Sunday, 30 April 2017 00:00

“እራስን በራስ” ኤልሳቤጥ እና ኤልሳቤጥ “ና ኑ ሳይለይለት ከገብርዬ ቤት”

Written by  በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(1 Vote)

ማለፊያ የሥነ-ጥበብ ትርዒት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚተዳደረው (?) የገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል ሞደርን አርት ሙዚየም ውስጥ ከሚያዝያ 13 ጀምሮ ለዕይታ ክፍት ሆኗል፡፡ “እራስን በራስ” የትርዒቱ ስያሜ፤ ሠዓሊ ኤልሳቤጥ ሃብተወልድ፣ የትርዒቱ አቅራቢ፤ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ደግሞ የትርዒቱ አጋፋሪ ናቸው። በዚህ ዓመት እስካሁን በከተማችን ከቀረቡ ትርዒቶች መሃከል ሁነኛና ፋና ወጊ ትርዒት ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ልምዴን አምነዋለሁ፡፡ እንደ ሥነ-ጥበብ  አጋፋሪ  ደግሞ ትርዒቱ የቆሰቆሳቸው ፋሞችን ገላልጬ የሥነ-ጥበብ ማህበረሰቡ፣ ማንኛውም ተመልካች፣ አንባቢ፣ የሚመለከተው አካልና ዜጋ ሁሉ ሊነጋገርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ  አቅሜ የፈቀደውን ለማለት ብዕሬን አንስቻለሁ፡፡ “ባትዋጋ እንኳ በል እንገፍ እንገፍ....” ይታሰባችሁ፡፡  
የትርዒቱ የመጀመሪያ ክፍል የኩልኮላ (Installation) ስራዎች ያሉበት፣ በሁለቱ የሙዚየም በሮች እንደገባን የምናገኘው ነው፡፡ ይህንን ክፍል ዘልለን በስተግራ ወዳለውና የቪዲዮ ሥራ በፕሮጀክተር ወደሚታይበት ብቸኛ ክፍል ልንሄድ እንችላለን፡፡ አልያም በስተቀኝ ስንሄድ የኩልኮላ ስራ ያለበት ክፍልና በትይዩው ሁለተኛ የቪዲዮ ሥራ ያለበት ክፍል ልንሄድ እንችላለን፡፡  እነዚህ ሁለት ክፍሎችንም ዘልለን በስተቀኝ ጥግ ወዳለው ሦስተኛ የቪዲዮ ስራ ወደቀረበበት ክፍል ልንሻገር እንችላለን፡፡ ምርጫው የተመልካች ነው፡፡ ትርዒቱ ጅማሮና መቋጫ እንደሌለው ተሰምቶኛል፡፡ ደስ ይላል፡፡ ደግሞ እንደዚያ ነው፡፡ ሰዓሊዋን ከየትና መቼ ነው የጀመርሽው? ብትሏት፣ እንደ ጅረት የሚፈስና የሚፈስ እንጂ እንደ ቧንቧ የሚከፈትና የሚዘጋ መልስ የምትሰጣችሁ አይመስለኝም፡፡ በየክፍሎቹ የቀረቡ ሥራዎችን በማጣጥምበት ወቅት እጅግ ዘና የማለት ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ ሰዓሊዋ በሰራቻቸው ሥራዎች ያሰፈነችው ፍትህ ለውስጤ ሰላም ይሰጡኝ ነበር፡፡ ሥነ-ጥበብን በነቢብ ለመረዳት የሚጓጓና ትርዒቱን ለመረዳት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲያስጨብጠው ለሚፈልግ አንባቢ ይኸ ጽሑፍ ጠቀሜታ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ሆኖም እንዲህ የሚያስብለኝ ምክንያቶችን የማወቅ ፍላጎት (curiosity) ላለው አንባቢ ግን ትርዒቱን የማየት ፍላጎት ቢያጭርበት ብዬ እቀጥላለሁ፡፡ ኦላፍር ኤልያስን የተሰኘ ጥበበኛ፤ ‹‹contact is content›› የሚለው ነገር አለ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ከአንድ የሥነ-ጥበብ ስራ ጋር በስሜት፣  በምክንያት፣ በነፍስ ወይም በመንፈስ አልያም ልንገልፀው በማንችለው አኳሃን ከተገናኘን፣ ይዘት ወይም ነገረ ሀሳብ፣ በዚሁ ሁሉ መሀል ሊገኝ ይችላልና ትርዒቱን ስመለከት የተሰማኝንና ያዳበርኩትን ልምድ ‹‹contact is content›› ስል እገልጸዋለሁ፡፡
ትርዒቱን በአጋፋሪነት አይን ሳየው የሚከተሉት ነጥቦች ቢቃኙ እላለሁ፡፡ የሰዓሊዋ ታላቅ ስኬት እይታዊ መዝገበ ቃላቷን በግኝት ደረጃ ማግኘቷ ነው። እንሰት ሁላችን የምናውቀው ተክል ነው። ሠዓሊ ኤልሳቤጥ፤ እይታዊ መዝገበ ቃላቷን የገነባችው በዚህ ተክል ዙሪያ ነው፡፡ በተለይ ከእንሰት ግንድ ከወፊቾ የሚሰራው የጀበና፣ የማሰሮና ወዘተ … ቁሶች ማስቀመጫ የሆነው ማቶትን ነው እንደ እይታዊ ቃል የተጠቀመችበት፡፡ ሶስት የተለያየ ርዝመት ያላቸው ቪዲዮችን ተጠቅማም ማቶት እንዲያወራ፤ ወፊቾ ሀሳቧን እንዲያዳውር፤ ስሜቷን እንዲገልፅ ስትገምድ ስትጠቀልል፣ ስትፈታና ስትሰነጥቅ እናገኛታለን። እናገኛታለን ስል ይህንን ሁሉ ስታደርግ፣ እኛ ስንመለከትና ስንጠይቅ፣ ጥያቄና መልስ ውስጥ ትከተናለች፤ በዚህ ጥያቄና መልስ ሠዓሊዋንና ምክንያቶቿን እናገኛለን ማለቴ ነው፡፡ እኛም ስለ ማቶት ወፊቾና እንሰት እናስባለን ‹‹contact ወደ content›› ወይንም ፈልገን የምናገኘው መልስ ይዘት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ መሐሉን አልናገርም፡፡ ሂዱና ፈልጉ፡፡ ታገኛላችሁ፡፡ እመኑኝ፡፡
ሠዓሊ ኤልሳቤጥ ሀብተወልድ፤ ማቶት ምርጫዋ ሆኖ አተኮረችበት እንጂ ማለቂያ የሌለው ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ የሚፈጥርላት ግኝት እንደተጎናፀፈች ግልፅ ነው። በዚህ ትርዒት እንደ ቅምሻ ማቶት ላይ ማተኮሯ ሊያስተቻት ባይችልም፣ የዳበረ እይታዊ ቋንቋ ወደ ሚቸራት የእንሰት ተክል ትኩረቷን ብትገራ፣ ጥልቅ ወደ ሆኑ ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ምርምሮች ውስጥ መዝለቅ ያስችላታል ባይ ነኝ፡፡  ለምሳሌ እንሰት በማንኛውም የሀገራች የአየር ሁኔታዎች መብቀል ይችላል። ድርቅን የመቋቋም እጅግ በጣም ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ በ1977 በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ መትረፍ የቻለው ቆጮን ተጠቅሞ ነው። አሁን በየሁለት ዓመቱ ለሚዘምትብን ድርቅ ምላሽ ሰጪ እንዳይሆን ያከላከለን ምንድን ነው? ስለ ቆጮ ከአባቴ አንደበት ከሰማኋቸው መሀከል፣ ሁለት የሰሜን ሰዎች ወደ ደቡቡ ወርደው ቆጮ በአይብና በክትፎ ቀርቦላቸው የተባባሉትን እንካችሁ፡-  ቆጮን ከአይብና ክትፎ እያጣበቁ ረሃባቸውን ካስታገሱ በኋላ ቆጮን ለብቻው ሞከሩት፡፡ በጥርሶቻቸው መካከል እየተንገዋለለ ወደ ጉሮሮ አልወርድ ቢላቸው አንደኛው ለሌላኛው፤ ‹‹ ኸረ ይኼ ነገር ጨዋ ነው፤ ያለ አሽከር አይገባም›› እንዳለው ይነገራል፡፡  ይህ ብዙ ርቀት ሊያስኬድ የሚችል ምርምር ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡ ከደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ጋር ስለ ትርዒቱ ስናወጋ፤ ከእንሰት ግንድ የሚገኘው የተለያየ የርጥበት ደረጃ ያለው ወፊቾ፤ በጉራጌ አከባቢ ሴቶች የወር አበባና የወሊድ ንፅህናን ለመጠበቅ ይጠቀሙበት እንደነበር ነግሮኛል፡፡ እንሰት አንዳች የሚጣል ነገር የሌለው ተክል ነው፡፡ ሠዓሊ ኤልሳቤጥም ሆነ አጋፋሪዋ ዶ/ር ኤልሳቤጥ የትርዒቱን ጥልቀት ይበልጥ ጥልቅ የሚያደርጉ ጥናትና ምርምሮች ለማድረግ ግዜ ቢወስዱ ወደ ፅንሰ ሀሳባዊ አቀራረብ ለመውሰድ የተደረገውን ሙከራ ያጠናክርላቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ቅምሻ ቢሆንም ቀምሶ ዝም ማለት ስላልቻልኩ ነው ይህችን ተጓዳኝ ሀሳብ ያነሳሁት፡፡
ኤልሳቤጥና ኤልሳቤጥ፣ ሠዓሊና አጋፋሪ ብቻ ሳይሆን ሠዓሊ አጋፋሪን ምን ያህል መኮርኮር፤ አጋፋሪ በሠዓሊ ሥራ ተመርኩዞ ፅንሰ ሀሳቦችን እንዲቀርፅ፣ ቲዎሪዎችን እንዲያዳብር በማድረግ አንዱ ለሌላኛው መመገብ የሚችለው የታየበት ትልቅ ትርዒት ነው ‹‹እራስን በራስ››፡፡ ትርዒቱ ደረጃውን የጠበቀ የካታሎግ ህትመትም አለው፡፡ በካታሎጉ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ የአጋፋሪነት መደንግጓን ሰፋ ባለ ሀተታ አቅርባለች፡፡ ሠዓሊዋም ባልተሽሞነሞነና የተመስጦዋን ጥግ በሚያስረዳ ሥነ-ጥበብ፣ በምትሻው ንጽህና የታጀበ ግልፅ መደንግጓን አካትታለች፡፡ ፋናዬ ገ/ህይወትና በማካራሬ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት እጩ የሆነው ስሜነህ አያሌው ከሠዓሊዋ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በመመስረትም ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ማለፊያ ድግስ ነው፡፡ ድግሱ የተሰናዳበትና የተከወነበት ሙዚየም አጋፋሪ የሆነችው ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮርጊስ፤ በካታሎጉ ካቀረበችው ጽሑፍ ውስጥ ትርዒቱ በተለይ ዘመናዊነት (Modernism) እና ድህረ ቅኝ ግዛት (post colonialism) ከቀረቡት ሥራዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያዛመተችባቸው የፅንሰ ሀሳብና የቲዮሪ ዳራዎች ሊሰናኙልኝ ባለመቻላቸውና በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ በቂ ንባብ አዳብሬ መመለስ እስክችል ለዛሬ አልፈዋለሁ፡፡ ሆኖም የሀገራች ዘመነኛ ሥነ-ጥበብ የመተንተኛ ማዕዘናት (frames of analysis)  እንዲሁም የሂሳዊ ትግበራ መልኮች (topographies of critical analysis)  የሌሉት እርቃኑን የቆመ፣ ኦና ቤት እንደሆነ ዶ/ር ኤልሳቤጥ በጽሑፉ መግቢያ የጠቀሰችው የሚያንገሸግሽ ‹አሉ-በ-አሉ-በል-ታ› ወይም አሉባልታ ስላስመረረኝ እንዲህ እተቸዋለሁ፡፡
የናይጄሪያ ተወላጁና በአለማች ከሚገኙ ኮከብ አጋፋሪዎች መሀል አንዱ የሆነው ኦክዊ ኤንዌዞርን ነው፤ ዶ/ር ኤልሳቤጥ የምትጠቅሰው፡፡ የአጋፋሪነት ሙያ በማዕቀፍ ሊያካትታቸው ከሚገቡ ነጥቦች መሀከል ‹‹የአፍሪካዊን ሠዓሊ ሥራዎች ለመረዳት የሚያስችል የተሻለ እውቀት እንዲሁም ውስብስብ ግንዛቤን ማዳበር›› ከአንድ አፍሪካ ውስጥ ከሚሰራ አጋፋሪ የሚጠበቅ እንደሆነ ያትታል፡፡ የትርዒት ማሳያ ቦታዎችም ሥነ-ጥበባዊ ሂስ ያነገቡ ሥራዎች፣ ታሪካዊ ትንታኔዎች እና ቲዎረቲካል ሀሳቦች የሚንፀባረቁበት እንደሆነ ያስገነዝባል፤ ኦክዊ፡፡ በዚህም የትርዒት ማሳያ፤ የምስል፣ የሥዕል፣ የዕቃ፣ የሀሳብ ትርጉምና አስፈላጊነት ምሁራዊ ዘረ-መሎች የሚፎካከሩበት እና የሚጋጩበት እንዲሁም አንዳች ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ የሚፈጠርበት ቦታ እንደሚሆን ኦክዊ ያስረግጣል፡፡  
ዶ/ር ኤልሳቤጥ በሚቀጥለው አንቀጽ  የዚህ ዓይነት አውድ በኢትዮጵያ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ ውስጥ በባትሪ ተፈልጎ የማይገኝ ይልቁንስ ትርዒት ማሳያ ቦታን  የመፍጠር ድግግሞሽን መከሰት እንጂ ሥነ-ጥበብ የመተንተኛ ማዕዘን ወይም አውታር ማበጀት ያልቻሉ እንደሆኑ ፅፋለች፡፡ ዘመንኛ የአፍሪካ  ሥነ-ጥበብ ምሁራን ለሚያበጁት ከቅኝ ግዛት ነፃነት በኋላ ለተነሱ ፍልስፍናዊ አስተምህሮቶች ቅርብ የሆኑ ስራዎችን የሚሰሩ ሠዓልያን በሃገራችን የሉም ላለማለት ግን እንደ ሠዓሊ ኤልሳቤጥ ሃብተወልድ ያሉ ጥቂት ሠዓልያንን ማውሳት እንደሚቻል ማስተባበያ አቅርባለች፡፡ ገሎ ማዳን፡፡ ያውም በጅምላ ጨራሽ አስተያየት ሁሉን ደምስሶ፣ ጥቂት ከዕልቂት ያመለጡ እንዳሉ መናገር ምፀት ይመስለኛል፡፡ ስላቅ አንጂ!
ይህ ለምን ሆነ? የዶ/ር ኤልሳቤጥ መላምት፣ ሃገራችን በቅኝ ግዛት ያለመገዛት ነጠላ ታሪክ ባለቤት መሆኗ የቅኝ ግዛት፣ የድህረ ቅኝ ግዛት ታሪክ እንዲሁም ከአፍሪካውያን ሠዓልያን ጋር የመገናኛ መረብ የሌላት በመሆኗ የዘመንኛ የአፍሪካ ሥነ-ጥበብ ጥልቅ የውይይት መድረኮችን (Discourses) እና ሂሳዊ ትግበራዎች (critical practices) የቀረጹ ምሁራዊ አውዶች ላይ ሥነ-ጥበባችን ‹አለሁ› የማለት አቅም አለማሳየቱን ምክንያት መሆኑን መላምት ታቀርባለች፡፡ የተንሻፈፈ ልክነት ቢኖረውም ይህ ማለት ዘመንኛ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ለሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምቀፋዊ ጥልቅ የውይይት መድረኮች (Discourses) የሚጋብዝ አቅም የለውም ማለት ነው? በጅምላ ጨራሽ አስተያየት እንዲሁም የአፍሪካ ታሪካዊ ዳራን ከኢትዮጵያ ጋር በሚጣረስ ዓውድ በማነፃፀር፣ የያዝነው ሁሉ ሳይፈተሽ፣ ሊንኳሰስ ይገባል? የኢትዮጵያ ዘመንኛ የሥነ-ጥበብ ታሪክ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረኮች ቦታ ያገኝ ዘንድ ያለንን መርምረን ማቅረብ እንጂ ወደ ኋላ ተመልሰን ቅኝ ልንገዛ አንችልም፡፡ እርግጥ ነው ዘመንኛም ሆነ ዘመናዊ ሥነ-ጥበባችን ወደ አህጉራዊ ጥልቅ የውይይት መድረኮች ጎራ ማለት አልቻለም፡፡ ይህ ደግሞ የጥናትና ምርምር ጉድለት እንጂ የሥነ-ጥበባችን አይደለም፡፡ ሠዓሊ ኤልሳቤጥ የወለደችው ሀሳብና አያሌ ዘመንኛ ሠዓሊዎችም የሚሰሩባቸው ሀሳቦች ከኢትዮጵያ መነሳቱ፣ አፍሪካን በምን መልኩ ነው የሚያገልለው? ይህ ውሃ ልኩን ያልጠበቀ የዶ/ር ኤልሳቤጥ መላምት፣ የሃገራችን ሠዓልያን ያመቁትን ወርቅ እንደ መዳብ ሳይሆን እንደ አመድ ከመቁጠር የመነጨ ነው እላለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ሠዓሊ ኤልሳቤጥ በስራዎቿ፣ የዶ/ር ኤልሳቤጥን ገታራ ጽንፍ አንበርክካ፣ ለአመታት ለኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን ዝግ የሆነውን፣ በከርታታው። ታላቁ ሠዓሊና ገጣሚ ገብርክርስቶስ ደስታ ስም የተሰየመውን ሙዚየም ቁልፍ ለመክፈት በመቻሏ፣ እንኳን ደስ ያለሽ ለማለት እወዳለሁ!
የሞደርን አርት ሙዚየም ገብረክርስቶስ ደስታ ሴንተር በ2005 እ.ኤ.አ ከተቋቋመ ጀምሮ ሶስት ዳይሬክተሮች መርተውታል፡፡ ረዥሙ የአመራር ዘመን በዶ/ር ኤልሳቤጥ ሥር ነው፡፡ ሙዚየሙ ሹም አስተዳደር የለውም፡፡ ዳይሬክተርም አጋፋሪም አስተዳዳሪም ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ናት፡፡ የሚመራው በአጋፋሪነት የውሳኔ ነፃነት (curatorial Authorship) ነው፡፡ የሙዚየሙ ተጠሪ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ፣ የሙዚየሙ የመተዳደሪያ ደንብ የአጋፋሪነት ውሳኔ ነፃነትን የሚጠብቅ መሆኑ፣ ለሙያና ለሙያተኛ ያለውን ክብር ያሳያል፡፡ ግን እስከ ምንና ለምን? ሙዚየሙ የዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት መስጫ እንደመሆኑ በተለይ በዩኒቨርስቲው ተምረው በዘመንኛ ሥነ-ጥበባችን አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉ ሠዓሊያን እንዲሁም መምህራን የቤታቸውን በር መክፈት ተስኗቸው ጎተ ኢንስቲትዪትና አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ የሚያንኳኩበት ሚስጢር ምን ይሆን? ሠዓሊ ኤልሳቤጥን ከሌሎች ሠዓልያን ላወዳድራት ፍላጎት የለኝም፡፡ አግባብም አይደለም፡፡ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታ በሩን ከፍታለች፡፡ ይህን በር መክፈት ሞክረው የተዘጋባቸው ሠዓልያንስ ምን አሳማኝ ነጥቦች ተሠጥቷቸዋል?
ሠዓሊ ታምራት ገዛኸኝ ከሁለት ዓመት በፊት በሙዚየሙ ሥራውን ለማቅረብ ሞክሮ፣ ዕቅዱን ለማቅረብ እንኳ ያልቻለበት ሁኔታ አለ፡፡ የሥራ ዕቅዱን (Proposal)  ለመመልከት ፈቃደኛ ያልሆነች የወቅቱና ያሁኑ የሙዚየሙ ኃላፊ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ናት፡፡ ይህ ጉዳይ በሥነ-ጥበባት ኮሌጅ ቢሮ ቢቀርብም መፍትሄ ሳይገኝለት ተድበስብሶ ነው የታለፈው፡፡ የሠዓሊ ታምራት ገዛኸኝ አቤቱታ ተረስቶ በምን አሰራር ነው ሙዚየሙ ሥራውን የቀጠለው? በወቅቱ በቃል የተሰጠው መልስ ሙዚየሙ የቡድን እንጂ የግል ትርዒቶችን ለማሳየት አይችልም የሚል ነው፡፡ ሠዓሊ ታምራት ገዛኸኝ በወቅቱ ያቀረበው (Proposal) ምን እንደሆነ ገልጦ ለማየት ፈቃደኛ ያልነበረ ሙዚየም፤ እንዴት ነው ሥራውን የሚሰራው? ሠዓሊው ሊያቀርበው የነበረው ሃሳብ ታምራትን ጨምሮ በ11 ሠዓሊያን ተመስርቶ ለስድስት ዓመታት የሃገራችንን ዘመንኛ የሥነ ጥበብ አቅም በአህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ደረጃ ሲያስተዋውቅና ሲያገናኝ የነበረው ነጻ አርት ቪሌጅ ለመልሶ ግንባታ ሲፈርስና ሠዓልያኑ ሲበታተኑ፣ ሠዓሊ ታምራት የነፃ አርት ቪሊጅ ጉዞንና ፋይዳ በኩልኮላ (installation)  እና በፎቶግራፍ ለማሳየት የወጠነበት ፕሮፖዛል ነበር፤ በሙዚየሙ ኃላፊ በዶ/ር ኤልሳቤጥ ለመታየት እንኳ ሳይበቃ ውድቅ የሆነው። ይህ ሃሳብ የትንተና ማዕዘናትና ሂሳዊ ትግበራ የለውም ለማለት የምትደፍር አይመስለኝም። ሠዓሊው ነፃ አርት ቪሌጅ በነበረበት ወቅትና ከዚያም በፊት ሲያደርገው እንደነበረው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራውን መስራት ቀጥሏል፡፡ ሆኖም በስደት ተንከራትቶ፣ ሙዚየሙ ፍሬ እንዲያፈራ ምክንያት በሆነው በሀገሩ ልጅ በተሠየመው ተቋም ባይተዋር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ እንዴት ታለፈ? ታምራት በእንጎርጎሮ ስንኝ ነበር ሁኔታውን ያለፈው!
እኔ ተከለከልኩ፤ አንተም ተከለከልክ፤
አንቺ ስትደመጭ እኔም ተደመጥኩ፤
ና ኑ ሳይለይለት ከገብርዬ ቤት፡፡
በግል ትርዒት ሳይሆን በጋራ ብቻ በሙዝየሙ ስራን ማቅረብ እንደሚቻል ነበር በወቅቱ የተናገረችው፡፡ በጽሁፍ ሳይሆን በቃል ስለነበር የተናገረችው ማንም ሊከስሳት አይችልም። በዩኒቨርሲቲ የሚተዳደር ሙዝየም፤ ህግጋቱን እንዳሻው መቀየር እንደሚችል ግን አሳይታናለች (የሠዓሊ ኤልሳቤጥ ስራዎች ብቁነት ሳይዘነጋ ማለቴ ነው)፡፡
ዶ/ር ኤልሳቤጥ ኦክዊን የጠቀሰችበትን ሙሉ ፅሑፍ ከድረ-ገፅ ፈልጌ አነበብኩት፡፡ የሚመቻትን ጠቅሳ የሚጠይቃትን ትታለች፡፡ መብቷ ነው፡፡ የፅሁፉ መደምደሚያ የአፍሪካዊ አጋፋሪ ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባው በጽንሰ ሃሳብና በቲዎሪ ደረጃ ሊቀረፅና ሊያንፀባርቅ የሚችል የአጋፋሪነት አቀራረብ እንደሚያሻን ያትታል፡፡ አንድ አጋፋሪ በአጋፋሪነት መስራት ብቻ ሳይሆን ቲዎሪቲካል ሞዴል፣ አዲስ ሥነ-ጥበባዊ ሞዴል ማበጀት የአፍሪካዊ አጋፋሪ ሚና ሊሆን ይገባዋል ይላል፡፡ ከዚህም ውስብስብ ምሁራዊ መሰረተ ልማት እየተገነባ፣ የዘመንኛ የአፍሪካ ሥነ-ጥበብን ለመተንተን፣ ለማሄስ፣ በታሪክ ሰነድ ለማቆየትና ለማሳየት ያስችላል ይላል፡፡
የሥነ-ጥበብ ትርዒቶች ይህን አይነት መልክ እንዲይዙ ከተደረገ ትርዒት የሚታይበት ቦታ የግለሰብ ሠዓልያን የግላቸውና የሠዓልያን ቡድኖች የጋራ እሳቤያቸውን የሚያራምዱበት መድረክ ይፈጠራል፡፡ ዶ/ር ኤልሳቤጥ የምትመራው ሙዚየም ይህን እያደረገ ከሆነ በምን አግባብ እንደሆነ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ማንኛውም የሥነ-ጥበብ ማህበረሰብ ይህን የመጠየቅ መብት ያለው ይመስለኛል፡፡ የለም ይህ የዩኒቨርስቲውና የኮሌጁ ጉዳይ ነው ከተባለም፣ የዩኒቨርስቲና የኮሌጁ ማህበረሰብ መብትስ እስከ የት ነው? እንደ አጋፋሪ ማን ምን እንደሰራና እየሰራ እንደሚገኝ የማጥናትና ትርዒቶችን የመከታተል ግዴታ ባይጣልበትም፣ ዶ/ር ኤልሳቤጥ በምን መልኩ ነው ትርዒቶችን የምትመርጠውና የምትጥለው?
ድህረ ሃተታ
ከላይ ያቀረብኩትን ጽሁፍ ካጠናቀቅኩ በኋላ በትርዒቱ ላይ የተደረገውን ውይይት አደመጥኩ። በሙዚየሙ አሰራር ዙሪያ “አልባሌ ዲስከሽኖች” መደረጋቸውን እንደሚያስታውስ የውይይቱ አስተባባሪ ተናግሯል፡፡ አልባሌ የተባለው ውይይት ሠዓሊ ታምራት መብቱን የጠየቀበት መሆኑ ነው፡፡ መብት መጠየቅ አልባሌ ከሆነ፣ መብት መከልከል ምን ሊባል ነው? ዶ/ር ኤልሳቤጥ፤ ሠዓሊ ታምራት “ለፈረንጅ ከሰሰኝ” ብላ ለውይይቱ ታዳሚያን ያላንዳች ሃፍረት ተናግራለች፡፡ መረጃዎች በኢሜይል ታትመው ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሠዓልያንና ቀራጽያን ማህበር ጉዳዩ ስለሚመለከተው፡ የጀርመን ባህል ማዕከል ሠዓሊው ሊያቀርበው የነበረውን ትርዒት ይደግፍ ስለነበር፡ የጀርመን ኤምባሲ ሙዚየሙ እንዲመሰረት ድጋፍ በማድረግና የዩኒቨርሲቲው ኮሌጅና አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ጉዳዩ በቀጥታ ስለሚመለከታቸው ግልባጭ ደርሷቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ በመካድ ጉድለቷን ለመሸፈን፣ ለፈረንጅ ከሰሰኝ ማለት ያሳፍራል፡፡ ታሪክንና ሃቅን ማንም ቢደብቅ ጊዜውን ጠብቆ መታወቁ አይቀርም፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሙዚየሙ ምስረታ ጋር ያላትን ቁርኝት በማንሳት በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት በድህረ ምረቃ ለምታስተምራቸው ኮርሶች ማሳያነት የሚውሉ ትርዒቶችን በሙዚየሙ እንደምታሳይ በግልጽ ተናግራለች፡፡ የዚህን አግባብነት ለዩኒቨርሲቲው፡ ለሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡና ለአንባቢ እተወዋለሁ፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ዕደ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ መካከከል ያለውን ልዩነት ምዕራባውያን ሊበይኑልን የሚሞክሩትን መቀበል እንደሌለብን በውይይቱ አንስታለች፤ ዶ/ር ኤልሳቤጥ። በዚያው አንደበቷ በአውሮፓና በዓለም ዙሪያ በአርት ሂስትሪ የፒኤችዲ ዲግሪ ያለው ሰው ብቻ ሞደርን አርት ሙዚየሞችን እንደሚመራ ትናገራለች፡፡ ይህ አይነቱ ከዕውነት የራቀ አጥር፣ የገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል ሞደርን አርት ሙዚየምን በርስትነት ይዛ ለመቆየት ያደረገችው አይደለም ቢባል እንኳ የምዕራባውያንን አካሄድ እንደ አስፈላጊነቱ ማንሳትና መጣል እንደምትችል ተረድቻለሁ፡፡ ለሃገራችን የሥነ-ጥበብ አቅጣጫ የሚበጅ ግልጽ አካሄድ ካላስቀመጥን ውይይታችንና ክርክራችን መቆም የለበትም፡፡ ባልጨርስም አቆማለሁ፡፡ የሚቀጥል ቢቀጥል የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ ቸር እንሰንብት!!

Read 1438 times