡ ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡ እኛ የአጥንት ጥርስ ባናበቅልም፣ በወተት ጥርሳችን አቅም ሞክረናል፤ የተዋጣ የተሳካ ስራ ሰርተናል ብለን መመፃደቅ አይዳዳንም፡፡ ነገር ግን ጀማሪ መሆን ብዙ ነገር እንዳለው ከልምድ እናውቃለን። ስለዚህ ራሴንም ቡድኑንም ወክዬ የምናገረው፣ ከዚህ በኋላ በመፅሀፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች ታሪኮች ዙሪያ በጣም በርካታ ስራዎችን ልንሰራ እንደምንችል ነው። በርካታ ስራዎችን ሰርተን ለዓለም ማህበረሰብ ማሳየት እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን፤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 3990 times