Sunday, 30 April 2017 00:00

ትልቁ ሞል በ3 ቢ. ብር ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 5 ሺህ ሱቆች፣ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎችና መኖሪያ ቤቶችን ያካትታል
                         
                           አክሲዮኖች እየተሸጡ ነው
                              

      ህዳሴ የተሽከርካሪና ማሽነሪ ገበያ አክሲዮን ማህበር፣ በአፍሪካ ትልቁን “ህዳሴ ግራንድ ሞል” በ3 ቢሊዮን. ብር ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በአፍሪካ ጆሀንስበርግ የሚገኘውንና እስካሁን በአህጉሪቱ በትልቅነቱ የሚታወቀውን  “ሞል ኦፍ አፍሪካን” በእጥፍ እንደሚበልጥም የአክሲዮን ማህበሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በሸራተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀዋል፡፡
ሞሉ ተገንብቶ ስራ ሲጀምር የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ስፋታቸው 5 በ5 የሆኑ 5 ሺህ ሱቆች፣  ባለ አራት ኮከብ ሆቴል፣ የመኖሪያ አፓርታማዎች እንደሚይዝና በህንፃው ምድር ቤት ለ5 ሺህ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ እንዲሁም ከህንጻው ጋር ተያይዞ በሚሰራ የመኪና ማቆሚያ 3 ሺህ ተሽከርካሪዎች እንደሚያስተናግዱ፤ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ መኮንን ተናግረዋል፡፡
 አክሲዮን ማህበሩን ያቋቋሙት ባለሀብቶች በተለያዩ የንግድ ስራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ እንደቆዩ የገለፁ ሲሆን ወደዚህ ፕሮጀክት የገቡበት ምክንያት የአዲስ አበባ 75 በመቶ የሚሆነው  ነጋዴ ሱቅ ተከራይቶ የሚሰራ በመሆኑ፣ ነጋዴውን የሱቅ ባለቤት ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ አንድ ሰው በዝቅተኛ ኢንቨስትመንት አንድ ሱቅ፤ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት አራት ሱቆች ብቻ መግዛት እንደሚችል የተናገሩት አቶ ደረጀ፤ ለአንድ ሰው ከአራት በላይ ሱቅ የማንሸጠው ሌሎችም ነጋዴዎች የሱቅ ባለቤት እንዲሆኑ እድል ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡ ሞሉ ተጠናቅቆ ስራ ሲጀምር ከ35 ሺ እስከ 50 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አህመዲን መሀመድ ተናግረዋል፡፡
አክሲዮን ማህበሩ ከጥር ወር ጀምሮ አክሲዮኖች መሸጥ የጀመረ ሲሆን 3 ሚ. አክሲዮኖች መዘጋጀታቸውንና የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1 ሺህ ብር መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልፀው፣ አንድ ሰው በዝቅተኛ ኢንቨስትመንት ስፋቱ 25 ካ.ሜ የሆነ ሱቅ ባለቤት ለመሆን 600 አክሲዮኖችን መግዛት ያለበት ሲሆን 100 ካ.ሜ ሱቅ ለማግኘት 2,400 አክሲዮኖችን መግዛት እንደሚጠበቅበት  ተናግረዋል፡፡
ሞሉ  ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረ በ5 ዓመቱ፣ 16 ቢ. ብር ገቢ ያስመዘግባል ተብሎ ሲጠበቅ ለጊዜው የግንባታውን ቦታ መግለፅ እንደማይቻል የገለፁት ኃላፊዎቹ፣ ለዲዛይን ክለሳ 6 ወር፣ ለግንባታ ሁለት ዓመት ተኩል በድምሩ 3 ዓመት እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዘመን ባንክና ወጋገን ባንክን እየገነቡ ያሉ ሁለት ትልልቅ የቻይና ኩባንያዎች ይህንን ሞል ለመገንባት  ፍላጎት እንዳላቸው በደብዳቤ መግለፃቸውን ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡

Read 3178 times