Sunday, 30 April 2017 00:00

ወፍ በረር የጥበብ ጉዞ፤ ወደ “ከአድማስ ባሻገር”

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(2 votes)

 በትንሣኤ ዋዜማ ዕለት ቅዳሜ፣ ምናቤ ወደ አንድ መፅሐፍ ገጾች ጉያ ይመሰጋል፤ ወደ “ከአድማስ ባሻገር”፡፡ የበዓሉ ግርማ ውብ ድርሰት። ከዘለአለማዊ ማህፀን በተወለደችው፣ በዚያች ዕለተ ቅዳሜ…. ቅዳም ስዑር፣ የትንሣኤ ዋዜማ፣ የአበራ ቤት ፀጥ! ረጭ ብላለች፡፡ የመቃብር ዓይነት የዝምታ አዚም ነግሷል፡፡ “ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል….” በዓሉ ልብወለዱን የጀመረበት ገለፃ ፅልመታዊ ነው፡፡ “ከአድማስ ባሻገር” ከዚህ የዝምታ አዘቅት ካረመመበት ኦና የአበራ ቤት ይጨለፋል፡፡ ……
“…… አበራ የሚኖረው በመሥፍን ሀረር መንገድ፣ ከሾላው በላይ፣ ተስፋዬ ቀጄላ ቤት ፊት ለፊት ……” ገፅ (7…) ‘ከዚህ ከአበራ ቤት በመነሳት ለምን የጥበብ ጉዞ አላደርግም’ ስል አሰብኩ፤ ‘የት ብለህ ልታገኘው?’ የሚል ጥያቄ ከሌላኛው የአእምሮዬ ጠርዝ ብቅ አለ፡፡ ከተስፋዬ ቀጄላ ቤት ፊት ለፊት የሚል አሳማኝ ምላሽ በውስጤ አለፈ፡፡
ተስፋዬ ቀጄላ የምናብ ሳይሆን በእውን የነበሩ ነጋዴ ናቸው፡፡ የአምባሳደር ህንፃ ባለቤት፤ በደርግ ተወርሶባቸዋል፡፡ አንድ አብሮኝ የሚጓዝ ሰው ያስፈልገኛል፡፡
ለዳንኤል መኮንን ደወልኩላት፤ አብሮኝ ሊጓዝ ፈቃደኝነቱን ገለፀልኝ፡፡ …..
ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፔጆ መኪናው ፒያሳ ደረሰ፡፡ በቀጥታ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ ጉዞ ጀመርን፡፡
“…. የጉዟችን ፍኖተ ካርታ መፅሀፉ ነው - “ከአድማስ ባሻገር” …. በመጀመሪያ መሥፍን ሀረር መንገድ ላይ የተስፋዬ ቀጄላን ቤት ማግኘት… ከፊት ለፊት አበራ የተከራየበትን  ቤት … በመቀጠል አበራና ሀይለማርያም በትንሳኤ ዋዜማ ወደ ሜክሲኮ ገነት ሆቴል፣ ከዚያም ወደ …..”
ዳንኤል አቋረጠኝ፤ “… የተስፋዬ ቀጄላን ቤት ስለማግኘታችን እጠራጠራለሁ …. የመንገዶች ስያሜ በተለምዶ ነው - ዛሬም ‘የሺ ደበሌ’፣ ‘አበቤ ሱቅ’… የተለምዶ ስያሜዎችን እየተጠቀምን ነው….! “አፍሪካ ህብረት የት ነው?” ብለህ ብትጠይቅ፣ “ከቃሲም ወፍጮ ቤት ወረድ ብሎ” የሚል ምላሽ ነው የምታገኘው…” ዳንኤል መኮንን እያሽከረከረ መደስኮሩን ተክኖበታል….. ወደ ቀጨኔ መታጠፊያ ቅያስ ጠርዝ ላይ “መስፍነ ሀረር” የሚል የመንገድ ስያሜ ምልክት አነበብን፡፡ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ በሚወስደው መንገድ ጥቂት እንደተጓዝን፣ በተለምዶ ሾላው የሚባለው አካባቢ ደረስን፡፡ …….
“አበራ … የሚኖረው በመሥፍነ ሀረር መንገድ፣ ከሾላው በላይ፣ ተስፋዬ ቀጄላ መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት ….” ገጽ (7) ከፔጆዋ ወረድን፡፡… አንድን አዛውንት እጅ ነስተን …. “የተስፋዬ ቀጄላን ቤት ያሳዩናል….”
“…. ተስፋዬ ቀጄላ ካረፈ ስንት ዘመኑ! መኖሪያ ቤቱ እዚያ ….” ብለው በምልክት ጠቆሙን፡፡ በግንብ የታጠረ ሰፊ ቅፅር ያለው ቪላ ቤት ደረስን። ያጋጠመን ግን የግለሰብ መኖሪያ ሳይሆን ኤምባሲ ነበር፡፡ የፖላንድ ኤምባሲ፡፡ ቅስም የሚሰብር ሁነት ነበር፡፡ መጥሪያውን አንጫረርን፡፡ ጥበቃው በሩን ለአመል ከፈት አድርጎ …..
“ምን ነበር?”
“ይህ ቤት የማን ነው?”
“የፖላንድ ኤምባሲ ነዋ!”
“ከማን ተከራይተውት ….”
“በፊት ኪራይ ነበር፤ አሁን ግን ሸጠዋለች ……”
“ማናት እሷ ….. የሸጠችው?”
“… ማን ተስፋዬ ነበር የሚሏት…. የተስፋዬ ቀጄላ ልጅ!”
“ቢንጎ!” አልኩ በውስጤ …..
የተስፋዬ ቀጄላን ቤት በእርግጠኝነት አግኝተነዋል፤ ከዚህ ቤት “ፊት ለፊት” ነው፣ አበራ የተከራየበት ግቢ የሚገኘው፡፡ …… ወደ ፊት ለፊት መንገዱን ተሻገርን፡፡ ከፖላንድ ኤምባሲ (ተስፋዬ ቀጄላ ቤት)  ፊት ለፊት ወደሚገኘው ቤት አዘገምን፡፡  
በሩን አንኳኳን፡፡
በሩን የከፈቱልን ከማርጀትም አልፈው የጃጁ አሮጊት ነበሩ፡፡….
“ምን ፈልጋችሁ ነው?”
“የሚከራይ ቤት!”
አሮጊቷ ከሌላ ፕላኔት የመጣን ይመስል፣ በግርምት አፈጠጡብን::
“…. እዚህ ግቢ በፍፁም የሚከራይ ቤት የለም …... ጥንት ድሮ ድሮ ….” አሉ አሮጊቷ፤ስለ ኦሪት ዘመን የሚያወሩ ይመስል፣ በሀሳብ ወደ ሩቅ ዓመታት ተጉዘው …..
“… ብላታ! መሀል ፒያሳ ቤት ስለነበራቸው፣ ይህንን ቤት ለመንግስት ሰራተኞች አከራይተውት ነበር…. ደርጉ ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ለቀዋል… ብላታም የራሳቸው መኖሪያ አድርገውታል…..”
አበራ ከእነዚህ የመንግስት ሰራተኞች፣ አንዱ ተከራይ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደዚያ ግቢ አማተርኩ። ከዚህ ግቢ ነበር የ”አድማስ ባሻገር” ተረክ ጅማሬ፣ በትንሳኤ ዋዜማ በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ወደ መፅሀፉ መለስ እንበል፤ “… እንደ ጫማህ መጣመሙን ተወውና ገነት ሆቴል ሄደን ብናመሽ፣ በዛሬ ሌሊት ክርስቶስ ከመቃብር ሲነሳ ተኝቼ ላንብብ ማለት መናፍቅነት ይመስለኛል….” (ገፅ 27) አበራ ነበረ፤ ለሀይለማርያም…
እናም ቁልቁል ወደ ሜክሲኮ፣ ወደ ገነት ሆቴል አመሩ - በከርካሳዋ የአበራ መኪና…..
እኔና ዳንኤልም የእነ አበራን ዱካ ተከትለን፣ ገነት ሆቴል አመራን፤ ዳንኤል ፔጆዋን ጥግ አቆማት፡፡ ወደ ገነት ሆቴል አዳራሽ ገባን፡፡ ፈረስ የሚያስጋልብ ሰፊ አዳራሽ፡፡ ፍፁም ፀጥታ አዳራሹ ላይ ነግሷል፡፡ አበራና ሀይለማርያም ወደ አዳራሹ በገቡበት ወቅት ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነበር፤….
“…. የብርጭቆና የጠርሙስ ቻቻታ፤ የጡሩንባው ኡኡታ … የህዝብ ጋጋታና ግፊያ፣ የመጠጥ ሽታና ጉም ከመሰለው የሲጃራ ጢስ ጋር ተደባልቀው የገነት ሆቴልን የዳንስ አዳራሽ ምድራዊ ገሃነም አስመስለውታል ….” ገፅ (30)
…. አበራና ሀይለማርያም እዚህ ቀውጢ አዳራሽ ተሰይመው አልኮል እየተጎነጩ ሳለ፣ ገድሉ አሰግድ ሹክክ እያለ ደርሶ፤ “ፅዋችሁን የምታነሱት ለራሳችሁ ጤንነት ነው? ወይንስ ለክርስቶስ ከሙታን መነሳት?” ገጽ (34)
…. በዚህ ኦና ሙት አዳራሽ የገድሉ ድምፅ እንደ ገደል ማሚቱ፣ ከግድግዳው ጋር እየተጋጨ በህሊናዬ አስተጋባ ……
ስለ ገድሉ በዛብህ ሳስብ፣ ሉሊት ከተደበቀችበት ስውር ዓለም ብቅ አለች፡፡ ሉሊት ታደሰ፡፡ ጠይም ጣኦት፡፡ እዚህ አዳራሽ ከአበራ ጋር ሲደንሱ፣ በእዝነ ህሊናዬ በገሃድ ታዩኝ …. የሉሊትን ዛቻ በዚያ ቀውጢ የዳንስ አዳራሽ ለምን አንሰማውም….
“… እንኳን አንተና ማንም ሱሪ የታጠቀ ወንድ፣ ሜዳ ላይ ጥሎኝ ሊሄድ አይችልም! አንተ ማን እንደሆንክ አውቃለሁ …. መጀመሪያ ትምህርት ሚኒስቴር፤ ከዚያም በኋላ ማስታወቂያ ሚኒስቴር፤ አሁን ደግሞ የምትሰራው አገር ግዛት ሚኒስቴር ነው! አይደለም ….” ገፅ (42)
አበራ ማለት እንዲህ ነው፤ ከመስሪያ ቤት፣ መስሪያ ቤት እየተንጦለጦለ፣ የባከነ ህይወት የሚገፋ ላጤ፡፡ ምክንያቱም በአያሌ ስነ-ልቦናዊ ውጥንቅጥ የተተበተበ ነው፡፡ ባለቅኔ ደራሲ ወይም ሰዓሊ የመሆን ፍላጎቱ ውስጡ ተቀብሯል፡፡ እናም ነፍሱ ሁልጊዜ እንደቃተተች ነው፡፡ በዓለም ላይ ቦታውን፣ መድረሻውንና ማንነቱን ስላላወቀ፣ የመንፈስ እረፍት የለውም፡፡
…… የአበራን ውሉ የጠፋ ህይወት እያሰላሰልኩ ሳለ፣ ዳንኤል፤ “ከዚህ ኦና አዳራሽ እንውጣ” አለኝ።……
አበራም ለሀይለማርያም “እንውጣ” እያለው ነበር….. ስቃይ ላይ ነበር፤ፋታ የማይሰጥ ስቃይ፡፡ ሉሊት የጫረችበትን የወሲብ ጣር ስቃይ ለማብረድ ተጣድፏል - እናም ገነት ሆቴልን ለቀው ወደ ገዳም ሰፈር…….
“በአዲሱ ቄራ መንገድ ወደ ላይ ወጥተው፣ ሜክሲኮ አደባባይን ወደ ግራ ትተው ……. ወደ ቸርቸል ጎዳና አመሩ” ገጽ (44)
እኔና ዳንኤልም በምታቃስተው ፔጆ፣ ቸርቸል ጎዳና ደርሰናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ዋና መ/ቤት ጋ ስንደርስ፣ ዳንኤል የመኪናውን ፍጥነት እያቀዘቀዘ …. ኢምግሬሽን መ/ቤትን እያሳየኝ …..
“ኢምግሬሽን የቀድሞ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ነበር ….. የአበራ መስሪያ ቤት እግረ መንገዳችንን ለምን ጎራ አንልም”
ወደ ግራ ታጥፈን ቁልቁል ወደ ኢምግሬሽን፣ የቀድሞ የአገር ግዛት ሚኒስቴር አመራን፡፡ …… በጥበቃ ጓዱ ቅን ትብብር ወደ ውስጥ ዘለቅን። መግቢያው ላይ ሁለት መንታ የሚመስሉ ሥነ ውበታቸው የሚማርክ፣ ዘመን ያስቆጠሩ ህንጻዎች ጀርባ፣ አያሌ ቢሮዎች በተዋረድ ተኮልኩለዋል፡፡ ከቢሮ ቢሮ ዞር ዞር አልን፡፡
ዳንኤል፤ “እነዚህ ቢሮዎች የአበራን የሥራ ባልደረቦች እነ ተሰማ ደጀኔን፣ ባልቻ ዋቆ፣ በቀለ ሮባ ያስታውሰኛል …. ከቢሮ ቢሮ የሚያዞራቸው የህይወት አባዜያቸው” ….  ወደ መፅሀፉ መለስ እንበል፡- ከተሰማ ደጀኔ እንጀምር፤ ከቢሮ ቢሮ ስለሚያዞረው አባዜ ….
“…. ተሰማ ደጀኔ ከቢሮ ቢሮ እየዞረ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ሰው በተለይ ደግሞ ስለ እናቱ ማውራት አለበት፤ ሳያወራ የዋለ እንደሆነ ይፈነዳል!” ገፅ (68)
ባልቻ ዋቆ
“…. ባልቻ ከቢሮ ቢሮ የሚዞርበት ምክንያት አለው፤ አራጣ አበዳሪዎች፣ ፖሊሶች፣ ቤት አከራዮች….. መጠጥ ሻጮችና ገንዘብ ያበደሩት አያሌ ሰዎች ቢሮው አያስቀምጡትም ….” ገፅ (69)
በቀለ ሮባ …
ስለ ራሱ የሚለውን እንስማው ……
“…. ፋሲካን ያሳለፍኩት አንዲት አገር አሸነፈች ከምትባል ኮረዳ ጋር ነበረ … ታዲያ ምን ይሆናል እያለቀሰች ስቃይዋ ደስታ ላይሆነኝ….” የማያስለቅሳት ሴት የለችም፤ ይህንኑ ጀብዱ ለማውራትና በየጊዜው የሚገዛውን ልብስ ለማሳየት ከቢሮ ቢሮ መዞር ግዴታው ነው….” ገፅ (71)
ወደ ጉዞአችን የመጨረሻ ምዕራፍ እየተቃረብን ነው፤ ወደ ገዳም ሰፈር፡፡
“… አበራ …. ወደ ዮሀንስ ቤተ-ክርስቲያን በሚወስደው ቁልቁለት ትንሽ እንደተጓዘ እንደገና ወደ ግራ ታጥፎ ወደ ገዳም ሰፈር ገባ ….” ገፅ (45)
እኔና ዳንኤልም ገዳም ሰፈር ደርሰን… አንድ ሰቀላ ቡና ቤት ገብተን ተሰየምን፤ በጥም ተቃጥለን ነበረ…. ቢራ ደጋገምን፡፡ በተለይ ዳንኤል መኮንን፣ በውሃ ጥም እንደተቃጠለ የበረሃ ግመል፣ በፍጥነት ስድስት ቢራ ጨልጧል…..
የአበራ ጥማት ግን ሌላ ነገር ….. ሉሊት የፈጠረችበት የወሲብ ስቃይ ጣር፡፡ …..
“….. አበራ ዳሌዋ ሰፋ ብሎ የታየውንና ሲገባ እንደ ሌሎቹ ወከክ ያላለችለትን ሴት መርጦ …. እጅዋን ይዞ እየጎተታት ወደ ውስጥ ገባ…..” ገፅ (47)
እነሆ በዚያች የፋሲካ ዋዜማ፣ ቅዳም ስዑር፣ ውድቅት ቢሆንም አበራና ኃይለማርያም ከገቡበት ቡና ቤት አልወጡም፡፡ …..
“… ሶስቱም ሴቶች ከጓዳ ተከታትለው ወጡ። ከመካከላቸው አንዷ የያዘችውን መሶብ አምጥታ ኃይለማርያምና አበራ ፊት አኖረች፡፡ አራቱም ሴቶች ቀረቡ፤ ከባንኮኒ ኋላ ቆማ የነበረችው ሴት ‘ብሉ እንጂ አብረን እንፈስክ፤ እንኳን ፆመ ሉጓሙን ፈታላችሁ’ አለቻቸው፡፡ ህዝበ ክርስቲያንም አብረው ቆረሱ፤ ፋሲካም ሆነ” ገጽ (50 ከአድማስ ባሻገር)      

Read 735 times