Sunday, 30 April 2017 00:00

7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው ምግብና መድኃኒት በህገ ወጥ መንገድ ሲገባ ተያዘ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ከተያዙት ነገሮች አብዛኛዎቹ ወደአገር ውስጥ እንዳይገቡ የታገዱ መድኃኒቶች ናቸው
6.7 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የምግብ የመድኃኒትና የመዋቢያ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መያዛቸው ተገለፀ፡፡
በተለያዩ መንገዶች የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የተለያዩ መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች፣ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦ እንዲሁም ልዩ ልዩ የመዋቢያ ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መያዛቸውን የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ይፋ አድርጓል፡፡
ከባለስልጣን መ/ቤቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፉት ዘጠን ወራት ብቻ በ18 የመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ለህብረተሰቡ ጤና እጅግ አደገኛ ናቸው የተባሉና የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ በተለያዩ መንገዶች ለብልሽት የተዳረጉ መድኃኒቶች፣ የታሸጉ ምግቦች የህክምና መገልገያ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያ ዕቃዎች መካል ደረጃቸውን ባልጠበቁ ጥሬ ዕቃዎች የተመረቱ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ እንዳይከፋፈሉ፣ እንዳይጓጓዙና እናዳይከማቹ የተከለከሉ እንደሚገኙበትም መረጃው ያመላክታል፡፡
በፍተሸው ከተያዙት ህገ ወጥ ምርቶች መካከል 127ቶን የሚሆን የታሸጉ ምግቦች ጥቅም ላይ እንዳየውሉ መደረጉም ተገልጿል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ ባቋቋመው አገር አቀፍ የቁጥጥር ኮማንድ ፖስት ለህብረተሰቡ ጤና እጅግ አደገኛ የሆኑና በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉ ምርቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል እንዲወገዱ የሚያደርግ መሆኑንም መረጃው አመልክቷል፡፡

Read 1526 times