Wednesday, 04 April 2012 09:04

የተናቀው መምህር!

Written by  ኤልያስ ግደይ
Rate this item
(3 votes)

ዘመድ ለመጠየቅ ዘመድ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ተማሪ ልጅ አለቻቸው፡፡ 5ኛ ክፍል፡፡ ስለ ትምህርት ጠየቅኋት፡፡ በተኮላተፈ አንደበት ት/ቤታቸው እንደተዘጋ ነገረችኝ፡፡ ለምን አልኳት? ፈጠን ብላ መምህራችን 70 ብር ብቻ ስለተጨመረላቸው አለች፡፡ አዘንኩም ደነገጥኩም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ እነዋለልኝ፣ ማርታ ለ”ሰፊው ህዝብ” ጥቅም ሲባል አውሮፕላን ጠለፉ፡፡ ከ40 አመት በኋላ ለሰፊው መምህር “ጥቅም” ሲባል ትምህርት ተቋረጠ፡፡ ጨቅላ ተማሪዎች ታገቱ፡፡ ተጠለፉ፡፡ ደመወዝ ካልተጨመረ አናስተምርም ተባለ፡፡ ማብራሪያ ማሳመኛ ምክንያቶች ተደረደሩ፡፡ በአዲስ አበባ ከፋዩ የሃብታም ልጅ በስነ ስርዓት ሲማር፣ የነፃ ተማሪው የድሀ ልጅ እንዳይማር በቀለም አባቱ ተፈረደበት፡፡ “አይ እናት አገር አንቺ እማማ” ያለው ማን ነበር? ቆሞስ ቢሰማ ምን ይል ይሆን?

መምህራን ትውልድ ቀራጮች ናቸው፡፡ አገሪቱ መክፈል የምትችለውን እንድትከፍል ግዴታ አለባት፡፡ ሌላው የእናት ልጅ፣ መምህሩ የእንጀራ ልጅ የሚሆንባት ኢትዮጵያ ለዘላለም አትኑር፡፡ እኩል እንኑርባት፡፡ መብት መጠየቅ መብት ነው፡፡ ግዴታን መፈፀምም እንዲሁ፡፡ ሰሞነኛ የወሬአችን ርእስ የመምህራን የደመወዝ ይጨመርልን ጥያቄ ነው፡፡ ያልተገባ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ ማንም ለመብት ትርጉም የሚሰጥ የሚደግፈው ጥያቄ ነው፡፡ የመምህራን ኑሮ መሻሻል አለበት፡፡ መምህርነት ሥራ መፈለጊያ ማቆያ ሆኗል፡፡ የተሻለ ጥቅማ ጥቅም ቢከበር መምህሩ ተረጋግቶ፣ ትውልድ የመቅረፅ ተግባሩን ይወጣል፡፡ ውጭ ውጭ አያይም፡፡ ወዘተርፈ፡፡

በሰሞኑ የመምህራን ጥያቄ ከቀረቡት ጥያቄዎች፣ መከራከሪያ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቱን እስኪ እንይ፡፡ እኛም በተራችን “ምህዳሩ ጠቧል” እንዳንል፡፡

1/ የመምህራን ደመወዝ ተጨምሯል ተብሎ በቴሌቪዥን መነገሩ የቤት ኪራይ እንዲጨምርብን ሆኗል፡፡

ይሄ አባባል የዛሬ 20-30 አመት ቢነገር ውሃ ይቋጥር ነበር፡፡ በዛን ወቅት ገንዘብ ያለው የመንግስት ሠራተኛ ስለነበር ዋጋ የሚወስነው ራሱ ነበር፡፡ አሁን ግን እንኳን የቤት ኪራይ የማኪያቶ ዋጋ የሚወሰነው በሌላው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በተወሰነለት ዋጋ መገበያየት የመንግስት ሠራተኛ የውዴታ ግዴታው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የጤፍ ዋጋን ማን እንደሚወስነው ይታወቃል፡፡ የቤት ኪራይም እንዲሁ፡፡ የቤት ኪራይ ተከራይቶ የሚኖረው ሾፌሩ፣ እንጨት ቤት፣ ጋራዥና የተለያየ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሁሉ ነው፡፡ አሁን የመምህር ደመወዝ ተጨመረ አልተጨመረ የቤት ኪራይ ዋጋ በዚህ አይወሰንም፡፡ ጐረቤታችን ተከራይተው የሚኖሩትን ብንጠይቅ፣ ብዙዎቹ የመንግሥት ሰራተኛ አይደሉም፡፡ እኛ የምንከራየው በነሱ በተወሰነልን ዋጋ ተወዳድረን እንጂ እኛ ወሳኝ አይደለንም፡፡ አልከራይም ብለን የምናስገድድበት ወርቃማ ጊዜያችን አልፏል፡፡ በድሮ በሬ ያረሰ የለም ይባል የለ፡፡ በጋራ ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ጋር መንግስትን የምንጠይቀው ጥያቄ ሲሆን ለብቻችን ተማሪ በማገት የሚመጣ ነገር የለም፡፡ የቤት ነገር እንደዚያ ነው፡፡ ሌላውም፡፡

2/ መምህራን ተንቀናል፡፡ 70 ብር ተጨመረልን፡፡ ማስፈጫ ነው ወይስ ምንድነው?

መንግስት የመምህራንን ጥያቄ ሲያስተናግድ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በተከታታይ ለቀረቡ ጥያቄዎች መንግሥት መልሶችን ሠጥቷል፡፡ በመምህራኑ ውሥጥ ሁሉም መምህር እኩል አይደለም፡፡ ዲፕሎማ ያለው ከሌላ ዲፕሎማ ካለው እንዲሁም ዲግሪ ያለው ከሌላ ዲግሪ ያለው ይለያያል፡፡ መምህራን በ6 ደረጃ ይለያያሉ፡፡ ጀማሪ፣ መለስተኛ፣ መምህር፣ ከፍተኛ፣ ተባባሪ መሪና መሪ መምህር በሚል ደረጃ ተከፍለዋል፡፡ የተለያየ የደመወዝ ጥቅማ ጥቅም አላቸው፡፡ የቆይታ ጊዜም አላቸው፡፡ ካንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ከ2-4 አመት የቆይታ ጊዜ በኋላ ተወዳድሮ ማለፍ ይቻላል፡፡ ከመምህራን ጥያቄዎች አንዱ፣ መምህራን በብዛት መሪ መምህር ደርሠው ሌላ ደረጃ የላቸውም፡፡ የሥራ ሞራላቸው ይቀዘቅዛል፡፡ ደመወዝ ጭማሪም የላቸውም የሚል ነበር፡፡ አንዱ በመጋቢት የደመወዝ ማስተካከያ የተመለሠው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ ከፍተኛ መሪ የሚባል ደረጃ፡፡ ሶስት አመት መሪ የነበረ መምህር፤ በሚቀጥለው አመት ወደዚህ ደረጃ ተወዳድሮ ማለፍ ይችላል፡፡ ይሄ አንዱና ትልቁ የመምህራኑ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህም እያንዳንዱ መምህር እስከ 540 ብር ጭማሪ ያገኛል፡፡ ጀማሪ መምህራንን በሚመለከት የተደረገው ጭማሪ የአንድ ዕርከን ነው፡፡ ይህ ጭማሪ ለሌሎች የመምህራን ደረጃዎችም ተጨምሯል፡፡ የሌላውን ለመገመት እስኪ ጀማሪ መምህራንን ለይተን እንይ፡፡ ከዩኒቨርስቲ አዲስ የተመረቀ የመንግስት ሠራተኛ የትም ይመደብ የትም (ከልማት ድርጅቶችና መንግስት በልዩ ከሚከፍላቸው ውጭ - እንደ ገቢዎች …) በፕሳ (ፕሮፌሽናል ሳይንስ) 1 መደብ ይመደባል፡፡ ደመወዙም ብር 1499 ነው፡፡

የጀማሪ መምህር ቅጥር ግን ከዚህ መደብ አንድ እርከን ተጨምሮ ብር 1571 ነበር፡፡ አሁን መንግስት ከሌላው የመንግሥት ሠራተኛ ከመጋቢት ጀምሮ በሁለት ዕርከን ተለያይቶ 1644 ብር እንዲሆን አድርጓል፡፡ መንግሥት እንዳቅሚቲ ለመምህሩ አዳልቷል፡፡ አዲስ አበባ የሚያስተምር መምህር፣ ተጨማሪ የቤት አበል ታክስ የማይደረግበት 300 ብር አለው፡፡ እንደኔ ማመፅ፣ ስለኑሮም አብዝቶ መጮህ ካለበት መጮህም ያለበት ሌላው አዲስ የመንግስት ተቀጣሪ እንጂ ጀማሪ መምህሩ መሆኑ ይገርማል፡፡ ማገቱ ሣይጨመርበት፡፡ አዎ፡፡ ኑሮ ተወዷል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ እየተቸገረ ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ ግን እናቱ ገበያ የሄደችበትና … እንደሚባለው አሁን የምንሠማው ግራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከፕሣ 1 የደመወዝ ደረጃ ወደሚቀጥለው ፕሣ 2 ለመድረስ፣ ሶስት ዕርከን አለው፡፡ ማለትም አዲስ ተቀጣሪ ፕሣ 1 ሲሆን አዲስ መምህር (በዲግሪ) ፕሣ 2 ሊደርሥ አንድ ዕርከን የቀረው ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ሥንሄድ ጀማሪ (ፕሣ 1+2 ዕርከን)፣ መለሥተኛ (ፕሣ2+2 ዕርከን)፣ መምህር (ፕሣ3+2 ዕርከን)፣ ከፍተኛ (ፕሣ4+2 ዕርከን)፣ ተባባሪ መሪ (ፕሣ5+2 ዕርከን) መሪ (ፕሣ6+2 ዕርከን) እንዲሁም አዲሱ የከፍተኛ መሪም (ፕሣ7+2 ዕርከን) መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ማለት ለፕሣ 8 አንድ ዕርከን የቀረው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፕሣ 8 (3871 ብር) በመንግስት መሥሪያ ቤት የሥራ ሂደት ባለቤት ደመወዝ ነው፡፡ በአንድ ትልቅ መሥሪያ ቤት ለሁለትና ሦስት ሠራተኞች ብቻ የሚከፈል ደመወዝ ነው፡፡ የሁሉም መምህር ደመወዝ ግን የሥራ ሂደት ባለቤት ከሚያገኘው ጋር እኩል ለመሆን አንድ ዕርከን የቀረው ይሆናል፡፡ በተለይ አንጋፋ መምህራንን ከዚህ በላይ ማክበር አለ እንዴ? “ተንቀናል! ተዋርደናል!” ያለው ማን ነበር? ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አሉ፡፡ ትንሽ ፖለቲካ ፖለቲካ ይላል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

እንደኔ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ አዲስ ምሩቃን በፍላጐት ወደ መምህርነት ሥራ የሚሳቡ ይመስለኛል፡፡ መቼም እሰርቃለሁ ብሎ ከሚያስበው ውጭ 1499 ከሚቀጠር 1644 እና 300 ብር የቤት አበል ያዋጣዋል፡፡ ለነገሩ የሌብነት ቀዳዳዎችም … መሬቱም ገቢውም ቀዳዳቸውን ለመድፈን እየተሞከረ ነው፡፡ መምህርነት የሥራ ነፃነት አለው፡፡ ለአለቃ ማሸርገድ የለም፡፡ አንድ መምህር በሳምንት በት/ቤቶች ከሚሰጠው 35 ፔሬዶች  ቢበዛ 20 ፔሬድ ቢያስተምር ነው፡፡ በቀን ከ3-4 ፔሬድ ብቻ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ነፃነት አለ፡፡ ነፃነት የሚፈልጉ፤ ከአለቃ ጋር ሽርጉድ የሌለው፤ አስተምሮ ብቻ ወደ ቤት የሚኬድበት፤ ከነገር የራቀ፣ ብቸኝነት (ፕራይቬሲ) ለሚፈልግ ነፃነት የሚሰጥ ሥራ ነው፡፡ መንግሥት መምህርነት ከሌላ የመንግሥት ሠራተኛ እንዲሻል ማድረጉ የሚያስመሰግነው ይመስለኛል፡፡ አልናቀንም፡፡ አላዋረደንም፡፡ በዚህ ለማትረፍ ተልኮ ከሚቅለበለብ በቀር፣ በቀና ላየው የሚያስቅም የሚያሳዝንም ነው - “አመፃችን”፡፡  አሁንም የተበደለው ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ በመሆኑ ጥያቄያችን መሆን ያለበት፣  ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ የፕሣ 1-9 ያለው ደመወዝ መነሻው ይቀየር ነው፡፡ ሁላችንም ለህዳሴውም ለትራንስፎርሜሽኑም መሳካት ሙሉ ተሳትፎ እንድናደርግ፡፡

የምንበላውን፣ የምንኖርበትንና የምንለብሰውን ዋጋ እያሰላሰልን ጭንቅላታችን ነፃ አያስብም፡፡ ከ11% ምናምን እድገቱ ሊያቋድሰን ይገባል፡፡ የመጨረሻ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ፕሣ 9 መሆኑ የስም ሃብታም (ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር) የሚናገርላቸው አጥተዋል ማለት ነው፡፡ ጥያቄያችንን እየሰራን እየሰራን አሁንም እየሰራን፡፡ ሻሎም!

በነገራችን ላይ በመጋቢቱ ጭማሪ የቆይታ ጊዜው 3 አመት ሆኗለ፡፡ ተቀንሷል፡፡ ማስተርስ ያላቸው ሲቀጠሩ (በፕሣ 3+2 እርከን) ደረጃ ነው፡፡ መጨረሻቸውም ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር የደረሰበት ደረጃ (ፕሣ 9+2 እርከን) ይሆናል፡፡ መምህር ልበል ወይስ በዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማዕረግ መምህር? እናመሰግናለን፡፡ ያቆይልን፡

 

 

 

Read 7226 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 09:17